መንግሥት ያለፕላን የሚያፈርሳቸው የግለስብ ቤቶች ወገናዊነት ያጣ ሀገወጥነትን ያሳያሉ

7 Oct

Forced homelessness

በታምሩ ጽጌ, ከሪፖርተር የተወሰደ

ሕገወጥ ግንባታ ተብለው በሚፈርሱ ቤቶች ምክንያት በቦሌ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶና በሌሎቹም ክፍላተ ከተሞች ውዝግብ እየተፈጠረ ነው፡፡ ቤቶቹ የሚፈርሱት ካላግባብ በመሆኑ ለጐዳና ላይ ኑሮ እየተዳረጉ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ በተለይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ ቡልቡላና አምቼ ፊት ለፊት ወረዳ አምስት ውስጥ የነበሩ ነዋሪዎች፣ ከአሥር ዓመታት በፊት በወቅቱ የነበረው የቀበሌው አስተዳደር በሰጣቸው ቤት ውኃ፣ ኤሌክትሪክና ስልክ አስገብተው እንደሚኖሩ፣ በ2002 ዓ.ም. አስተዳደሩ ባወጣው መመርያ መሠረት ሕጋዊ መሆናቸው እንደተረጋገጠላቸው፣ ነገር ግን ባላወቁትና ባላሰቡት ጊዜ በላያቸው ላይ ቤቱ እንደፈረሰባቸውና በጐዳና ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አስተዳደሩ ባወጣው መመርያ መሠረት የኤሌክትሪክ ወይም የውኃ ቢል ያለው ነዋሪ፣ የያዘው ቦታ ተለክቶ የባለቤትነት ሰነድ እንደሚያገኝ መደንገጉን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ እነሱም ያላቸውን ማስረጃና ሰነድ ይዘው ወደ ወረዳው ቢቀርቡም የሚሰማቸውና የሚቀበላቸው ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት አምቼ ፊት ለፊት ከ15 ዓመታት በፊት መኖር መጀመራቸውን የሚገልጹት ነዋሪዎቹ በወቅቱ ከአፋር፣ ከጋምቤላና ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የተውጣጡ ሠልጣኞች ዕድገት የጐልማሶች ትምህርት ቤት ገብተው ሲማሩ የምግብ ቤት፣ የጥገናና የጥበቃ ሠራተኞች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ትምህርቱ ሲያበቃ በወቅቱ ለመኖርያ ቦታ የተሰጣቸው ቢሆንም፣ አሁን ግን ሰዎች ለሰዎች ለሚባለው ድርጅት ተሰጥቷል በሚል ወረዳው አስወጥቶ መንገድ ላይ እንደጣላቸው አስታውቀዋል፡፡ መንግሥት ዜጐቹን የመጠበቅ፣ የማስተዳደርና መጠለያ የመስጠት ኃላፊነት ስላለበት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ነዋሪዎቹ የሚያነሱትን ቅሬታና ጥያቄ በሚመለከት የቦሌ ክፍለ ከተማ የቤቶች ልማት አስተዳደር፣ ነዋሪዎቹ ሕገወጦች መሆናቸውን፣ አስተዳደሩ ያወጣውን መመርያ የሚያሟላ ምንም ነገር እንደሌላቸውና የቀድሞ አስተዳደር እንደሰጣቸው የሚያረጋግጡበትም ሆነ ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል አለመኖሩን ገልጿል፡፡ ይዞታው ሰዎች ለሰዎች ለሚባለው ድርጅት ከተሰጠ አንድ ዓመት እንደሞላውና በአግባቡ ንብረታቸውን እንዲያነሱ በማወያየት ቢጠየቁም ሊስማሙ ባለመቻላቸው፣ በሕጉ መሠረት ክፍለ ከተማው ሊያስለቅቅ መገደዱን አስታውቋል፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ስሙ መስታወት ፋብሪካ አካባቢ ያሉ ከ50 የሚበልጡ አባወራዎችም “ሕገወጦች ናችሁ” ተብለው በላያቸው ላይ ቤታቸው እንደፈረሰባቸው ገልጸዋል፡፡ ከ1997 ዓ.ም. በፊት ጀምሮ ይኖሩ እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ግብር የሚገብሩበትና የተለያዩ ሕጋዊ ሰነዶች እያላቸው ቤታቸው መፍረሱን በመግለጽ፣ የአስተዳደሩ መመርያ ሕጋዊ ቢያደርጋቸውም ሹማምንቱ መመርያውን በመጣስ አውላላ ሜዳ ላይ እንደጣሏቸው ተናግረዋል፡፡ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ማስረጃቸውንና መመርያውን በማመሳከር እንዲታደጋቸውም ለምነዋል፡፡ ማብራርያ እንዲሰጡን የክፍለ ከተማውን ኃላፊዎች ለማግኘት የተደረገው ጥረት “ስብሰባ ላይ ናቸው” በመባሉ አልተሳካም፡፡

%d bloggers like this: