የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ከታቀደው የ2.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በ36.5% ዝቅተኛ መሆኑ የውጭ ምንዛሪ ችግር እንዲሚባባስ ይጠቁማል

13 Feb

በዮሐንስ አንበርብር: ከሪፖርተር

• ለስድስት ወራት ከታቀደው 2.2 ቢሊዮን ዶላር 1.4 ቢሊዮን ብቻ ተገኝቷል

መንግሥት ለግብርና፣ ለማኑፋክቸሪንግና ለማዕድን ዘርፎች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከዘርፎቹ የሚገኙ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪውን ለማሳደግ ቢያቅድም እንደ ዕቅዱ እየተሳካለት አይደለም፡፡ በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ከዕቅዱ በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሏል፡፡

የተጠቀሱት ዘርፎች ምርቶቻቸውን በብዛትና በጥራት በማምረት ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ በ2005 የበጀት ዓመት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ለመንቀሳቀስ በመወሰን፣ መንግሥት ከዚህ መሠረት ላይ በመነሳት በበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ 5.023 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ወጥኖ ነበር፡፡

የወጪ ንግዱን የሚከታተለው የንግድ ሚኒስቴር በዓመቱ መጨረሻ ለማግኘት ያቀደውን የውጭ ምንዛሪ በብቃት ለማስፈጸም ዕቅዱን በወቅቶች የከፋፈለ ሲሆን፣ በግማሽ ዓመት ጊዜ ወስጥም ከተጠቀሱት ዘርፎች 2.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ሲጥር ቆይቷል፡፡

የሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ በተደጋጋሚ እንደሚገጥመው ሁሉ የግማሽ ዓመት ውጥኑም እንዳልተሳካና ከተገቢው በታች ማሽቆልቆሉን የግማሽ ዓመት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ በግማሽ ዓመት ውስጥ ካቀደው የ2.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የተገኘው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ሲሆን፣ ይህም የዕቅዱን 64 በመቶ ነው፡፡

ከተገኘው ገቢ ውስጥ የግብርና ምርቶች 781.95 ሚሊዮን ዶላሩን ሲይዙ፣ የማኑፋክቸሪንግና የማዕድን ዘርፎች ደግሞ የተቀረውን 618.05 ሚሊዮን ዶላር አስገኝተዋል፡፡ የንግድ ሚኒስቴር የግብርና ምርቶች የወጪ ንግድን የማበረታታትና የማሳደግ ኃላፊነት የተጣለበት ሲሆን፣ በግማሽ ዓመት ዕቅዱ መሠረት ኃላፊነቱን በመወጣት 491,620 ቶን መጠን ያላቸው የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በመላክ 984.6 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ዕቅድ ነበረው፡፡

ይሁን እንጂ ለመላክ የቻለው 405,299 ቶን የግብርና ምርቶችን በመሆኑ፣ ያገኘው የውጭ ምንዛሪም 781.95 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህም በመጠን ደረጃ የዕቅዱ 82.4 በመቶ ገቢው ደግሞ 79.4 በመቶ መሆኑን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ ከግብርና ምርቶች ውስጥ ቡና ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ምርት ቢሆንም በግማሽ ዓመት ውስጥ ግን ውጤታማ አልነበረም፡፡

በተጠቀሰው ወቅት ለመላክ የታቀደው የቡና መጠን 113,376 ቶን ሲሆን፣ የተከናወነው ግን 91,941 ቶን ነው፡፡ ከዚህ መጠን የተገኘው ገቢም 361.1 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ፣ ይህም የዕቅዱን 77.7 በመቶ መሆኑን መረጃው ያትታል፡፡

ዕቅዱን ለማሳካት በየደረጃው ያለው አመራርና ፈጻሚ ባለሙያ ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ በመስጠት ረገድ ያሳየው ውስንነት፣ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በሕገወጥ አሠራሮች ምክንያት መጓተት፣ እንዲሁም በዓለም ገበያ ዋጋ መቀነስ ከቡና ምርት ለተገኘው ገቢ ዝቅተኛ መሆን በምክንያትነት በሪፖርቱ ውስጥ ተቀምጧል፡፡

TE – Transforming Ethiopia

%d bloggers like this: