በዓመት 10 ሺሕ ቶን ሰሊጥ መግዛት የሚሻው የእንግሊዝ ኩባንያ በሰምሀር ሀብተጽዮን አማካሪነት ሻጮችን እፈያላለገ ነው

29 Mar
ሰምሀር ሀብተጽዮን የእንግሊዝ ኩባንያ ተወካዮች (Photo Reporter)

ሰምሀር ሀብተጽዮንና የእንግሊዝ ኩባንያ ተወካዮች (Photo Reporter)

  የአዘጋጁ አስተያየት

  በዚህ ሪፖርት እነደተመለከተው፡ ከሁሉም የሚያስገረመው ኢትዮጵያ ምርቷን በቀጥታ ለገበያ ማቅረብ ሳትችል ቀርታ (ለዚያውም processed and value added ሳይሆን)፤ እንግሊዞች ለሃግራችን የሚውሉላት ውለታ: እነርሱ ከእኛ አምራቾች ቡናና ስሊጡን በርካሽ ገዝተው ለቻይና ማቅረብና ይበልጡን ትርፍ መውሰዳቸው ሆኗል። ይህን ሲያደርጉ ለምርቱ መሻሻል የሚያደርጉት አስተዋጾኦ ይኖራቸዋል ለሚለው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ የለም – እንግሊዝ እያንንዣበበ ካለው የአውሮፓና የዓለም የኤኮኖሚ ቀውስ እራሷን ለመታደግ በዚህ ዓመት ኩባንያዎቿን በዚህ ዓይነት መንገድ ወደተለያዩ አገሮች ማሰማራት የጀመረች ከመሆኗ ባሻገር!

  ይህም እንግሊዞች ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የዘየዱት የራሳችውን የገበያ ጥቅም ማበራከቻ ለማድረግ ብቻ ያዘጋጁት እንዳይመስል፡ ለኢትዮጵያ አስበው መሆኑነን: የኢትዮጵያን የተወሳሰቡ ችግሮች ደጋግመው ያሰታውሱናል። በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ግሬግ ዶሪ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይህንኑ ሊያሳምኑ ሲሞክሩ በተደጋጋሚ ይደመጣሉ። በርሳችው አመለካከት – “ኢኮኖሚው ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ [እንግሊዞች ሃገሪቱን] በበጎ አይን እያወቋት መምጣታቸውም አስተዋጽኦ እንዳደረገ [መሆኑንና] ከጥቂት ዓመታት በፊት እነባንድ ኤይድ የሚያስተዋውቋት ኢትዮጵያ፣ በረሃብና በድርቅ የምትታወቅ ነበረች ይላሉ፡፡”

  ይህም ሆኖ በኢትዮጵያ የገበያው መጧጧፍ፡ የእንግሊዝና የኢትዮጵያ በፖለቲካ፡ በንግድና ኢንተለጀንስ መተሳሰር ሌላው ቀርቶ እንግሊዝን በአዲስ አበባ የነበራትን የኤምባሲዋን የቪዛ ክፍል ከአዲስ አበባ ወደናይሮቢ ከማዛወር አልገታም። ይህም የሆነበት ምክንያት እነርሱ የራቸውን ጥቅም በሚገባ ስለሚያውቁና ማስከበር ስለሚችሉ ነው።

  በመሳሳይ መንገድ፤ ስሊጡንና ቡናውን እንግሊዞች ከኢትዮጵያ ገዝተው ለቻይና አቅራቢ ከሆኑ መሠረተ ልማት (መንገድ፡ ስልክ፣ መብራትና ወዘተ) በብድር እየሠሩ ለሚያቅርቡት ቻይናዎች ኢትዮጵያ ራሿ ለምን አቅራቢነቷን አሻሽላ ተጠቃሚ አትሆንም? ለመንደርደር እንዲያስችልም፡ ለጊዜውም ቢሆን የመህል አትራፊውን ከመጥቀም ይልቅ፡ በጊዜያዊነት ቻይናዎች ጋር 15% ሆነ 20% የሚሁነውን ምርት ለቻይናዎቹ፤ በተስማሚ የውጭ ምንዛሪ ስምምነት ኢትዮጵያ ብድሮቿን ለመክፈል
  ለራሿ ጥቅም ብታውለው የተሻለ ይህናል – መሃል ቤት አትራፊ ኩባንያዎችን ከማክበር ይልቅ።

  ደርግ የውጭ ምነዛሪ ባጣበት ዘመን የቀድሞ የምሥራቅ አውሮፓ ሶሻሊስት ሃገሮች ሸቀጣሽቀጦችን በብድር በማቅረብ ከኛ በርካሽ የውሰዱትን ቡናና ሌሎች ምርቶች እነርሱን የተሻሉ ኤክስፕርተሮችና ተጠቃሚዎች ከማድረጉ እንደሕዝብ ልንማርበትና ልናርመው የሚገባ ትምህርት የሚሰጥ ይመስለኛል፡

  ለማንኛውም የእንግሊዞ ቹአሠራር ከብዙ ዘመን ልምዳቸው የተማሩት ዘዴ ስለሆነ፡ አሁንም ጥቅማቸውን ለማራመድ የሃገሩን በሬ በአገሩ ሠርዶና በሃገሩ እምቧይታ ለማግባባት በደንቡ ተሰናድተው ነው የመጡት። እኛስ የሃገራችንንና የአምራችቻችን ጥቅም ማስከበር እንችል ይሆን?

 
ከዚህ በታች የሠፈረው በርፖርተር ጋዜጠኛ በብርሃኑ ፈቃደ የተዘጋጀ ዘገባ ነው

በዓመት አሥር ሺሕ ቶን ሰሊጥ የሚገዛው የእንግሊዝ ኩባንያ ሻጮችን እያፈላለገ ነው

ከሌሎች ጊዜያት በበለጠ በዚህ ዓመት በርካታ የእንግሊዝ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉትም ኢንቨስት ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ጥናት እያካሄዱ ያሉትም ቁጥራቸው ቀላል አልሆነም፡፡

ለንግድ ሥራ ጉዳይ በርካታ የንግድ ልዑካን እንደመጡ ሁሉ ከአራት ያላሰኑ በሚኒስትር ደረጃ የተመሩ ጉብኝቶች ከለንደን ወደ አዲስ አበባ ተደርገዋል፡፡ በዚህ ዓመት የሚደረገው የንግድ ልዑካን ምልልስም ይበልጥ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡

እንግሊዝ በተለየ ሁኔታ በዚህ ዓመት ወደተለያዩ አገሮች አነስተኛና መካከለኛ ኩባንያዎቿን ማሰማራት የጀመረች ሲሆን፣ ይኸውም አገሪቱ ደርሶባት ከነበረው የኢኮኖሚ ቀውስ ለማገገም ከተጠቀመችበት መላ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ ኩባንያዎቿ በሌሎች አገሮች ገንዘብ እየሠሩ ወደእንግሊዝ እንዲያጎርፉ ለማድረግ የታሰበበት ይህ ዘዴ፣ በአፍሪካ ቀና ቀና ማለት ለጀመረው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በጎ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በተለይ በቻይናና በሌሎች የሩቅ ምሥራቅ አገሮች የተጥለቀለውን የሸቀጥና መሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ፣ አውሮፓውያኑ በፉክክር መምጣታቸው ከጥራት አኳያ በተለይ ተፈላጊነቱ እየተነገረለት ነው፡፡

ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር መኖርያ ቤት ተገኝተው ከኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰቡ አባላት ጋር የተነጋገሩና የተደራደሩ ስድስት ያህል ኩባንያዎችም መስተንግዶ ተደርጎላቸው ነበር፡፡

ከስድስቱ ኩባንያዎች መካከል ከኢትዮጵያ የቅባት እህሎችና ቡና ለመግዛት፣ በምትኩም ለቻይናና ለሌሎች ደንበኞቹ ለማቅረብና ከኢትዮጵያውያን አቅራቢያዎች ጋር ለመደራደር የመጣው ፋስ ትሬድ ኤንድ ኢንቨስትመንት የተሰኘው ኩባንያ አንዱ ነው፡፡ የኩባንያው የሽያጭ ኃላፊ ፋሬስ ኦውፊ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በዓመት እስከ 10 ሺሕ ቶን ሰሊጥ ለመግዛት አቅደዋል፡፡

የሁመራ ሰሊጥ በቻይናውያኑ ዘንድ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ ሲሆን ይኸውም ተጨምቆ ከሚወጣው ዘይት ባሻገር፣ እህሉ ለሌላ ተግባርም ተፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡ ጃፓንም ልትገዛቸው የምትችልበት ዕድል እንዳለ ፋሬስ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከሱዳን ሲገዛ የቆየው ኩባንያ፣ በተለይ ሰሊጥ ለመግዛት እንደመምጣቱ ከኢትዮጵያ ለመግዛት በሚፈልጉት ሰሊጥ ላይ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች የግድ መሟላት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

በጊዜ ምርቱን የማቅረብ፣ የዋጋ ጉዳይና ጥራት እንደሚሳስባቸው የገለጹት ፋሬስ፣ በተለይ በምርት አቅርቦት ጉዳይ ላይ በአስተማማኝ ሁኔታ ምርቱ ሳይዘገይ ካልተጫነ በቀር ከደንበኛቸው ጋር ያላቸው የንግድ ግንኙነት እንደሚበላሽ ሲገልጹ፣ በሎጂስቲክስና በሌሎች ጣጣዎች ሳቢያ የምርት ጭነቱ ቢበዛ እስከ አሥር ቀን ቢዘገይ ተቀባይነት የሚኖረው ቢሆንም፣ ከዚያ በላይ ግን እስከ አንድ ወርና ከዚያም ለሚልቅ ጊዜ ከዘገየ ተቀባዩ ደንበኛ ንግዱ ስለሚጎዳበት አንቀበለውም ብለዋል፡፡ ይህ በስምምነት ሰነድ ላይ በግልጽ ሰፍሮ የሚተገበር እንዲሆንም ይጠይቃሉ፡፡

ምርቱን በጊዜ ከማድረስ ባሻገር ኢትዮጵያውያኑ ኤክስፖርተሮች ለሚያቀርቡት ምርት ቁርጥ ዋጋ እንዲጠይቁ፣ ለዚህም የክፍያ አፈጻጸሙ በሰነዱ ላይ በተደረገበት ስምምነት መሠረት (Payment Against Document) እንደሚሆንም ፋሬስ አስታውቀዋል፡፡ ሌላኛው በጥብቅ የሚፈለግ መስፈርት ደግሞ ጥራት ነው፡፡ ስምምነት በተደረገበት ደረጃ ጥራቱ የተጠበቀ ሰሊጥ የሚያቀርብ ደንበኛ ቢያገኙ፣ በዘላቂነት ከ10 ሺሕ ቶን ያላነሰ ግዥ በየዓመቱ ለመፈጸም መምጣጣቸውን ፋሬስ ገልጸው፣ እስካሁንም ከኤክስፖርተሮች ጋር መነጋገራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛው ኩባንያ ደግሞ ቱዶር ኤክስፖርት የተሰኘው ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት ወኪል ድርጅቱን እዚህ ከፍቶ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ በተለይ ለፎቶግራፍ ሕትመት የሚያገለግሉ የወረቀት ምርቶችን በማምረት ከ50 ዓመታት በላይ በእንግሊዝ ያስቆጠረ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በፊልም፣ በፎቶግራፍ ማተሚያ ወረቀት እንዲሁም በኬሚካል ውጤቶች የተሳካለት ሆኖ አፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅን እያዳረሰ እንደሚገኝ የኩባንያው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በላባራቶር፣ በኤሌክትሪካል ምርቶች፣ ለጥጥ ምርት የሚሆኑ ፀረ ጠባይ መድኃኒቶችን የሚያመርተው፣ ሆክሊይ ኢንተርናሽናል የተባለው ኩባንያም ለግብርናው ዘርፍ የሚሆኑ ግብዓቶችን ለማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

ኩባንያዎቹን በመምራት አዲስ አበባ ያመጣቻቸው በዩናይትድ ኪንግደም፣ የንግድና የኢንቨስትመት ተቋም ውስጥ የዓለም አቀፍ ንግድ አማካሪዋ ሰምሀር ሀብተጽዮን ናት፡፡ ከኩባንያዎቹ መካከል ቢሮ የሚከፍቱ፣ ከሌሎች የንግድ ወኪሎች ጋር በጋራ የሚሠሩ እንደሚኖሩ ገልጻለች፡፡

በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ግሬግ ዶሪ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተበራከተ የመጣው የእንግሊዝ ንግድ ልዑካን ጉብኝት ምናልባትም ኢኮኖሚው ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ አገሪቱን ብዙዎች በበጎ አይን እያወቋት መምጣታቸውም አስተዋጽኦ እንዳደረገ የሚገምቱት አምባሳደር ግሬግ፣ ከጥቂጥ ዓመታት በፊት እነባንድ ኤይድ የሚያስተዋውቋት ኢትዮጵያ፣ በረሃብና በድርቅ የምትታወቅ ነበረች ይላሉ፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ አራት ያህል የእንግሊዝ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር የተያያዘ ጉብኝት ያደረጉ እንዳሉ ሁሉ እግረ መንገዳቸውንም በንግድና በኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ለመምከር የመጡትንም ይጨምራል፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ የወቅቱ የአፍሪካ ሊቀመንበርነትን በመያዟ፣ እንግሊዝም የቡድን ስምንት የወቅቱ ሊቀመንበርበነትን በተመሳሳይ የያዘች በመሆኗ ጭምር፣ የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ በሶማሊያና በሱዳን ጉዳይ ከሚመክረው የሁለቱ አገሮች የወቅቱ ሊቀመንበርነት፣ ከዚህም በላይ በአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ላይም ትኩረት እንደሚያደረግ፣ በመጪው ወርም በሶማሊያ መንግሥት አሳሳቢና ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል በሚባሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ ይጠበቃል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካከል የነበረው የንግድ ግንኙነት ዝቅተኛ እንደነበር በአሁኑ ጊዜ ግን ይህ እየተሻሻለ፣ እንደዲያጆ ያሉ ኩባንያዎች 225 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ ሜታ ቢራን መግዛቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ዱዌት፣ ኤኤንኤስ ፉድስና ሌሎችም ትልልቅ ኩባያዎች መምጣታቸውን አምባሳደሩ አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ኤምባሲው የቪዛ ክፍሉን ከአዲስ አበባ ወደናይሮቢ ማዛወሩ የንግድ እንቅስቃሴው ላይ ምንም እክል እንዳልፈጠረ የገለጹት አምባሳደሩ፣ ቀድሞ በሚሰጥበት የጊዜ ገደብ መሠረት ከኬንያ ቪዛው እየተሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ የቪዛ ክፍሉን ወደኬንያ ማዛወር ያስፈለገው በአንድ ማዕከል እንዲመራ ለማድረግና ወጪ ለመቀነስ ታስቦ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን የቪዛ ክፍሉ ወደኬንያ መዛወሩን እስካሁን ባይገነዘቡም፣ ዓመት ሊያስቆጥር መቃረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡

TE- Transforming Ethiopia

%d bloggers like this: