Precipitous forex dip: Ethiopia realizes only 59% of its exports target in three quarters

10 May

ብርሃኑ ፈቃደ – ከኢትዮጵያ ሪፖርተር

    ካለፈው ዓመት ዘጠኝ ወራት አኳይ በዘንድሮው ዘጠኝ ወራት አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ያስመዘገቡ የኤክስፖርት ምርቶች፡- የቅባት እህሎች፣ አበባ፣ የቁም ከብት፣ ያለቀለት ቆዳ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ሥጋና የሥጋ ውጤቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ቅመማ ቅመሞች በዚህ ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ያስመዘገቡት ገቢ፣ አምና ካስመዘገቡት በታች ሆኖ የተመዘገበባቸው ዘርፎች መሆናቸውን የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መረጃ ያሳያል፡፡

መንግሥት ከኤክስፖርት ምርቶች ይገኛል ብሎ ያቀደው የውጭ ምንዛሪ ገቢ መጠን ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በ2005 ዓ.ም. በተጠናቀቁት ስምንት ወራት ደግሞ የገቢው መጠን 3.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን አስልቶ ነበር፡፡

ሆኖም በስምንቱ ወራት ያገኘው ሁለት ቢሊዮን ዶላር ብቻ ሆኖ ተጠናቅቋል፡፡ 1.7 ቢሊዮን ብር ማግኘት ሳይቻለው የወጪ ንግዱ ደካማ አፈጻጸም አሳይቶ አልፏል፡፡

በዘጠነኛው ወር የታየው አፈጻጸም ከ238.96 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገቢ ቢገኝበትም፣ በዚህ ዓመት ይገኛል ተብሎ የሚታሰበውን የገቢ መጠን ለማሳካት የማያስችል ክንዋኔ እንደታየ አኀዞቹ ያመላክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደተለያዩ አገሮች ከተላኩ ልዩ ልዩ የወጪ ምርቶች የተገኘው አጠቃላይ ገቢ 2.238 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ምንም እንኳ ይህ መጠን ካለፈው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት አኳያ ሲታይ የ60 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ እንዳለው ቢያሳይም፣ ከዕቅድ በታች እጅግ ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየበት ነው፡፡

ንግድ ሚኒስቴር በስምንት ወራት የተመዘገበውን የወጪ ንግድ ገቢ በማስመልከት በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው በሁለት ዓመታት ውስጥ የተገኘው የገቢ መጠን ዕድገት እጅግ ዝቅተኛው ነው፡፡ አምና በስምንት ወራት ውስጥ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቶ ነበር፡፡ የዘንድሮዎቹ ስምንት ወራት ግን ሁለት ቢሊዮን ዶላር ተገኝቶባቸዋል፡፡ ንግድ ሚኒስቴር ባለፉት ስምንት ወራት መገኘት ካለበት 3.7 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ብቻ ተገኝቶ ቢጠናቀቅም ቡና፣ ወርቅ፣ የቅባት እህሎች፣ ጫት፣ ጥራጥሬ፣ አበባና ሌሎች የምርት ዓይነቶች እንደየቅደም ተከተላቸው ከፍተኛውን ምርት ማስመዝገባቸውን አስታውቆ ነበር፡፡

ቡና ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ያስመዘገበው 452.9 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር የንግድ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ እስካለፈው መጋቢት ወር ድረስ ባሉት ዘጠኝ የበጀት ዓመቱ ወራት ቡና 515.4 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት አሁንም መሪነቱን እንደጨበጠ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መረጃ ያመለክታል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የቡና ገቢ 505.6 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ ከሁለት በመቶ ያነሰ ዕድገት (የ9.81 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ) ለማስመዝገብ መቻሉ ታውቋል፡፡ ሆኖም ከየካቲት እስከ መጋቢት 2005 ዓ.ም. የነበረው አፈጻጸም ሲታይ ደግሞ የ62.5 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ስለሚታይ በአንድ ወር ውስጥ የታየው ለውጥ ባለፈው ዓመት ዘጠኝ ወራት ከታየው አፈጻጸም አኳያ ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው ያመለክታል፡፡ ከስድስት እጥፍ በላይ ብልጫ አለው፡፡ ነገር ግን የዛሬ ሁለት ዓመት ከተገኘው 860.4 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር አፈጻጸሙ ደካማ ነው፡፡

ወርቅ እስከ የካቲት መጨረሻ አስመዝግቦት የነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 389.1 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ እስከ መጋቢት መጨረሻ በነበሩት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ግን የተገኘው ገቢ ወደ 432.1 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን ያሳያል፡፡ በመሆኑም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የ43 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ አስመዝግቧል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ወርቅ ባለፈው ዓመት ዘጠኝ ወራትና በዚህ ዓመት ዘጠኝ ወራት ካስመዘገበው ብልጫ ይልቅ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገበው ልዩነት አስገራሚ ነው፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የወርቅ የወጪ ንግድ ገቢ 415 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ከዚህ ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ገቢ ጋር ሲነፃፀር በሁለቱ ዓመታት ዘጠኝ ወራት መካከል የ16.2 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ቢታይም፣ በዚህ በጀት ዓመት ስምንተኛው ወርና ዘጠነኛው ወር መካከል የታየው ልዩነት የቡናውን ያህል አስገራሚ ነበር፡፡ እስከ የካቲት 2005 ዓ.ም. የነበረው የወርቅ ገቢ 389.1 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ እስከ መጋቢት መጨረሻ የተመዘገበው ገቢ ደግሞ 432.1 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን የገቢዎች መረጃ ያሳያል፡፡ በመሆኑም በሁለት ወራት ውስጥ የታየው የገቢ መጠን ልዩነት 43 ሚሊዮን ዶላር ሆኖ ይታያል፡፡

በጫት ላይም ተመሳሳይ ታሪክ ተከስቷል፡፡ የዚህ ዓመት የዘጠኝ ወራት የጫት የውጭ ምንዛሪ ገቢ 199.29 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በዚህ ዓመት ስምንት ወራት ውስጥ የታየው የጫት ገቢ 177.8 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በሁለቱ ወራት መካከል የ20.49 ሚሊዮን ዶላር ልዩነት ይታያል፡፡ ባለፈው ዓመት ስምንት ወራት ደግሞ 181.26 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የቅባት እህሎች፣ አበባ፣ የቁም ከብት፣ ያለቀለት ቆዳ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ሥጋና የሥጋ ውጤቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ቅመማ ቅመሞች በዚህ ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ያስመዘገቡት ገቢ፣ አምና ካስመዘገቡት በታች ሆኖ የተመዘገበባቸው ዘርፎች መሆናቸውን የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መረጃ ያሳያል፡፡

The Ethiopia Observatory

%d bloggers like this: