ለአማሮች መፈናቀል ተጠያቂ የተባሉ 2 የቤኒሻንጉል ጉምዝ ምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት ተነሳ: ምን ይፈይዳል?

16 Jun
    የአዘጋጁ አስተያየት

    የተፈናቀሉት አማሮች መመለሳቸው ቢነገርም፡ መንግሥት ወንጀሉ የሚገባውን ክብደት ባለመስጠቱ፤ አሁንም ችግሩ እንደቀጠለ ነው። በመሆኑም የተመለሱት ግለስቦች፡ አሁንም በአጥቂዎቻቸው ክፋትና ወንጀል እይተፈጸመባችው መሆኑ በብዙ ምንጮች ይነገራል። መንግሥት ገና ከጥዋቱ ጉራ ፈርዳ ላይ ወስዶ ቢሆን ኖሮ፡ በሌሎችም ክልሎች መስፋፋቱ ብቻ ሳይሆን፡ በቤኒሻንጉል መደጋገሙ ባልተስማ ነበር። ሁኔታው መንግሥት እራሱን እንደዚህ ዐይነት ዓላማና አስተሳሰብ ካላቸው ግለስቦችና ድርጅቶች ማጽዳቱን አጠራጣሪ አድርጎታል።

    ለዚህም ነው እንዲህ ያለ የዘር ማጽዳት ወንጀል ኢትዮጵያ ውስጥ በያዝነው 21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን መካሄዱ፡ ዛሬም ነገም ገና ብዙ የሚያነጋግር አሳዛኝ ድርጊት የሚሆነው።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ጉባዔው በአማራ ክልል ተወላጆች ማፈናቀል ላይ ተሳታፊ ናቸው ያላቸው ሁለት የምክር ቤቱ አባላትን ያለመከሰስ መብት አነሳ፡፡
ምክርቤቱ ያለመከሰስ መብታቸውን ያነሳው በክልሉ የካማሺ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዞኑ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊን ነው፡፡

ምክር ቤቱ በዋና አስተዳዳሪው አቶ ወልተጂ በጋሎ እና በኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ በአቶ ገርቢ በጊዜ ላይ ከክልሉ ፓሊሲ ኮሚሽን እና ከፍትህ ቢሮ የምርመራ ቡድኖችን አደራጅቶ መረጃዎችን በማጠናከር ግለሰቦቹን ለህግ ለማቅረብ የሚያስችል ጥልቅ ምርመራ መደረጉን ገልጿል፡፡

የግለሰቦቹ አድራጎት የክልሉ መንግስትና ህዝብን ስም ያጎደፈ በመሆኑ ከስልጣናቸው ተነስተው በህግ እንዲጠየቁ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡

(የዜና ምንጭ ፡ – ኤሬቴድ)

ሰመጉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቃዮች አሁንም በደል እየደረሰባቸው ነው አለ

የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተወላጆች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ቢደረግም፣ ንብረታቸው በመወሰዱና በመጥፋቱ ለመቋቋም አለመቻላቸውን ገለጹ፡፡

ሰመጉ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ከካማሽ ዞን የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች የደረሰባቸውን ችግር የተመለከቱ የመተከል ዞን ተፈናቃዮች፣ ወደነበሩበት አካባቢ ለመመለስ አልደፈሩም በማለት ይገልጻል፡፡

በሥፍራው ተገኝቶ ችግሩን እንደተመለከተ የሚገልጸው ሰመጉ፣ የካማሽ ዞን የአማራ ተፈናቃዮች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ቢደረግም ንብረታቸው በመወሰዱና በመጥፋቱ ቀድሞ ወደነበሩበት የኑሮ ሁኔታ መመለስ አልቻሉም ይላል፡፡ ምክንያቱንም ሲገልጽ ወቅቱ የእርሻ በመሆኑ ለእርሻ የሚሆን ዘርና ማዳበሪያን የመሳሰሉ ግብዓቶች መግዛት አልቻሉም ይላል መግለጫው፡፡ ግብዓቶች በብድር እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም ብሔራቸው እየተጠቀሰ አድልዎ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ሰመጉ ማጣራቱን ይገልጻል፡፡

እነዚህ ተፈናቃዮች የደረሰባቸውን ችግር ያወቁ አምስት ሺሕ የሚጠጉ የመተከል ዞን ተፈናቃዮች ወደ ሥፍራው ለመንቀሳቀስ አለመቻላቸውን ገልጿል፡፡ ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል በሚገኙት ጓንጓና ቻግኒ ከተሞች በችግር ውስጥ ሆነው እየኖሩ መሆኑን የሰመጉ መግለጫ ያስረዳል፡፡

እነዚህ ተፈናቃዮች በደልና እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን የሚገልጸው ሰመጉ፣ መንግሥት ለዚህ ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ሕገወጥ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ የፀጥታ ኃይሎችና በጉዳዩ ላይ የተሰማሩ ባለሥልጣናት ሕግ ፊት እንዲያቀርብ ጠይቋል፡፡

ከዚሁ ጋር ሰመጉ ከሕግ አግባብ ውጭ ለተፈናቀሉ ዜጐች፣ ቤተሰቦች፣ በግፍ ለተበደሉና ለቆሰሉ፣ ለእስራት ለተዳረጉና ንብረታቸው ያላግባብ ለተወረሰባቸው ሁሉ መንግሥት ተገቢውን ካሳ እንዲከፈላቸው ማድረግ እንዳለበት መንግሥትን አጥብቆ ጠይቋል፡፡

ሰመጉ ያወጣውን 126ኛ መግለጫ ለሕግ አውጪው፣ ለሕግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው እንዲሁም ለሁሉም ክፍሎች አሰራጭቷል፡፡

ይህንን የሰመጉን ሪፖርት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደማይቀበለው ገልጿል፡፡ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚደንት አቶ አህመድ ናስር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሰመጉ መግለጫ የፖለቲካ ፍጆታ ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ ነው፡፡

አቶ አህመድ እንደሚሉት የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ወደ እርሻቸውም ተሰማርተዋል፡፡ ለጠፋባቸው ንብረትም አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ይህን ሁኔታ በመጠቀም የሚያጭበረብሩ አሉ የሚሉት አቶ አህመድ፣ ‹‹አምስት ኩንታል [እህል] የጠፋባቸው 20 ኩንታል ነው የጠፋብኝ፤›› የሚሉም አሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

መጋቢት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡ ድርጊቱ የተካሄደው በስህተትና በግብታዊነት በተወሰደ ዕርምጃ ነው በሚል ተፈናቃዮቹ ወደነበሩበት እንዲመለሱ መደረጉን አቶ አህመድ መግለጻቸውን ተጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

(የዜና ምንጭ ፡ – ሪፖርተር)

ከዚሁ ጋር ተዛማጅ ጽሁፍ

ኢትዮጵያ ወደአደገኛ አግጣጫ እያመራች ነው

Posted by The Ethiopia Observatory

%d bloggers like this: