መንግሥት 3ኛው ታላቁ ኢንቨስተር ሆኗል – የስቴት ፍጆታ ተጠናክሯል፤ ቁጠባ ተኗል፤ የግሉ ዘርፉ ተገፍቷል፤ የሀገር ምርቶች ቀጭጨዋል

19 Jun

Posted by The Ethiopia Observatory

በአስራት ሥዩም*

• የግሉ ዘርፍ ከመጨረሻ ስድስተኛው ዝቅተኛ ኢንቨስተር ተባለ

• “አሁን ግን መንግሥት ያላደገውን ኢኮኖሚ የበለጠ እንዲንቀሳቀስ ግፊት ማድረጉን ገታ አድርጐ፣ የግሉ ዘርፍ በሒደት እየተረከበ የሚሄድበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት”

የዓለም ባንክ በገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አነሳሽነት ባጠናቀረው ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም በከፍተኛ መጠን ኢንቨስት ያደርጋሉ ከሚባሉ ሦስት መንግሥታት መካከል መሆኑን ይፋ አደረገ፡፡ የግል ዘርፉ ግን ስድስተኛው ዝቅተኛ የዓለማችን ኢንቨስተር መሆኑን አስታውቋል፡፡

የባንኩ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጉዋንግ ቼንግና የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር አብርሃ ተከሰተ በተገኙበት በሸራተን አዲስ ማክሰኞ ይፋ የተደረገው ይህ ሪፖርት፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ማክሮ ኢኮኖሚ በስፋት የዳሰሰ ሲሆን፣ በተለይም በአገር አቀፍ ቁጠባ ምጣኔና በወጪ ንግድ መስተንግዶ (ትሬድ ሎጂስቲክስ) ላይ ትኩረት ሰጥቶ አትቷል፡፡

በጥቅሉ የሪፖርቱ ዋነኛ ትኩረት መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ሚና የሚመለከት ሲሆን፣ በተለይ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ እየጨመረ የመጣው የመንግሥት ኢንቨስትመንትን በጥልቀት መርምሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመንግሥት ኢንቨስትመንት ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ሁለት ሦስተኛ የሚሆነውን ድርሻ የሚወክል መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ በጣም በሰፊው ኢንቨስት እያደረጉ ከሚገኙ መንግሥታት ተርታ ተመድቧል፡፡ ሪፖርቱ እንደሚለውም በኢንቨስትመንት ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥትን ሁለት አገሮች ብቻ ይበልጡታል፡፡ እነዚህም ተርክሜኒስታንና ኢኳቶሪያል ጊኒ ሲሆኑ፣ ከአጠቃላይ ምርታቸው 38.6 በመቶና 24.3 በመቶ የሆነውን ኢንቨስት ያደረጉ አገሮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አቻቸው ደግሞ 18.6 በመቶ የኢንቨስትመንት ድርሻ ማስመዝገቡን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

ይህ ደረጃ የግል ዘርፉን ያለ ቅጥ በማቀጨጭ የመጣ መሆኑን ይኼው ሪፖርት ያስረዳል፡፡ የግሉ ዘርፍም በበኩሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንቨስትመንት ምጣኔው ከመጨረሻ ወደ ላይ ስደስተኛ ደረጃን ነው የያዘው፡፡

በጥቅሉ ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ውስጥ 6.9 በመቶ የሚሆነው የግል ዘርፍ ኢንቨስትመንት ውጤት ነው፡፡ ነገር ግን በሪፖርቱ የተመለከተው ሌላ ጉዳይ ይህ ምጣኔ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እየተቀየረ እዚህ የደረሰ መሆኑን ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2003/04 ገደማ ለምሳሌ ወደ 71 በመቶ የሚጠጋው የአገር ውስጥ ምርት በግል ዘርፉ ፍጆታ የተመዘገበ ነበር፡፡

ይህ እንግዲህ በሪፖርቱ ኢኮኖሚው ያሳያቸው መዋቅራዊ ለውጦች ተብለው ከተጠቀሱ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ መዋቅራዊ ሽግግር ታይቶበታል ካላቸው ጉዳዮች መካከል አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ከፍጆታ ወደ ኢንቨስትመንት ፅንፍ ማድላቱ ዋነኛውና የመጀመርያው ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የመንግሥትም ሆነ የግሉ ዘርፍ የፍጆታ መጠን በአገር ውስጥ ምርት ላይ ሚዛን መድፋት አለመቻሉን ሲሆን፣ ይልቁንም በሁለቱም ዘርፎች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ከፍጆታው በልጦ አጠቃላይ ምርትን የተቆጣጠረው ይመስላል፡፡ ከዚህም በላይ የመንግሥት ዘርፍ ኢንቨስትመንት ከግሉ ዘርፍ ጋር ሲነፃፀር ሦስት እጥፍ መሆን መቻሉ ሌላው በአትኩሮት የተነገረ ጉዳይ ነው፡፡

በጥቅሉ የመንግሥት የልማታዊ አጀንዳ የታለመለትን ውጤት ማምጣቱን በአንክሮ የጠቀሰው የዓለም ባንክ ሪፖርት፣ ‹‹አሁን ግን መንግሥት ያላደገውን ኢኮኖሚ የበለጠ እንዲንቀሳቀስ ግፊት ማድረጉን ገታ አድርጐ፣ የግሉ ዘርፍ በሒደት እየተረከበ የሚሄድበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት፤›› ብሏል፡፡

የልማታዊ መንግሥት ዓላማ የግሉ ዘርፍና ገበያው የኢኮኖሚውን ዕድገት ለማስጀመር የሚገጥሙዋቸውን እንቅፋቶች መቅረፍ መሆኑን ያወሳው ሪፖርቱ፣ ይህ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ጀማሪ አገሮች ላይ ወሳኝ ዕርምጃ ስለመሆኑ የአገሮቹን ልምድ ጠቅሶ ሪፖርቱ አብራርቷል፡፡ ነገር ግን ይህ አማራጭ ዘላቂ አለመሆኑን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ የግሉ ዘርፍን በሒደት ወደ መሪነት የማምጣት አማራጭ መታየት አለበት ብሏል፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን የዓለም ባንክ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የተመዘገበው የ10.7 በመቶ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት ከቀጠለ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ለመሠለፍ ከአሥር ዓመት በላይ ላይፈጅባት እንደሚችል አስታውቋል፡፡ በ11 ዓመት ከግማሽ ውስጥ ይህ ግብ በትክክል ሊሳካ ይችላል ያለው የባንኩ ሪፖርት፣ እ.ኤ.አ በ2011/12 የበጀት ዓመት ከዓለም 12ኛው ፈጣን ዕድገት መመዝገብ መቻሉን አውስቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በዓለም ባንክ ሪፖርት የተዳሰሱት የኢኮኖሚው የቁጠባ ምጣኔ ደረጃና የወጪ ንግድ መስተንግዶ ጉዳዮች ደግሞ ከላይ የተጠቀሰውን ግብ ለመምታት ወሳኝ ተብለዋል፡፡ በአንድ በኩል የአገር አቀፍ ቁጠባ ጉዳይ በተለይ አገሪቱ እያስመዘገበችው ካለችው የዕድገት ደረጃ አንፃር በጣም ዝቅ ማለቱ አሳሳቢ ነው ይላል ባንኩ፡፡ በዚህ ረገድ እየተለጠጠ ያለውን የኢንቨስትመንት መጠን በተቻለ መጠን የቁጠባ ደረጃውን ከፍ በማድረግ ኢኮኖሚውን መደገፍ ያስፈልጋል ሲል የዓለም ባንክ ሪፖርት ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል በአገሪቱ የተፈጠረውን የመልቲ ሞዳል ሥርዓት ችግር ጠቅሶ፣ በተለይ በወጪ ንግድ ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ሌላው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አሳስቧል፡፡

ምንጭ፦ * ሪፖርተር የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግሥት ሦስተኛው የዓለም ታላቁ ኢንቨስተር ሆኗል አለ

%d bloggers like this: