የአማራ ብሔር ተወላጆች ዳግም ከጉራፈርዳ እየተፈናቀሉ ናቸው ተባለ

28 Jul

Posted by The Ethiopia Observatory

– ሰማያዊ ፓርቲና መኢአድ ክስ እንመሠርታለን አሉ

በደቡብ ክልል በቤንቺ ማጂ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ እየሩሳሌም ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የአማራ ብሔር ተወላጆች፣ ዳግም እየተፈናቀሉ መሆኑን ሰማያዊ ፓርቲና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አስታወቁ፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች ሐምሌ 18 ቀን 2005 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት መንግሥት ቀደም ብሎ በጉራፈርዳ ወረዳ፣ በሸፒ ቀበሌና በተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ነዋሪ የነበሩት የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀላቸውን ተከትሎ፣ መንግሥት በአፈናቃዮቹ ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ ቢያሳውቅም፣ ዜጐቹ ግን እስካሁን እየተፈናቀሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ተወካይ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው ለዓለም ሕዝብ ጭምር በሰጡት ማብራሪያ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንዲፈናቀሉ የተደረጉ የአማራና የኦሮሞ (የዘር ማጥራት ወንጀል እንዳይመስል) ተወላጆችን ያፈናቀሉ ኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ፣ መንግሥት ዕርምጃ እንደሚወስድና ተፈናቃዮችም ወደ ቀያቸው በአስቸኳይ እንደሚመለሱ የተናገሩ ቢሆንም ተግባራዊ አልሆነም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ቀደም ብሎ ከ21 ሺሕ በላይ የአማራ ተወላጆች ከተፈናቀሉበት፣ ከቤንቺ ማጂ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ እየሩሳሌም ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ከሐምሌ 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ የአማራ ብሔር ተወላጆች እየተፈናቀሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌታሁን በበኩላቸው፣ ‹‹መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳ ስላጡ ትኩረታቸውን ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማድረጋቸውን ይናገራል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በድህነት በዓለም ካሉ አገሮች ከመጨረሻዎቹ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ላይ በሆነችበት ሁኔታ በመንግሥት ላይ አጀንዳ ለማንሳትና ለመንቀፍ ከበቂ በላይ ምክንያት አለ፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹መንግሥት በመገናኛ ብዙኀን ቀርቦ ለዓለም ጭምር ያሰማውን ዲስኩር ተግባራዊ ቢያደርገውና ተፈናቃይ ዜጐች ወደቤታቸው ቢመለሱ፣ መሬታቸው ቢመለስላቸው፣ ለጠፋባቸው ንብረት ካሳ ቢከፈላቸውና በድጋሚ ሌላ የማፈናቀል ወንጀል እንዳይደረስባቸው ጥበቃ ቢያደርግላቸው እኛ ሌላ ምን እንፈልጋለን?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ክልሉ ድረስ በመጓዝና ተፈናቃዮቹን ቃለ መጠይቅ በማድረግ፣ በክልሉ ተወላጆቹ ከተፈናቀሉባቸው ቀበሌዎች፣ የአማራ ተወላጆች በሦስት ቀናት ለቀው እንዲወጡ የተለጠፈውን ስም ዝርዝራቸውን ጭምር በማስረጃነት በመሰብሰብ፣ ሙሉ ማስረጃው ተጨምሮ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰኔ 5 ቀን 2005 ዓ.ም. ደብዳቤ መጻፉን ገልጸዋል፡፡

ለጊዜው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተነሳውን ተቃውሞ ለማብረድ መንግሥት ልዩ ትኩረት ያለው በማስመሰል የተወሰኑ ግለሰቦች መታሰራቸውንና ክስ መመሥረቱን፣ ተፈናቃዮቹ ወደመጡበት መመለሳቸውን የገለጸ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ ተፈናቃዮቹ ወደቤታቸው አለመመለሳቸውን፣ ገሚሶቹ ወደተለያዩ አካባቢዎች ተሰደው በቀን ሥራ የልጆቻቸውን ነፍስ ለመታደግ እየሠሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር በመሆናቸው የተናገሩትን ይፈጽሙ ዘንድ፣ በዓለም አቀፍ የሕግ ምሁሩ፣ ጠበቃና የሕግ አማካሪው ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ከነማስረጃው ደብዳቤ ቢጽፉላቸውም፣ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ምላሽ ሳይሰጧቸው መቅረቱን የፓርቲዎቹ ተወካዮች ተናግረዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ጥንታዊና የረጋ መንግሥት ያላት አገር ነች፤ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች በቅርብ ዘመናት ማንነታቸውን አግኝተው እንኳን እንደኛ አገር የሚያዋርድ ተግባር አይፈጽሙም፤›› ያሉት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር፣ በዚህ ዘመን የዘር ማጥራት ወንጀል ሥራ መሥራት ፍፁም ስህተትና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የጣሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተባረሩ ኢትዮጵያውያን የተፈጸመባቸው ወንጀል በይርጋ የማይታገድ መሆኑን የገለጹት ፓርቲዎቹ፣ በተፈናቃዮቹ ላይ ለተፈጸመው ጉዳት የመጀመሪያው ተጠያቂ የአገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በመሆናቸው፣ እሳቸውን ጨምሮ በክልሉ ያሉ ባለሥልጣናት ደረጃውን ጠብቆ በቅርቡ ክስ የሚመሠረትባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአገር ውስጥ ባሉ የፍትሕ ተቋማት ክሱ ተጀምሮ ውጤታማ የማይሆን ከሆነም፣ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተባርረው እንዲመለሱ መንግሥት ካዘዘ በኋላ እንዳልተመለሱና ከፍተኛ በደል እየደረሰባቸው ነው ስለተባሉት የአማራ ተወላጆች ምላሽ እንዲሰጡን፣ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ አህመድ ናስርን በስልክ ብናገኛቸውም፣ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ከመግለጽ ውጭ ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡

Source: Reporter

ይህንንም ይመልከቱ:

ኢትዮጵያ ወደአደገኛ አግጣጫ እያመራች ነው

Ethiopia: Behind the Ethnic Cleansing in Benishangul-Gumuz

%d bloggers like this: