የመንጃ ፈቃድ ሰልጣኞች በየትኛውም የማሰልጠኛ ተቋማት ትምህርት መጀመር እንደሌለባቸው ወ/ሮ ትብለጽ አስግዶም አስታወቁ: ፋና ስለዚህ ምናለ?

3 Oct

Posted by The Ethiopia Observatory

Tiblets Asgedomአዲስ አበባ መስከረም 21/2006 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ማንኛውም የመንጃ ፈቃድ ሰልጣኝ ከጥቅምት 1ቀን 2006 በፊት በማናቸውም የአሸከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ ትምህርት መጀመር እንደሌለበት አሳሰበ። ቢሮው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የአሸከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ ያደረገውን ግምገማ ውጤይ ይፋ አድርጓል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ትብለጽ አስግዶም ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በአዲስ አበባ ከተማ የአሸከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ ረዥም ጊዜ የወሰደ ክትትልና የቅርብ ግምገማ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚሁ መሰረት ተቋማቱ የተቀመጠላቸውን መስፈርት ተግባራዊ ማድረግ አለማድረጋቸውን እንዲሁም ያሉበትን ደረጃ በመገምገም እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

የቢሮው የትራንስፖርት ዘርፍ የኦፕሬሽን ዋና የስራ ሒደት መሪ አቶ ወጋየሁ አሰፋ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ58 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ በተካሄደ ፍተሻ ከ52 ነጥብ 5 እስከ 80 በመቶ ማግኘታቸውን አብራርተዋል፡፡ ፍተሻ ከተካሄደባቸው ተቋማት መካከል አስሩ ከ70 በመቶ በላይ በማግኘታቸው የሚሰጡትን ስልጠና እንዲቀጥሉና ክፍተቶቻቸውን በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲያሟሉ ተወስኗል። አቶ ወጋየሁ እንዳሉት 33 ተቋማት ደግሞ ውጤታቸው ከ60 እስከ 69 በመቶ በመሆኑ ለቀጣዮቹ ሶስት ወራት ስልጠና እንዳይሰጡ ታግደዋል።

ተቋማቱ ቀደም ሲል ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ላስተላለፏቸው ሰልጣኞቻቸው ብቻ ለአንድ ዙር እንዲያስፈትኑ ተወስኗል። ቀሪዎቹን ሰልጣኞች ደግሞ ሌሎች ስልጠና ለሚሰጡና መስፈርቱን ላሟሉ ተቋማት እንዲያስረክቡ ታዘዋል።

በቢሮው ግምገማ ውጤት መሰረት 15 ተቋማት ውጤታቸው ከ59 ነጥብ 9 በታች በመሆኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የማሰልጠን ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ተወስኗል። ተቋማቱ ቀድመው ለቢሮው ያሳወቋዋቸው ሰልጣኞች ካሉ ለአንድ ዙር ብቻ እንዲስፈትኑ ታዘዋል።

ሃላፊው እንዳሉት ቢሮው በስልጠና ስራቸው እንዲቀጥሉ የተፈቀደላቸውንና የታገዱት ተቋማትን ዝርዝር ጥቅምት 1ቀን 2006 ይፋ ከማድረጉ በፊት ማንኛውም ሰልጣኝ በየትኛውም ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ ትምህርት መጀመር የለበትም።
 
ምንጭ፡

መስከረም 21:2006
 
===========================================================================================================
ይህንኑ ዜና ፋና እንዴት እንደዘገበው ከዚህ በታች ይመልከቱ

ጥያቄው ሁለቱ ባለሥልጣኖች (ወ/ሮ ትብለጽ አስገዶምና አቶ አቶ ወጋየሁ አሰፋ) ለጋዜጣዊ መግለጫ አብረው ከቀረቡ በኋላ ፋና ብሮድካስቲንግ ወ/ሮ ትብለጽ የሚባሉ ኅላፊ እንዳልነበሩ አንዴም ሳይጠቅሳቸው ያልፋል። ለምን ይሆን፡ እርሳቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ሆኖ ሳለ?
==============================================================================================================

በአዲስ አበባ 48 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ማሰልጠን እንዲያቆሙ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ካሉ 58 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ 48 ያህሉ በጊዜያዊነት ማሰልጠን እንዲያቆሙ ተወሰነ።

የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ባወጣው መስፈርት መሰረት 13 መስፈርቶችን በመተግበር የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማትን ይመዝናል።

በመስፈርቱ መሰረት 85 በመቶ ያመጡ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት በጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ማስልጠናቸውን እንዲቀጥሉ ሲፈቀድ፥ ከዚያ በታች የሆኑት ግን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የማሰልጠን ፈቃዳቸው እንዲቀማ ነው የተቀመጠው ህግ የሚያዘው።

ሆኖም በ2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባሉ 58 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ በተደረገ ግምገማ 58 ያህሉ ከሰማንያ በመቶ በታች በማምጣታቸው ፤ በአዲስ አበባ የማለፍያ ነጥቡ ዝቅ እንዲል ተወስኗል።

በዚህም ከ70 እስከ 80 በመቶ ያመጡ በጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ማሰልጠን እንዲቀጥሉና በሁለት ወራት ውስጥ ክፍተታቸውን እንዲያስተካክሉ ፣ ከ60 እስከ 69 ነጥብ 9 በመቶ ያመጡ ደግሞ ማሰልጠን አቁመው ጉድለታቸውን እንዲያሟሉ ፣ ከ59 ነጥብ 9 በመቶ በታች ያመጡ ደግሞ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ፍቃዳቸው እንዲሰረዝ ወስኗል።

አስር ተቋማት ብቻ ከጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ጋር ስልጠናቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉን ነው በአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ የትራንስፖርት ዘርፍ የኦፕሬሽን ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ወጋየሁ አሰፋ የተናገሩት።

33 ተመሳሳይ ተቋማት ለሶስት ወራት ከማሰልጠን ታግደው እና በሶስት ወራት ውስጥ ጉድለቸውን አስተካክለው ወደ ስራ መመለስ ይችላሉ ተብሏል።

15 ያህል ተቋማትም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ፈቃዳቸው የሚሰረዝ ሲሆን ፥ በ6 ወራት ውስጥ ያሉባቸውን ጉድለቶች ካላስተካከሉ ፍቃዳቸው እንደማይታደስ ነው የተገለጸው።

ይህ ከመስከረም 30 ጀምሮ ተግባራዊ ስለሚደረግ አሽከርካሪነት ለመሰልጠን እንደ አዲስ መመዝገብ የሚፈልጉ ሰዎች እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2006 ዓ.ም እንዳይመዘገቡ አቶ ወጋየሁ አሳስበዋል።

በ58 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ በተደረገ ግምገማም 23 የሚሆኑት በቂ የማስተማርያ ቁሳቁስ ሳይኖራቸው፣ 51 የሚጠጉት ተቋማት ደግሞ ብቃት በሌላቸው መምህራን ሲያስተምሩ በመገኘታቸው ለቅጣት መዳረጋቸውም ነው የተመለከተው።

የታገዱት ማሰልጠኛ ተቋማት ስም ዝርዝርም ለተቋማቱ ደብዳቤ ከደረሰ በኋላ ይፋ እንደሚደረግም ነው አቶ ወጋየሁ ያስታወሱት።

በካሳዬ ወልዴ ከፋና
 

*Updated.

%d bloggers like this: