ሙሉ ክፍያ የከፈሉ የ40/60 ተመዝጋቢዎች ራሳቸውን ችለው ቤቶቻቸውን እንዲያሠሩ ማግባባት ተጀመረ

22 Oct

በውድነህ ዘነበ: ከሪፖርተር – Posted by The Ethiopia Observatory

የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን መቶ በመቶ የከፈሉ የ40/60 ተመዝጋቢዎች በመኖርያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር ወደ ተነደፈው ፕሮግራም እንዲዛወሩ የአዲስ አበባ አስተዳደር ማግባባት ጀመረ፡፡

መንግሥት በቅርቡ የመኖርያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ ባወጣው አራት የመኖርያ ቤቶች ፕሮግራም የ40/60 እና የመኖርያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር ፕሮግራሞች የተሻለ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት ስበው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ነገር ግን በመኖርያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፕሮግራም ለሚገነቡ ቤቶች ለተነሺዎች ካሳ እንዲከፈል የሚያስገድድ በመሆኑ፣ የተሻለ ገቢ ያላቸው ቤት ፈላጊዎች በአብዛኛው ትኩረታቸውን 40/60 ፕሮግራም ላይ አድርገው ምዝገባቸውን አካሂደዋል፡፡

በ40/60 ፕሮግራም የተመዘገቡ የተሻለ ገቢ ካላቸው ነዋሪዎች መካከል የማይናቅ ቁጥር ያላቸው የሚጠበቅባቸውን ሒሳብ መቶ በመቶ መክፈላቸው ይታወቃል፡፡ ይህንን ያጤነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እነዚህን መቶ በመቶ የከፈሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማግባባት ወደ መኖርያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፕሮግራም እንዲዛወሩ ለማድረግ ጥረት ማድረጉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሥር የሚገኘው የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማደራጃ ጽሕፈት ቤት ምንጮች እንደገለጹት፣ የተሻለ ገቢ ያላቸው ቤት ፈላጊዎች ወደ 40/60 ፕሮግራም ትኩረታቸውን ያደረጉት ለተነሺዎች በሚከፍለው የካሳ ክፍያ ሥጋት አድሮባቸው ነው፡፡ እነዚህ ምንጮች እንደሚሉት፣ ለግንባታው ከሚፈለገው ቦታ ላይ ለሚነሱ ባለይዞታዎች የሚከፈለው ክፍያ በካሬ ሜትር 500 ብር ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ግንባታው በሚያርፍበት ቦታ ልክ ተባዝቶ በማኅበሩ አባላት ቁጥር ሲካፈል የሚመጣው ገንዘብ አነስተኛ ሊሆን ይችላል የሚሉት ምንጮች፣ ካሳ የማያስከፍሉ ቦታዎችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ያስረዳሉ፡፡

ነገር ግን የአዲስ አበባ አስተዳደር ይህንን የካሳ ክፍያ መመርያ ረቂቅ በማዘጋጀት ከከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር ጋር እየመከረበት ይገኛል፡፡ ረቂቁ በቅርቡ ፀድቆ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በእስካሁኑ ሒደት በማኅበራት ተደራጅተው ቤት ለማግኘት ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁት አንድ መቶ ማኅበራት ብቻ ናቸው፡፡

ምንጮች እንደሚሉት፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር በርካታ ማኅበራት ይደራጃሉ የሚል ግምት ቢኖረውም የተደራጁት ግን አነስተኛ ናቸው፡፡ አንድ የከተማው አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ ከ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ውስጥ መቶ በመቶ የከፈሉት ወደ ማኅበራት እንዲዛወሩ የተፈለገው እነዚህ ወገኖች መቶ በመቶ የመክፈል አቅም ካላቸው፣ የራሳቸውን ቤት ራሳቸው እንዲገነቡና መንግሥት ላይ ያለው ጫና እንዲቀንስ በሚል ሐሳብ ነው፡፡

በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም 81,257 ነዋሪዎች መመዝገባቸው ይታወሳል፡፡ በሦስቱም የመኖርያ ቤቶች (10/90 እና 20/80) ፕሮግራሞች የተመዘገቡ ነዋሪዎች 2.5 ቢሊዮን ብር መቆጠባቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የእነዚህን ቤቶች ግንባታ ለማስጀመር መንግሥት ተጨማሪ 7.5 ቢሊዮን ብር እንደመደበ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሐሙስ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጸዋል፡፡
 

ይህንንም ይመልከቱ

    The Diaspora Controversy

 

%d bloggers like this: