Ethiopia to become wheat exporter – ‘thanks to 1 x 5 system, instead of wheat beggar’ – PM Hailemariam!

20 Jan

Posted by The Ethiopia Observatory

(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል አርሲ ውስጥ ከአንድ ሄክታር መሬት ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ 111 ነጥብ 5 ኩንታል የስንዴ ምርት ከአርሶ አደሩ ማሳ ማስመዝገብ ተችሏል። ለዚህ ከፍተኛ ውጤት መገኘት ደግሞ በፈጣንና ዘላቂ ልማት ድህነትን ለማስወገድ የተቀየሰው ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከዘልማዳዊ አሠራር ተላቆ በቴክኖሎጂ በምርምርና ስልጠና ታግዞ በመሰራቱ ነው።

ባለፉት ዓመታት የተመዘገበው ተከታታይ ዕድገትም ለቀጣዩ የተጠናከረ ሥራ መነሻ ሆኖ የሚታይ ሲሆን ጅምሩን አጎልበቶ ማስቀጠል ከተቻለ የሚታሰበው የዕድገት ግብ እውን መሆኑ የማይቀር እንደሆነ ይታመናል ።

የተገኘው የኢኮኖሚ ዕድገትም በዋነኛነት በግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ ምክንያት ለስኬት የበቃ መሆኑ ግልጽ ነው። ቀደም ሲል አርሶ አደሩ ይቀርብለት የነበረውን የተሻሻለ ቴክኖሎጂና ግብዓት ተቀብሎ ባለው ውስን መሬት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የነበረው ግንዛቤ አነስተኛ ነበር ።

ዛሬ ግን አርሶ አደሩ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችንና ግብዓቶችን ኢንዲጠቀም ለማስቻል በተፈጠረው መድረክና የተግባር ሙከራ በሂደት የአርሶ አደሩን የተሻሻለ ቴክኖሎጂና የግብአት ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል ።

ሞዴል አርሶ አደሮችን በመምረጥ የተሻሻሉ ቴክኒሎጂዎችና የግብአት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ምርታቸውን ለማሳደግ እንዲችሉ በየደረጃው በተደረገው ጥረት ብዙሃኑን አርሶ አደር ፍላጎት ለማምጣት አስችሏል ።

በዚሁ ጥረት በየአመቱ ምርትና ምርታማነትን በዓይነትና በመጠን ለማሳደግና በርካታ አርሶ አደሮችን ወደ ባለሀብትነት ለማሸጋገር ተችሏል። በአነስተኛ የአርሶ አደር መሬት ምርታማነትን በማሳደግ ኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት አይታሰብም በማለት ለሚሞግቱ ኃይሎችም በተገቢው መንገድ ምላሽ ሰጥቷል ።

በሀገሪቱ ከፍተኛ አምራች ከሚባሉ አከባቢዎች አንዱ በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው አርሲ ዞን ነው ።የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የዞኑን የ2005/2006 ምርት ዘመን የግብርና ሥራ እንቅስቃሴን ለመጎብኝት የአርሶ አደሩ ቀዬ ድረስ በቅርቡ ተገኝተው ነበር ።

በቆይታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በአርሲ- ሙኔሳ ፣ዲገሉናጢጆ ወረዳዎች የሞዴል አርሶ አደሮችን የእርሻ ማሳ በመጎብኘት ባዩት ሁሉ በእጅጉ ተደምመዋል ።

Wheat farm in Arsi (Courtesy of ENA)

Wheat farm in Arsi (Courtesy of ENA)

የእርሻ ማሳቸው የተጎበኘው የቀጨም-ሙርቂቻ እና የፍቴ አንድ ቀበሌ ገበሬ ማኀብር ሞዴል አርሶ አደሮች መካከል አብዮት ውቤ ፣ተስፋዬ አበበ እና ወይዘሮ አለሚቱ ደሜ በምርት ዘመኑ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት በመተጋገዝ ስንዴን በመስመር በመዝራትና ለሰብል ተገቢውን ክብካቤ በማድረጋቸው ከአንድ ሄክታር እስከ 120 ኩንታል እናገኛለን ብለው እንደሚጠብቁ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ገልጸውላቸው ነበር።

ከእነዚሁ አርሶ አደሮች መካከል ታዲያ ተስፋዬ አበበ የተባሉት ታታሪ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ሄክታር መሬት ላይ 111 ነጥብ 5 ኩንታል የስንዴ ምርት በማግኘት ታሪክ ሰርተዋል።

አርሶ አደር ተስፋዬ እንደሚሉት ለ2005/06 የምርት ዘመን ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በተለይ ስንዴን በመስመር በመዝራት፣ ምርጥ ዘር; ዩሪያና ዳፕ ማዳበሪያን በማመጣጠንና በመጠቀም እንዲሁም ለሰብል ተገቢውን እንክብካቤና ክትትል በማድረጋቸው ለውጤት በቅተዋል ።

አምና ከተመሳሳይ መሬትያገኙት 60 ኩንታል የሚጠጋ ሲሆን በዘንድሮው የምርት ዘመን የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረጋቸውና የዝናብ ስርጭቱና የአየሩም ፀባይ ምቹ በመሆኑ ውጤቱም የዚያኑ ያህል አርኪ በመሆኑ መደሰታቸውን ለጉብኘቱ ተሳተፊዎች ገልጠዉላቸዋል።

በመኽሩ እርሻ እንቅስቃሴ ከወረዳቸውና ከዞኑ አርሶ አሮች ጋር በምርታማነት ለመሸለም እየተፎካከሩ ነበር ነገር ግን ውጤታቸው ከዞኑና ከክልሉ አልፎ በአገር አቀፍ ደረጃ ስላበቃቸው ይበልጥ ለመስራት ተነሳስተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጉብኝታቸው ወቅት አስተያየታቸውን ለመስጠት ቀዳሚ ነበሩ ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ከአነስተኛ ማሳ ላይ ከፍተኛ ምርት ማግኘት አይቻልም ለሚሉ ወገኖች አርሶ አደሩ ተግቶ በመስራት ይህን አፍራሽ አስተያየታቸዉን ዉድቅ አድረጎታል ። የተገኘዉ ከፍተኛ የምርት ውጤት የአገሪቱን የግብርና ፖሊሲ ትክክለኛነት እንደሚያረጋግጥም አጽእኖት ሰጥተዉ ተናግረዋል።

ይህም ኢትዮጵያ የስንዴ ሻጭ እንጂ የስንዴ ለማኝ የማትሆንበት ደረጃ ላይ መደረሷን አመለካች መሆኑን ጠቁመው ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር በየደረጃው የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

አንድ ለአምስት የአካባቢ አደረጃጀቶች የግብርናውን ዘርፍ ዘመናዊ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት በመደገፍ በኩል ውጤታማ ተግባር በማከናወን ላይ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ ያወሱት ።

አምራች ኃይሉ የግብርና ግብአትን በአግባቡ በመጠቀም ;ዘር በመስመር በመዝራት፣ በአነስተኛ መሬት የቤተሰብን ጉልበት ተጠቅሞ ከፍተኛ ምርት ማግኘት እንደሚቻል በተጨባጭ ማስመስከሩን እንዲሁ።

መንግስት የግብርናው እድገት በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ሰፊ ስራ መስራቱን የተናገሩት አቶ ኃይለማርያም በዚህም ለምርትና ምርታማነት ብሎም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ዘርፉ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመኑ ግብርናውን ከወቅቱ ገበያ ስርአት ጋር የተሳሰረ ለማድረግ ዘመናዊ አሰራርን መከተሉ የተሻለ ተጠቃሚነትን ስለሚያረጋግጥ ሁሉም አርሶ አደሮች የሞዴል አርሶ አደሮችን ፈለግ መከተል እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ማርያም አሳስበዋል ።

የአርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳዳት ነሻ በበኩላቸው በ2005/06 የምርት ዘመን በዞኑ 24 ወረዳዎች ከለማው 599ሺ 401 ሄክታር መሬት ላይ ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል ።

ባለፉት ሦስት አመታት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሕዝባችንን የኑሮ ሁኔታ ለመቀየር እና የአምስት አመቱን መሪ እቅድ ለማሳካት በዞኑ የሚገኙትን ከ325ሺ በላይ አርሶ አሮች በ64ሺ 645 የልማት ሠራዊት እንዲደራጁ ተደርጓል።በዚህም አርሶ አደሩ ሙሉ የግብርና ፓኬጅን ለመተግበር ያሳየው ቁርጠኝነትና ለልማት ያለዉን መነሳሳት አመልክቷል ብለዋል ።

በተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችና አሰራር በምርት ማሳደጊያ ግብአት አጠቃቀም የነበረበትን ክፍተት ለመሙላት ቁርጠኝነቱንም አሳይቷል ። የ2005 ግብርና ሥራ አፈጻጸም ከቀበሌ እስከ ዞን ተገምግሞ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተለይተው ወደ ስራ በመገባቱ በያዝነው የምርት ዘመን ከሌላው ጊዜ በተሻለ መልኩ የአከባቢው አርሶ አደሮች ሙሉ ጊዜያቸውንና አቅማቸውን አሟጠው ለመጠቀም አስችሏቸዋል- እንደ ዋና አስተዳዳሪው::

በዚህም መሰረት ዘርን በመስመር ለመዝራት፣ ለአንድ ሄክታር አንድ ኩንታል ማዳበሪያ ለመጠቀም፣ የቢቢ ኤም ማረሻ መሳሪያን ጨምሮ የተባይና የአረም መከላከያ ኬሚካል በአግባቡ ለመጠቀምና ከዘር ስራ አንስቶ እሰከ ምርት አሰባሰብ ድረስ ለሰብል እንክብካቤ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀሳቸውን አስረድተዋል ።

በግንባር ቀደም አርሶ አደሮች የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በሁሉም አርሶ አደሮች ዘንድ ለማስፋፋት ብርቱ ርብርብ መደረጉን ገልጸው በዚህም እንቅስቃሴ 349ሺ 967 ሄክታር መሬት በመስመር 68ሺ 503 ሄክታር መሬት ደግሞ በቢቢ ኤም ማረሻ መሳሪያ ለመዝራት መቻሉን ተናግረዋል ።

የስብል ምርታማነትን ለማሳደግ ለመስኖ; ለበልግና ለመኽር እርሻ ሥራ 407ሺ 727 ኩንታል ዳፕና ዩሪያ ማዳበሪያ እንዲሁም 152ሺ 939 ኩንታል የተለያዩ ምርጥ ዘሮች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ጠቁመዋል ።የመሬት ለምነትንና እርጥበትን ለረዥም ጊዜ ጠብቆ በማቆየት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ 5 ሚሊዮን ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የዞኑ አርሶ አደሮች አዘጋጅተው በመጠቀም ውጤታማ ሆነዋል።

በዞኑ 24 ወረዳ ከሚገኙ 337ሺ 832 አባወራና እማወራ አርሶ አደሮች መካከል 78 ነጥብ 77 በመቶ የሚሆኑት የተሻሻለ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የግብርና ፓኬጅን ሙሉ ለሙሉ ተግብረዋል። በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላትና የልማት ጣቢያ ሰራተኞች እሰከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ለልማት ኃይሉ አርሶ አደር ተከታታይነት ያለው ሥልጠናና የሙያ እገዛ በማድረግ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገባቸውን ከአቶ ሳደት ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።

የአርሲ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊና የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጎሳ ጸጋዬ የምርምር አካላት፣ የግብርና ባለሙያዎች እና የመስተዳድር አካላት በተገኙበት ባለፈው ህዳር በተካሄደው ውቂያ 111 ነጥብ 5 ኩንታል ከፍተኛ ምርት የተመዘገበው በዲገሉ-ጢጆ ወረዳ ፊቴ ከተራ ቀበሌ ገበሬ ማኀበር ውስጥ ነው።

ምርቱን ያገኘው አርሶ አደር ተስፋዬ አበበ ባለፈው ምርት ዘመን በዞኑ ስሬ ወረዳ ውሰጥ ተመዝግቦ የነበረውን ከሄክታር 101 ኩንታል የስንዴ ምርት ክብረ ወሰን ለመስበር ችሏል ። በተለይ የዞኑ ምርታማነት በሚፈለገው መልኩ እንዲጨምር የግንዛቤና የአመለካከት ማነቆዎች ያሉባቸውን አካባቢዎችን በመለየት አመራር አባላትን፣ ባለሙያዎችንና አርሶ አደሮችን ያሳተፈ ጉባኤ መካሄዱ ለውጤቱ መገኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ይናገራሉ።

በዞኑ ከ148ሺ የሚበልጡ ሞዴል አርሶ አደሮችን ጨምሮ ሁሉም የዞኑ አርሶ አደሮች ከግብርና ምርምር እና ሌሎች ተቋማት በሚያቀርቡላቸው የተሻሻሉ ዝርያዎች በመጠቀም ምርታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ ላይ ናቸዉ።

የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ በሞዴል አርሶ አደሮች የተገኘውን መልካም ተሞክሮ በሁሉም ዘንድ ተግባራዊ ለማድረግ በተደረገው ጥረትም ሰብልን በመስመር ማልማት ልዩ ትኩረት መሰጠቱንና በዚሕም አበረታች ውጤት መገኘቱን አስታውቀዋል።

የቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገላልቻ በበኩላቸው አርሶ አደሮች የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ልምዳቸውና ፍላጎታቸው በእጅጉ እያደገ በመምጣቱ በገበሬ ማሳ ከሄክታር ከ100 እስከ 114 ኩንታል መርት ስንዴ ሊገኝ እንደሚችል አረጋግጠዋል። ከልሉ በዞኑ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አርሶ አደሮችን ቁጥር ለማስፋፋትና በጥናትና ምርምር ይበልጥ ለመደገፍ የሚያስችለውን ፕሮግራም በማካሄድ ላይ መሆኑንም ጨምረው አስታውቀዋል።
 

One Response to “Ethiopia to become wheat exporter – ‘thanks to 1 x 5 system, instead of wheat beggar’ – PM Hailemariam!”

Trackbacks/Pingbacks

  1. AU leaders end 22nd summit in Addis Abeba, without rising above the usual sham and hypocricy | THE ETHIOPIA OBSERVATORY - February 4, 2014

    […] As for agricultural successes, in Ethiopia the regime did not even want to wait until the end of the Comprehensive Africa Agriculture Development Program (CAADP) successor for 2025 was adopted. It would be recalled that it was on January 18, 2014 that Prime Minister Desalegn announced Ethiopia’s readiness to soon become wheat exporter. […]

    Like

Comments are closed.

%d bloggers like this: