በ13 ቢልዮን ብር የብረታብረት ኮርፖሬሽን ኢንቨንቶሪ ሽፋን፡ የሕወሃት ባልሥጣኖች ለኩባንያዎቻቸው (EFFORT) ታክስ ቅናሽ ጠየቁ

2 Feb

የአዘጋጁ አስተያየት፥

  የገበያ ዕጦት እየገፋ ሲሄድ፡ በተያዘው የምርት ዓመት ውስጥ ክምችቱ የበዛ ኢንቬንቶሪ መፍጠሩ የታወቀ ነው። ይህ ደግም ገንዝብ አስሮ ይይዛል። በወቅቱ ካልተቀረፈ፤ እንዲህ ያለ ችግር፡ ኪሣራ ያስከትላል፡ የሠራተኞችን መባረርንና የድርጅቱን መዘጋት ያመጣል።

  የዚህም ችግር መንስኤ፡ አንድም የኤኮኖሚው መዳክም፡ ሌላም፣ የአምራቾቹ ዋጋ ውድነት፡ ወይንም የምርቶቻቸው ላይ ተጠውቃሚው ኅብረተስብ ያጋጠመው የጥራት እምነት ችግር ሊሆን ይችላል። በተለይም በብረታ ብረት ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን ሥራዎች ይህ የአመኔታ ዕጦት ብዙ ጊዜ ተነስቷል።

  ተደረገ ተብሎ በጄነራሉ የሚነገርለት ጥናት ስለዚሀ ጉዳይ በዕልፍታ ዳሩን እንኳ አይነካም።

  ያለአንዳች ጥርጥር፡ 13 ቢልዮን ብር ($677 ሚልዮን) በኢንቪንቶሪበ ብረታ ብረት ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን መክማቸቱ አስፈሪ ከመሆኑም በላይ፤ ኢትዮጵያ እጅግ ብዙ ያስውራችለት ማንፋክችሪንግ እንኳ ባለፉት ሶስት የአምስቱ ዓመታት ፕላን ወደዚህ ጠጋ ያለ ገቢ እንኳ አላስገኝም። ብዙውን የታክስ ገቢ ለውጭ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ አስላፋ ሰጥታ: ዜጎቻችን በባርነት እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑን በቅርቡ የፈረንሣ ቴቭ2 በመስከረም ዶኪመንታሪው ማረጋገጡ ይታወሳል።

  ብረታ ብረት ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን በ2003 ከተቋቋመ ጀምሮ፡ በኢትዮጵያ ኢንዱድስትሪ ልማት ስም፡ በትዕዛዝ የመንግሥት ድርጅቶ – ለምሳሌ አንበሳ አውቶቡስ፡ ወዘተ – ኢንዲገዙ ሲደረግ ተቆይቷል። ይህም አዳዲስ አውብቶብሶች ተብለው የመጡት መንገድ ዳር ፈዘው መቅረታቸው፡ ከመብራት ኃይልም ጋር በተደጋጋሚ የተከሰተው ውዝግብና ሙስና ይታወሳል።

  በተጨማሪም፡ ድርጅቱ ዘላቂነት ያለው ፕሮግራም ይዞ የሚሠራ ሳይሆን፡ ያየው ሁሉ የሚያምረው ነው። ሆቴሎች ገዝቶ ከማስተዳደር ባሻገር (ለጄኔራሎቹ መናኛ በየከተማዎች)፡ የግል የባህር ትራንስፖርት መርክብ ካልገዛሁ ብሎ፡ የመርከብ ግዥና ሽያጭ ውስጥ መግባቱ ሲታወስ፡ ምን ዐይነት አዙሪት ውስጥ መሆኑን ማየታ አያዳግትም።

  ለማንኛውም፡ ችግሩ ከአምራች ድርጅቶቹ አይደለም ቢባል እንኳ፡ ሌላው መንስኤ መንግሥት የሚክደው የኤኮኖሚ መቀዛቀዝ በውል ገብቷል ማለት ነው። ይህም ማለት፡ አንድም የኤኮኖሚው መዳክም፡ ሌላም፣ የአምራቾቹ ዋጋ ውድነት፡ ወይንም ምርቶቻቸው ላይ ተጠውቃሚው ኅብረተስብ ያጋጠመው የጥራት እምነት ችግር ሊሆን ይችላል – በተለይም በብረታ ብረት ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን ሥራዎች።

  ቀድሞውንስ ቢሆን፡ በሚስቱ ተራኪነት አይደል እንዴ (ራሷን በትግሬዎች ዘንድ ያላትን ተቀባይነት ለመካብ)መለስ በአምስት ዓመታት ውስጥ ትግራይን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ሲሠራ ነበር ብላ የሕወሃትን ምሥጢር የዘከዘከችው!

  በዚህ ሁኔታ ውስጥ፡ ችግሮቹን ለማቃለል ከመጣር ይልቅ፡ የራሳቸውን ድካም ሸፋፍነው፡ ከማስብ መናገር የሚቀላቸው ገልስቦች ከግንባር በመሆን፡ ታክስ ለማስቀነስ የሚያደረገው ሙከራ አሳፋሪ ነው። ይህንን ነው የሕወሃት ባልሥልጣኖች ራሳቸውን ለመጥቀም ሲሉ፡ የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ ግንባታ ሽፋን ዘይቤአቸው አድርገው የቀረቡት።

  ሌላው ጉዳይ፡ የኢትዮጵያና የብዙ አፍሪካ አገሮች የፖሊሲ ችግር፡ በቂ ታክስ ከአምራች ድርጅቶች ለመስብስብ አለመቻል መሆኑ እየታወቀ: እንዲሁም የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታተ ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናንም በ 2013 Africa Progress Report እንዳመላከቱትና፡፡ ሌላው ቀርቶ በዚህ ሣምንት የወጣው አዲሱ የዩኔስኮ ጥናት (Teaching and Learning: Achieving Growth for All) ጭምር በተለይም ኢትዮጵያን አስመልክቶ እንደዘገበው፡ አሁን ሕወሃት ክባንያውን ለመጥቀም (EFFORT): ጄኔራሉን ከፊት – ከመሃል ዋና የኢንዱስትሪ ማዕከሉን (መሥፍን ኢንጂነሪንግና ሠልፈኞቹን) – ቻይናን ከጀርባ አስልፎ (ሊፋን) – ለታክስ ክፍያ ቅነሳ ዘመቻ መጀመሩ ወደ ሌላው አሳዝኝ አፋኝ ማፊያዊ ምዕራፍ ኢትዮጵያ መሸጋገሯን የሚጠቁም ነው።

  ታዲይ ለሕወሃት ባልሥጣኖች ክፉኛ የተሟሸ ጣዕማቸው ሲዳብር ገቢያቸው መመንመኑ እምዬ ኢትዮጵያ መንጥፏ እነርሱንም ጎድቷቸው ይሆን?

 

Posted by The Ethiopia Observatory

  – ኮርፖሬሽኑ ብቻ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ የምርት ክምችት ገጥሞታል

የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንና ሌሎች የግል የኢንጂነሪንግ ተቋማት ዘርፉ በከፍተኛ የገበያ እጦት ችግር ውስጥ መውደቁን በመግለጽ፣ አስቸኳይ የፖሊሲ ለውጥና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ለመንግሥት ባቀረቡት ቅሬታ አስታወቁ፡፡

ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እንደግዝፈቱና እንደ ዓመታዊ የምርት መጠኑ ዋነኛ የገበያ እጦት ችግሩ ገፈት ቀማሽ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከሌሎች 36 የሚሆኑ የግል ኢንጂነሪንግ ተቋማት ጋር ሆኖ ነው አቤቱታ ያቀረበው፡፡ ለአብነት ያህል መስፍን ኢንጂነሪንግ፣ ማሩ ብረታ ብረት፣ በላይ አብ ኢንጂነሪንግ፣ አምቼ፣ ሊፋንና ሌሎችም የገጠሟቸውን ተመሳሳይ የገበያና ሌሎች ችግሮች በማስጠናት ለመንግሥትና ለባለድርሻ አካላት አቅርበዋል፡፡

የችግሩ ስፋትና ሊፈጥር የሚችለውን የኢኮኖሚ ቀውስ በመረዳት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመለከታቸውን የመንግሥት ተቋማትና ከፍተኛ ኃላፊዎችን፣ እንዲሁም የኢንጂነሪንግ ምርት ተጠቃሚዎችን ባለፈው ሐሙስ በፓርላማው የመሰብሰቢያ አዳራሽ በመጋበዝ የዘርፉን አጠቃላይ ችግር የዳሰሰ ውይይት እንዲካሄድ አድርጓል፡፡

ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በአውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ፣ በኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች፣ በእርሻ መሣሪያዎችና መለዋወጫዎች፣ በአጠቃላይ ማሽኖችና መለዋወጫዎች፣ በአጠቃላይ የኤሌክትሪክ ምርቶች መሰማራቱ ሲታወቅ፣ በግል ከተቋቋሙ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር በትስስር እንደሚሠራ የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር የመሪነት ሚና ተሰጥቶት በ2003 ዓ.ም. መቋቋሙ ሲታወስ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎችን፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን፣ የእርሻ መሣሪያዎችን፣ ማሽነሪዎችንና መለዋወጫዎችን በብዛት ለገበያ በማቅረብ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ይሁን እንጂ ኮርፖሬሽኑ ያቀረባቸው ምርቶች ከማምረት አቅሙና በአገሪቱ ካለው የገበያ ፍላጐት ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ ያረጁ የመንግሥት ፖሊሲዎች፣ ተደራራቢ ታክሶች፣ ተጠቃሚዎች ለአገር ውስጥ ምርቶች ያላቸው ዝቅተኛ አመለካከትና የብድር አቅርቦት እጥረት ኮርፖሬሽኑ ያመረታቸውን ምርቶች በመጋዘኑ አከማችቶ እንዲቀመጥ ማድረጉን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

Gen. Kinfe Dagnew

Gen. Kinfe Dagnew

ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ምርቶቹ ገበያ አጥተው ተከማችተው እንደሚገኙ ኮርፖሬሽኑ ያቀረበው ጥናት ያስረዳል፡፡ ከዚህ ውስጥ 10.2 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን የምርት ክምችት የሚወክሉት የእርሻ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ኮርፖሬሽኑ አጥንቶ ያቀረበው ሪፖርት በተሽከርካሪ ተጐታች አካላት ቅጥቀጣና መገጣጠም ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ የተመረጡ የግል ተቋማት የገበያ እጦት ችግርንም ዳሷል፡፡

በዚህም መሠረት ማሩ ብረታ ብረት፣ መስፍን ኢንጂነሪንግ፣ በላይ አብ ኃላፊነቱ የተወሰነ ማኅበር፣ አሚዮ ኢንጂነሪንግና አምቼ ኢንጂነሪንግ ከ2004 እስከ 2006 ዓ.ም. ጊዜ ውስጥ ያመረቷቸውና ገበያ አጥተው በክምችት የሚገኙ 89.02 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ምርቶች መኖራቸውን ያስረዳል፡፡

‹‹ይህ ከፍተኛ የገበያ ችግር የተፈጠረበት ምክንያት የአገሪቱ ኢኮኖሚ መግዛት የማይችል ሆኖ አይደለም፡፡ ቀረጥና ታክስ ላይ ያለው የመንግሥት አሠራር ችግር ስላለበት ነው፤›› ሲሉ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል ክንፈ ዳኘው ገልጸዋል፡፡

የአገር ውስጥ አምራቾች እያመረቱ ለገበያ እያቀረቡ በሚገኙበት ወቅት አስመጪዎችም ተመሳሳይ ምርት ከውጭ ያውም የተሻለ የታክስና ቀረጥ ጠቀሜታ አግኝተው እያስገቡ ይገኛሉ ሲሉ፣ በአገሪቱ ያለው ተደራራቢ የታክስ ሥርዓት የአገር ውስጥ አምራቾችን እየጐዳ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአገር ውስጥ እየተመረቱ ለሚገኙ የኢንጂነሪንግ ውጤቶች በግብዓትነት የሚያገለግሉ ጥሬ ዕቃዎችና ሌሎች ወደ አገር ሲገቡ ኤክሳይዝ ታክስ እንደሚከፈልባቸው፣ ግብዓቶቹን በመጠቀም የሚፈጠረው የኢንጂነሪንግ ውጤት (መኪናና ማሽነሪዎች) ለገበያ በሚቀርቡበት ወቅት በድጋሚ ኤክሳይዝ ታክስ እንደሚከፈልባቸው ብርጋዴር ጄነራል ክንፈ አስረድተዋል፡፡

አስመጪዎች ግን ለሚያስገቡት መኪናም ሆነ ማሽነሪ የሚከፍሉት ታክስ አንድ ጊዜ ብቻ በመሆኑ፣ ለተጠቃሚዎች በተሻለ ዋጋ በማቅረብ ገበያውን እንደሚቆጣጠሩት አስረድተዋል፡፡

‹‹በመሆኑም መንግሥት የታክስ ከለላ እንዲሰጠን ሳይሆን እኩል ታክስ እንድንከፍል ሊያደርግ ይገባል፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የአገሪቱ ባንኮችም ለአገር ውስጥ አምራቾች ከማበደር ይልቅ ለአስመጪዎች ማበደርን እንደሚመርጡ፣ ከውጭ የመግዛት ትልቅ በሽታ በአገሪቱ እንደነገሠ ብርጋዴር ጄነራሉ አስረድተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ዘጠኝ ሺሕ የተለያዩ ትራክተሮችን እንዳመረተ፣ ‹‹ወኪንግ ትራክተር›› የሚባለው የእርሻ መሣሪያ ዋጋ 35 ሺሕ ብር ሆኖ በአንድ ቀን 1.5 ሔክታር ማረስ የሚችል መሆኑን፣ ነገር ግን ገበሬው የብድር አቅርቦት ስለሌለውና በአንዴ መግዛት ደግሞ የሚቸግረው በመሆኑ ተጠቃሚ መሆን አልቻለም፡፡

‹‹እነዚህ ትራክተሮች ከሁለት በሬዎች ዋጋ ትንሽ ከፍ ቢሉ ነው የሚሰጡት አገልግሎት ግን ሦስት እጥፍ ነው፤›› ሲሉ ምርትና ተጠቃሚ እንዴት እንዳልተገናኙ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹ፖሊሲዎቻችንን ማስተካከል ያለብን ይመስለኛል፡፡ አመለካከታችንን መቀየር ይኖርብናል፡፡ ዓላማው ለኮርፖሬሽኑ ሳይሆን አገርን ለመጥቀም ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከበላይ አብ ሞተርስ የተወከሉ ግለሰብ በበኩላቸው፣ የመንግሥት ተቋማት በሚያወጧቸው ጨረታዎች መኪኖችን ለማቅረብ በተደጋጋሚ ድርጅታቸው ተሳትፎ የቴክኒክም ሆነ የገንዘብ ሰነድ ምዘናውን ማለፉን፣ ነገር ግን ከጨረታ መገምገሚያ ውጪ በሆኑ መሥፈርቶች በተደጋጋሚ ከውድድር ውጪ መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

ከጨረታ መመዘኛ ውጪ እየቀረበ የሚገኘው መሥፈርት የሚቀርቡ መኪኖች ቢያንስ ለአምስት ዓመት የተነዱ መሆን አለባቸው የሚል እንደሆነና ይህ ደግሞ በአገር ውስጥ የተመረቱ መኪኖችን ጨርሶ ከገበያ ውጪ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ተወካይ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ በአስቸኳይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ችግሩን ማጥናትና አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት የፓርላማው አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው፣ ‹‹የመልካም አስተዳደር አንዱ ገጽታ መልስ መስጠት ነው፡፡ ችግሩን በፍጥነት ጠርጐ ማስወገድ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግሥት ተቋማት ከፍተኛ ግዥ ፈጻሚዎች መሆናቸውን ያስታወሱት አፈ ጉባዔው፣ ‹‹የመንግሥት ተቋማት የአገር ውስጥ ምርት ሊገዙ ይገባል፡፡ ለምንድን ነው መኪና ከውጭ የሚገዛው? የሰባት ሚሊዮን ብር ኮብራ መግዛት መቆም አለበት፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፖሊሲው መሻሻል ይገባዋል የሚል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት አፈ ጉባዔ አባዱላ፣ ለምሳሌ ብረታ ብረት ኮርፖሬሽን የሚያመርታቸውን አውቶብሶች ለመግዛት የሚሹ የውጭ ድርጅቶች አሉ ብለው፣ ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ አውቶብሶቹን ኤክስፖርት ለማድረግ የሚስተናገድበት የታክስና ቀረጥ ሥርዓት የለም ሲሉ ያለውን ክፍተት አሳይተዋል፡፡

በመሆኑም በአስቸኳይ ኮሚቴ ተቋቁሞ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት ተገቢ መሆኑን ገልጸው፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችም የጥራት ደረጃዎቻቸውን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በቅርቡ ደቡብ ኮሪያን እንደጐበኙ የተናገሩት አቶ አባዱላ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀስ አንድም የውጭ አገር ምርት የሆነ ተሽከርካሪ ባለማየታቸው መገረማቸውን፣ በዚህ ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያን የጐበኙ የደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ልዑካንን ለመቀበል የቤተ መንግሥት መኪኖች ቦሌ ኤርፖርት ቢደርሱም፣ ልዑካኑ በአገራችን መኪና ብቻ ነው የምንቀሳቀሰው በማለት የደቡብ ኮሪያ ምርት የሆኑ ተሽከርካሪዎች ተፈልገው ልዑካኑን መቀበል መቻሉን አስረድተዋል፡፡

‹‹የደቡብ ኮሪያ ልዑካን ሞኞች ይመስሏችኋል?›› በማለት የጠየቁት አፈ ጉባዔው፣ ‹‹ደቡብ ኮሪያውያን ለአገራቸው ምርት ያላቸውን ስሜት የትም አገር በኩራት ይገልጻሉ፤›› በማለት፣ በኢትዮጵያ ያለውን በውጭ ምርት የመኩራራት አመለካከት መቀየር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ምንጭ፡ – ሪፖርተር
 

%d bloggers like this: