የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መስመር ድልድይ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ማሳለፍ ተስኖታል

3 Feb


Posted by The Ethiopia Observatory
By The Reporter

ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ በመገንባት ላይ የሚገኘው አዲሱ የባቡር መስመር የሚያልፍበት የአዳማ አካባቢ ድልድይ ከፍተኛ ጭነት የያዙ ተሽከርካሪዎችን ማሳለፍ አልቻለም፡፡

ከጂቡቲ ወደብ ወደ አዲስ አበባ የቢራ መጥመቂያ ጋኖችን ጭነው እየመጡ የነበሩ ከባድ ተሽከርካሪዎች ሰሞኑን አዳማ ከመድረሳቸው 26 ኪሎ ሜትር አካባቢ ቢደርሱም፣ በሥፍራው የተገነባው የባቡር መስመር ማለፊያ ከጭነቱ ከፍታ ጋር ባለመጣጣሙ ለማለፍ ተቸግረው ነበር፡፡

በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተሽከርካሪዎቹ ድልድዩን ለማለፍ ባለመቻላቸው ለአሥር ቀናት ድልድዩ አጠገብ ቆመው መፍትሔ ለመጠበቅ ተገደዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኢንጂነር ጌታቸው በትሩ ችግሩ መፈጠሩን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ አንድ የቢራ ፋብሪካ ያስመጣቸው የመጥመቂያ ጋኖች ከድልድዩ ቁመት በላይ በመሆናቸው ችግሩ መፈጠሩን የሚናገሩት ዶ/ር ጌታቸው፣ መንገዱን ከሚገነባቸው ኮንትራክተርና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ጭነቱ ማለፍ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን ችግሩ ለወደፊት እንዴት ይቀረፋል በሚለው ጉዳይ ላይ ከኮንትራክተሩ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የድልድይ የከፍታ ደረጃ (የመጨረሻው) አምስት ሜትር ከ40 ሳንቲ ሜትር መሆኑን፣ ይህ የባቡር መስመር ማለፊያ ድልድይም በደረጃው መሠረት መገንባቱን ገልጸዋል፡፡

‹‹በዚህ የአዲስ አበባ ጂቡቲ አዲስ የባቡር መስመር ላይ ተመሳሳይ የሆኑ ስድስት ድልድዮች እየተገነቡ በመሆናቸው፣ ችግሩ አሁን በመፈጠሩ መፍትሔውን በፍጥነት ለመስጠት ይረዳናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ችግሩ በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው በሦስት መንገዶች ነው፡፡ አንደኛ የድልድዩን ርዝመት በተቻለ መጠን ከፍ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛ እንደዚህ ዓይነት ጭነት ይዘው የሚመጡ መኪኖች የባቡር መስመሩን ረግጠው የሚያልፉበትን ሌላ መስመር መፍጠር ነው፡፡ የመጨረሻ የሚሆነው የባቡር መስመሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ግዙፍ ጭነቶችን በባቡር ማመላለስ ነው፤›› ሲሉ የተለያዩ አማራጮችን አመልክተዋል፡፡

በመፍትሔ አማራጮቹ ላይ ከኮንትራክተሩ ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝና የመጨረሻ ውሳኔ እንዳልተሰጠበት ዶ/ር ጌታቸው አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን የድልድዩን ርዝመት እንዲጨምር ማድረግ ማለት አጠቃላይ የባቡር መስመር ግንባታ ወጪውን እንደሚያንረው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይገልጻሉ፡፡

‹‹በባቡር መስመር ዝርጋታ ላይ 1.8 ሜትር ከፍታ (Slope) ለመጨመር ከ100 ሜትር መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ አዋጭ አይደለም፡፡ በዚህ መንገድ አንሥራ ብንል የአዋሽ ድልድይ ከፍታን ማስተካከል ያስገድደናል፤›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጂቡቲ የአስፋልት መንገድ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጉዳዩን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጥ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስኪያጁ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፣ በጉዳዩ ዙሪያ በቂ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መስመር በሁለት የቻይና ኩባንያዎች እየተገነባ ሲሆን፣ አጠቃላይ ወጪውም 2.8 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
 

%d bloggers like this: