በትግራይ 34 የገጠር አካባቢዎች 24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኑ

20 Jun

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

መቀሌ ሰኔ 12/2006 (ኢዜአ):- በትግራይ ክልል የሚገኙ የ34 የገጠር አካባቢ ነዋሪዎች የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት በማግኘታቸዉ በኑሯቸዉ ላይ ለዉጥ ማምጣታቸዉን አስታወቁ።

ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል በእንደርታ ወረዳ የሞቶጎ መንደር ነዋሪ የሆኑት ቄስ ታረቀ ተስፋይና አቶ ህንደያ ረዳኢ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት የመብራት አገልግሎት በማግኘታችን ለዘመናት ከነበርንበት ችግር ወጥተናል።

የመብራት አግልግሎት በመዘርጋቱ ልጆቻቸን ትምህርታቸዉን ያለችግር ለማጥናት ከመቻላቸዉም በላይ በኩራዝ ጭስ ምክንያት በጤናቸዉ ላይ ከሚደርስ ጉዳት ተላቀዋል ብለዋል።

በአገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም የትግራይ ክልል ተወካይ አቶ ካሕሱ ገብረመድህን እንደገለጡት በፕሮግራሙ በክልሉ ከሚገኙ 636 የገጠር ቀበሌዎች እስካሁን 300 ያህሉ የመብራት አገልግሎት አግኝተዋል።

ሌሎች 170 የሚሆኑትን የገጠር አካባቢዎች ነዋሪዎች በቅርቡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የመስመር መዘርጋትና ሌሎች የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወነላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በሚቀጥለው ዓመት በሚጠናቀቀው የአምስት ዓመቱ የልማት መርሃግብርም ቀሪዎቹ ቀበሌዎች የመብራት አገልግሎት እንዲያገኙ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት 50 በመቶ ላይ ያለዉን የመብራት ሽፋን በቀጣዩ ዓመት መጨረሻ ወደ 75 በመቶ ለማሳደግ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አቶ ካህሱ አስታዉቀዋል።
 

%d bloggers like this: