የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አኃዝ ለማውረድ የተያዘው ዕቅድ ውጤታማ ሆኗል ይላል ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ – የኤጀንሲው ሚና ምን ሆነ ማለት ነው?

20 Jun

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2006 (ኢዜአ) በዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ ዘመን የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አኃዝ ለማውረድ የተያዘው ዕቅድ ውጤታማ መሆኑን ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

በሚያዝያ ወር 9 ነጥብ 1 በመቶ የነበረው የዋጋ ግሽበት በግንቦት ወር ወደ 8 ነጥብ 7 በመቶ የወረደ ሲሆን የዋጋው መረጋጋት አሁን ባለበት ሁኔታ ቢቀጥል ለኢኮኖሚው ጤናማ እንቅስቃሴና ለህብረተሰቡ ኑሮ ጥሩ መሆኑንም ኤጀንሲው ገልጿል።

በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የቤተሰብ ጥናትና የዋጋ ስታቲስቲክስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ተፈሪ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት የዋጋ ግሽበቱ በከፍተኛ ሁኔታ የመጨመር አዝማሚያ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም ከመስከረም 2003 ዓ.ም ጀምሮ ግን እየቀነሰ መጥቷል።

ባለፉት የአንድ ዓመት ከሦስት ወር ጊዜያትም የዋጋ ግሽበቱ ነጠላ አኃዝ የሆነ ሲሆን፣ በዚህም በዕድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ግሽበቱን በነጠላ አኃዝ እንዲቆይ ለማድረግ የተያዘው ዕቅድ ውጤታማ ሆኗል ማለት ይቻላል ብለዋል።

የኤጀንሲው መረጃ እንደሚያመለክተውም በ2002 ዓ.ም ነሐሴ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ 40 ነጥብ 6 በመቶ ደርሶ ነበር። ከመሰከረም 2003 ዓ.ም ጀምሮም እየቀነሰ መጥቶ በግንቦት 2006 ዓ.ም 8 ነጥብ 7 በመቶ ሆኗል።

አቶ አለማየሁ እንደሚሉት የዋጋ ግሽበቱ ይህን ያህል መቀነሱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የተሻለ የዋጋ መረጋጋት መፈጠሩን ያሳያል።

ለዚህም የምግብ ዋጋ የመጨመር አዝማሚያ መቀነሱ ሲሆን መንግስት በገንዘብ አቅርቦቱ በኩል ተግባራዊ ያደረገው ፖሊሲ የዋጋ ግሽበቱ ከነጠላ አኃዝ እንዳይበልጥ አግዟል።

ምግብ መሰረታዊ በመሆኑ በዋጋ ንረቱ ላይ በ57 ከመቶ ከፍተኛ ድርሻን ይይዛል፤ ቀሪው 43 ከመቶ ደግሞ ምግብ ያልሆኑ ሸቀጦች ድርሻ ነው። በዚህም የተነሳ በምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሲጨምር ወይም የአቅርቦት እጥረት ሲፈጠር የዋጋ ግሽበቱም በዛው ልክ ያሻቅባል፤ ምግብ ያልሆኑት ግን ቀስ አያሉ የሚለወጡ በመሆናቸው በግሽበቱ ላይ ከፍተኛ ድርሻ የላቸውምይላሉ ዳይሬክተሩ።

በሚያዚያ ወር የነበረው የምግብ አማካይ ዋጋ ግሽበት 8 በመቶ የነበረ ሲሆን በግንቦት ወር ወደ 6 ነጥብ 3 በመቶ ቀንሷል።

በአንፃሩ በነዚህ ወራት ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ የመጨመር አዝማሚያቸው በአማካይ 10 ነጥብ 3 በመቶ የነበረ ሲሆን በግንቦት ወር ወደ 11 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ማለቱ የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል።

ይሁን እንጂ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች በዋጋ ግሽበቱ ላይ ያላቸው ድርሻ አነስተኛ በመሆኑ በግሽበቱ ላይ ተፅዕኖ አላመጡም ብለዋል ዳይሬክተሩ።

አቶ አለማየሁ የዋጋ ግሽበት ከ10 በመቶ በታች ሆነ ማለት ዋጋ ቀነሰ ማለት አይደለም፤ እንደበፊቱ በየወሩ የሚታየው ጭማሪ ከፍተኛ ሳይሆን መጠነኛ ጭማሪ አሳይቶአል ማለት ነው።የዋጋ ግሽበቱ ከዜሮ በላይና ከአስር በታች መሆኑ መጠነኛ ቢሆንም የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ያሳያል ነው ያሉት።

የዋጋ ግሽበት ሁኔታ በገበያ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ነው፤ የገበያ ሁኔታ መለዋወጥ በግሽበቱ ላይም የመለዋወጥ ሁኔታ ያሳያል ያሉት ዳይሬክተሩ፣
ከ2005 ዓ.ም ግንቦት ወር ጀምሮ 7 ነጥብ 7 በመቶ በመሆን ወደ አንድ አኃዝ መውረድ የጀመረ ቢሆንም ባለፈው የፋሲካ በዓል ሰሞን በተፈጠረው የገበያ ውድነት ምክንያት ግሽበቱ ወደ 9 ነጥብ አንድ በመቶ ከፍ ብሎ ነበር፣ በግንቦት ወር ደግሞ እንደገና በማሽቆልቆል ወደ 8 ነጥብ 7 በመቶ ወርዷል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉትም ከልምድ እንደሚታየው በክረምት ወቅት የምርት አቅርቦት እጥረት ስለሚያጋጥም በሚቀጥሉት የክረምት ወራት ግሽበቱ መጠነኛ ጭማሪ ሊያሳይ ይችላል።ይሁን እንጂ ከቀጣዩ ዓመት መስከረም ጀምሮ ወደ ነበረበት እንደሚመለስ ይገመታል።

አቶ አለማየሁ አንዳሉት ለዋጋ ግሽበቱ የገንዘብ አቅርቦቱን ጨምሮ የምርት አቅርቦት እጥረት፣ የፍላጎት መጨመርና ምርትን በማከመማቸት የሚፈጠር ዕጥረት አርቴፊሻ መሆኑ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፣ እነዚህን በመቆጣጠር መንግስት ባለፉት 3 ዓመታት በተለይ ብሔራዊ ባንክ ያደረገው ቁጥጥር ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።

የዋጋው መረጋጋት አሁን ባለበት ሁኔታ ቢቀጥል ለኢኮኖሚው ጤናማ አንቅስቃሴና ለህብረተሰቡ ኑሮ መልካም ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም ፖሊሲ አውጪዎች በዋናነት በዋጋ ቁጥጥር ላይ ሳይሆን ፍላጎትና አቅርቦት ሚዛናቸውን እንዳይስቱ መከታተል ላይ ቢሰሩ መልካም ነው ብለዋል።

የዋጋ ግሽበት ላስፐርስ በተባለ ዓለም አቀፍ የስሌት ቀመር የሚለካ ሲሆን በመላ አገሪቱ ባሉ 25 የኤጀንሲው ቅርንጫፎች አማካይነት ከ119 የገበያ ቦታዎች የዕቃዎችን ዋጋ በማሰባሰብና ወደ ዋናው ቅርንጫፍ በማምጣት በባለሙያዎች ተተንትኖ በየወሩ ይፋ ይደረጋል።
 

%d bloggers like this: