በመቀሌ ከተማ በብር 830 ሚልዮን ($42.3mil) የተገነባ የብረታ ብረት ፋብሪካ ተመረቆ ሥራ ጀመረ

21 Jun

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

መቀሌ ሰኔ 14/2006 (ኢዜአ) ዩናይትድ ስቲልና ሜታል ኢንዱስትሪ የግል ማህበር በ830 ሚልዮን ብር ወጪ ካስገነባቸው ሶስት የብረታ ብረት ፋብሪካ አንዱና በመቀሌ ከተማ የተገነባው ፋብሪካ ተጠናቆ ተመረቀ።

ፋብሪካውን ዛሬ መርቀው ስራ ያስጀመሩት የትግራይ ክልል ርእስ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ሀይሌ ናቸው።

ማህበሩ የብረት ውጤቶችን በማምረት ወደ ገበያ ከሚያቀርቡት ሶስት የብረታ ብረት ፋብሪካዎቹ ሁለቱ በመቐለ አንዱ በአዲስ አባባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የተገነባ መሆኑን የፋብሪካዎቹ ባለቤት አቶ አዘዞም አየለ ተናግረዋል፡፡

ሶስቱም ፋብሪካዎች ተመጋጋቢ የብረታ ብረት ምርቶችን በማምረት ለግንባታ፣ለቤት ጣሪያ ክዳን ቆርቆሮ የሚያገለግል ግብአትና ሽት ብረቶችን በማምረት በውጭ ምንዛሪ የሚገቡትን ምርቶች የሚተኩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዛሬ የተመረቀው ፋብሪካ የብረት ቱቦ፣ ሴክሽኖች፣ለግንባታ የሚውሉ ኤል ቲዜድና ሌሎች የብረት ምርቶችን በማምረት ወደ ገበያ የሚያቀርብ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ታደሰ ሀይሌ እንዳሉት ከጥቂት ዓመታት በፊት በሀገሪቱ ጥቂት የብረታ ብረቶች ማምረቻ ፋብሪካዎች ብቻ በመኖራቸው በመካሄድ ላይ ያለውን ልማት የሚመግብ የብረታ ብረት ምርት ችግር ነበር፡፡

መንግስት የኢንዱስትሪ ስትራታጂ እቅድ በመንደፍና ድጋፍ ማድረጉ በየዓመቱ ለውጥ ከመታየቱም ሌላ የንኡስ ዘርፉ የብረታ ብረት ኢንዱስቱሪ ተካታታይ እድገት ማስመዝገቡ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልሎች መቋቋም መጀመራቸው ከፍተኛ ለውጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዩናይትድ ስቲልና ሜታል ኢንዱስትሪ በዓመት 70 ሺህ የብረታ ብረት ምርቶችን በማምረት ወደ ገበያ የሚያቀርብ በሀገሪቱ ትልቁ ፋብሪካ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲዩቱት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ደለለኝ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ረደጃ በዓመት ይመረት ከነበረው 540 ሺህ ቶን የብረታ ብረት ውጤት ወደ 610 ሺህ ቶን ከፍ በማድረግ እያንዳንዱ የነፍስ ወከፍ ዜጋ በዓመት አንድ ኪሎ ግራም ግራም የሚጠጋ የብረታ ብረት ምርት እንዲያገኝ የሚያስችለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ሀገር ይገባ የነበረውን የአርማታና የተለያየ የብርታ ብረት ምርት አሁን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን ሀገሪቱ መቃረቧን ዋና ዳሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

የብረታ ብረት ማአድን ለማልማት ፍቃድ የወሰዱ የውጭ ባለሀብቶች መኖራቸውን ገልጸው ከሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በኋላ በሀገሪቱ የብረት ማአድን ማውጣት ይጀማራል የሚል ተስፋ እንዳለ አስታውቀዋል፡፡

የፋብሪካው ባለቤት አቶ አዘዞም አየለ ፋብሪካቸው ለ220 ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ከመፍጠር ሌላ የብረታ ብረት ውጤት ከሚያመርቱ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት፣መካከለኛና ከፍተኛ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ተመጋጋቢና በጋራ እንዲያድጉ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ፋብሪካቸው በየዓመቱ በሚከበረውን የሰማእታት ሰኔ 15 ቀን ዋዜማ መመረቁ ከፍተኛ መስዋእት የተከፈለበት የሰላም ውጤት በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው አስታውቀዋል፡፡

ማምረት የጀመረውን ፋብሪካ የክልሉ ርእስ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ሀይሌ፣ የፌደራልና የክልሉ ባለስልጣናት ተዘዋውረው ገብኝተዋል፡፡
 

%d bloggers like this: