የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የ2006 አፈጻጸም ከዕቅዱ 50 በመቶ በታች ሆነ

27 Jul

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት የታቀደ ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ ግን 397.7 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ ታወቀ፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ሲጀመር ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ይገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 256 ሚሊዮን ዶላር ስለነበር፣ በዕቅዱ መጨረሻ ዓመት ላይ 2.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ውጥን ተይዟል፡፡ የዕቅድ ዘመኑ ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት ሲቀረው ማለትም በ2006 ዓ.ም. ከዘርፉ ለማግኘት ታቅዶ የነበረው 1.2 ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ በተለያዩ ችግሮች የተነሳ ይህንን ማሳካት አለመቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የበጀት ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያስረዳል፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ዋነኛ የገቢ ምንጮችና በመንግሥት ተስፋ የተጣለባቸው የኢንዱስትሪ መስኮች ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ናቸው፡፡

ከጨርቃ ጨርቅና ከአልባሳት በ2006 ዓ.ም. 350 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 111.4 ሚሊዮን ነው ማግኘት የተቻለው፡፡ በተመሳሳይ ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች 347 ሚሊዮን ዶላር በዚህ የበጀት ዓመት ይገኛል ተብሎ ታቅዶ፣ የተገኘው 132.9 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስጥ ከሚካተቱ ሌሎች የምርት ዓይነቶች መካከል ሥጋና ወተት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከእነዚህ የምርት ዓይነቶች 250 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የተገኘው ግን 75.9 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ለማግኘት ታቅዶ የነበረው 110 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የተገኘው 64.8 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

የዘርፉ አፈጻጸም ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት ከግብዓት አቅርቦት የጥራት ችግር ጋር የግብዓት እጥረት መከሰቱ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ የፋብሪካዎች የእርስ በርስ ትስስር ዝቅተኛ መሆንና የአገር ውስጥ ገበያ ላይ ትኩረት መስጠት ሌሎች ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡

የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የገጠመውን ከፍተኛ የጥጥ አቅርቦት ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቅረፍ፣ በዘርፉ ተዋናይ የሆኑ ኢንዱስትሪዎች በራሳቸው ከውጭ ጥጥ ማስገባት የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸትና ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን የሚመለከተው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በ2006 ዓ.ም. ይገኛል እንዲሁም ዘርፉ ያድጋል ተብሎ በታቀደው መሠረት እየሄደ አይሁን እንጂ፣ የዘርፉ ዕድገት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መሆኑን በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

ለአብነት ያህል የጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንደ ቅደም ተከተላቸው 12.5 በመቶና 8.3 በመቶ ከ2005 ዓ.ም. ብልጫ ያሳየ ገቢ ማስገኘታቸው ተገልጿል፡፡

በአጠቃላይ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ወደ ሥራ ከገባበት በ2002 ዓ.ም. ካሳየው የ10.2 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት፣ በ2006 ዓ.ም. ከ18 በመቶ በላይ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምንጭ፡ ሪፖርተር
 

%d bloggers like this: