በ2015 ምርጫ ዋዜማ፡ የስለላ ኤጀንሲ ኢንሳ የመንግሥትን ሚዲያን በአዲስ መልኩ እያደራጀ ነው፤ ተማሪዎች ተቃውሞ ማሰማታቸውን ቀጠሉ

16 Sep

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

አዲስ አበባ መስከረም 5/2007 (ኢዜአ)፡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የመረጃ አቅርቦትና ተደራሽነቱን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር ተፈራረመ።

ስምምነቱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴንና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢንሳ/ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ ፈርመዋል።

በስምምነቱ መሰረት ለስራው የሚያስፈልገው የሲስተም አቅርቦትና የአገልግሎት ስራ በመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አማካይነት ይከናወናል።

በህዝብና መንግስት መካከል ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ቀልጣፋ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ያለመው የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ፕሮጀክት ዝርጋታ ላለፉት ስድስት ወራት በሰባት ሚሊየን ብር ወጪ ሲከናወን ቆይቷል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን እንዳሉት ፕሮጀክቱ የጽህፈት ቤቱን ለህዝብ ወቅታዊ መረጃ የመስጠት አቅም የሚያጎለብት ነው።

በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ኢትዮጵያን የተመለከቱ መረጃዎችን ሰብስቦ ለማቅረብና በአሉታዊ መልኩ የሚሰጡ መረጃዎች ካሉም ዝርዝር ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት ያስችለናልም ነው ያሉት።

እንደ አቶ ሬድዋን ገለጻ “ፕሮጀክቱ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የገጽታ ግንባታ ሥራ ለመስራት፣ ከመረጃ ጋር ተያይዞ ወቅታዊ ምላሽ የመስጠትና ተጠያቂነትና ግልጽነት የሰፈነበት ስርዓት ለመዘርጋት ይረዳል”።

መረጃ ለመሰብሰብ ረዘም ያለ ጊዜ ይወስድ የነበረውን አካሄድ በማስቀረትም መረጃዎችን በአጭር ጊዜ ወደ ጽሁፍ በመቀየር ለህዝብ ለማድረስ ያስችላል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢንሳ/ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ በበኩላቸው “ፕሮጀክቱ የጽህፈት ቤቱን የመረጃ ተደራሽነት ለማዘመን፣ በይነ-መረብን መሰረት ያደረገ የመረጃ ፍሰት ለማረጋገጥና በማህበራዊ ድረ-ገጾች ወቅታዊና ተከታታይ መልዕክት ለመልቀቅ ያስችላል” ነው ያሉት።

የመረጃ ትንተና ውጤቱን መሰረት በማድረግም የመንግስትን አቋምና ሀሳብ ለህዝብ በዘመናዊ የመገናኛ አማራጮች ለማቅረብ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ዘመናዊ ፕሮጀክቱ በፌዴራልና የክልል የመንግስት ተቋማት ድረ-ገጾች ላይ የሚጫኑ መረጃዎችና የተለያዩ የመንግስት መልእክቶችን ይዘት ልዩነት የሌለውና የሚናበብ ያደርገዋል።

ቀልጣፋ የመረጃ ፍሰት በመፍጠር ህዝብ በመንግስት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጅዎችና የስራ አፈጻጸሞች ላይ የተቋሙን የመረጃ ቋትና ማህበራዊ ድረ-ገጾች በመጠቀም በቀጥታ ግብረ-መልስ እንዲሰጥ የሚያስችለውን ስርዓትም ይዘረጋል።
 

በሌላ በኩል ደግሞ፡ ……

ተማሪዎቹ እየወሰዱት ያለው ስልጠና በአገሪቱ እድገት ላይ እምቅ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ መደላደል ይፈጥራል ይካል ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ መስከረም 5/2007 ለከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የሚሰጠው የፖሊሲና ስትራቴጂ ስልጠና ተማሪዎች በአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ላይ ያላቸውን እምቅ ኃይል አሟጠው እንዲጠቀሙ መደላደል እንደሚፈጥር የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአገሪቱ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በመማር ላይ የሚገኙ የአዲስ አበባ ተወላጆች በመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ ዙሪያ ሁለተኛ ዙር ስልጠና በኮተቤ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ዛሬ ጀምረዋል።

ሚኒስትር ደኤታ አቶ ፉአድ ኢብራሂም በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያን ህዳሴ ከማፋጠን አንጻር ስልጠናው የተማሪዎችን አቅም ለመገንባት የጎላ ሚና አለው።

የብሄር ብሄረሰቦች ታሪክ የስልጠናው አካል በመሆኑ ሰልጣኞቹ ስለ አገሪቱ አጠቃላይ ገጽታ እንዲያውቁ በማድረግ ወደፊት አገሪቱን ተረክበው ሲመሩ የሚገጥማቸውን ፈተና በአግባቡ ለማለፍ ይረዳቸዋል ነው ያሉት ሚኒስትር ደኤታው።

በመሆኑም ይህ አይነቱ አገራዊ ስልጠና ወጥና ተከታታይ በማድረግ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ፉአድ አረጋግጠዋል።

የኮተቤ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የአካዳሚና ምርምር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ደሞዝ አድማሱ በበኩላቸው ተማሪዎቹን ተቀብሎ ለማስተናገድ በዩኒቨርስቲው በኩል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተከናውኗል ብለዋል።

ከዝግጅቶቹ መካከልም ተማሪዎቹ የሚሰለጥኑበትን ቦታዎች ማመቻቸትና ስለ ስልጠናው በቂ የሆነ ገለጻ እንዲያገኙ ማድረግ ተጠቃሾች ናቸው።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ሰልጣኞች ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ከተማሩት ትምህርት ጋር በማዋሃድ ለአገሪቱ እድገት የላቀ ሚና ሊጫወቱ ይገባል።

በስልጠናው ላይ በአጠቃላይ 2ሺህ ተማሪዎች እየተሳተፉ ሲሆን ለ15 ቀናትም እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል።
 

በፕሮፓጋንዳና በፓለቲካ መስክ ተማሪዎችን ለማሠልጠን ሕወሓት ከሚያደርገው ጋር በተያያዘ…

 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሕወሃት/ኢሕአዴግን ስብሰብ ረግጠው ወጡ! – አቡጊዳ እንደዘገበው፤

ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ፣ ሕግ መንግስቱን በጣሰና የከፍተኛ ተቋማት ገለልተኛነትን በመጋፋት፣ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን የሞያ ስልጠና ከመስጠት አልፈው ተራ የፕሮፖጋንዳ መንዢያ ቦታዎች እንዲሆኑ በማድረግ፣ የፖለቲክ ስልጠና በሚል፣ የተለያዩ ስብሰባዎችን በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች እየጠራ መሆኑ ይታወቃል። በስብሰባዎቹ ተማሪዎች ለባለስልጣናቱ የተለያዩ ጥያቄዎች በመጠየቅ፣ ስልጠናዎቹ እንደታሰበው አለመሄዳቸው በስፋት ተዘግቧል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተደረገው ስብሰባ፣ አገዛዙን ወክለው የመጡት አቶ ሬድዋን ሁሴን በሚናገሩበት ጊዜ ተማሪዎች ስብሰባዉ ረግጠነው እንደወጡ ዘገባዎች ይጠቁማሉ። በከፍተኛ ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች በዘር በመከፋፈል፣ መግባባትና መመካከር እንዳይኖር ማድረጉ፣ ዋን መሳርያው የሆነው ገዢው ፓርቲ፣ ሰሞኑ በከፍተኛ ተምህርት ተቋማት እየታየ ያለው የተማሪዎች መተባበር፣ ትልቅ ራስ ምታት እንደፈጠረም ተንታኞች ይናገራሉ።

« የወያኔን ስብሰብን ርግጦ እስከ መዉጣት ሰው ከደረሰ፣ ፖለቲካው መክረሩን አመላካች ነው» ያሉት በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝ « በተለይም ደግሞ የተማሪዎች ተቃዉሞ በአንድ ቦታ ብቻ ሳይሆን በሁልም የአገርቷ ክፍሎች ባሉ ተቋማት መሆኑ፣ ለአገዛዙ ሁኔታዎች በጣም ያወሳስበዋል» ሲሉ ሕወሃት/ኢሕአዴግ በአስገዳጅነት እያደረገ ያለው የተማሪዎች ስልጠና ፣ በራሱ እግር ላይ ሽጉጥ እንደመተኮስ እንደሆነበት ይናገራሉ።

በደርግ ጊዜ ከፍተኛ ተቋማት ዲያለከትካል ማቴሪኡአልም የኮሚኒስ ማኒፌስቶ የመሳሰሉ ኮርሶችን ተማሪዎች እንዲወስዱ ይደረግ እንደነበረ ያስታወሱት እኝሁ ተንታኝ፣ አሁንም ሕወሃት/ኢሕአዴግ በኢቲቪና በመሳሰሉት ሕዝብን የሚያደነቁረው አንሶት፣ ተማሪዎች፣ ሳይንስ፣ አርት፣ ኢንጂነሪን፣ ሕክና በሚማሩበት ተቋማት ፣ ለእውቀታቸዉና ለጊዜያቸው የማይመጥን ፣ ተራና ኋላቀር ስልጠናዎችን ለመስጠት መሞከሩ፣ ዳግማዊ ደርግ መሆኑን የሚያመላከት እንደሆነ አክለው ይናገራሉ።
 

%d bloggers like this: