የተድበሰበሰው የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ሁኔታና የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ቀን በፓርላማ

17 Oct

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ችላለች ወይ? ወይንስ ይህ ጉዳይ የተለመደው የሕወሃት/ኢሕአዴግ ፕሮፓጋንዳ ይሆን በማለት ሐሙስ ጥቅቅምት 16: 2014 በፓርላማ በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ብቸኛ ተወካይ ለቀረቡላቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሰጡት መልስ አንድ የመንግሥት ተወካይ ለሃገሩ ሕዝብና ለተቃዋሚው ወገን ሊሰጠው የሚገባ እውነተኛውና ትክክለኛው መልስ ነው ለማለት እቸገራለሁ።

በዚያች የ4:16 ደቂቃ ቪዲዮ (ገጹ ላይ ይመልከቱ) እንደተመለከትኩት፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀራረብ፣ “ብለናልና መልሱም እርሱው ነው” የሚለው ክብደት አዳማጩን ይጫናል። በአጠቃላይ፡ ቃናቸው በአንድ በኩል የሥነ መንግሥትን አሠራር በሌላ በኩል ደግሞ የሕዝብ ውክልና ጥምር ምንነትና የሥልጣን ምንጭነት ፈጽሞ ያገናዘበ አይመስልም። በአጭር አባባል፡ መላ ሳይኮሎጅያችው፡ ከእርሳቸው ጋር ያልቆመውን ሁሉ እናንተ አሽባሪዎች፡ የሃገር ልማትና ዕድገት እንቅፋቶችና አፍራሾች የሚል ጣት ጥንቆላው አላስፈላጊ ነበር።

እውነቱን ለመናገር፡ በሥልጣን ማማ ላይ ለተቀመጡ ሰዎች በገሃድ የማይታያችው፡ የዚህ ዐይነቱ ባህሪ ለሃገራችንም ለእርሳቸውም እስከዛሬ አልበጀም፤ ለነገም ተነጎዲያውም አይበጅም!

በግብርና መስክ ሰለማካሄደው ልማትና ግሥጋሴ በቅርብ እንደሚከታተል፡ እንደሚያነብና እንደሚጽፍ ዜጋ፡ እርሳቸው ከሚሰጡት መልስ፡ ሃገራችን በምግብ ምርት ደህንነቷን (ሉዐላዊንቷን) ለማረጋገጥ የመጣችበትን ርቀትና ምን ደረጃ ላይ እንደምትገኝ – ለነገሩ የዚህ ኃላፊነት ካለበት – የእርሳቸው ‘መንግሥታዊ’ገለጻ’ ችግሮቿን በግልጽ እንድገነዘብ በተደረግሁ ምን ያህል በተደሰትኩ ነበር።

መልስ አሰጣጣቸው ሃገርና ሕዝብን ለማሳመን ከመጣር ይልቅ፡ ለአሥርተ ዓመታት ሕወሃት/ኢሕአዴግ የተለማመደበትን “እኔ ካልኩኝ ሃቁም ሕጉም እርሱ ነው” ወደሚለው አመላክች እንጂ፡ የኢትዮጵያን የምግብ ሁኔታ አያንጸባርቅም። ለነገሩማ፡ እንደአቶ ኃይለማርያም የጥቅምት 2013 ፍንደቃ ቢሆን ኖሮ፡ በነዚህ አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሃገሮች ስንዴ ለመሸጥ የትራንስፖርት መንገድና የገበያ ጥናት ሥራዋን ገና ድሮ ባጠናቀቀች ነበር!

ከሁሉም አሳፋሪው፡ የተወካዩ ጥያቄ በቴሊቭዥን በቀረበበት መልኩ ሕዝቡ ሙሉውን እንዳይሰማው መቆረጡ፡ አስተዳደራቸው ፈሪ፡ በማያስፈልግ ቦታ ሁሉ ጥላውን ተጠራጣሪ፡ ዘወትር ያዙኝ ልቀቁኝ ባይና አፋኝ (ባለሳንሱር) ሆኖ መቅረቡ ሃገራችንና ወገኖቻችንን አስከፊውን የአፈና ጽዋ ጋች ሆኖ ቀርቧል!


በአቶ ኃይለማርያም ገለጻ ውስጥ የሚታየው ችግር የምግብ ደህንነትን በተመለከተ የዓለም የምግብ ድርጅት (Food and Agriculture Organization -FAO) ካቀረባቸው ለዓለም መንግሥታት አቅርቦ ካጸደቃቸው የፓሊሲ አቋሞችና አማራጭ መለኪያዎችና የተግባር መመሪያዎች መካከል የሚፈልጉትን በመምረጥና የማይስማማቸውን መጣላቸው ነው።

ለማንኝውም፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሁኑ ገለጻቸው፡ ባለፈው ግንቦት ወር ለኢትዮጵያ ሕዝብ በአዲስ አበባ ስቴዲየም ካደረጉት ንግግር በሶስት መልኩ ለየት ያለና በጣም የተሻለ ነበር። ይህንንም የምልበት ምክንያት፡ እንዳለፈው ጊዜ ምን ያህል ሃገሪቱ እንደበለጸገች ለማየት ኢትዮጵያውያን በባንክ ያላቸውን በሚልዮንና ቢልዮኖች የሚገመት ብር ቁጠሩ አለማለታቸው የመጀመሪያው ነው።

ክዚያ ውጭ የዓለሙን ኅብረተስብ ምስክራቸው መሆኑና ያ እነርሱ ያሉትንም የሚያረጋግጥ የምግብ ደህንነትና (food security) በምግብ ራስን የመቻል መሥፈርት (standard) መኖሩን ጠቁመዋል። በምግብ ምርት ራስን ስለመቻል መለኪያ ስለመኖሩ ትክክል ናቸው። ነገር ግን እርሳቸው ያልተገነዘቡት ወይንም ሊቀበሉት ያልፈለጉት፡ ኢትጵያ በምግብ ደህንነት ከፍተኛ ጥረት እያደረገችና – ሁኔታዋ ካለፈው ሻል ያለ ቢሆንም – አሁንም ራሷን አለመቻሏን ነው። ደግመው ደጋግመው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያደበላልቁት ነገር፡ ከዚህ በታች እንደሠፈረው፡ ‘የምግብ ደህንነት’ና (food security/food sovereignty)፣ ብሔራዊ ምርት በነፍስ ወከፍ የሚፈጥረውን ድርሻ (food self-sufficiency) በመቁጠር ላይ ያተኮረ ነው።

ሶስተኛው ደግሞ፡ በቃላት ባይገልጹትም፡ አቶ ኃይለማርያም አፋቸውን ሞልተው ኢትዮጵያ በምግብ ደህንነቷን አረጋግጣለች ለማለት እምብዛም ውስጣዊ ጥንካሬ ያገኙ አይመስሉም። የኛ ሃገር ፖለቲካ ጉዳይ ሆኖ፡ ተቃዋሚ እስካነሳው ድረስ፡ የማፍረስና የመበታተን እልህ ነው የታየባቸው! በተጨማሪም፡ የተ.መ.ድን. የሚሌኒየም ልማት ግቦችን እንደ ምግብ ደህንነት መለኪያ አድርገው ሲያቀርቡ ተደምጠዋል –  የልማት ግቦቹ ዋና ዓላማ ሥራ በመፍጠርና ገቢ በማስገኘት ርሃብንና ድህንነትን መቀነስ ሆኖ ሳለ።

እስከ ድረስ ትክክል ቢሆንም፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሉት እንደሚከተለው (በራሳቸው ቃላት) ሲደመጥ ግጭቱና ድብልቅልቅነቱ ገሃድ ይሆናል፦

    “ሃገራችን በምግብ ራሷን ለመቻል የደረሰች መሆኗን ለመገንዘብ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ አለ። እንደዚሁም ደግሞ በሚሌኒየም የልማት ግቦች አማካይነት የተቀመጡ ግቦች አሉ። እነዚህን ግቦች አስቀድማ ያሳክች ሃገር መሆኗን የተ.መ.ድ. ጭምር የተቀበለ መሆኑን፡ የመንግሥት ፕሮፓጋንዳ ተብሎ የቀረበው የዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ጭምር የተቀበሉት በዚህ መሥፈርት መሠረት በምግብ ራሳችንን መቻላችንን ያረጋበጥነበት ሁኔታ አለ። የምርት መጠን በምናይበት ጊዜ ወደ 300 ሚልዮን ኩንታል ደርሰናል። ይህ ማለት ላለን የሕዝብ መጥን በምናካፍልበት ጊዜ ዓለም አቀፍ ስታንዳርዱ በምግብ ራስን ለመቻል ካሰቀመጠው መሥፈርት ጋር የተጣጣመና ከእርሱ ያለፈ በመሆኑ በምግብ ራሳችንን መቻላችን በዚሁ ብቻ ማረጋገጥ ስለሚቻችል፡ ይህ በሚገባ ሊያዝ ይገባል። ይህ ማለት ግን በእያንዳንዱ ቤተሰብ ያለ የምግብ ዋስትና ተረጋግጧል ሁሉም ቤተስብ የሚፈለገውን ያህል የምግብ ጥንቅርና ምምም እያገኘ ነው ማለት አይደለም።”

ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በምስክርነት ስለመጥራት፡ ምናልባትም አሠራራቸውን በሚገባ ካለመገንዝብ፡ ወይንም አዳማጩን በመናቅ ላይ የተመሠረተ አስተሳሰብ ይመስለኛል። ለምሳሌ ለተ.መ.ድ. ጠቅላላ ጉባኤ የቀረበው የሚሌኒየም ልማት ሪፖርት አንድ ነገር ይላል በተለይም በአጠቃላይ የአፍሪካን ግቦቹን ለማሳካት አለመቻል አስመልክቶ። የኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች ግን በግቦች አንድ ድህነትንና ርሃብተኝነትን ቁጥር በመቀነስግብ ሁለት በትምህርት መስክግብ አራት በሕፃንት ሞት ላይ ኢትዮጵያ ክስምንቱ ሶስት ግቦችን ታሳካለች የሚለው ተቀይሮ፡ የድርጅቱ ምስክርነትም ተጋኖ ሁሉንም እንዳጠናቀቀች ተደርጎ ያላንዳች ዕፍረት ያዙን ልቀቁን እያሉ ነው።

ለምሳሌም ያህል፡ ከለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሕወሃት መልዕክተኛ ለእንግሊዝ የፓርላማ አባላት ጥቅምት 16፣ 2014 ራት ላይ ያላንዳች መሸማቀቅ ባደረገው ንግግር ኢትዮጵያ ስምንቱንም የሚሊኔየም ግቦች እንደምታሳካ ሲያረጋግጥ ስሰማ፡ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ እውነት እንደፈለጓት የምትሳል መሆኗን ያላንዳች ማወላወል መገንዘብ አስችሎኛል። ለማንኛውም የዛሬውም ሆነ መጭው ትውልድ በየደረጃው ኢትዮጵያውያን ምሁራን በሚያሰባስቧቸው መረጃዎች ላይ በመነተራስ እየተፈእጽሙ ያሉትን ቅጥፈቶች ሊመረምሩና ወደፊት እንዳይደገሙ ግልጽ አቋም ሌወሰዱ ይገባል!

አንድ ትልቅ ችግር ሆኖ የሚታየኝ ጉዳይ፡ ሠፋፊ የእርሻ መሬትና ምቹ የአየር ጠባይ ላላት ሃገር: የኢትዮጵያ ምርት አሁን ካለበት ደረጃ በአፋጣኝ ካልተለወጠ ኢትዮጵያ በምግብ ምርት ራሷን ችላለች ወይንም ወደፊት ትችላለች የሚለው አጠራጣሪ ነው። ይህም ትግል ለአስተዳደራቸው እጅግ ፈታኝ በመሆኑ፡ አሁን እንዳውም ባዮቴክኖሎጂ የፈጠራቸው (GMOs) የዘር ማፍላት ሥራ ከዚህ ዓመት ጀምሮ በሥፋት ተጀምሮአል። በዚህም ተግባር የሕወሃትና የኢሕአዴግ የፖለቲካ ቢዝነሶች ዋነኛ መሪዎች መሆናቸውንም ከዚህ በፊት መጻፌን አስታውሳለሁ።

ከአቶ ኃይለማርያም ንግግ ርቅር ከተሰኘሁበት መካከል፡ 300 ሚልዮን ኩንታል እናመርታለንና የምግብ ደህንነታችንን አረጋግጠናል የሚለው ይገኛል። ከላይ እንደገለጹት፡ ይህንንም ለማለት ያበቃቸው ምርቱን በኩንታል ለሕዝብ ቁጥር በማካፈል ነው። የዘነጉት ነገር ግን፡ ከ1961 ዓ.ም.ጀምሮ የዓለም የምግብ ድርጅት ዳታ (FAOSTAT) እንደሚያሳየው፡ በብዙ የእህል ምርቶች ኢትዮጵያም ከብዙ የአፍሪካና ሌሎችም ሀገሮች የበለጠ ታመርት ነበር። ነገር ግን ያ ማለት በሃገሪቱ ውስጥ የምግብ ደህንነት ነበር ለማለት የሚያስችል አይደለም – የተደጋገመ ርሃብም እንዳሳየው። አሁንም ያ ሁኔታ እምብዛም አልተለወጠም።

በቀጥታ ሲተረጎም፡ ይህም የአል አሙዲ 13 ቢልዮን ዶላር ውስጥ ኢትዮጵያውያን ወይንም አሜሪካኖች በቢል ጌትስ 75 ቢሊዮን ዶላር ላይ ድምጽና ድርሻ አላቸው ከማለት ተለይቶ አይታይም።
ለመሆኑ የምግብ ደህንነት ምንድነው?

ባለፈው ጊዜበአቶ ኃይለማርያም ግንቦት 2014 ንግግር በመበሳጨት፣ ይህ አሁን በተደጋጋሚ ስታንዳርድ የሚሉትን ለማብራራት በአስተያያት መልክ ብገለጸውም፡ አሁንም በአጭሩ እርሳቸው ከተናገሩት ጋር በማገናዘብ ለማብራራት ሞክራለሁ።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳከተመና የተባበሩት መንግሥታት እንደተቋቋመ፡ ትልልቆቹን ሃገሮች ካሳሰቧቸው ጉዳዮች አንዱ የዓለም ሕዝብ ቁጥር ማሻቀብና የምግብ ምርት እርምጃውን ከዚያ ጋር ለማጣጣም አለመቻሉ ነበር። ይህ ችግር ዛሬም በዓለም ዙሪያ ይታያል። በወቅቱ የተደረገውና ዛሬም የሚደረገው ትግል ብዙ ምዕራፎች ቢያልፍም፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም መንግሥታት የምግብ ፖሊሲ የቀረጹት በ1974 ዓ.ም. ባንግላዴሽ በክፉ ርሃብ በመታቷ ሳቢያ የመጀመሪያው የዓለም ምግብ ኮንፈረንስ እንዲካሄድ ምክንያት በሆነችበት ሁኔታ ውስጥ ነበር። በዚያን ዓመት የዓለም የምግብ ምርትም ክፉኛ አሽቆልቁሎ ነበር፤ ያ ሁኔታም በ1975 እንደሚቀጥል መረጃዎች ያሳዩ ነበር።

አንዱ ትልቁ የጉባኤው ውጤትና ትኩረቱ ዓለም በቂ ምግብ (World Food Security) እንዳላትና እንደሌላት የሚለካበት ሥርዓት እንዲፈጠር መወሰኑ ነበር። በዚያን ወቅት በብሔራዊ ደረጃ ይህንን ለመመልከት የሚያስችል ስታንዳርድ ባይኖርም፡ የምግብ ደህንነት (food security) ሃሣብ የመነጨው በዚያን ወቅት ነበር። ሆኖም፡ ያ የግለሰቦችን መታረዝ በሚያረካ መንገድ ባይሸፍንም፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፡ ጉባኤው በወሰነው መሠረት፡ መንግሥታት ለረሃብ ጊዜ በቂ የምግብ ከምችት እንዲይዙ የሚያደርግ መመሪያ ላይ ስምምነት ተደረስ።

የምግብ ደህንነት ከመንግሥታት ኃላፌነት ወደ ግለስቡ የተላለፈው በ1996 ዓ. ም. በተካሄደው የዓለም የምግብ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ነው። በዚያ ጉባኤ ውሳኔ መሠረትም፡ የምግብ ደህንነት ትርጉም ተግባራዊ መሆን ተጀመረ። በዚያ ውሳኔ የድርጊት መርሃ ግብር (Plan of Action) መሠረትም፡ በትርጉም ደረጃ በሃገሮች መካከል የምግብ ደህንነት ላይ ስምምነት እንድሚከተለው ተደረስ:-

“Food security exists when all people, at all times, have physical and economic access to sufficient, safe and nutritious food to meet their dietary needs and food preferences for an active and healthy life. In this regard, concerted action at all levels is required.”

እነዚህን ሃሣቦች አቶ ኃይለማርያም ቢገልጿቸውም፡ ትኩረት ሊሰጡት ያልፈለጉት፡ የዓለም የምግብ ፖሊሲ ከተባበሩት መርሆች አንጻር፡ ከዓለም የምግብ ድርጅት የድርጊት መርሃ ግብር አንጻር ሲታይ፡ የምግብ ደህንነት በሶስት መርሆች መመሠረቱን ነው። እነዚህም፦

    (ሀ) በማናቸውም ጊዜ የምግብ መኖር (availability)

(ለ) የምግብ አቅርቦት መረጋጋት (stability)

(ሐ) የምግብ በተፈለገ ጊዚ መገኘት (access)

ይህንን ከሚከተለው ቻርት መመልከት ይቻላል፦

FAO: Concepts of food security

FAO: Concepts of food security

 

ለማንኛውም፡ አንዲት ሃገር የምግብ ደንነቴን አረጋግጫለሁ ማለት የምትችለው፡ እያንዳንዱ ዜጋ ከላይ ከ(ሀ) እስክ (ሐ) የተጠቀሱት ሲሟሉለት ነው። በዓለም የምግብ ድርጅት የምግብ ደህነንት ኮሚቴ፡ በአንድ ሃገር ውስጥ የተለያየ ችግር የሚያጋጥማቸው ግለስቦችና አካባቢዎች ሊኖሩ መቻላቸውን በማስገንዘብ መለኪያው ከግለስብ ይልቅ ቤተሰብ ላይ እንዲያተኮር ጠይቋል። ለዚህም የማሻሻያ ሃሳቡ በትክክል ለመሥራቱ መለኪያው “physical and economic access to adequate food for all household members, without undue risk of losing such access” እንዲሆን ተደርጓል።

አቶ ኃይለማርያም ይህንን በተመለከተ ኢትዮጵያ በቤተስብ ደረጃ የምግብ ድህንነት ማረጋገጥ እንዳልቻለች አምነዋል። እየሠራንበት ነው ማለትና ኢትዮጵያ በምግብ ምርት ብሔራዊ ደህንነቷን አረጋግጣለች የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም።

ሃገራችን ውስጥ ድህነት የተንሰራፋ በመሆኑ፡ የአንድ ዓመት ድርቅ ሕዝቡን ለስድስትና ሰባት ዓመታት የባስ ድህነት ውስጥ የሚከተው ነው። ይህም አብዛኛውን የገጠር ሕዝብ የመገበያየት አቅም ይነሳዋል። አብዛኛው የኛ ሕዝብ የተመጣጠነ ምግብ ለማግኘት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፡ የሚቀመስም የሌላቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም።

ችግሩ አሁንም በመቀጠሉ፡ በሃገሪቱ ውስጥ ካሉት ወረዳዎች ከግማሽ በላይ ያህሉ ዕርዳታ ፈላጊ እንደሚሆኑ ታስቦ ከ 2015 እስክ 2020 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ የምግብ ዕርዳታና የገንዘብ ድጋፍ የተድረግ ስምምነት ተፈርሟል (Productive Safety Net Project – PSNP IV)። በቅርቡም የዓለም ባንክ አሥር ሚሊዮን ኢትዮጵያውንን ለመርዳት የሚያስችል $600 ሚሊዮን በብድር መስጠቱ ይታወቃል።

እንዲት ነው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ በምግብ ደህንነቷ ተረጋግጧል፤ ራሷን ችላለች የሚባለው – የትርጉም ለውጥ እስካልተደረገ ድረስ! በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል የቀረበው ጥያቄ አግባብ አለው። የቀረበው ጥያቄ ሕወሃት/ኢሕአዴግ በየሶስትና አራት ወሩ ስንዴና ሌሎች የምግብ ዐይነቶች ከውጭ ገበያ በብድር በተገኝ ገንዘብ ወይንም ከቡናና ጫት ሽያጭ በተገኘ ገቢ ምግብ ወደ ሃገር ውስጥ ማስገባቱ በምግብ ምርት ኢትዮጵያ ራሷን ችላለች የሚለው አባባል ብዙም አያስኬድም።

እዚህ ላይ መታየት ያለበት አንድ ሃገር በአጋጣሚ በሚፈጠር ችግር ምግብ መግዛቱ ራሱን አለመቻሉን አያስይም፤ ሆኖም ሃገሪቱ በቂ ገቢ ሳይኖራት፡ ዘላቂ የምግብ ገበያተኛነትን አይጭምርም።

በአንድ በኩል ፋክቱን ከማቅረብ ይልቅ ተ.ም.ድን በምስክርነት በመጥቀስ፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሚጠቀሱትም ምስክርነቶች ለፖለቲካውና ፕሮፓጋንዳው የሚያመቹት እንጂ ድህነትን በመቀነስ ዳታ መካከልና በምግብ ደህንነት መካክለ ያለው ግንኙነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ በሚገባና በተግባር አልተሳሰረም። ለምሳሌ ያህል ክስምንቱ የሚሌኒየም ግቦች የመጀመሪያው ድህነትን ማጥፋትና ርሃብን መቀነስ መሆኑን ነው የሚናገረው። ለአፈጻጸሙም ሶስት ግቦች (targets) ተሠርተውለታል። በአሠራርም ደረጃ የግብርና ሚኒስቴር ግብ አንድን ሲሰራበት ቆይቷል፣ ምንም እንኳ ሃገሪቱ አሁንም ክፍተኛ የርሃብተኛ ቁጥር ቢኖራትም!

ምግብ (ስንዴ) ከውጭ መግዛት ችግር አይኖረውም ነበር፣ በተወሰነ ችግር ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ በዕርዳታ ጭምር ቢገባም። ነገር ግን ዛሬ የሕዝቡ የምግብ ፍላጎትና የሃገሪቱ በልማት ጎዳና በዘላቂነት ለመጓዝ፡ በሁለቱ መካከል ያለውን ፍላጎትን የማርካት ግጭት ማስተንፈስ ያስፈልጋል! አሁንም ባለንባት ደቂቃ ውስጥ ሃገራችን ይህንን ማድረግ ሳትችል ነው፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምና ሚኒስትሮቻቸው ኢትዮጵያ በምግብ ምርት ራሷን ችላለች የሚሉን!

የምግብ ደህንነትንና በምግብ ራስን መቻልን ዓላማዎች ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ማንበርከኩ ሃገራችንን በተግባር ተጠቃሚ አያደርጋትም።
ጥቂት ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ

ከዚህ ቀጥዬ የማነሳው ነጥብ፡ የአቶ ኃይለማርያምን አያያዝና አሠራር የሚመለክት ሲሆን፡ ዓላማውም ለመሳለቂያነት አይደለም፤ – እስካሉ ድረስ ለነገሮች ተሰሚነትና መደማመጥን ለመፍጠር በመመኘት ነው።

ኃየለማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ግንባር ቀደም ሚና ወደ ሚጫወቱበት ሚና የተሸጋገሩት: በፓርላማ የገዥው ፓርቲ ተወካይ ሆነው ስለነበረ፡ አሁንም ወደፓርላማ ሲመጡ በየጊዜው ቁጣቸው ሲጨምር ይታያል። ይህም የሚሆነው፡ በቀድሞው ሥራቸው፡ በመለስ መመሪያ የኢሕአዴግ የፓርቲ አባላትን ማሾርና ማሸከርከር ስለነበር ነው።

አሁን እንኳ ወደ ፓርላማ የሚመጡበት ምክንያት በሕግ የተደነገገና ስለአሰተዳደራቸው ለፓርላማና በዚያም በኩል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትክክለኛ መረጃ መስጠት ግዴታቸው በመሆኑ ነው! ታዲያ ለምንድነው በየጊዜው ግንፈላቸው እየተባባሰ የመጣው?

ከቁጣው ቀነስ አድርገው – ትክክለኛ መረጃ በመስጠት- ከሕዝብ ጋር ለመነጋገርና ለመደራደር (reason out) መቻል አለባቸው! እስረው፡ ፍለጠው፡ ግረፈው፡ ግደለው … ብዙም አያስኬድም!

ትክክለኛ ምርጫ በሚካሄድባቸው፣ የምርጫ ኮሮጆ በማይገሰሰባቸው ሃገሮች እኮ፣ መራጩ ለምንድነው ሚኒስትሩ ወይንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤቴ በቴሌቪዥን መስኮት ገብቶ የሚደነፋብኝ በማለት አይቀጡ ቅጣት ይጥል ነበር! እርሳቸው ከሃገር አሳደው የጨረሷቸው ጋዜጠኞችም፡ ስለሁኔታው ከሕዝብ ጋር በገሃድ መረጃ መለዋወጥ በቻሉ ነበር!
*Updated.

%d bloggers like this: