ኦርቶዶክስ ክርስትና በካድሬው ፓትሪያርክ ቅጥረኛነትና ከቤተ መንግሥት በሕወሃት ሲታመስ

22 Oct

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
ሃራ ዘ ተዋህዶ

  “አባ ማትያስ አላበደም፤ መልዕክቱን እያስተላለፈ ነው” … [ራስፑቲን* ትዝ ብሏቸው ይሆን?]

  “እግዚአብሔር ላበዱት አይምሯቸውን ይመልስልን፤ ላላበዱትና ለማበድ ለተዘጋጁት አይምሯቸውን ይጠብቅልን፡፡”

  – አባ ማትያስ

  “አጠቃላይ ጉባኤውን ፀረ-ማኅበረ ቅዱሳን አቋም ለማስያዝ ፓትርያርኩና ጥቂት አማሳኞች በዋና ሥራ አስኪያጁ ላይ ጫናቸውን አጠናክረዋል”

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ኻያ አንድ አመታት በርዕሰ አበውነት ‹ሲገዙ› የነበሩትን የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ሞትን አስከትሎ ስድስተኛውን ዘመነ ፕትርክና የምደባ ያህል የተረከቡት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀናኢ ሊቃውንትና ምእመናን ለዘመናት ሲያንገሸግሽ የቆየውን አድሏዊ አሠራር ፤ ጎጠኝነትና ሙስና በመጠኑም ቢኾን ይፈታሉ የሚል ግምት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡

Credit: Awde Mihret

በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ንግግር ሲያደርጉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቃውንትና ምእመናን ብሶትና የዕለት ከዕለት ምሬት የተሰማቸው በሚመስል ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው ከሚንቀሳቀሱባቸው የሥራ ዘርፎች መካከል፤ በዋነኝነት ሙስናንና ጎጠኝነትን መዋጋት እንደሚሆን መጥቀሳቸው ይታወሳል፡፡

አፍዓዊ መግለጫቸው ተከትሎም በቤተክህነቱ መዋቅራዊ ለውጥ ተደርጎ የአገልግሎት አሰጣጡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዋንኛ ተልእኮ ማስፈጸም የሚያስችል ይሆናል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ ተወስዶ ነበር፡፡ ቅዱስነታቸውም በአንደኛ ዓመታቸው በዓለ ሲመት አከባበር ሥነ-ሥርዓት ላይ “የዛሬ ዓመት የተናገርኳቸው ቃላት ኹሉ እንደጸኑ ናቸው፤ አልተበረዙም፤ አልተከለሱም፤ እንዲያውም ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከምእመናን ጋር በመሆን አጠነክራቸዋለሁ” ከማለት አልፈው ለተቋማዊ ለውጡ በቁርጠኝነት የተነሱ በሚመስል ሁኔታ በለውጡ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የጥናት ቡድኖች እንዲቋቋሚ በጎ ፍቃዳቸውን ያሳዩ መስለው ‹ተወኑ› ፡፡ በአንዶቻችን ዘንድ አቡኑ ጉዱ ካሳን የሆኑ እስኪመስለን ድረስ የለውጥ አባት ተደርገው ተወስደውም ነበር፡፡

በኋላ ግን ኾነው የተገኙት መስለው የተናገሩትን ሳይሆኑ ከቅድስት ሀገር እየሩሳሌም እስከ አሜሪካ ኖረውታል የሚባለውን ምንነታቸውንና ማንነታቸውን ነው፡፡ መልካም አስተዳደር በማስፈን ኾነ ጎጠኝነትን ኾነ ጥቅመኝነትን መሠረት ያደረጉ አድሏዊ አሠራሮችን በማስቀረት፤ ሙስናን በመዋጋትም ኾነ በቤተ ክህነቱ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሊቃውንቱንና የምእመኑን ቅሬታ የሚፈቱና አመኔታቸውን ያተረፉ ኾነውና በቅተው አልተገኙም፡፡

Liqe Tiguhan Zekarias Haddis "የቅዱስ ፓትርያርኩ መብት ተጥሷል›› እያላችኹ ጉባኤተኛው ውድቅ ባደረገው የቅስቀሳ አጀንዳ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማስወገዝ ‹‹መድረክ ይከፈትልን" በሚል በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ላይ የምታደርጉት ግፊት ሀገረ ስብከቱን ይኹን የሀገረ ስብከቱን ገዳማትና አድባራት አይወክልም! (Credit: Hara Ze Tewahdo

Liqe Tiguhan Zekarias Haddis “የቅዱስ ፓትርያርኩ መብት ተጥሷል›› እያላችኹ ጉባኤተኛው ውድቅ ባደረገው የቅስቀሳ አጀንዳ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማስወገዝ ‹‹መድረክ ይከፈትልን” በሚል በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ላይ የምታደርጉት ግፊት ሀገረ ስብከቱን ይኹን የሀገረ ስብከቱን ገዳማትና አድባራት አይወክልም! (Credit: Hara Ze Tewahdo

ይባስ ብለው ሞያዊ እውቀታቸውን ለቤተ ክርስቲያን እድገትና ደህንነት አስራት አድርገው ያቀረቡ ሙያተኞችን አግልለው ድጋፍ ነስተው፤ ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ከሚያስቀድሙና ለቤተ ክርስቲያኒቱ እድገትና ለውጥ የዘመናት እንቅፋቶች የሆኑ አማሳኞችና አድር-ባር ፖለቲከኞች ጋር ማኅበርተኝነት መስርተው ተገኙ፤ ይባስም ብለው ወጣኒያኑን “ቀኝ ገዥ” ብለው አረፉት፡፡ ርእሰ አበውነታቸውን ዘንግተው የስርዓቱ ጭቃ ሹምና ምስለኔ በመሆን የማይገባቸውን ሥልጣን ከሚገባቸው ነጥቀው ከያዙት፤ ድኻውን ካህን ባለፉት 23 ዓመታት ሲበዘብዙ እና ሲያሰቃዩት ከኖሩት፤ የካህኑን ቤተ-ሰብእ ለዘመናት ከእጅ ወደ አፍ የሠቆቃ ኑሮ እንዲገፋ ካደረጉት፤ ሊቃውንቱን በተዋራጅነት፤ በድህነት ፤ በእርዛትና በበሽታ እየተሰቃዩ እና እየተጎሳቀሉ አስከፊ ኑሮ እንዲያሳልፉ ያደረገውን አማሳኝና አድር ባይ ቡድን ጠባቂ ሆነው አረፉት፡፡

ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ 33ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በስብከተ ወንጌል አዳራሽ የተጀመረው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ መልዕክት በማስተላለፍ ነበር፡፡ አቡነ ማትያስ እንደ አሞራ በከበቧቸው ያበዱ መካሪያን ሁለት ድፍን ዓመት በመንበሩ ተክለሃይማኖት ላይ ሳይሞላቸው ቅድስት ቤተክርስቲያን በ”ቅኝ ገዥ” መያዟን ለጉባኤው አውጀዋል፡፡ እስኪ መልዕክታቸውን ቃል በቃል ለአንባቢያን እንዲህ አቀረብነው፡፡

  … ሁሉንም ማወቅ አለባችሁ ብያለሁ፤ ስለ ቤተክርስቲያናችን ወቅታዊ ሁኔታ እንድታውቁ እፈልጋለሁ ፤ ወቅታዊም አይደለም ችግሩ የኖረ ነው፡፡ ሰለ ቤተክርስቲያናችን ሁኔታ ያለኝን ለጉባኤው ልገልጽ እፈልጋለሁ፡፡ ይሄ ጉባኤ የሚገኝው በአመት አንድ ጊዜ ነው፤ ይህ እድል እንዲያመልጠኝ አልፈልግም ፤ ያለውን ችግር ሁሉ ማሰማት አለብኝ ፤ ችግሩ ምንድነው? ትሉኝ እንደሆነ፤ ችግሩ ቤተ ክርስቲያናችን በቅኝ ግዛት ተይዛለች፤ ቤተ ክርስቲያናችን በቅኝ ገዥዎች ተይዛለች፤ በቅኝ ግዛት ተይዛለች ይህን ማወቅ መረዳት አለባችሁ፤ በኋላ አልሰማንም አላየንም እንዳትሉ፤ ማነው ቀኝ ገዥው? አንድ ሁላችሁም የምታውቁት ማኅበር ነው (……ጭብጨባ…. )፤ በምንድነው ወደ ቅኝ ግዛት የተዳረገቸው?፤ በራስዋ በተሰበሰበ ገንዘብ በቅኝ ግዛት እንድትገዛ አድርገዋታል፡፡ በእውነት ከዚህ የባሰ ክፉ ነገር የለም ፤ እኔ እናገራለሁ ፤ በስራ ላይ መዋል አለማዋሉ የራሳችሁ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ይህን ጉዳይ ከራሴ አወርዳለሁ፤ ብትወዱም ባትወዱም የቤተ ክርስቲያናችን መብቷ ክብሯ ሀብቷ ሁሉ ተወስዷል ፤ ገንዘቧ ንብረቷ ተወስዷል ፤ ይሄ መመለስ አለበት፤ ባሳለፍነው ዓመት አንድ ውሳኔ አሳልፏሁ ነበር፤ “ማኅበሩ በቁጥጥር ስር ይዋል፤ ቤተ ክርስቲያን ትቆጣጠረው፤ ወደ ስርዓት ወደ ሕግ ይግባ” ብሎ ጉባኤው ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ከውሳኔው ውስጥ አንድም አልተደረገም ፤ ምክንያቱም እነሱም ፍቃደኞች አይደሉም ፤ ማንስ ጠይቋቸው? እና ይህን ጉዳይ ሁላችሁም እንድታውቁት እፈልጋለሁ፤ እኔ ስራዬ መናገርና ማወጅ ብቻ እንጂ እኔ ብቻዬን የምሰራው ነገር የለም:: ቤተ ክርስቲያናችን ከቅኝ ተገዥነት ትውጣ ፤ ካህናቱ ከችግር ከሰቀቀን ከመከራ ይውጡ ( ….ጭብጨባ….)፡፡ እኔ መልዕክቴን ማስተላለፍ አለብኝ፤ እኔ ይችን ቤተ ክርስቲያን ለመጠበቅ ነው የተቀመጥኩት ነው ብዬ የማምነው ፤ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሁለት ቤተ ክርስቲያን የለም፤ እኔ አንዷን ቤተክርስቲያን ብቻ ነው የምመራው፤ ሌላ ቤተክርስቲያን የለም፤ ሁለት ቤተ ክርስቲያን ልመራ አይደለም የተቀመጥኩት፤ ሁለት ቤተክርስቲያን ልመራ አልተቀመጥኩም፤ አንድ ኦርቶዶክሳዊት ታሪካዊት ቅድስቲቱን ቤተ ክርስቲያን ልመራ ነው የተቀመጥኩት ፤ አሁን ይህን አዋጅ እናንተ በዚህ ሁኔታ እንድታውቁት እና እንድትሰሩበት ነው እየነገርኳችሁ ያለሁት፡፡ አባ ማትያስ አላበደም፤ መልዕክቱን እያስተላለፈ ነው፤ ለእናንተ ስለዚህ ይህን መልዕክት በጸጋ ተቀበሉ ብዬ እማጸናችኋለሁ፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ ችግር ስለሆነ ነው የተናገርኩት፡፡

የራሳቸውን ቅኝ ግዛት በኢትዮጵያ ላይ ለማስፋፋትና አማራውን ለመምታት ሲሉ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተሰገሰጉት የሕወሃት ካድሬዎች ሌላውን የማጥላላት ዘመቻቸውን አስፋፍተውታል! ይህም የተጀመረው በመለስ ዜናዊ እንደሆነ ማንም ያስታውሰዋል። ስለሆነም አሁን ጉዳዩ ፓትርያርኩ እንደሚቀባጥረው፡ ማኅበረ ቅዱሳንን ለመስቀል አይመስለንም!

http://ethsat.com/video/waza-ena-kumneger-18-oct-2014-2/
 

*ጊኦርጊ ራስፑቲን በ1869 ተወልዶ በ47 ዓመቱ የተገደለ ካለምንነት ተንሰቶ ሩሲያዊ ውስጥ ራሱን ሃይማኖታዊ ምሁር አድርጎ ተሰሚነቱን በሃገር ውስጥ ማስፋፋት የቻለ፡ የፈውስ ችሎታ: ከእግዚአብሄር ጋር የማማለድ ብቃት አለኝ ይል የነበረ ተደማጭ ግለስብ ነበር። ያከበሩትና ያደምጡት የነበሩትን ያህል: ቀባጣሪ ብለው ሊያጠፉት የፈለጉት በርካቶች ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ችሎታዎቹ ተደማምረው የቤተ መንግሥት አማካሪ ለመሆን በቅቶ ነበር። አንድም ከታወቀበት ባህሪው ሴት ለመጥገብ አለመቻሉ ነበር (እንደ አቡነ ጳውሎስ ሁሉ)። ጊዜ እየገፋ ሲመጣ፡ የራስፑቲን ባህሪ ብዙ የሩስያ ፖለቲከኞች አልዋጥላቸው እያለ መጣ። በ1913 አራተኛው ዱማ በሁኔታው ላይ ተነጋግሮበት፣ ንጉሱም ሩስያን ለቆ ወደ ሠርቢያ እንዲያመራ ቢመክሩም ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል። ለሩስያ ብሔርተኞች ግን የዚህ ግለስብ በቤተክርስቲያንና ቤተመንግሥት ላይ ይህን የመሰለ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልዋጥ ብሏቸው ስለነበር፡ ገዳዮ በታሪክ ጸሃፊዎች መኳንንት ፈሊክሽ ዩሱፖቭ ነው ቢባልም፡ ቤተ መንግሥቱ ወይንም ቂም የያዙበት ብሔርተኞች ወይንም ቦልሼቪኮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል።
 

ተዛማጅ ጽሁፍ፡

Abune Mathias assigned sixth EOTC Patriarch: TPLF accused of pushing ethnicity down the church’s throat
 

%d bloggers like this: