የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ብሔራዊ ባንክ $600 ሚል (ብር 12 ቢል) ለእህልና $120 ሚል (ብር ሰድስት ቢል) ለስኳር ግዥ ብድር አዘጋጅቻለሁ አለ

27 Oct

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

አዲስ አበባ ጥቅምት 16/2007 (ኢዜአ): በአገሪቱ በእህልና በሌሎች የፍጆታ ዕቃ ግብይት ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ከ600 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ብድር ማመቻቸቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

የባንኩ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በዚህ ዓመት ብድሩ የተመቻቸው ለስንዴ፣ ለምግብ ዘይት፣ ለስኳር እንዲሁም ለሌሎች የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጦች አቅርቦት ነው፡፡

በእነዚህ ሸቀጦች ላይ እጥረት ተከስቶ የዋጋ ንረት በአገሪቱ እንዳይከሰት በብሔራዊ ባንክ በኩል 600 ሚሊዮን ዶላር ወይም 12 ቢሊዮን ብር ብድር መመደቡን ተናግረዋል፡፡

መንግስት በአሁኑ ወቅት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅቶች ማጠናቀቁን ገልጸው ሸቀጦቹን ከውጭ ለማስመጣት እንዲቻል የተጠቀሰው ብድር እንደሚለቀቅ አስረድተዋል።

በአገሪቱ በተለይ የስኳር እጥረት እንዳያጋጥም ለመጠባበቂያ ከ120 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ መመደቡን አቶ ተክለወልድ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ተግባር ከወዲሁ መከናወኑን ጠቁመው የችግሩ መነሻዎች መለየታቸውን የባንኩ ገዢ አስታውቀዋል።

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ባለ ሁለት አሀዝ እድገት እያስመዘገበ መምጣቱን የጠቆሙት አቶ ተክለወልድ ለዚህም ግብርናው ከ 5 ነጥብ 4 በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት በማምጣት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል በአገሪቱ እየተከናወኑ ላሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የብድርና የውጭ ምንዛሪ መመቻቸቱን ገልፀው በተያዘው በጀት አመት 45 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብድር መመቻቸቱን ገልጸዋል።

የአገሪቱን የቁጠባ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ነው ያሉት አቶ ተክለወልድ የቁጠባው እድገት 67 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ ከዕቅድ በላይ 85 በመቶ መከናወኑን ተናግረዋል ።

በ2002 ዓ.ም ዘጠኝ በመቶ የነበረው የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል በአሁኑ ወቅት 22 በመቶ መድረሱንም አመልክተዋል።

ብሔራዊ ባንክ በተለይም በፋይናንሻል ዘርፉ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ከሚጠበቀው በላይ ማሳካቱንና በ2002 በአገሪቱ 680 የነበረ የባንኮች ቅርንጫፍ ቁጥር በአሁኑ ወቅት 2ሺህ 208 መድረሱን አቶ ተክለወልድ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ አመት 86 ቢሊዮን የነበረው ቁጠባ አሁን 295 ቢሊዮን ብር ደርሷል ብለዋል፡፡
 

ተዛማጅ ዜና:

Ethiopia’s GDP, measured in falling birr, now estimated at 1.5 trillion
 

%d bloggers like this: