ሰማያዊ ፓርቲ በብሄራዊ ደረጃ ለሚደረገው ትግል ሕዝቡ ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አቀረበ

29 Oct

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

    “ባሳለፍናቸው ሁለት ወራት ብቻ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች በመንግስት ሀይሎች ተገድለዋል – ቆስለዋል – ተሰደዋል ያለው ፓርቲው፣ በኦጋዴን_ መንግስትን የተቃወሙ ዜጎች ወደ ግጭት እንዲገቡ በሚገፋፋ መልኩ ጥያቄዎቻቸውን በመግፋት በርካታ ዜጎች በመንግስት ሀይሎች ህይወታቸው ተቀጥፏል”

ጥቅምት ፲፰ ቀን ፳፻፯ ዓ/ም (ኢሳት ዜና):-ፓርቲው ባወጣው መግለጫ የሀገራችን አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሱና እየከፉ የመምጣታቸውን ያህል ገዢው ፓርቲ ቆም ብሎ ከማሰብ ይልቅ ወደ ማይወጣው አዘቅት ውስጥ ሀገሪቷን ጭምር እያንደረደራት ይገኛል ብሎአል።

ኢህአዲግከዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ፍፁም በማይጣጣም መለኩ ዜጎችን ለአንድ ሀሳብ ብቻ እንዲገዙ አስገዳጅ መንገዶችን ጭምር በመጠቀም አፋኝ መዋቅሩን በማናለብኝነት እያስፋፋ እንደሚገኝ የሚገልጸው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ገዢው ፓርቲ ለማናቸውም አስተዳደራዊም ይሁን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ሀይልን በመጠቀም ለመደፍጠጥና ለማጥፋት ቆርጦ በመነሳት ፍፁም አምባገነንነቱን ገፍቶበት የበርካቶች ህይወት እንዲቀጠፍ አድርጓል ብሎአል።

ካለፈው ዓመት የክረምት ወራት መጨረሻ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የምርጫ ቅስቀሳ በሚመስል መልኩ ለዜጎች በተሰጠ አስገዳጅ ስልጠና ወደ 1 ቢሊየን የሚጠጋ የህዝብ ሃብት ማባከኑን ፓርቲው ጠቅሶ፣ ሕገ መንግስቱን በሚፃረር መልኩ በሕትመት ሚዲያዎቹ ባለቤቶች፣ አዘጋጆች፣ በጋዜጠኞቹና ሰራተኞቻቸው ላይ ማስፈራራትን ጨምሮ በርካታ ስነ ልቦናዊ ጫና በማሳደሩም በርካቶች ለስደት ሲዳረጉ ጥቂቶች ደግሞ ለእስር መዳረጋቸውን አስታውሷል፡፡

ባሳለፍናቸው ሁለት ወራት ብቻ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች በመንግስት ሀይሎች ተገድለዋል – ቆስለዋል – ተሰደዋል ያለው ፓርቲው፣ በኦጋዴን_ መንግስትን የተቃወሙ ዜጎች ወደ ግጭት እንዲገቡ በሚገፋፋ መልኩ ጥያቄዎቻቸውን በመግፋት በርካታ ዜጎች በመንግስት ሀይሎች ህይወታቸው መቀጠፉን አመልክቷል።

ይህም ሳያንስ ሬሳቸው እንኳን ክብር በሌለው ሁኔታ መሬት ለመሬት መጎተቱን የገለጸው ሰማያዊ ፓርቲ በጋምቤላም በተመሳሳይ መልኩ የህወሓት ሰዎች መሬት በሕገ-ወጥ መንገድ መቀራመታቸውን የተቃወሙ ዜጎች ወደ ግጭት የተገፉበት እና በርካታ የሰው ህይወት የተቀጠፈበት አሳዛኝ ሁኔታ መንግስት የተያያዘው መንገድ ወደ ከፋ ሁኔታ ሀገሪቷን እየወሰዳት ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ብሎአል።

“የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት መላው የሀገሪቱ ህዝብ፣ በውጪ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ለሀገር ተቆርቋሪ ተቋማት እንዲሁም በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ስር ሆናችሁ ለውጥን የምትሹ ወገኖች ሁሉ ሀገራችንን ወደ አደጋ እየወሰዳት ያለውን አፋኝ ስርዓት በቻላችሁት ሁሉ በመቃወምና ከስርዓቱ ጋር ባለመተባበር በብሔራዊ ደረጃ የሚደረገው ትግል አካል እንድትሆኑ” ጥሪ እናስተላልፋለን ሲል መግለጫውን ቋጭቷል።

ሰማያዊ ፓርቲ በመግለጫው በብሄራዊ ደረጃ ስለሚደረገው የትግል አይነት ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
 

%d bloggers like this: