ጠ/ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ልማት የአፍሪካ ሞዴል ስለመሆኗ መግለጫ ሠጡ፡ “ወጡ ሳይወጠወጥ…” ለአፍሪካ መሪነት መሮጥ

7 Nov

የአዘጋጁ አስተያየት፡

    ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም አስቸጋሪ ከሆኑት ነገሮች መካካል አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባሎቻቸውን የሚመሠርቱባቸውን ቁጥሮች ከየት እንደሚያመጡዋቸው ለማወቅ አለመቻሉ ነው። የፖለቲካ ሕይወታቸውን በፖለቲካ ካድሬነት የጀመሩ ሰው በመሆናቸው፡ በአመራርና በፖሊስ ላይ ተቀምጠው፡ አሁንም ከካድሬ ፕሮፓጋንዲስትነታቸው ለመላቀቅ አለመቻላቸው በኢትዮጵያውያን እይታ ቁጥር ከኪሳቸው እያወጡ ያልሆነውን ቆርጠው የሚቀጥሉ አስመስሏቸዋል።

    በየት በኩል ነው ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ልማት የአፍሪካ መሪ መሆን የቻለችው? ጥቂት ሃገሮች፡ የራሳችውን የኤኮኖሚና የፖለቲካ ጥቅም ለማበራከት ሲሉ (ለምሳሌ፡ ደቡብ ኮሪያ)፡ ኢትዮጵያን የዚህ ሞዴል፡ የዚያ ተምሳሊት እያሉ ሲናገሩ ሴሚናር ሲያዘጋጁ ይታያሉ። ያ ግን በምርትና በቁጥር ተተርጉሞ የኢትዮጵያ አመራር በሕዝቧ ዘንድ እሰይ ሲባል አይታይም፤ አይሰማም።

    በUNIDO በኩልም፡ ዳታውን በተመለከተ፡ ኢትዮጵያ በማኑፋክቹሪንግ እጅግ ኋላ ቀር ከሆኑት ሃገሮች መካከል ናት። በ2013 መጨረሻ ላይ የነፍስ ወከፍ የኢትዮዮጵያውያን ድርሻ (Manufacturing Value Added per capita) $12 ነበር። እሴት የተጨመርበት ማኑፋክቸሪንግ 5 ከመቶ (Share of Manufacturing Value Added (MVA) in GDP (2013) መሆንን ዳታ ያሳያል።

    በባለፉክክር የኢንዱስትሪው ተወዳዳሪነትን (Competitive Industrial Performance – CIP rank) በተመለከተ፥ በ2013 UNIDO ኢትዮጵያን ከ136 ሃግሮች 134ኛ አድርጓታል። ምኑ ነው ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ልማት የአፍሪካ ግንባር ቀደም መሪና ሞዴል የሚያደርጋት?

    የዚህ ዐይነቱ የማጋጋልና የማጋነን ዘውትራዊ ባህሪ አገራችንን የትም አያደርሳትም። እንዳውም በየቀኑ እየተቆረጠ የሚለጠፈው የውሸት ፖለቲካ ሕዝባዊ ቁጥናን ምሬት የበለጠ ያቀጣጥለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ከበሬታ ይገፋቸዋል!

 

Posted by The Ethiopia observatory (TEO)

አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2007 (ኢዜአ): ኢትዮጵያ በአፍሪካ በኢንዱስትሪ ልማት እያሳየች ያለችው መልካም ጅምር ሞዴል እንድትሆን መመረጧ የዘርፉን የመሪነት ሚና ለማሳደግ ለተያዘው ጥረት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

መድረኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነትና ተቀባይነት እንደሚያሳድግላትም አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ትናንት ቪዬና ውስጥ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት ቃለምልልስ እንዳስረዱት የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ)አገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር የኢኮኖሚ ሽግግር ባለችበት ወቅት ከአህጉሪቱ ሁለት አገሮች አንዷ መሆኗ እንቅስቃሴዋን ለማጠናከር ያስችላታል።

ድርጅቱ ባለፈው ዓመት የአህጉሪቱን የዘርፉ እንቅስቃሴ ለማወቅ ባደረገው ጥናት ኢትዮጵያና ሴኔጋል መምረጡን አስታውሰው፣ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማሳደግ እያደረገችው ባለችው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ”ተስፋ የተጣለባት አገር” ተብላ መሰየሟን አብራርተዋል።

በቪዬና በተካሄደው ሁለተኛው የአሳታፊና ዘላቂነት ያለው የኢንዱስትሪ ልማት መድረክ ያገኘችው ዕውቅና ልማቱን በተሻለ ብቃት ለማካሄድ እንደሚያስችላትም አቶ ኃይለማርያም ተናግረዋል።

በራስ መተማመንና የተያያዘችውን የዕድገት ጎዳና ለማስቀጠል እንደሚያስችላትም አመልክተዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ተሞክሮ መቅረባቸውና ልምዶቿም ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያገኘቡት በዚህም የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ መልካም አጋጣሚ የተፈጠረበት እንደነበርም አስታውቀዋል።

”ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው የኢንዱስትሪ ልማት አካሄድ ጉልበትን በሰፊው የሚጠቀምና ግብርናን መሠረት ማድረጉ የዘርፉን ልማት ለማካሄድ አመቺ ሆኗል”ሲሉም የዘርፉን አካሄድ ያስገኘውን ጥቅም አብራርተዋል።

መድረኩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መዘጋጀቱ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን ለማሳተፍና በኢትዮጵያ የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎትና እምነት እንዲያድርባቸው ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እምነታቸውን ገልጸዋል።

”መድረኩ አገሪቱ የዘርፉን ልማት ለማካሄድ እየተከተለች ያለችው አካሄድ ትክክለኛና ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ ያመለከተ ነው”ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት በተለይም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን በተገተርባቻቸው አራት ዓመታት በዘርፉ እያስመዘገበች ያለችውን ዕድገት አበረታች ቢሆንም፤ዘርፉ በኢኮኖሚው ያለው 5ነጥብ 5 በመቶ ያላለፈ ድርሻ ለማሳደግ የተጠናከረ ጥረት መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በፊት በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለው እንቅስቃሴ ምንም ከሚባልበት ደረጃ ላይ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የተያዘውን እንቅስቃሴ በማጠናከር መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ለመፍጠር የአገር ውስጥ ባለሀብቶችንና የማምረቻ ዘርፉን ያካተተ የተጠናከረ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

በመድረኩ የተሰጠው ዕውቅና አገሪቱ ዘርፉን ወደ መሪነት ለማድረስ ያሉባትን የክህሎትና የፋይናንስ ችግሮችን ለማቃለል እንደሚረዳም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አስታውቀዋል።

%d bloggers like this: