የኃይለማርያም ‘የወራቤ ንግግር’ ለያዙት ሥልጣን ደቂቅነታቸውን አጋለጠ፤ የሔርሜላ ምስክርነት

17 Dec

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

ምነው ይህን ያህል ተናዳፊነት፡ ያውም መልስው መናደፍ የማይችሉትን? ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ፣ ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ በስንት ውጣ ውረድ ያገኙትን ሥልጣን ጥርሳቸውን ነክሰው ከያዙ ሁለት ዓመት ከሁለት ወርና 26 ቀን አስቆጥረዋል። በእነዚህ ወራት ውስጥም፡ ኃይለማርያም ሥልጣን የረገጡ ቀን ስለራሳቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጡት ምስክርነትና ግምት ከዛሬው ኃይለማርያም በአያሌው የተለያዩ ናቸው። ገና መጀመሪያ ላይ ከመለስ ጀርባ ከጦር አዝማችነታቸው ወጥተው (በካድሬነታቸው) በሙቱ ማግሥት የሥልጣንን በር ሲይንኳኩ፣ ኃይለማርያም ሕዝቡን የቀረቡት በተለማማጭነትና በየዘርፉ በሕልውና ተዳዳሪነታቸው ስያሜ በመጥራት፣ ማለትም –”እናንተ ሥራ አጦች፡ ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎች…” በማለት ተለሳልሰው ነበር።

በሌላ አባባል፡ ጌታ ወደ ምድር ሥጋ ለብሶ መጥቶ የሰው ልጆችን ለማዳን ካደረገው የአዲስ ሕይወት በረከት የተኮረጀ ቲአትር ነበር። በመሆኑም፡ ኃይለማርያም ብዙም ሳይቆዩ፡ በሥልጣን የመባለግ ዝንባሌያቸው ሳይውል ሳያድር በሚጠቀሙት የባለገ፡ አዋራጅ ቃላት፣ ውሽትና ኃይልን የመጠቀም ርሃባቸው፣ በተለይም “የእርገጠው፣ እሠረው፡ ግረፈው፣” ፖሊሲ ተሟጋችነታቸው (በተቃዋሚ ፓርቲዎች፡ የሃይማኖት ነጻነትና ዲሞክራሲን በሚሹ ዜጎች ቤታችንና መሬታችንን ተቀማን በሚሉት ወዘተ ላይ) በተለያዩ አጋጣሚዎች ይፋ በመሆኑ፡ ሌላው ቀርቶ “እስቲ ጊዜ እንሳጣቸው፤ ያለፈው የከፋ ነበርና ካለፈው ይሻሉ እንደሆን እንጂ አይከፉም” በማለት ዕድል የሠጧቸው ሁሉ፡ ዛሬ በራቸውን ዘግተውባቸው ማለዳ በመርህ ምክንያት ካልተቀበላቸው ሕዝብ ጋር መቀላቀላቸው ለራሳቸውም፣ መራዋለሁ በሚሉት የኢሕአዴግ ግንባሮች ጥምር ጭምር፤ በተለይም ለሕወሃት ግልጽ ከሆነ ውሎ አድሯል።

በሁሉም በኩል፡ ችግሩ ግን ምድረ በዳ በተደረገ ሃገር የሃብት ድህነት ብቻ ሳይሆን፡ የትብብር ድህነንትና መተማመን በጠፋባት ኢትዮጵያ፡ ሕዝቡ ባለፉት አርባ ዓመታት ነጻነቱንና መብቶቹን በመገፈፉ፡ ምን እንደሚደረግና የትኛው አቅጣጭ እንደሚሻል ምርጫውም አስቸጋሪ ሆኖ ቢቆይም፡ ከዚህ የከፋ ግን አይመጣም የሚለው ስሜት እጅግ ተጠናክሯል።

በትንሹም ቢሆን፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አደፍራሽነት፡ ለምሳሌም ያህል፡ ወራቤ፡ (ሥልጤ) አሥረኛ ዓመቷን ስታከብር፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ታይቷል። ኃይለማርያም ያደረጉት መቀበጣጠር፡ በፖለቲካ ይዘቱ ከንቱና ወራዳ (gutter, ignorant & insensitive) ከመሆኑም በላይ፣ ወይ ጥራቱ የተጠበቀ የትምህርት ዕድል የሌላቸው፡ ወይንም ሥራ ለማግኘት ትክክለኛው ዝርያና የፖለቲካ ንኪኪ በሚጠይቅ ሃገር፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ የተቃጣ ድንጋይ የሚሰብር ቅል ጥቃት (opportunistic attack) ሆኖ ታይቷል።

ልጆች ሊያጠፉ ይችላሉ። ያጠፋሉም። የወላጆችን ቆሽት ሊያበግኑ ይችላሉ። ግን የትኛው ወላጅ ይሆን ኃይለማርያም ከአዲስ አበባ መጥቶ ልጄን በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ወረፈልኝ ብሎ የሚደሰት ወይንም ለመሻሻሉ ተስፋ የሚያደርግ? የጠቅላይ ሚኒስትሩም ጉብኝት ዓላማም በሚኒስትር ረድዋን ሁሴንና ካሱ ኢላላ ገፋፊነት የተቀነባበረ ከሆነም ይህ አይደለም ማለት ይቻላል – ሶስቱም የአንድ ፓርቲ ሰዎች ቢሆኑም፡ ቢያንስ ቢያንስ ሁለቱ በሌጄሩ ክንፎች ውስጥ ያሉትን የገቢና ወጭ ሚዛን በሚገባ ማየት እስከ ድረስም መግነዘብ ይችላሉና!

ለነገሩ የቀድሞ የሕወሃት ምክትል ሚኒስትር ኤርምያስ ለገሠ የመለስ ትሩፋትቶች በሚለው መጽሐፍ ውስጥ እንዳመለከቱት፡ ኃይለማርያምን “ጉራጌ መራሽ አብዮት” II አሳስቧቸው ይሆን ይህን አሳፋሪ መዘባረቅ የፈጸሙት? መልሱን አላውቅም! ልገነዘብ የቻልኩትን ያህል። ያን ጊዜ እብደቱ የተፈጸመው ሕወሃት ለጉራጌና ሥልጤ መከፋፈል የቀመመው አፍዝ አደንግዝ እራሱን ስለበላው፡ መለስ ዜናዊ በግንባር መጥቶ ይቅርታ እንዲጠይቅ የተገደደበት ሁኔታ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

ከሁሉም የሚያስገርመው፡ ለወቀሳ የመጡ ይመስል፡ በተገኙበት በዓል አከባበር ላይ የማህበረሰቡን ልጆች በአዲስ አበባ “ድንጋይ ወርዋሪ” የልማታዊ መንግሥት ጠላቶች ብለው ፈርጀዋችዋል፤ ከዚህ በታች በቀረበው የኦዲዮ ፋይል ውስጥ ዲያስፖራውንና በውጭ ሃገሮች ግለሰቦች ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩትን ኢትዮጵያውያን ሴቶች እንዴት እንደሚወርፏችው ማዳመጥ ይቻላል።


 

ኃይለማርያም ልጆቻቸውን – እንደሌሎቹ የመንግሥትና ፓርቲ ባለሥልጣኖች ልጆች ሁሉ – ወደ ግል ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው ሲሰዱና አሜሪካን ሃገር በእውቁ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምሩ፤ የሠፊውን ሕዝብ ልጆች ግን በሃገራቸው በሰላም እንኳ እንዳይኖሩ፥ እርሳቸው የሚመሩት ግራ የተጋባ ተናካሽ ፓርቲ አባል እንዲሆኑ በማስገደድና ካልፈለጉ የትምህርትና የሥራ ዕድል በመንሳት፡ በየቀኑ በፓሊስ በማሳፈስ ብዙ ወንጀል ከመፈጸማቸውም ባሻገር፡ ለወጣቶች ከሃገር ለመሰደድ ዋናው ምክንያት ናቸው።

እንዲሁም፡ በዚህ ወቅት በውጭ ንግድ አሠራሯ በእርሳቸው አመራር ሃገሪቱ ማግኝት ያልቻለችውን ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በዓመት የሚለግሳትን ዲያስፖራ ዘላባጅ በሆነው ንግግራቸው በስም በመጥቅስ እንደ ቀጣፊ፡ አታላይ በማጥላላታቸው፤ የአስተሳሰባቸውን አናሳነት ከማሳየታቸውም ባሻገር፣ ከመጭው ምርጫ ጋር መያያዙን ደመነፍስ ያለው ሁሉ ሊገነዘበው የሚችል ነገር ነው።

ለዚህም፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የገዥው ፓርቲ የምርጫ ድል ማንዋል ተብሎ በትምህርት ሚኒስቴር ስም ህዳር 2014 በተበተነው ማንዋል እንደተመለከተው: የዜጎችን የዕውቀት መግብያ ቦታ፣ የከሠረ ፖለቲካቸው መቸርቸሪያ ቦታ ማድረጋቸው ምን ያህል ለሃገር እንደማያስቡ አመላካች ነው።

ለሃገሪቱ ኪሳራው ግን ግልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ እርሳቸው ሥልጣን ላይ ከወጡ ወዲህ የተከሰቱትን ሁኔታዎች ብንገመግም፡ ሥርወ መሠረታቸው ካድሬያዊ በመሆኑ፡ አስተሳሰባቸው፡ አመራራቸውና የፖሊሲ አፈጻጸማቸው በዘፈቀደና ውጤት አልባ መሆኑ ይታያል። በዚህም መንስኤ፡ አዲሱ ለገሠ ባለፈው ሐምሌ ወር 2014 የአመራር ግንባታና የትራንስፎርሜሺን ጉዞ ላይ እንደጠቆሙት፡ በአመራር ዕጦት ምክንያት “ኢሕአዴግ ፈተና ውስጥ መሆኑን” ፓርቲውም ያምናል።

በመሆኑም፡ በእነዚህ 26 ወራት በታዩት ችግሮች ምክንያት፡ ቆንጂት ስታረጅ ምን ትሆናለች እንዲሉ፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ማጠፊያው ሲያጥርባቸው፡ ከምርጫው በፊት ዜጎችንና ቤተስቦችን በመከፋፈል፡ ሕወሃትን ለማስደሰት ብዙ መሞከራቸውን ለማሳየት ታቅዶም የሚሠሩ ብዙ ነገሮች ይታያሉ። በአከናወናቸው ተግባሮችም ሲለኩ፡ እርሳቸው ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ፡ የሚከተሉት ችግሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ተባብሰዋል፦

  *   ካድሬያዊ የሥልጣን ጉጉነትና በተለያዪ ምክንያቶች በሕዝቦች መካከል ክፍፍሎች እንዲፈጠሩ መጣር

  *   በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ያፋፋሙት ግድያና አፈና መባባስ (አርሲ፡ አዲስ አበባ፡ ደሴ፡ ባሌ፡ ሐረር ወዘተ)

  *   በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የፈጸሙት ግድያዎችና ማሠቃየቶች

  *   በኦቶዶክስ እምነት ተከታዮች ወጣቶች ላይ ያነጣጠረው ሽብራቸው

  *   በሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ላይ እየተፋፋመ ያለው ማሳደድና በተክርስቲያኖችን ማፈራረስ

  *   በጋዜጠኞች ላይ የቃጡት የሕልውናና የሳይኮሎጂክል ጦርነቶች

  *   በከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ላይ እየተካሄደ ያለው የተጠናከረ መውጭያ መግቢያ የሚያሳጣ የማሳደድና አስገድዶ የፓርቲ አባል የማድረግ ዘመቻ

  *   በአዲስ አበባ ውስጥ የተካሄዱት የመሬት ዘረፋዎችና ደጋፊ የሌላቸውን ወገኖች ቤቶች በሕገ ወጥ መንገድ ማፈረሶችና ተመጣጣኙን ካሳ አለመክፈል

  *   በገጠር የመሬት ዘረፋ በማካሄድ ሕዝቡንና ማኅበረሶብችን ማፈናቀል (ጋንቤላ፡ ደቡብ ኦሞ፡ አዲስ አበባ ዙርያ ወዘተ። ይህንን በሚመለከት ሕዝቡ ፍትህ ለማግኝት ችግሩን ለማሰማት ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ተወካዮችን ሲልክ፡ የኃይለማርያም መልስ የመጡትን የሕዝብ ተወካዮች በፓሊስ በማስደብደብ ብዙዎቹ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው እስር ቤት መወርወራቸው

  *   የሕገ መንግሥታዊ መብቶች ክፉኛ መሸርራቸው

  *   ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ እስረኞች የሚገኙባት ሃገር መሆኗ ይገኙበታል

  *   ከተግባራዊ ክንውኖች ይልቅ የሃስት ፕሮፓጋንዳዎች ተጠናክረዋል

  *   በኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ የዓለም ጭራ ለመሆን በቅታለች።

 

ስለኃይለማርያም በሥልጣን መስከር የተሰጡ ምስክርነቶች

ቀደም ሲል ለሠራተኛ ማህበራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር በኢሕአዴግ አስተዳደር የሠራተኛው በማህበራት መደራጀት ቀደምት ዓላማ የመብት ጉዳይ ሳይሆን፡ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን ነው ሲሉ የሠነዘሩት የሠራተኛውን ድሎች ለመቀልበስ ያላቸውን ዓላማ ፤ እንዲሁም የንግዱን ዘርፍ (private sector) አስመልከተው ያድረጉን ንግግር የሕልውናው ትርጉም የሚለካው: መንግሥት በሚመራው ልማት ውስጥ (ብድር ለውጭ ባለሃብቶችና የሕወሃት ሰዎች እየተለገሠ) ተባባሪ ብቻ እንዲሆን መጋበዛቸው ብዙዎችን ማስቆጣቱ ለአስተሳሰባቸው ኋላ ቀርነት የማያጠራጥር ምልክት ነው!

በሥራ መስክም፡ ባለፈው ሐምሌ ወር ከግል ንግዱ ማህበረስብ (private sector) ጋር ውይይት ሲደረግ፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ የቃዡበት ነገር ነበር። ብዙ አንባብያንን ያስገረመው፣ ግለስቡን ከሚያውቋቸው መካከል አንዱ ለAddis Fortune እንዲህ ሲል ነበር የገለጿችው፦

  “I don’t know what power does to people,” a prominent businessman, who has known the Prime Minister for many years, commented, in observing the changes he says he has seen in Hailemariam. “He wasn’t like this before.” – “ሥልጣን ሰዎችን ምን እንደሚያደርግ አላውቅም። ይህ ግን ቀድሞ የማውቀው ኃይለማርያም አይደለም።”

 

እስቲ ኃይለማርያምን መካከለኛ ው ምሥራቅ ውስጥ በቤት ሠራተኝነት ክሚሠሩት ጋር የሚያላትም ምን ተፈጠረ?

ከላይ ኦዲዮ ላይ እንደተደመጠው ‘ልዩ ዐይነት ሰው’ አድርገው ራሳቸውን የሚያዩት ኃይለማርያም፡ በቤት ሠራተኛነት ዕዳ ገብተው፡ ሥራ አግኝተው ስንት ደጅ ጠንተው ዘመዶቻቸውን ውጭ ሃገር ሆነው የሚረዱትን ኢትዮጵያውያን ሴቶች ‘ገረድ’: ‘እንዳበደ ውሻ ‘… በሚል አዋርደዋቸዋል፤ ስሜቶቻቸውንም ክፉኛ ጎድተዋል። ብዙኢትዮጵያውያንንም ሰሞኑን በሬዲዮና በጽሁፍ እንደቀረበው ሁሉ፡ እጅግ አዝነዋል፡ ተቆጥተዋልም! ይህ ከንቱ ጥላቻና ጣላትነት ለምን አስፈለገ ለሚለው መልሱን አላውቅም! እርሳቸውም የሚያውቁት አይመስለኝም። ምናልባትም አንዴ መናገር ከጀመሩ የማይያዘውን ሁሉ ዝም ብለው ሲቀጣጥሉ አዳልጧቸው ሊሆን ሰለሚችል!

አንዷ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአናሳ ግለስብ መካክል መቆጠሯ ያስቆጣት፡ በቤት ሠራተኛነት በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ የምትኖረው ሔርሜላ የተባለች ኢትዮጵያዊት – ኃይለማርያም ‘ውሻና ገረዶች’ በማመሳስለ ማንቋሸሻቸው ማነታቸውን ቁልጭ አድርጎ አሳይቷት – ወረቀቷንና ብዕሯን በማገናኘት ግሩም የሆነ ግጥም ከትባ ለኢሣት በመላኳ – ይህ ገጽም የዚያ ተቋዳሽ በመሆን ለአንባቢዎቹ በከፊል የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ስንኞች እንደሚከተለው አቅርቦታል፦

  “አትበሉን እብድ ውሻ፤ ከሃገር ርቀን እኛ ብንሰደድ
  እኛ ለለፋነው እኛ ለደክምነው አላቹሁን ገረድ?

  ሎቶሪ ደርስዎት ሥልጣን ላይ ቢወጡ
  የሥራ ድርሻዎን ምንም ሳይረዱ ሳያውቈት በቅጡ
  ስለኛ ግርድና አፎን ለመክፈት አደባባይ ወጡ?

  የሃገርን ገንዘብ ዘርፈን ስላልሸጥን?
  የደሃዎችን ደም ስላላፈሰስን?
  የምስኪንን ሕይወት ስላላጠፋን?
  የስም መጠሪያችን እብድ ውሻ ነውን? አይ ጠቅላይ ሚኒስትር

  ተላላኪ ዱዴ መሆኖን አውቀው፣
  አፎን ከመክፈት የኛን ሥራ ንቀው
  ምናለ ቢያገኙ እራስዎን ፈልገው?

  ከሚጎርሱት ሥጋ አጉርሱን አላልንም
  ከሚጠጡት ውስኪ አጠጡን አላልንም
  እርስዎ በምን መሥፈርት እብድ ውሻ አረጉን? …

  ፍትህ ተቸግረን ነጻነት ብናጣ፡
  ተስፋ ስንቀን ለስደት ብንወጣ
  እብድ ውሻና ገረድ የሚል ስም ታወጣ?”…

 

ከኢሣት የተገኘውን የሔርሜላን ግጥም በሙሉ ለማዳመጥ ከዚህ በታች ያለውን ይጫኑ፦

 

ኢትዮጵያ ለምን እንዲህ መጫወቻ ለመሆን ተደረገች?

እርቃኑን የቀረው ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 72 “የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ሥልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡” ይላል። ፓርላማና ፍርድ ቤቶች አሉ ቢባልም – ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃገሪቱ ፊደራል አስተዳደር ሥልጣን ቁንጮና ባለሙሉ ባለሥጣን ሆኖ – በሕወሃት (መለስ) ሽፍጠኛ አሠራር ምክንያት፡ በእነዚህ አካሎች ውስጥ ቅጥረኞችንና ማነንታቸውን እንኳ ጠንቅቀው በማያውቁ ተክሎች በመሙላት በመንግሥት ሥልጣን ክፍፍል ውስጥ የሕግ የበላይነትና ቁጥጥር እንዳይኖር ደባ ተፈጽሟል። የአሁኑ ብቻ ሳይሆን፡ ይህም ሃገራችንን ለረዥዝም ዘመናት ሲጎዳት ይኖራል – ዛሬ ቢታረምም እንኳ!

ዛሬ ይህ ሥልጣን በደህነንቱ፣ ወታደሩና በሕወሃት ከፍተኛ ካድሬዎች እጅ በመሆኑ፣ ኃይለማርያም በጠቅላይ ሚኒስትር ስም የተቀመጡ ጉዳይ አስፈጻሚ ብቻ ናቸው። በዚህም ምክንያት፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕግ የሚሠራው በሥልጣን ላይ ላሉት፣ ለተቧደኑ ወገኖችና ከእነርሱ ጋር ለተሳሰሩ ሃብታሞችና ዘራፊዎች ነው። ለምሳሌም ያህል፡ ሕወሃት አርባኛ ዓመቱን ለማክበር ይዘጋጃል። የምንሰማው ነገር ግን አሳፋሪ ዘረፋ ነው፤ ሕዝቡ ታክስ ብሎ የከፈለውን ገንዘብ – EFFORT እያለ- ስንት ችግር ያለባት ሃገር ለፖለቲካ ፓርቲ ፈንጠዝያ የሕዝብ ገንዘብ እንዲባክን መደረጉ!

በዘመነ ሕወሃት እየታየ ያለው ይህ ሁኔታ የሚያረጋግጠው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 72 እና 74 ላይ እንደሠፈረው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃገሪቱን የማስተዳደር ከፍተኛው የፌዴራል መንግሥት ሃላፊነት ኃላፊነት ቢኖርበትም፡ ‘ሙስኝነትንና ኪራይ ስብሳቢነትን እንዋጋለን ‘ እያለ በየቀኑ ጨረባ ወፍ ይመስል፡ ሁኔታውን ለተቧደኑት ኃይሎች ማመቻቸን የዕለት ተዕለት ተግባሩ አድርጎ የሕዝቡን ጥቅሞች ወደጎን ሲገፋ ቆይቷል። ለዚህም ዋናው አጋሩ የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ነው!

በየትኛውም ሃገር ይህ የሚከሰተው፡ የበላይ አስተዳዳሪው ደካማ ሆኖ፡ ሕግና አስተዳደር በጠንካራ ቡድኖች መካከል የመታገል ወይንም የመተካከከ ነገር እንዲኖር ሁኔታው ሲያስገድድ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የኃይለማርያም ሥልጣን በመለስ ጊዜ እንደነበረው ተወዳዳሪ ሳይሆን፡ የቡድኖችን ጥቅም ብቻ በማስከበር ላይ ያተኮረ ነው – የሕወሃትን! በዚህ ሁኔታ ውስጥ ወደአዘቅቱ እየተገፋች ያለቸው ኢትዮጵያና የሕዝቧ ጥቅሞች ናቸው!

ኃይለማርያም ግን ለሃገርና ለወገን ጠቃሚ ነገሮች ለመሥራትና ለዚህ ኃላፊነት ብቁ ሆነው ለመገኘት የአዕምሮ ነጻነት፡ ቅንነት፡ ታማኝነትና ብሔራዊ ስሜት ይጎድላቸዋል። ምናልባትም፡ መለስ እንዲህ ያለሰው ለመመልመል መቻሉ ከፍተኛ ችሎታ የነበረው መሆኑን ማመን ያስፈልጋል፤ በተለይም ከአንድ ባህር የተቀዱ ይመስል (clones) ከመቃብር በታችም ሆኖ ታማኝ አገልጋይ ለማግኘት መቻሉ!

ስለሆነም፡ በሥራቸው ኃይለማርያም ንፋስ የመታው ግንድ ይመስል፡ የሕዋሃትን ሰዎች ግንባር እየተመለከቱ፣ የየቀኑን እርምጃ ይቀይሳሉ እንጂ ኢትዮጵያ በትክክለኛ ፖለቲካ፡ ብሄራዊ ጥቅሞች፣ ፖሊሲና ሕግ ላይ የተመሠረተ አቅጣጫ እንድትይዝ የሚረዱ ግለስብ አይደሉም።

አንቀጽ 74 ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚከተሉት እንደሚጠበቁ ያሳያል፦ “[ጠቅላይ ሚኒስትሩ] የመስተዳድሩን ሥራ አፈጻጸምና ብኝት ይቆጣጠራል፣ አስፈላጊ የሆኑ የእርምት እርምጃዎችን ይወስዳል፡” ይላል።

ነገር ግን ለምሳሌም ያህል፡ ዚጎች መሬቶቻቸውን ሲነጠቁ ኃይለማርያም ደግመው ደጋግመው ቢሰሙም፡ የተጎጂ ዜጎችን መብቶች ለማስከበር ቅንጣት እርምጃ ወስደው አያውቁም። ከላይ እንደተጠቀስው፡ አቤት ባዮችን በማስደብደብና በማሠር ታውቀዋል!

በኃይለማርያም አመራር ሥር፡ ፍርድ ቤቶች የባሰ ፍርደ ገምድሎች መሆናቸው የየቀኑ ሁኔታ ነው። የድሃውን ሁኔታ እንኳ ብንተው፡ በቅርቡ አንድ የእራት ግብዣ ላይ የሶል ረቤልስ ባለቤት ቤተልሄም ጥላሁን መብቷንና ያቋቋመችውን ቢዝነስ ስም በአንድ የካናዳ ኩባንያ ስትነጠቅ፡ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ለውጭው ኩባንያ ፈረደ። እርሷም ክሷን ወደውጭ ሃገር በመውሰድ ለኢትዮጵያዊነት አሳዛኝና አሳፋሪ በሆነ መንገድ፡ በአሜሪካን ፍርድ ቤት መብቷን ለማስረከብ ችላለች!

ክዚህ ምን ትምህርት ተገኘ? ኃይለማርይም ምን አደረጉ? ምን ተሻሻለ? ምንም!

ይባስ ብሎ፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፍርድ ቤቶች አሠራር አንዳንድ የሕወሃት አባሎችን እያሳሰባቸው መጥቷል። ቆሽታቸው የደበነውን፡ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ወደ ጎን ትተን፡ አንዳንድ የሕወሃት አባሎች በገጾቻቸው ላይ “ይህ ለምን ተደረገ: ለምን ይሆናል?” በማለት ጥያቄዎችን ማንሳት ጀምረዋል። ከዚህ በፊት እንዲህ ያለነገር ያደርጉት የነበረው፡ ትግሬዎችን የሚመለከት ነገር ሲመጣ ነበር! ሁኔታው እውነትም፡ ወይዘሮ ዘውዴ ወልደማርያም ላይ የተፈጸመው ወንጀል፡ ማለትም ፍርድ ቤት የወሰነባቸው ሃገሪቱ መንግሥት አላት ብሎ ለማመን የሚያስቸግር በመሆኑ ነው።

ይህ የሚያሳየው የፍርድ ቤትችን ብቃት ማነስ ሳይሆን፡ ሌቦች በሥልጣን ውስጥና ዙሪያ በመቆናጠጣቸውና በአንቀጽ 72 መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሸከመውን ሃላፊነቱን ለመወጣት ብቃት እንደሚያንሰው የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም በአንቀጽ 74 መሠረት፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፖሊሲ አፈጻጽምና ተግባራዊነት መሰናክል የሚሆኑትን ችግሮችና መሰናክሎች መፍትሄ ለመሻትና ለመስጠት ወይ ፍላጎት ከማጣት ወይንም፣ የኃላፊነቱን ዳር ድንበርና ጥልቀት ለመገንዘብ ካለመቻልም ሊሆን ይችላል።

ካድሬዎች ብዙ ጊዜ የሚታወቁት በአነብናቢነታችውና ያለአራት ነጥብ አንድ መጽሐፍ ያህል ለመተርከ መቻላቸው ነው። በተደጋጋሚ እንደታየው፡ አንዱ የኃይለማርያምም ችግር ከተናገሩት ውስጥ ገለባው እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ነው። በድፍረት ብዙ ሲናገሩ፡ ዕውቀት ሊያስመስሉት ይችላሉ።

እርግጠኛ ሆነን መናገር እንችላለን – አዋቂዎች እንደሚሉት በጀብደኝነትና በጉብዝና መካከል ትልቅ ልዩነቶች አሉ – ፈረንጆች temerity እና courage መካከል የሚፈጥሩት ልዩነቶች ዐይነት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ይህንን ያልተገነዘቡ በመሆናቸው፡ ብዙ በተናገሩ መጠን አዳማጮቻቸውን ያሳመኑ እርሳቸውም እራሳቸውን ሲያዳሙ፡ አዋቂ ሆነው ይሰማቸዋል፡

ለዚህም መለኪያው እርሳቸው ሌሎች ዜጎችን ለማዋረድ ‘ነጻ’ መሆናቸው ነው!
*Updated.
 

ተዛማጅ ጽሁፍ:

  Is the PM in any form or shape to praise his role in protecting Ethiopians in Saudi Arabia? Part I

 

%d bloggers like this: