አቤት የሕወሃት ግፍ! የፖለቲካ እስረኞች የሆኑት በማረሚያ ቤት የሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ዝርፊያ ተፈጸመብን አሉ

28 Dec

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

በወንጀል ድርጊት ተካፋይ በመሆን፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፈራረስ፣ ግንቦት 7 እና ዲምሕት (ትሕዲን) ከሚባሉ ቡድኖች አመራሮች ጋር በህቡዕ በመገናኘት ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና ግለሰቦች፣ በእስር ላይ በሚገኙበት ማረሚያ ቤት ዝርፊያ እንደተፈጸመባቸው ታህሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

ዋስትና ተከልክለው ክስ ተመሥርቶባቸው ከጥቅምት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ በሚገኙበት ማረሚያ ቤት ታህሳስ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት እስከ ታህሳስ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 5፡00 ሰዓት ድረስ ዝርፊያ የተፈጸመባቸው፣ የማረሚያ ቤቱ አካል (አባል) ባልሆኑ የፌዴራል ፖሊስና የደኅንነት አባላት መሆኑን፣ ተጠርጣሪዎቹ በጠበቃቸው አማካይነት ክሳቸው እየታየ ላለበት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት አመልክተዋል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በመዝገብ ቁጥር 166/07 ክስ ከመሠረተባቸው አሥር ተጠርጣሪዎች መካከል፣ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) አመራሮች አቶ ሀብታም አያሌውና አቶ ዳንኤል የሺዋስ፣ የዓረና ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሸዋስ አሰፋ፣ እንዲሁም አቶ ዘለዓለም ወርቅ አገኘሁ፣ አቶ ዮናታን ወልዴና አቶ ባህሩ ደጉ በጠበቃቸው አቶ ተማም አባቡልጉ አማካይነት ‹‹ተፈጸመብን›› ስላሉት ዘረፋ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ጠበቃው አቶ ተማም እንደገለጹት፣ በተጠቀሰው ቀን በእሳቸው ደንበኞች ላይ ብቻ የፌዴራል ፖሊስና የደኅንነት አባላት ሕገወጥ በሆነ መንገድ ዕቃቸውን በመበርበር ማስታወሻዎቻቸውን፣ ለክርክር የሚረዷቸውን ሐሳብ ያሰፈሩባቸውን ወረቀቶችና መጠኑ ያልተገለጸ ገንዘብ ወስደውባቸዋል፡፡

በፍተሻ ስም በደንበኞቻቸው ላይ የተፈጸመው በደል በሦስት መንገድ የሕግ ጥሰት መሆኑን ጠበቃ ተማም ሲያስረዱ፣ አንደኛ ፍተሻው ከማረሚያ ቤቱ አባላት (አካላት) ውጪ መደረጉ የሕግ ጥሰት ነው ብለዋል፡፡ ፍተሻ ይካሄድ ቢባል እንኳን መደረግ የነበረበት በማረሚያ ቤቱ አባላት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ፍተሻ ሊካሄድ የሚችለው ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12፡00 ሰዓት ብቻ መሆን ሲገባው፣ ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 5፡00 ሰዓት መደረጉ ሕገወጥ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በመጨረሻም የደንበኞቻቸውን ገንዘብና ማስታወሻዎች በሕገወጥ መንገድ መውሰዳቸው የመከላከል መብታቸውን የሚያጣብብ በመሆኑ፣ ተገቢ ያልሆነና ሕግን የጣሰ ድርጊት መሆኑን አቶ ተማም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ፍትሕ የማግኘት መብታቸውንም ጭምር የሚያጣብብ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በመሆኑም አቶ ተማም ፍርድ ቤቱን የጠየቁት የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ደንበኞቻቸውን በመበርበር ማስታወሻዎቻቸውንና ገንዘባቸውን የወሰዱት ማንነት እንዲገልጹ፣ ብርበራውን ያደረጉት የፌዴራል ፖሊስና የደኅንነት አባላት ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ያለቦታቸው ማረሚያ ቤት ድረስ ሄደው በፈጸሙት ሕገወጥ ተግባር እንዲጠየቁላቸውና ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ወንጀል እንዲከሰሱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡ ከደንበኞቻቸው ያላግባብ የተወሰዱት ገንዘብና ሰነዶች በአስቸኳይ እንዲመልሱላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውም ጠይቀዋል፡፡

ሌላው አቶ ተማም ለፍርድ ቤቱ ያመለከቱት፣ ከውጭ (ከማረሚያ ቤቱ አካላት ሌላ) የመጡ ኃይሎች በደንበኞቻቸው ላይ ብርበራ ሲፈጽሙ፣ ማረሚያ ቤቱ የደንበኞቻቸውን ደኅንነት ለመጠበቅ ብቃትም ሆነ ፈቃደኝነት እንደሌለው እንደሚያሳይ ጠቁመው፣ ፍርድ ቤቱ ዋስትና ከልክሎ ወደ ማረሚያ ቤት የላካቸው አስተማማኝ ጥበቃ ያገኛሉ በሚል የነበረ ቢሆንም፣ ያ ሳይሆን በመቅረቱ ዋስትናቸው ተጠብቆ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ ጥያቄያቸው የሚታለፍ ከሆነ ማረሚያ ቤቱ በማይቆጣጠረውና ለደኅንነታቸው በማያሠጋ ቦታ እንዲሆኑ እንዲታዘዝላቸውም አቶ ተማም በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቤቱታውን ካቀረቡ በኋላ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው አስተያየት፣ ሕገ መንግሥትን መሠረት አድርጐ የተቋቋመን የመንግሥት ተቋም ‹‹ብቃት የለውም›› እያሉ ማጣጣል ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ ንፁህ ዘረፋ የሚል ቋንቋ መጠቀምም ተገቢ አለመሆኑን ዓቃቤ ሕግ ተቃውሞ፣ ጠበቃው የደንበኞቻቸው ዋስትና እንዲጠበቅ ያቀረቡት አቤቱታ ቀደም ባለ ችሎት ብይን ያገኘ በመሆኑ የሚለው እንደሌለ ተናግሯል፡፡ የተጠርጣሪዎች ጠበቃና ከሳሸ ዓቃቤ ሕግ አቤቱታቸውንና ተቃውሞአቸውን ለፍርድ ቤቱ ካስረዱ በኋላ ፍርድ ቤቱ በልዩነት ብይን ሰጥቷል፡፡

ሰብሳቢ ዳኛው በብይን ሐሳባቸው በመለየት እንደተናገሩት፣ ተጠርጣሪዎች ሁልጊዜ በማረሚያ ቤት ላይ የሚያቀርቡትን አቤቱታ ፍርድ ቤት የመቀበል ሥልጣን የለውም፡፡ መቀበልም የለበትም፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞብናል የሚሉ ከሆነ ለፖሊስ አመልክተው እንዲጣራ ካደረጉ በኋላ፣ ፖሊስ ያጣራውን የምርመራ ውጤት ዓቃቤ ሕግ መርምሮ ክስ ሲመሠርት ፍርድ ቤት የሚያየው እንጂ፣ በቀጥታ ታሳሪ ስለሆኑ ብቻ ፍርድ ቤት ተቀብሎ ማየት እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡

በሐሳብ የተለዩት የግራና ቀኝ ዳኞች በአብላጫ ድምፅ እንደገለጹት፣ ማረሚያ ቤት በቀረበው አቤቱታ ላይ ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች መልስ ከሰጡ በኋላ፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤትን ምላሽ የማየት ሥልጣን አለው? ወይስ የለውም?›› የሚለው የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

(Credit: Semayawi Party)

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ ተማም ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጐ የተቋቋመውን የመንግሥት ተቋም (ማረሚያ ቤትን) ‹‹ንፁህ ዘረፋ፣ ብቃት የሌለው›› የሚሉ ቃላትን መጠቀማቸው አግባብነት የሌለው በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

ጠበቃው በተናገሩት ላይ ሁለቱ ዳኞች የሰጡት ሐሳብ የሳቸውም እንደሆነ የገለጹት ሰብሳቢው ዳኛ ጠበቃውን በማስጠንቀቂያ እንዳለፏቸው በመጠቆም፣ ንግግራቸው ከሕግ ባለሙያ የማይጠበቅ በመሆኑ ለወደፊቱ ሊያስቡበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ጠበቃው በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተፈጽሟል ባሉት ድርጊት ምክንያት ተቋሙን መናገራቸው ‹‹የበቀል ዕርምጃ›› ሊያስወስድ እንደሚችል፣ ማለትም ማረሚያ ቤቱ አሳጥተውኛል በሚል ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ሲናገሩ፣ ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው የሚናገሩት እንዳላቸው በመግለጽ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ጠበቃው እንዲናገሩ ፍርድ ቤቱ ሲያስታውቅ ከጠበቃው ጋር ተነጋግረው አቶ ሀብታሙ እንዲናገሩ ተፈቀደላቸው፡፡

ፍርድ ቤቱ ዋስትና ከልክሏቸው ማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከራከሩ ብይን መስጠቱን ያስታወሱት አቶ ሀብታሙ፣ ተበደልን ብለው ለፍርድ ቤተ በመናገራቸው ማረሚያ ቤቱ የበቀል ዕርምጃ የሚወስድባቸው ከሆነ፣ ወደ ማረሚያ ቤት እንዴት ሊመለሱ እንደሚችሉና የደኅንነታቸው ጉዳይ ሥጋት ውስጥ የከተታቸው መሆኑን አስረዱ፡፡ አቶ ሀብታሙ እንደጨረሱ የመሀል ዳኛው እሳቸው ማለት የፈለጉት ተጠርጣሪዎቹን ወደ ማረሚያ ቤት የላካቸው ፍርድ ቤቱ ሳይሆን ሕጉ መሆኑን ለመግለጽ እንደሆነ አስረዱ፡፡ ማረሚያ ቤቱ የበቀል ዕርምጃ ይወስዳል ማለት ፈልገው ሳይሆን፣ በግለሰብ ደረጃ ሊያጋጥማቸው ይችላል በሚል መሆኑንም በማከል እሳቸው የተናገሩትን ወደ ሌላ ማዞር ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በዕለቱ መዝገቡን ቀጥሮ የነበረው ሰባተኛ ተጠርጣሪ ማለትም አቶ አብርሃም ሰለሞን እንዳልደረሳቸው የገለጹትን በምርመራ ወቅት ለፖሊስ የሰጡት ቃል መድረስ አለመድረሱን ለማረጋገጥ የነበረ በመሆኑ፣ ከላይ የተገለጸው አቤቱታ ሊቀርብ ችሏል፡፡ ተጠርጣሪው ሰነዱ ደርሶአቸው በጽሕፈት ቤቱ በኩል የክስ መቃወሚያቸውን ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው የፍርድ ቤት ውሎ ጠበቃ ተማም የደንበኞቻቸው ቤተሰቦች ከሌሎች ተጠርጣሪ ቤተሰቦች በተለየ ሁኔታ ስማቸው ተመዝግቦ መያዙ ሥጋት እንደፈጠረባቸው በማመልከታቸው ምክንያት ማረሚያ ቤቱ ቀርቦ እንዲያስረዳ የታዘዘ ቢሆንም፣ ማረሚያ ቤቱ በላከው የጽሑፍ ማስረጃ የተባለው አቤቱታ ሐሰት መሆኑንና የሚስተናገዱት እንደማንኛውም ተጠርጣሪ ቤተሰብ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ጠበቃው የማረሚያ ቤቱ በጽሑፍ ሳይሆን በአካል ቀርቦ እንደሚያስረዳ መታዘዙን ቢያስረዱም፣ ፍርድ ቤቱ መልስ ስጥ ተብሎ መታዘዙን አስታውሶ በጽሑፍ በቂ መልስ መስጠቱን በመግለጽ የጠበቃውን ክርክር አልፎታል፡፡

ተጠርጣሪዎች ሰነድ እንደተወሰደባቸውና ገንዘባቸውን እንደተዘረፉ ላቀረቡት አቤቱታ ማረሚያ ቤቱ ቀርቦ እንዲያስረዳና ዓቃቤ ሕግ በቀረበበት የክስ መቃወሚያ ላይ ምላሹን ለታህሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ይዞ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

/ምንጭ፦ ሪፖርተር – በማረሚያ ቤት ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ዝርፊያ ተፈጸመብን አሉ
 

%d bloggers like this: