የማይክሮፋይናንስ አመራር ላይ ሆነው ተቋሞቹን ለኤኮኖሚ ዕድገት ሳይሆን የሕወሃት የማፈኛ መሣሪያ ያደረጉት የኤኮኖሚክስ ምሁሩ የዋጋ ግሽበቱ ባለበት ሊገታ ይገባል ይላሉ

2 Jan

የአዘጋጁ አስተያየት፡

  ዶ/ር ጣሰው ወልደሃና የሚታወቁት ለሕወሃት አመራር ካላቸው ቅርብነትና በየዓለም አቀፉ ጉባኤ ቋሚ መልዕክተኛ በመምሰላቸው ነው። ክዚያ በተጨማሪም፡ እንደወዳጃቸው የአካባቢና ብሔራዊ አመራር ሁሉ፡ ክልላዊና ብሔራዊ የማይክሮፋይናንስ አሠራሮችን አሻሽለው፡ ተጠቃሚ ለሚሆነው ለደሃው ኅብረተስብ ባድረጉት አስተዋጽኦ አይደለም።

  ኢትዮጵያ ውስጥ በማይክሮፋይናንስ ዕርዳታ ስም ብዙ ገንዘብ ገብቷል። የተ.መ.ድ. የኢንቪስትመንት ዘርፍ (UN Fund for Capital Development – UNCDF) በተለይም ባለፉት ስምንት ዓመታት ከለጋሾች ጋር በመተባበር፡ ብዙ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል።

  ነገር ግን የተ.መ.ድ. የልማት ማኅበርም (UNDP)፡ በተገኘው የዕርዳታ ገንዘብ ለነዶ/ር ጣሰው ወዳጆች የኮንሰልተንሲ ፕሮግራሞችና ሃገሮች ጉብኝቶች ከማዘጋጀት፡ የውጭ እንግዶችን ከማስተናገድ ውጭ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማይክሮፋይናንስ በኩል ያስገኙት ውጤት እምብዛም ነው። ሌላው ቀርቶ አንድ ግለስብ ከማይክሮፋይናስ ብድር ሲፈልግ፡ ከሚታዩት ጥንካሬዎቹ መካከል፡ ለኢሕአዴግ ያለው ድጋፍና ተባባሪነት ነው።

  ማይክሮፋይናንስ ሃገሪቷን ብዙ ለመጋጥ የሚቻልበት፡ ጥቅማ ጥቅሞች የሚገኙበት አካባቢ በመሆኑ፡ ከ2011 ጀምሮ የሕወሃት ጄኔራሎችም በመከላከያ ሚኒስቴር ስም ማይክሮፋይናንስና የመከላከያ ባንክ ለማቋቋም ዕቅዳቸውን አጠናቀው በ2012 በሚኒስትሩ በሲራጅ ፈርጌሳ አማካይነት ጥያቄ ማቅረባቸው አይዘነጋም።

  ማይክሮፋይናንስ ኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ የተበከለና የሕወሃት የዘርና ስትራቴጂያዊ ግባ ማሳኪያ በመሆኑ፡ ለደሃው ሕዝብ ጥቅሙ እንደሌሎቹ በማደግ ላይ እንደሚገኙት ሃገሮች ሊሆን አልቻለም።

  እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ በማይክሮ ፍይናንስ አማክይነት በመካሄድ ላይ ባሉ ፕሮጀክቶች ላይ UNCDF እና ሌሎችም በራሳቸውና በውጭ ኦዲተሮች ሥራቸውና መጽሐፋቸው ይታይ ሲባሉ፣ በሰበብ አስባብ እያስተላለፉ፡ በአፍሪባ ውስጥ ኢትዮጵያ ተገቢው የግምገማ ሪፖርት ያልቀረበባት ሃገር ናት። አሁንም ከ2015/16 በፊት ምንም ዐይነት ግምገማ አይኖርም – UNCDF እንዳመለከተው።

  በዚህም ምክንያት ሕወሃትም በነዶ/ር ጣሰው አይያዝ በመርካቱ፡ ይህን በተመለከተ ምንም እንቅስቃሴ አይታይም።

  በ2013 የወጣ አንድ የMicroLead ሪፖርት MicroLead Mid-Term Evaluation እንዳሳየው ከሆነ የኢትዮጵያ ማይክሮፋይናስ ድርጅቶች በማኔጅመንት ማትሪክስ ትንተናና በመረጃ አሰጣጥና ትብብርም ዝቅተኛውን ነጥቦች ካገኙት ሃገሮች መካከል ናቸው።

  ዶ/ር ጣሰው በበላይ ሥራ አስፈፃሚነት ከ2000 ጀምሮ የሚመሩት የኢትዮጵያ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማህበር 30 አባላት ያሉት ሲሆን (ዝርዝራቸው)፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የተቋማቱ እንቅስቃሴ ለውጭው ዓለም የሚገለጸው እሳቸው ዋና አዘጋጅ በሆኑበት Microfinance Development Review ነው።

  ታዲያ በየቀኑ የድሃውን ሕዝብ ሁኔታ የሚመለከተው የማይክሮፋይናንስ አመራራቸው ሳያሳስባቸው፡ እንዴት ነው አሁን ዶ/ር ጣሰው ወልደሃናን የዋጋ ግሽበቱ ያለበት ደረጃ ላይ ቱፍታቸውን የሚሰጡት?


 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 22፣ 2007 (ኢዜአ) አገራዊ የዋጋ ግሽበቱ ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ ለጤናማ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ መደላድል የሚፈጥር በመሆኑ መንግሥት ባለበት ሊዘልቅ የሚችልበትን ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ኃብት ምሁር አስገነዘቡ።

ኢትዮጵያ ካስመዘገበችው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጎን ለጎን የዋጋ ግሽበትን በነጠላ አኃዝ ማቆየት እንደቻለች ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምና የዓለም ባንክን ጨምሮ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የዋጋ ግሽበቱ በነጠላ አኃዝ መቆየቱም ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ጤናማና ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ የመገኘቱ ማሳያ እንደሆነም ነው ተቋማቱ በሪፖርታቸው በተደጋጋሚ ያመለከቱት።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ከ30 በመቶ በላይ ደርሶ የነበረውን የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አኃዝ ለማውረድ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል። በዚህም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አጠቃላይ አገራዊ የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አኃዝ ለማውረድ የተያዘውን ዕቅድ መሳካቱን አሳውቋል።

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተው አጠቃላይ አገራዊ የዋጋ ግሽበቱ ለ21 ተከታታይ ወራት በነጠላ አኃዝ ቀጥሏል። በተያዘው ዓመት የህዳር ወር የዋጋ ግሽበትም 5 ነጥብ 9 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ነው የተመለከተው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ምሁርም የዋጋ ግሽበቱ በነጠላ አኃዝ መቆየቱ አገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ጤናማነት የሚያረጋግጥ እንደሆነ በዓለም ባንክና በዓለም የገንዘብ ድርጅት የተገለጸውን አቋም ይጋራሉ።

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር ጣሰው ወልደሃና እንደገለጹት አሁን ያለውን ነጠላ አኃዝ ግሽበት ዘላቂ እንዲሆን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል።

የዋጋ ግሽበት ማለት በአንድ አገር ውስጥ ያሉት አጠቃላይ የሸቀጦች ዋጋ ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበራቸው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ያለው ጭማሪ እንደሆነም ምሁሩ አብራርተዋል።

“የዋጋ ግሽበት ቀነሰ ሲባል የኑሮ ርካሽነትን ሳይሆን የሸቀጦች ዋጋ የመጨመር ፍጥነት መቀነስ የሚያመለክት ነው” ሲሉም ዶክተር ጣሰው አስረድተዋል።

ወቅታዊ የዋጋ ግሽበቱ የምርት አቅርቦቱና የኅብረተሰቡ ፍላጎት እየተመጣጠነ መምጣቱን የሚያሳይ እንደሆነ ነው ምሁሩ የተናገሩት።

%d bloggers like this: