የራያ ዩኒቨርሲቲ መሠረት ድንጋይ በሕወሃት/ኢሕአዴግ ባለሥልጣኖች ተቀመጠ፤ ኢትዮጵያ የምትሰማውን ግን ማመን አዳጋች ነው

26 Feb

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በፍቃዱ ሞላ፤ አዲስ ዘመን

    የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፤ “ዩኒቨርሲቲው ከሦስት ዓመት በኋላ የሕብረ ብሔራዊነት ምልክት ይሆናል…በመላው አገሪቷ ለተስፋፋው ትምህርት የህወሓትና የትግራይ ህዝብ ትግል መሰረት ነው!” – አዲስ ዘመን

 

የራያ ዩኒቨርሲቲ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ  (ፎቶ አዲስ ዘመን)

የራያ ዩኒቨርሲቲ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ (ፎቶ አዲስ ዘመን)


የአዘጋጁ ጥያቄ:

    እነዚህ ትግራዊ ያልሆኑ ባለሥልጣኖች (በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የተቀመጠውን ግለስብ ጨምሮ) በየትም ሃገር ሕጋዊ መንግግሥት ውስጥ ዛሬ ያሉበትን የሥልጣን ደረጃ የማይመጥኑና ሳይሰሩ ያካበቱት ሃብት ያላለሙት ምቾት በመሆኑ፤ እንዲህ ለሃገሪቱ ሰማይ እንደተከፈተላት አድርገው እንዲያቅራሩ የሚያደርጋቸው ከሆነ ለምን በየቀኑ የሚረገጠውን፡ ለአፈናና እሥራት ክፉኛ የተጋለጠውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የእነርሱ ብስናት አሽታችና በእነርሱ ሣንባ የሚተነፍስ ያሰመስሉታል?


 
የራያ ዩኒቨርሲቲ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ «ዩኒቨርሲቲው የትጥቅ ትግል ትሩፋት ነው» – አቶ አባይ ወልዱ

በትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጮው ከተማ በ200 ሄክታር መሬት ላይ ለሚገነባው የራያ ዩኒቨርሲቲ ትናንት የመሰረት ድንጋይ በተቀመጠበት ወቅት አቶ ሽፈራው እንደገለፁት፤ የትግራይ ሕዝብ እና ህወሓት ከመላው ህዝብ ጋር ተባብረው ባካሄዱት ትግል በተገኘው ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የአገሪቷ የትምህርት ሽፋን ባለፉት 23 ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል።

ከደርግ ውድቀት በፊት አንድ ዩኒቨርሲቲ፣ አራት ሺ ትምህርት ቤቶች እና አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ተማሪዎች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ሽፈራው፤ ባለፉት «23 ዓመታት ይህን አሃዝ መከላከያና ፖሊስን ጨምሮ 35 ዩኒቨርሲቲ፣ 33ሺ ትምህርት ቤቶችና 24 ሚሊዮን ተማሪዎች ማድረስ ተችሏል» ብለዋል።

የራያ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከተያዙት አንዱ መሆኑን የገለፁት አቶ ሽፈራው፤ ከሦስት ዓመት በኋላ «ከመላው አገሪቷ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተውጣጡ ተማሪዎችን በማስተናገድ የሕብረ ብሔራዊነት ምልክት ይሆናል» ብለዋል።

የህወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የትጥቅ ትግል ትሩፋት ከመሆኑም በላይ በህወሓት 40ኛ ዓመት በዓል ላይ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ ልዩ ያደርገዋል።

«የትግራይ ሕዝብ ባካሄደው መራራ የትጥቅ ትግል መስዋዕትነት ከፍሏል፣ ድልም ተቀዳጅቷል» ያሉት አቶ አባይ፤ የደርግን ሥርአት በመደምሰስ የተገኘውን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማጨለም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን አስተሳሰብ በመመከት ረገድ ህዝቡ በንቃት እንዲሳተፍም አሳስበዋል።

የደቡብ ትግራይ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኃይለ ፍስሀ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው አገሪቷ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ዞን ለምታደርገው ሽግግር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው።

ዩኒቨርሲቲው ለዞኑ ታሪክ፣ ባህል፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች የምርምር ማዕከል እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው በከተማቸው መመስረቱ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር፣ ትምህርትን በቅርበት ለማግኘኘት ያስችላል።
 

%d bloggers like this: