የትግራይ ክልል በብዙ መልኩ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የተሻለ ተጠቃሚ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ! ለምን የሌሎች ክልሎች ለውጥ እንዲህ አይታይም?

10 Apr

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

ሰለትግራይ ብዙ መገንዘብ የሚቻለው፡ አሉ ከሚባሉት ተቃዋሚዎች ሳይሆን፡ በቀጥታ ከራሳቸው ሕወሃት ከሚያስተዳድራቸው መገናኛዎች (ኢብኮ፤ ኢዜአ፣ ዋልታ፣ ፋና፤ ኢቲቪ፤ ወዘተ) በማንበብና በማዳመጥ ነው። ተቃዋሚዎችማ፡ ሕወሃት እንደሚለው ሳይሆን፡ እኛም የትግራይም ነዋሪዎች ሁላችንም ድሆች ነን ሲሉ ነው ዘውትር የሚደመጡት።

እንደውም አንድ ጊዜ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ስለዚሁ ጉዳይ አንስተው የትግራይ ሕዝብ በወያኔ ምክንያት የከፋ ችግር ላይ ነው ሲሉ የጻፉት ትዝ ይለኛል። በአጭሩ ለመጥቀስም እንዲህ ነበር ያሉት፡-

  “በትግራይ ዙሪያ ያለው ምንድን ነው? የትግራይ ሕዝብ በየትኛው አቅጣጫ ነው አንደልቡ እየተዘዋወረ ለመሥራትና ለመኖር የሚችለው? ወያኔ የትግራይን ሕዝብ ከሰሜን ከወገኑ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ደም አቃብቶታል፤ በደቡብ-ምሥራቅ ከወሎ መሬት ቆርሶ የወሎን ሕዝብ ቂም አስቋጥሯል፤ በደቡብ-ምዕራብ ከጎንደር መሬት ቆርሶ የጎንደርን ሕዝብ ቂም አስቋጥሯል፤ የራስን ወገኖች አስቀይሞ ሱዳንን በመሬት ለመደለል የሚደረገው ጥረት ሁሉ ፋይዳ የለውም፤ ሱዳን ለራሱም ያልበጀ አገር መሆኑ እየታየ ነው፤ ወደፊት ደግሞ ይበልጥ ይታያል፤ በትግራይ ውስጥ ደግሞ ወያኔ የፈጠረው አፓርቴይድ የወያኔን የኑሮ ደረጃ ወደሰማይ ሲያስጠጋው፣ የቀረውን ወደአንጦርጦስ የደሀነት ገደል ውስጥ ከቶታል፤ በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ከነልጆቻቸው እየተዘዋወሩ የሚለምኑ ሞልተዋል፤ ይህ ልመናም ለወያኔ ለመገበር ነው፤ ብዙዎቹ እንደሚናገሩት የሚለምኑት የማዳበሪያ ዕዳቸውን ለወያኔ ለመክፈል ነው።”

በተለዋጭ ስናየው ደግሞ፡ ዛሬ ትግራይ ውስጥ የሚድረገው መረባረብ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ለምሳሌም ያህል፡ መጋቢት 26፡ 2007 ኢዜአ በትግራይ ክልል ከ90 ከመቶ በላይ ህዝብ የዘመናዊ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኗል በሚል ርዕስ መመልከቱ እጅግ ጠቃሚ ነው። መልካም የልማት ዜና ነው፤ ዜናውንም ሲተነትን፡ ኢዜአ እንዲህ ይላል፡-

  “በትግራይ ክልል ባለፉት አራት ተኩል ዓመታት በመንገድ ልማት ዘርፍ በተካሄደው ጥረት 90 ከመቶ የሚሆነውን የክልሉ ህዝብ የዘመናዊ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ኮንስትራክሽን መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

  በቢሮው የልማታዊ እቅድ ደጋፊ የስራ ሂደት አቶ ፀጋይ ብርሀነ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት በመንገድ ልማት ዘርፍ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በእቅዱ የትግበራ ዓመታት ከ1 ሺህ 430 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው መንገዶች ግንባታና ደረጃ የማሳደግ ስራ ተከናውኗል፡፡ የአዳዲስ መንገዶች መገንባትና ደረጃ ማሳደግ ስራ በመከናወኑ ከ534 በላይ የገጠር ቀበሌዎች አርስ በርስና ከዋና መንገድ ጋር እንዲገናኙ አስችሏል፡፡

  በመንገድ ዘርፍ የምእተ አመቱ የልማት ግቦች ለማሳካት በተካሄደው ሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድም ከ2 ሺህ 76 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ተሰርቶ ለአገልግሎት በቅቷል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በክልሉ የህዝብ ትራንስፖርት የሚመደብላቸው የመንገድ መስመሮች ከ60 አይበልጡም ነበር ያሉት አቶ ፀጋይ መንገዶቹ ተገንብተው ለአገልግሎት በመብቃታቸው የመንገድ መስመሮችን ወደ 181 ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

  በትግራይ በልማት መስክ፡ በዕቅዱ መሠረት ከ1 ሺህ 430 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው መንገዶች ግንባታና ደረጃ የማሳደግ ስራ ተከናውኗል ፍቶ ኢዜአ)

  በትግራይ በልማት መስክ፡ በዕቅዱ መሠረት ከ1 ሺህ 430 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው መንገዶች ግንባታና ደረጃ የማሳደግ ስራ ተከናውኗል (ፍቶ ኢዜአ)

  በመጠናቀቅ ላይ ባለው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የህዝብ መጓጓዣ ትራንስፖርት የስራ ስምሪት መከናወኑን ገልፀው በዓመት ከ11 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ከቦታ ወደ ቦታ መጓጓዙንም ተናግረዋል፡፡የመንገድ ተደራሽነት ከዓመት ዓመት እጨመረ በመሄዱ 90 ከመቶ የሚሆን የክልሉ ህዝብ የዘመናዊ ትራንስፖርት ተጠቃሚ እንዲሆን እንዳስቻለው ደጋፊ የስራ ሂደቱ አስረድትዋል፡፡ የመንገድ ተደራሽነት በመስፋቱ ወደ ከተማና ገጠር የሚጓጓዙ የምግብና የተለያዩ ሸቀጦች ቀልጣፋ ምልልስ እንዲኖራቸው አስችሏል ብለዋል፡፡

  ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከቢሮ አዲስ የሰሌዳ ቁጥር ተሰጥቶአቸው ወደ ስራ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከ15 ሺህ በላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

  በክልሉ ምእራባዊ ዞን የወልቃይት ወረዳ ነዋሪ የሆኑ አቶ ጥላሁን አሻግሬ እንደገለፁት ከአምስት ዓመታት በፊት ወደ ሽሬ እንዳስላሴ ለመጓዝ ከአራት ቀናት በላይ በእግር መጓዝ ይጠይቃቸው እንደበር ገልፀዋል፡፡

  በተለይም ወረዳቸው የሰሊጥ አብቃይ በመሆኑ ያመረቱት ምርት በመንገድ እጦት ምክንያት ለመሸጥ ይቸገሩ እንደነበር አስረድትዋል፡፡

  መንግስት ደረጃው የጠበቀ የአስፓልት መንገድ ወደ ሽሬ እንዳስላሴ፣ ዳንሻና ሁመራ የሚያገናኝ በመስራቱ አሁን ከአንድ ቀን በማይበልጥ ጊዜ ስራቸውን ጨርስው ለመመለስ የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡

  እንዲሁም ከወልቃይት ከተማ ወደ ምንምነና ቃቓ የሚባሉ የገጠር ቀበሌዎች የገጠር መንገድ በመዘርጋቱ ማህበራዊ ተቋማትን ለማስፋፋት እገዛ ከማድረጉ በተጨማሪ እናቶች በወሊድ ጊዜ የአንቡላንስ እርዳታ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል ብለዋል፡፡

  የራያ ዓዘቦ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ አቶ ለገሰ ሀጎስ በበኩላቸው ሁሉም ቀበሌ ገበሬ ማህበራት በመንገድ እንዲገናኙ በመደረጉ የአከባቢው ማህበረሰብ ባጃጅ በመግዛት አገልግሎት እንዲሰጡ እንዳስቻለ ገልፀዋል፡፡”

 

ከዚሁ ጋር በተያያዘ፡ ማክሰኞ መጋቢት 28፡ 2007 ኢዜአ እንደዘገበው: የትግራይ ክልል አዲረመጽ- ደጀና- ዳንሻ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ከ95 በመቶ በላይ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት ይህ ፕሮጀክት 98 ኪሎ ሜትር የሚሸፈን ሲሆን ከዚህ ውስጥም 60 ኪሎ ሜትሩ የጠጠር መንገድና ቀሪው ደግሞ ምንም አይነት የመንገድ መሰረተ ልማት ያልነበረበት ነው።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ በሶስተኛው የመንገድ ልማት ዘርፍ የሚጠቃለለው ከአዲረመጽ ዳሸና ድረስ ያለው መንገድ አብዛኛው ስራ ተጠናቋል።

ቀደም ብሎ የተጀመረው ከእንዳስለሴ ደደቢት የሚደርሰው 71 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን ከደደቢት አዲረመጽ ድረስ ያለው 82 ኪሎ ሜትር ደግሞ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል።

ሶስቱንም ምእራፎች ለመገንባት ከ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን አጠቃላይ ወጪው በኢትዮጵያ መንግስት እንደተሸፈነ ለማወቅ ተችሏል።

መንገዱ አካባቢው ያለውን የሰሊጥ፣ የዕጣንና የፍራፍሬ ምርት በቀላሉ ወደ መሃል አገር ለማጓጓዝ የሚያስችል ሲሆን በአካባቢው የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴም በማቃለል ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።

የእንዳስላሴ-ደደቢት-አዲረመጽ-ደጀና-ዳንሻ 254 ኪሎ ሜትር መንገድ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ከሽሬ ወደ ዳንሻ ለመጓዝ በጎንደር አልያም በሁመራ በመዞር ከ10 ሠዓት በላይ የሚፈጀውን ጉዞ ወደ 3 እና 4 ሰዓት መቀነስ ያስችላል።

የመንገዱ ግንባታ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰበት በመሆኑ በአካባቢው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና የመስተዳድር አካላት ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያደርጉለት ባለስልጣኑ ጥሪ አቅርቧል።

የመንገዱ ግንባታ ከዚህ ቀደም ወደ ጤና ተቋማት ወደ ተለያዩ ጉዳዮች ለመሄድ የሚፈጅባቸውን ረዘም ያለ ጊዜ እንዳሳጠረላቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና ሾፌሮች ገልፀዋል።
 

ድህነት ኢትዮጵያ ውስጥ በክፍለ ሃገሩ ሲመዘን

ድህነት በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የተንሰራፋ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም፡ ትምህርንትን፡ ጤነነትንና የኑሮ ሁኔታን መሠረት ያደረገው መለኪያ (Oxford Poverty and Human Development Initiative (OPHI) እንደሚያሳየው ከሆነ፡ እጅግ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኘው የትግራይ ሕዝብ ብዛት 66.2 በመቶ ሲሆን፡ በአማራና በኦሮሚያ 74.6 እና 74.9 ከመቶ መሆኑን የኦክስፎርድ ጥናት ከዚህ በታች በሠፈረው ሠንጠረዥ አማካይነት ያሳያል።

OPHI Ethiopia Index.png
 

በትግራይ ክልል የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በይፋ ተጀመረ

መቀሌ የካቲት 03/2007 (ኢዜአ) የህወሓትን 40ኛ አመት የምስረታ በዓል የምናከብረው ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በመጠበቅና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማጠናከር መሆን እንዳለበት የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ ።

በትግራይ ክልል የሚካሄደው አመታዊ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ትናንት በይፋ ተጀምራል።

የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራው በእንደርታ ወረዳ በጣቢያ ዓራቶ ትናንት ሲጀመር የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኪሮስ ቢተው እንደተናገሩት ከ20 ዓመታት በላይ በተካሄደው የተቀናጀ የአፈርና ውሀ ስራ በክልሉ ያለው የተፈጥሮ ሀብት አገግሞ የመስኖ ልማት እንዲስፋፋ የጎላ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

ህወሓት ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ትኩረት ካደረገባቸው ስራዎች መካከል የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ አንዱ መሆኑን ያወሱት አቶ ኪሮስ እስካሁን ከ77 በመቶ የሚበልጠውን የክልሉ መሬት ከአፈር መከላት ለመከላከል የተቀናጀ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ የተሰራለት መሆኑን ገልጠዋል።

የደቡባዊ ምስራቅ ዞን አስተዳዳሪ ወይዘሮ አረጋሽ በየነ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃን ማእከል ያደረገ ስራ በመከናወኑ የመስኖ ልማትን ጨምሮ የዞኑ ምርት እንዲያድግ ማስቻሉን አስታውቀዋል።

ከጣቢያው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አኸዛ ገብረስላሴ ” ውሀና መሬት ከእኛ ጋር እያለ ጠንካራ አመራር ባለመኖሩ ብቻ መሬታችን ለእንስሳት ማዋያ ብቻ በመዋሉ ተፈጥሮን ስናወድም ቆይቻለሁ” ካሉ በኋላ ” ካለፉት አስር አመታት ወዲህ ግን መስኖ በስፋት በማካሄድ ከመስኖ በማገኘው ገቢ ሁለት ክፍል ቆርቆሮ ቤት ሰርቻለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

“ሶስት ልጆቼ በማስተማር አሁን በባንክ 50 ሺህ ብር አለኝ ” ያሉት ወይዘሮ አኸዛ ገብረስላሴ “ምርቴን ለገበያ የማቀርበው በሞባይል ስልክ በመጠቀም በመሆኑ ይህ ሁሉ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ውጤት ነው ” ብለዋል።
ቄስ ኪሮስ ደስታ ” ቀደም ሲል በዓል በመቁጠር በአንድ ወቅት ያመረትነውን ለተስካርና ሰርግ ስናባክን የነበረው የስራ ባህል አሁን ተቀይሯል” በማለት ” የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ባለበት ውሀ አለ ውሀ ባለበት መስኖ በመኖሩ መስኖ የሚጠቀም ጎረቤቱን እያየ ቁጭ የሚል አርሶ አደር በአሁኑ ሰዓት የለም ” በማለት የአካባቢያቸውን መለወጥ ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ልማት ዘመቻው 40ኛውን ዓመት የህወሓት ምስረታ ለመዘክር በሁሉም የክልሉ ገጠር ቀበሌ ሲጀመር የክልሉና ደቡባዊ ምስራቅ ዞን ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ህዝቡ በሚያበረክተው ነፃ ጉልበት 100 ሺህ ሄክታር የሚሸፍን መሬት የሚሰራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በልማት ስራው አንድ ነጥብ አራት ሚልዮን ህዝብ ከ91 ሺህ በሚበለጥ የልማት ቡድን ተደራጅቶ በመሳተፍ ላይ ሲሆን ባለፈው ዓመት የተጀመረው የጠረጴዛ እርከን ስራ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ባለፉት ዓመታት ህዝቡ ባካሄዳቸው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች ከሶስት በመቶ በታች የነበረው የክልሉ የደን ሽፋን አሁን ወደ 19 በመቶ ሲያድግ ከ15 ሜትር በታች ከጉድጓድ ይገኝ የነበረው ውሀ በአሁኑ ወቅት በአማካይ እስከ ሰባት ሜትር ጥልቀት ሲገኝ ምንጮችም እየጎለበቱ መሆናቸውን በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ዋና የስራ ሂደት ባለቤት ገልጸዋል።

በ1995 በክልሉ አምስት ሺህ የማይሞላ መሬት በመስኖ ይለማ እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ግን ከ241 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ በማልማት የክልሉን አመታዊ ምርት በማሳደግ ልማቱን ህዝቡ በየዓመቱ እንደ ባህል አድርጎ እየወሰደው መሆኑን አስታውቀዋል።
 

%d bloggers like this: