ትግራይ – “ውሃ መያዝ ብቻ ሳይሆን ውሃ መፍጠር የቻለ ህዝብ” – በተካ ጉግሣ/ኢዜአ፥ መቀሌ/

12 Apr

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (አዜአ)

  “የትግራይ ህዝብ ከ40 ዓመታት በፊት ይደርስበት የነበረውን ጭቆና ለማስወገድ ባደረገው መራር ትግል የተገኘው ድል በመላ ኢትዮጰያ የጎላ ስፍራ አለው።የትግራይ ህዝብ ከመሪ ድርጅቱ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ/ህወሓት/ ጎን በመሰለፍ አምባገነኑን የደርግ ስርአት ለመደምሰስ በፅናት ታግሏል፣ልጆቹን ወደ ጦር ሜዳ መርቆ ሸኝቷል፣ በአሸናፊነት ሲመለሱም እልል ብሎ የጀግና አቀባበል አድርጎላቸዋል።

  “የትግሉ መነሻ ህዝቡ ቋንቋውን፣ማንነቱና ባህሉን ለማስከበርና ለዘመናት ከነበረው አድሏዊ ስርዓት ለመላቀቅ በመሆኑ የደርግ ስርዓትን ማስወገድ አማራጭ ያልነበረው ትግል ማካሄድ እንደነበር ቀደምት የድርጅቱ ታጋዮች ተናግረዋል።

  ከ60 ሺህ የሚበልጡ የትግራይ ልጆች በአላማ ፀንተው በየተራራውና ሸለቆው ታግለው አሁን ያለውን ስርዓት ሲያስረክቡ የአሁኑ ትውልድም አደራቸውን ጠበቆ በልማት ጎዳና ቀና ደፋ በማለት የአገሪቱ እድገት ቀጣይነት ባለው ሁኔታ እንዲረጋገጥ በማድረግ ላይ ይገኛል።

  ከ24 ዓመት በፊት አገሪቷን ተረክቦ ማስተዳደር የጀመረው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር አገሪቱን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ የልማት ስትራቴጂና ፖሊሲ በመቅረፅ ለተግባራዊነቱ ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ በፈጣን የእድገት ጎዳና በመራመድ ላይ ካሉት የአለም አገራት ተርታ ለማሰለፍ እየተጋ ነው።

  ከተቀየሱት የልማት ስትራቴጂዎች አንዱ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሲሆን ለዚህ መነሻም በትጥቅ ትግሉ ወቅት ህወሓት/ኢህአዴግ የነበረውን ተሞክሮና ለትግራይ ህዝብ ያስገኘው ውጤት ምን እንደሚመስል ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል።

  ዘንድሮ የሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በእንደርታ ወረዳ በጣቢያ ዓራቶ ጥር አንድ ቀን 2007 ሲጀመር የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኪሮስ ቢተው እንደተናገሩት ከ20 ዓመታት በፊት የተካሄደው የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ስራ በክልሉ ያለው የተፈጥሮ ሃብት እንዲያገግምና የመስኖ ልማት እንዲስፋፋ የጎላ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

(ፎቶ አዜአ)

(ፎቶ አዜአ)

  ህወሓት ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ትኩረት ካደረገባቸው ስራዎች መካከል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ አንዱ እንደነበር ያወሱት ሃላፊው እስካሁን ከ77 በመቶ የሚበልጠው የክልሉ መሬት የአፈር መከላት እንዳያጋጥመው የሚያስችል የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተከናወነለት መሆኑን ገልጸዋል።

  አቶ ሙሉጌታ ገብረስላሴ ይባላሉ በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ዋና የስራ ሂደት ባለቤት ናቸው። ስለአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው አጀማመር ሲያስረዱ ” ህወሓት በህዝቡ ላይ ይደርስ የነበረውን ችግር በማየት ከሚያካሂደው ጦርነት በተጓዳኝ ለተፈጥሮ ሃብት ክብካቤ ልዩ ትኩረት በመስጠት 054 የሚል ክፍል አቋቁሞ የአፈርና ውሃ ጥበቃና የመስኖ ስራ እንዲካሄድ ያደርግ ነበር ” ብለዋል።

  “የቃሌማ፣የሽዋጣና የተከዜ ወንዞችን በመጥለፍ የመስኖ ስራ ተጀምራል ” ያሉት አቶ ሙሉጌታ ከ1978 ዓም ጀምሮ እስካሁን ከሀያ እስከ አርባ ቀን በነፃ ጉልበት ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በየዓመቱ ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን የሚበልጡ ነዋሪዎች ስራው ላይ እንደሚሰማሩ ይናገራሉ።

  ባለፉት ዓመታት ህዝቡ ባካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከሶስት በመቶ በታች የነበረው የክልሉ የደን ሽፋን አሁን 19 በመቶ ላይ እንዲደርስ አስችሏል፣ከ15 ሜትር በታች ይገኝ የነበረው የውሀ ጉድጓድ በአሁኑ ወቅት በአማካይ እስከ ሰባት ሜትር ጥልቀት እንዲገኝ አስችሏል ብለዋል።

  የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተካሄደባቸው አካባቢ የከርሰ ምድር ውሃ እየጎለበተ በመምጣቱ ምንጮች በብዛት ሲፈልቁ የመስኖ ልማት እየተስፋፋ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ አስታውቀዋል። በመሆኑም ህዝቡ ውሃ መያዝ ብቻ ሳይሆን እስከ መፍጠር ደርሷል ሊባል ይችላል ብለዋል።

  በ1995 አምስት ሺህ ሔክታር የማይሞላ መሬት በመስኖ ይለማ የነበረው በአሁኑ ወቅት ከ241 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በመስኖ እየለማ ነው ብለዋል።ከአስራ አምስት አመት በፊትአመታዊ የክልሉ ምርት ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ብቻ የነበረው ባለፈው ዓመት ከ35 ሚሊዮን በላይ ኩንታል የደረሰው የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ በመካሄዱና በግብአት አጠቃቀም የህብረተሰቡ ግንዛቤ በማደጉ ጭምር ነው።

  በአንድ ወቅት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እንደተናገሩት በትግራይ የተፈጥሮ ሃብትን ማእከል በማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ከቀጠሉ በ1980ዎቹ መጀመሪያ በአገሪቱ የነበረው ዓመታዊ የግብርና ምርት በትግራይ ብቻ ከመስኖ ሊለማ ይችላል።

  በወቅቱ የነበረው አገራዊ ምርት ከ30 ሚሊዮን ኩንታል የማይበልጥ የነበረ ሲሆን ባለፈው ዓመት በትግራይ ከመስኖ ልማት ብቻ 27 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱ የእኚህ ባለራእይ መሪ ምኞትና ህልም ምንያህል እየተሳካ መሆኑን ለመረዳት ይቻላል።

  በአሁኑ ወቅት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በክልሉ እያደገ በመሄዱ ህዝቡ በየዓመቱ እንደ ባህል አድርጎ እየወሰደው መሆኑን ከአቶ ሙሉጌታ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል።

  ዘንድሮ የሚከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ 100 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን ህብረተሰቡ ከ91 ሺህ በሚበልጥ የልማት ቡድን ተደራጅቶ ስራውን በመስራት ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

  በዋነኛነት ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው የጠረጴዛ እርከን በየትኛው አካባቢ መሰራት እንዳለበት ተለይቶ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ ሆኗል ውሃ ባለባቸው አካባቢ የተደራጁ ወጣቶች ላይ እንዲያተኩር መደረጉንም አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል።

  ለዚሁ ስራ 106 ተፋሰሶች ተለይተው በየዓመቱ የተገኙ ልምዶችን በመቀመር ጥራቱን በጠበቀ ሁኔታ ስራው እንዲመራ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

  ከጣቢያው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አኸዛ ገብረስላሴ “ውሃውም መሬቱም ከእኛ ጋር እያለ ጠንካራ አመራር ባለመኖሩ ለከብቶች ማዋያ ብቻ የነበረውን የተፈጥሮ ሀብት ስናወድም ቆይተናል ” ብለዋል።

  ” ካለፉት አስር አመታት ወዲህ ግን መስኖ በስፋት ማካሄድ በመጀመሬ ከመስኖ በማገኘው ገንዘብ ሁለት ክፍል ያለው ቆርቆሮ ቤት ሰርቻለሁ፣ ሶስት ልጆቼን እያስተማርኩ በባንክ 50 ሺህ አለኝ፣ ምርት ለገበያ የማቀርበው በሞባይል ስልክ በመጠቀም ነው ይህ ሁሉ አፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ውጤት ነው” በማለት ተናግረዋል።

  ቄስ ኪሮስ ደስታም ” ቀደም ሲል በዓል በመቁጠር በአንድ ወቅት ያመረትነውን ለተስካርና ሰርግ ስናባክን የነበረው ሁኔታና የስራ ባህላችንም አሁን ሁሉም ተቀይሯል ” ብለዋል። ምክንያቱ ደግሞ ይላሉ ቄስ ኪሮስ “የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባለበት ውሃ አለ ውሃ ባለበት መስኖ አለ ስለዚህ በመስኖ የሚጠቀመውን ጎረቤቱ እያየ ቁጭ የሚል አርሶ አደር አሁን የለም ” በማለት አካባቢያቸው ምን ያህል እየተለወጠ መምጣቱን ተናግረዋል።

  በክልሉ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተገኘው ውጤት ይበልጥ እንዲጠናከር የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል መልእክታችን ነው።”

 

ተዛማጅ ጽሁፎች፡

  የትግራይ ክልል በብዙ መልኩ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የተሻለ ተጠቃሚ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ! ለምን የሌሎች ክልሎች ለውጥ እንዲህ አይታይም?

  ዘረኝነቱ በስፖርት መስክም? ትግራይ የራሷ የሆነ አትሌቲክስ ቡድን በማቋቋም ላይ ትመስላለች! ለምን አስፈለገ ይሆን በብሔራዊ ደረጃ ከሁሉም የተውጣጣ ፉክክርና ምርጫ ደህና እየተካሄደ ሳለ?

  TPLF’s hunger for cash crops & forex has been forcing more land grab and the consequent evictions & dehumanization of Ethiopians

  TPLF’s Abay Tsehaye’s ‘ልክ እናስገባችዋለን’

  አባይ ፀሐዬ – ‘ልክ እናስገባችዋለን’ የተባለች ቃል ከየት እንደተወሰደች አላቃትም’ (ጽሑፍና ቪዲዮ) እርሳቸው ሳያስቡት፡ ምንም ሳይታወቃቸው እነዚህ ተቃዋሚዎች – ትሕዴን: ግንቦት 7፡ ሰማያዊ ፓርቲ፡ ኢሣት፡ ኦነግ፡ ኦብነግ፡ አንድነት: ኤርትራ ወዘተ – እነዚህን ቃላት አፋቸው ውስጥ ከተውባቸው ይሆን?

 

%d bloggers like this: