የእያንዳንዱ ዜጋችን ሥቃይና ግድያ – በየትኛውም ሥፍራና ሥርዓት – የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሥቃይና ሞት ነው!

26 Apr

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

ከዚህ በታች የሠፈረውን ግጥም ያቀረቡት፡ ዶ/ር ስብስቤ ለሜታ* አርብ ሚያዝያ 16 ቀኑን ሥራ ውለው በሊቢያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው ሥቃይና አደጋ ዕንቅልፍ ሲነሳቸው፤ ከአልጋቸው ወርደው በዚያንው ሌሊት ደርስው ያደሩት ነው። ሚያዝያ 17 2007፡ የኢትዮጵያ ማኅበር በፊንላንድ እነዚያን በሊቢያ የወደቁትን ወገኖቻችንን፡ በሕይወትም ሆነው እዚያ የሚሠቃይትን ዜጎች፡ እንዲሁም በየአካባቢው በችግር ላይ ያሉትን ወገኖቻችንን ለማሰብና በሃሳብ ከእነርሱ ጋር ለመሆን ባዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ይህንኑ ግጥም የስሜታቸው መገለጫ አድርገው አቅርበውታል።

በምሽቱ ግጥሙ ከእራት በኋላ አንዴ ከተነበበ በኋላ፡ የዕለቱ ታዳሚዎች በድጋሚ እንዲነበብ በጠየቁት መሠረት፡ ዶ/ር ስብስቤ በድጋሚ በንባብ አሰምተውታል!ታዳሚዎቹ ሞቅ ባለስሜትና ጭብጨባ ተቀብለውታል!

ግጥሙን TEO በእትመት ለአንባብያን ለማስነበብ ላቀረበላችው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ በመስጠታቸው፡ በዚህ ገጽ ላይ እንደሚከተለው ለማቅረብ በመቻላችን ዶ/ር ስብስቤን ከልብ እናመስግናለን።

Dr Sebsibe Lemeta & young Natan

የወጣትነት ጉልበቱ ዕድሜው በከንቱ ሲያልፍ ሲያየው
መማር ጥረት ማድረግ ከንቱ ሆኖ ሲያገኘው
ተስፋ ሲያጣ ማለም ሲሳነው
ግራ ሆነ ቀኙ ጨለማ ሆኖ ታየው።

ያሳደገች እናቱ ጉልበቷ ሲያይ አቅም ተስኗት
እኔ ደርሼ እናቴን ረድቼ የሚለው የልጅነት ሕልሙ ውል ብሎት፤
የዛሬው እሱነቱ ግን ከንቱ እንደሆነ ሲያውቀው
በሃገሩ ሠርቶ ለራሱ መሆን ሲሳነው
በውጭ ሃገር ሆነ የተስፋ ብርሃን የሚታየው።
ስደት ግዴታ ሆኖ ታየው።

ሌለት ጎህ ሳይቀድ ተንስቶ
ባርኪኝ መርቂኝ አላት እናቱን ጉልበቷ ሥር ተደፍቶ
ልታቆመው፡ ልትመልሰው እንደማትችል በልቧ አውቃ
ኃዘን፡ ሥጋቷን በውስጧ አምቃ
እንባዋን ዋጥ አድርጋ፣ ከጉልበቷ ሥር አነሳችው ሆዷን እስር አድርጋ።

እምዬ!

ለጋው ልጇን፡ ሙሽራ ልጇን ዐይን ዐይኑን እያየችው
ይቅናህ ታቦቱ አድባሩ ይክተሉህ አለችው!

ዘመድ ሳይሰማ ጎረቤት ሳይሽኘው
ጸጥ ብሎ አንገቱን ደፍቶ ወጣ ሃገሩን ለቆ
ምኞት ተስፋውን በልቡ ሠንቆ።
ብዙም አልቆየ መንገድም አልቀናው
ያ ክፉ ዕድሉ አረመኔ እጅ ጣለው።

አሁንም አንገቱን ደፍቶ በራሱ በሃገሩ አፍሮ
አለፈ በሰው ሃገር ሕልሙን ምኞቱን ተሸከሞ።

የግዜ ነገር ሆኖ አንጂ
ስላም፣ ፍቅር ስምምነት አጥተን እንጂ
እንደ ድሮ ቢሆን እንደ ጥዋቱ
የዚህ የታረደው ልጅ እናቱ
መጠለያ ሰጥታ ነበር ለፕሮፌቱ
የሩቁ ታሪክ እንኳ ቢረሳ በቅርብ ጊዜ ታሪኳ
መደበቂያ ነበረች ሃገሩ
ለተቸገረ መረድሻ ላጣ አረብ ሁሉ።
ባካባቢው ካሉት ሁሉ ስሟ የገነነ
የተስፋ ቅርጫት የተለባሰ።

ይህንን ዝና የስሙ ይመጡ ነበር ከቀርብ ከሩቁ
በእኔ ዕድሜ እንኳን አውቃለሁ፣
የአረብ ቤት ሲባል አስታውሳለሁ፣
የአርመኖች ሠፈር ሲባል ሰምቻለሁ።

ዛሬ እናታችን ስሟ ጠፍቶ የተስፋ ቅርጫት መሆኗ ቀርቶ
ችግር፡ መከራ ሆኖአል ኑሮዋ ረሃብ ሆኖአል ምልክቷ።

ፕሮፌት መሃመድ ያስታውሳሉ የደጎች ሃገር ይሏታል።
ማንዴላ ያስታውሷታል የሰብዕናቸው መኩሪያ ይሏታል።

ይህ ትውልድ ግን ከዳተኛ አረመኔ ነው!
ያጎረሰውን እጅ ነካሽ ነው!

ሃገሬ አልቅሽ፤ ዛሬ ጥቁር ልበሺ፤
ጅግናዬ ብለሽ የጠራሽው
ባለሽ አቅም ተንከባክበሽ ያሳደግሽው
በበረሃ ተሰይፏል፥ ወገን፣ ሃይማኖት የሌለው ይመስል!
ያለፀሎት፡ ያለግንዛት ስም የለሽ መቃብር ውስጥ ተወርውሯል።

እነዚያ ሰዎች ሲዘግቡ ኢትዮጵያውያንን ገደልን አሉ!
ትግሬ፡ አማራ፡ ኦሮሞ ብለው ዝርዝር ውስጥ ሳይገቡ፤
እኛ ግን ከንቱዎቹ በክልል፡ በዘር እንባላለን
ከአንድነት ይልቅ ልዩነታችንን እናወድሳለን።

ያልገባን ነገር በቅጥ ያልተረዳነው
በሞት፡ በፍርዳችን ቀን ስማችን ኢትዮጵያዊ ነው!
 

* ዶ/ር ስብስቤ ልመታ የቤተስብ ሃላፊና የሁለት ልጆች አባት የሆኑ በፊንላንድ ኢትዮጵያዊ-ፊንላንዳዊ ሐኪም፡ ናቸው። በተጨማሪም 2009 ዓ.ም. በካንሠር ጥናት PhD አግኝተዋል።
 

One Response to “የእያንዳንዱ ዜጋችን ሥቃይና ግድያ – በየትኛውም ሥፍራና ሥርዓት – የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሥቃይና ሞት ነው!”

  1. Elias k/mariam April 30, 2015 at 16:10 #

    ወንድሜ ዶ/ር ሰብስቤ ልመታ ፡፡ባለህበት ሰላምታዩን አቀርባለሁ ፡፡ የወገኖችህ ስቃይ አስጨንቆህ እስቲ ልተንፈስ ብለህ ግሩም የሆነ መልዕክት በግጥም መልክ አቀርበሀል ፡፡ የተወለድንበትና ያደግንበት ሰፈር ሰሞኑን የስቃይ ዋይታ እየተሰማበት ነው፡፡ አንተም እንዳልከው በአንድ ወቅት ሀገራችን ከየመንና ከአርሜኒያ የመጡ ህዝቦችን አሰተናግዳለች በአሁን ግዜም ቢሆን ከደቡብ ሱዳን ከሶማሊያ ከኤርትራ የመጡ ስደተኞችን እያሰተናገደች ነው ፡፡
    ሀገራችን ለ አፍሪካ ህዝቦች ነፃነት የሰጠቸው ድጋፍ መልሱ ይህ መሆን አልነበረበትም፡፡

    Like

Comments are closed.

%d bloggers like this: