የሽፍታ/ወንበዴ መንግሥት በኢትዮጵያ

6 May

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

በሃገራችን ታሪክ አንድ ግለሰብ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ላይ ወይንም በትውልድ አካባቢው ንጉሣዊ አስተዳደር ላይ አምጾ መነሳትና በረሃ መግባት አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ ፊታውራሪ እገሌ፡ ወይንም ደጃዝማች እገሌ ወይንም ማዕረገ አልባው አቶ እገሌ ሸፈተ ሲባል መስማት ወይንም ማንበብ ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እስከ 1960ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ይሰማ ነበር – ዕድሜ ለቢቢሲና ሌሎችም አውሮፓ ውስጥ የሚታተሙ ሣምንታዊ መጽሔቶች፥ ጎጃም፣ ባሌ፣ ሸዋ፥ ትግራይ፣ ኤርትራ፥ ወዘተ እንዲህ ሆነ የሚለውን ዜና ላስታወስ!

ዛሬም፡ መንግሥት በደል ፈጸመብኝ፤ ዳኛው አለአግባብ ፈረደብኝ፤ የአካባቢው ሚሊሽያ ወይንም ፌዴራሎች ጥቃት አደረሱብኝ በማለት በዛሬው ወንበዴው መንግሥት ላይም የሚሽፍቱ ስዎች አማራ አካባቢ በተለይም ሸዋና ጎንደር መኖራችው ወይንም መያዛቸውን ወይንም መገደላቸውንና ሕዝቡም “አይፈረድበትም፤ እንዲህና እንዲያ አስተዳደሩ/ፌዴራሎች በደል ፈጽመውበት ነው” ተብሎ አልፎ አልፎ በኢሳት ዜና ላይ ሲነገር እንሰማለን – መቼም የሕወሃት ዜና አውታሮች “ፋና ኮርፖሬት”ን ጨምሮ ይህንን ዐይነት ዜና አይነግሩንምና!

ኅብረተስቡ ውስጥም፡ የእነዚህ ግለሰቦች ዓላማና ስለእነርሱ ማንነትና ምንነት በማን እንደሚነገርላቸው ይወስናል!
ሽፍትነት እንደሥልጣን መሣሪያ

ለነገሩ እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ሸፍቶ የተሳካለትና ተሳክቶለት መንግሥት ገልብጦ ሥልጣን የያዘ ቡድን አልነበረም። ምናልባት ስለዚህ ስንነጋገር፣ አንዳንድ ሰዎች በ1966 ዓ.ም. ኮለኔል መንግሥቱ ኅይለማርያም የመሩትን ደርግን እንዴት ዘንግቶ ነው እንዲህ የሚለው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡

እዚህ ላይ ልዩነቱ በመዋቅርና በሠፊው ሕዝብ ተደግፎ ማመጽንና አንድ ወይንም ጥቂት ግለሰቦች ቡድን መሥርተው (ለምሳሌም ያህል፡ የኤርትራ ተገንጣዮች፣ በባሌ በኩል ኦሮሞች ላይ የተፈጸሙ በደሎችን ለመቋቋም ብቅ ብለው የነበሩት የተለያዩ ድርጅቶች፡ ወዘተ) ግላዊ ቂም በቀሎቻቸውንና ወገናዊ ጥያቄዎቻቸውን ለማንሳት/ለመፍታት፣ ጥቃቶቻቸውን ለማስቆም፣ ወይንም ያለውን የአካባቢውን ሥልጣን የያዘ ቡድን ለመለወጥ በሚያደርጉት መካከል ትልቅ ልዩነት ያለው፡፡

የሚገርመው ግን፥ ያን ጊዜም ሆነ ዛሬ፡ ከኤርትራዎቹ ቡድኖችም ይበልጥ በወንበዴነት ዐይን ይታይ የነበረው ሕዝባዊ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት) ነበር። ደርግም ሕወሃትን ሃገር ሻጭ የወንበዴ ቅጥረኛ አድርጎ በመመልከቱ፡ በተለያዩ መንግሥታት (በተለይም ጣልያን፡ አሜሪካ፡ ኖርዲክ ሃገሮች ወዘተ ሕውሃትና የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም እንዲደራደሩ ቢጠየቅም፡ ከኤርትራ ቡድን እንጂ፣ ከተራ ሽፍቶች ጋር እንደማይደራደር በተደጋጋሚ ማሳወቁ ይታወሳል።

አንዳንድ ሰዎች ይህ የደርግ ፕሮፓጋንዳ መሳካቱን ነው የሚያሳየው ሲሉ፤ በአንጻሩ ይኸ የሆነው የሕወሃት ሰዎች ከንጋቱ ጀምሮ በሥልጣን ላይ የፈጸሟቸው ብልግናና ድርጊቶች (የገለሰቦቹ ባህሪዎችና የድርጅቱ አመለካከት) በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ሕጋዊነትንና ተቀባይነት ስላሳጣው ነው የሚሉ በዛ ያሉ ምሁራን፥ በግብርና የሚኖሩ፡ በጉልበታቸውና በዕውቀታቸው ጥረው ግረው የሚተዳደሩ ዜጎች አሉ።

ወደ ታሪካችንም ዞር ስንል፣ በትንሹም ቢሆን፡ ከሽፍትነት ወደ መንግሥትነት ተሸጋገረ ለማለት ቀረብ የሚለው፡ የአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ነበር። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ንጉሡን ለማንገሥ ስታመነታ፡ የንጉሡ ሕጋዊነት ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። ለዚህ ቀራቢው፤ ሃገራችን ቀደም ሲል ዘመነ መሣፍንት (Era of Princes) በመባል በሚታወቀው ዘመን የተነሱትና የመጨረሻውም የዘመነ መሣፍንት ንጉሥ የነበሩት፤ የጎንደሩ ካሣ ኃይሉ (የአጼ ቴዎድሮስ) ሽፍታነት ነበር። ለዚህም ሁለት ምክንያቶች አሉ፡፡

አንደኛ፡ አጼ ቴዎድሮስ በፖለቲካ ፍልስፍና ያልዳበረ አመለካካት ቢኖራቸውም፣ በተለይም ልባችውና ስሜታቸው ከጥንቱ በድሃ ወገንተኝነት ጋር ያበረ በመሆኑ፡ እውሮፓ ውስጥ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በመስፋፋት ላይ ከነበረው የሕዝብ ወገናዊነት (Populism) ከሚለው ጋር የሚቀራረብ ነበር፡፡

ሁለተኛ፡ አጼ ቴዎድሮስ ከመጀመሪያው ዓላማቸው በሥልጣን ላይ ያሉትን ገፍትረው ሥልጣን መያዝ ብቻ ሣይሆን፣ ሃገሪቱን በየመንደሩ ዘውድ ከደፉ ሽፍቶች (ዘራፊዎች) አጽድተው አንድ ኢትዮጵያን ለመመሥረት ነበር፡፡ የቋራው ገዥ የደጃዝማች ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ ልጅ እንደመሆናቸው፡ አጼ ቴዎድሮስ ሥልጣን ምን እንደሆነና በሥልጣን ምን ሊደረግ እንደሚቻል ያውቁ ነበር። ስለሆነም፣ ልባችውና ስሜታቸው ግን ከጥንቱ የሮቢን ሁድ ድሃ ወገንተኝነት የሚቀራረብ ነበር፡፡

የአጼ ቴዎድሮስ የትምህርት ደረጃ ከቄስ ትምህርት ቤት ያላለፈ ሲሆን፡ ዋናው ችሎታቸው ወታደራዊ ሙያ ነበር። መጀመሪያ የአጎታቸውንና በኋላም ለጥቂት ጊዜ የጎጃሙ ጦር መሪ የጎሹ ዘውዴ ጦር ውስጥ ባገኙት የውትድርና ዘመናቸው ከፍተኛ ችሎታን በማስመዝገብ ስማቸው ገኖ በ1839 ዓ.ም. በደጃዝማችነት ማዕረግ የቋራ አስተዳዳሪ ሆነው መሾማቸው በታሪክ ተመዝግቧል። ቀጥለውም፡ በ1847 ራሳቸውን ንጉሥ ካሣ ብለው በመሰየምና፡ በሰሜናዊ ባላባቶች ላይ በተከታታይ በመዝመትና በማንበርከክ፡ ከ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲወራረድ የነበረውን የንጉሥ ሰሎሞንን መሥመር ሥርወ መንግሥት ፍጻሜ አረጋገጡ።

በትውልዳቸው ከገዥው መደብ ቢሆኑም – በእርሳቸው አመለካከት – ሃገር አጥፊ አድርገው የተመለከቱት መሣፍንቱንና ቀሳውስቱን የወከለችውን ቤተክርስቲያንን ጭምር ነበር (የመጤው ሃይማኖት አፍቃሪዎችን ጭምር)። በአውሮፓውያን ታሪክ ተንታኞች ዘንድ በንግሥት ቪክቶሪያና በአጼ ቴዎድሮስ መካክል ያለው ተመሣሣይነት፡ ሁለቱም እስላምን ለማሸነፍ ተባብረው መሥራታቸው ነበር ይላሉ ሃሮልድ ማርከስ። በ1848 ግብጽ ደባርቅ ድረስ የመያዝ ፍላጎቷን ግልጽ በማድረጓ፣ የአጼ ቴዎድሮስ የውጭ ችግር ምንጭ ነበረች።

ለማንኛውም የአጼ ቴዎድሮስ ዓላማ ከጊዜያቸው የቀደመ ቢሆንም፡ ለኢትዮጵያ ሰላምና ታላቅነት ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ታወቆ፣ እርሳችውም – ልክ ዛሬ ሕወሃት እንደሚያደርገው ሁሉ – ሕዝብን ወደ ዓላማቸውና ፖሊሲያቸው ከማምጣት ይልቅ፣ በመግደልና በመግረፍ በማተኮራቸው – ዓላማቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ካለመቻላቸውም በላይ፡ ለጠላቶቻቸው ምቹ በመሆን የአጼ ቴዎድሮስ የትግልና የሥልጣን ዘመን ሁለት አስርት እንኳ ሊደፍን አልቻለም!

ሕወሃትም ዛሬ ያለበት ውጥረትና ሥጋት እጅግ ከፍተኛ ነው። ምናልባትም ብዙ ሳንርቅ፣ ትልቁ የሕዝብ ዕልቂት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነሳው አመጽና እየጎላ የመጣው ጥላቻ፤ እነ ፀጋይ በርሄ ኢትዮጵያውያን ሊቢያ ውስጥ ከታረዱ በኋላ፡ እንዲሁም በየመንና በደቡብ አፍሪካ በዚጎቻች ላይ ለተፈጸመው ወንጀል ኢትዮጵያውያን ሥልጣን ላይ ያለውን የወንበዴ መንግሥት ዐይንህ ላፈር በማለታቸው ፤ በመደናገጥ ሃገሩቱ ውስጥ ያሉትን ትግሬዎች ካአሁኑ በይበልጥ አስታጥቀው ሊፈጽሙ የሚያሰሉት ደባ ሃገሪቱን የመተላለቅ ማዕከል እንዳያደርጋት ሃገር ውስጥም ውጭም ከፍተኛ ሥጋት አለ።

ለማንኛውም ፀጋዬ በርሄ ይህንን በይፋ ማናፈሱ፡ ትግሬዎች ጭምር የወንበዴውን ቡድን በሥጋት እንዲያዩት ማድረጉ ይሰማል። ከሁሉም ጠቃሚው ግን ከሃገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር ሕወሃት የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፈጸም መዘጋጀቱን በጠቅላይ ሚኒስትር ተብዬው አማካሪ በመገለጹ፡ በእርጋታና በጥንቃቄ፡ ለዓለም ሕዝቦችና መንግሥታት፡ ለአናሊስቶችና የሚዲያ ፐርሶናሊቲስ ይህንን ማሳወቁ ጠቃሚ ነው፡፡

የዚህን ወሮበላ ቡድን ማንነት በጊዜ ማጋለጥ ቸል የሚባል ጉዳይ አይደለም!
ወንበዴዎች ሥልጣን ይዘው ሩብ ምዕተ ዓመት አስቆጠሩ

ከአጼ ቴዎድሮስ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ተሳክቶልት ከሽፍታነት ወደ መንግሥት ሥልጣን የተሸጋገረው የወንበዴ ቡድን ሕዝባዊ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት) ነው። የሃገራችን ጽዋ ፈንታ ሆኖ ደርግን የጣለው ሕወሃት ሥልጣን ላይ ከወጣ 24/5 ዓመታት ቢያስቆጥርም – ያውም ለመማር፣ ለመሻሻል፣ አማካሪዎች ለማሰባስብ በሚቻልበት ዓለም ውስጥ እየኖረ – መንግሥት ሳይሆን የሽፍታ መንግሥት መሥርቶ ሽፍታ ሆኖ የቀጠልው ሕወሃት ብቻ ነው!

ከወታደራዊ ብቃቱ ይልቅ ደርግን የጣለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምሬት መሆኑን ወደ ጎን በመተው፣ እስከዛሬ ያንን ወታደራዊ ድል ብቻ በማስመሰል፡ ለአፍታም ወደተዋጣለት መልካም አስተዳደር (Good Governance) ያልለወጠው ሕወሃት፥ እንደ ደርግ ሁሉ የሕዝብ ምሬትና ጥላቻ እየተባባሰ፡ ከሥልጣን እየገፋውና እንዲወድቅ፡ ያመጣው ሃሣብ ሁሉ እንዲመክን የሚሠሩ ወገኖች ቁጥራቸው እንዲበራከት አድርጓል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከንጋቱ ጀምሮ የምናውቀው ትግራይ ለንጉሥ ነገሥቱ ተገዥ ነን እንገብራለን ቢሉም፡ ዘወትር በመንግሥቱ ላይ ሲያሴሩ እንደኖሩ በታሪክ ብዙ ማስረጃዎች አሉ፡፡ በዘመነ ቴዎድሮስ፡ ትግራይ ከንጉሡ ጋር ከመጣላት ይልቅ፡ ሥጦታ አበርክታ፡ አጼ ቴዎድሮስ እንደፈለጉት ቅባት የሚያዳርጉት አቡነ ሰላማ ከትግራይ እንዲመለሱ፣ እርሳቸውም ለንጉሡ ዘውዱን ባርከው መተባበራቸው ይታወሳል። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ፡ በትግራይ መሣፍንት በኩል በተለይም እነ ዋግሹም ገብረመድኅን ከነንጉሤ ወልደሚካኤል ጋር በማበር፡ ቴዎድሮስን ለመጣል ማሴራቸውና በሚሥጢር ከፈረንሣይ ጋር መደራደራቸው የሚዘነጋ አይደለም። መጨረሻ ላይ ሰለተደረሰባቸው በጦር ተማርከው ተገድለዋል።

የዚህ ዐይነት ክህደት በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ሌሎች ክፍሎችም ታይተዋል።

ምናልባትም አጼ ቴዎድሮስ እንደ ጠቃሚ ትምህርት አድርገው የወሰዱት፡ ትግራይ ኢትዮጵያን በበላይነት ለማስተዳደር ያላትን ቋሚ ጕጕት ነው! በተለይም በ1769 ዓ.ም. ትግራዊው አስተዳደሪ ራስ ሚካኤል ስሁል ጎንደር ተቀማጭ የሆነውን የአቢሲኒያ መንግሥት በመገልበጥ፤ ዙፋኑ ላይ የነበሩትን ንጉሥ ገድለው በወቅቱም – ዛሬ ሕወሃቶች በየክልሎቹና በመንግሥት የሥልጣን አውታር ላይ የራሳቸውን ሰው እንደሚያስቀምጡት ሁሉ – ያንጊዜም ጎንደር ላይ የትግራይ አሻንጉሊት የሆኑትን ንጉሥ ኢዮአስን በትረ ሥልጣን አስጨብጠው ትግራይ መመለሳቸው ይታወሳል፡፡

በሌላ አባባል፡ ያ መንግሥት በስም የአቢሲኒያን ሕዝብ የሚወክል ነው የተባለው – በተግባር ግን ዛሬ በብሄረሰቦች እኩልነት ስም በሚኒስትርነት ማዕርግ፡ በሚኒስትሩ አማካሪነት፡ በካድሬነት፣ በመምሪያ ኃላፊነት ወዘተ በየመሥሪያ ሕወሃት ለተለያዩ ብሔረሰቦች ተወካዮች ሃላፊነት ቢያስቀምጥም፡ የሚከናወነው ሥራ ግን የሕወሃቶችን ጥቅም የሚያራምድ ነው!

ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 25 ዓመታት ሥልጣን የያዘው መንግሥታዊ አስተዳድር ሳይሆን፥ የሽፍታ ቡድን ነው የሚባልበት ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ፡የ ተለያዩ በቂ ምክንያቶች አሉ እነዚህንም እንደሚከተለው አስቅምጣቸዋለሁ፦

(ሀ) ሕወሃት በሙያ፡ በትክክለኛ ፖሊሲዎች፡ በአፈጻጸም ብቃት፥ ግልጽነትና የሕዝብ ድጋፍ ሊያገኘ የሚችለውን ቸል ብሎ፣ ሁሉን ነገር በውሸትና ቅጥፈት በየሰከንዷ ለመያዘ መሞከሩ፡ ሁለተኛ የተፈጥሮ ባህሪው መሆኑን በግልጽ አሳይቷል። ይህንን ሕዝቡም አውቆ፡ አውጥቶና አውርዶ በግልም በቡድን ወንበዴው ሕወሃት የዋሾዎች፡ ቀጣፊዎችና ቅሌታሞች ስብስብ መሆኑን አሳምኗል፡፡

(ለ) ሕወሃት እንደ መንግሥት በመዋቅርና ግልጽ በሆነ መንግሥታዊ ውክልና (mandate) መሥራት ስለማይችል (ተጠያቂነትን ለማሽቀንጠር)፡ በተለያዩ ሹመት ላይ ያሉት የሕወሃት አባሎችና ተባባሪዎቻቸው (የክልሉ ተወላጆች) ድርብርብ ሥራዎችን በምሥጢር ሲሠሩ፡ ንብረት ላይ፡ ትግራዊ ባልሆኑ ግለስቦች ሕይወትና ላይ ደጋግመው ጥቃት ይፈጽማሉ፡ ያስፈጽማሉ።

ከላይ የተጠቀሰው ጥሩ ምሣሌ የሚያገኘው፡ አቶ ኤርምያስ ለገሠ፡ “የመለስ ትሩፋቶች፡ ባለቤት አልባ ከተማ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ በሕወሃት የተወከሉ ሶስት ካድሬዎች: (u) ተስፋማርያም፡ (ለ) ሞንጆሪኖና (ሐ) ፍሥሐ መሲህ – ምንም ዓይነት የሕዝብ ውክልና ሳይኖራቸው፤ ከመጋረጃው በስተጀርባ ሆነው እንዴት አደርገው አዲስ አበባን በነተወልደ ወልደማርያም የበላይ አመራር ከካዛንችስ እንደሚያሽከረክሩ የሚገልጽ ነው።

ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አክብሮ ሊያስተዳድር ይገባው የነበረው ሕወሃት፡ እንደእባብ የተንኮሉን መንገድ ብቻ በመቀየስ የዛሬው አስፈሪ ሁኔታው ውስጥ ተዘፍቋል። የቅሌቱ ቅሌት ለሃገሪቱ አመራር የሚሰጠው ፓርቲውም (ሕወሃት/ኢሕአዴግ) ሆነ የመንግሥት አካል ተወካዮች ምንን ከምን ከማይለዩ ከእነዚህ ሰዎች መመሪያቸውን በየዘርፎቻቸው ሲቀበሉ ከርመዋል።

የአዲስ አበባን መሬትና ቤቶች መቀራመትም ጥንስሱ ይኽው ‘የካዝንችሱ መንግሥት’ ነበር። ዛሬም በተለያዩ የመንግሥትና የግል መዋቅር ውስጥ ባሉ የሕወሃት ሰዎች ይኸው ተግባር ይካሄዳል። በዚህና ተመሳሳይ ‘ሥራዎች’ የሕወሃት ሰዎች ጥቅሞች ይወጠናሉ። ይከናወናሉ። ከዳር ይደርሳሉ።

በቅርቡ በጻፍኩት አንድ ትችት፡ የፋና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ብሩክ ከበደ አሁን ያለው የሕወሃት ሰዎችና ቤተስቦቻቸው የዘረፉት መሬት በስሞቻቸው በይዞታነትና ሕጋዊነት እንዲረጉላቸው ሰለአዲስ ካዳስትራል ተግባራዊነት፡ ስብሰባዎች ሲያካሄዱ ስንብተዋል። ዓላማው እንዴት ይህንን ፍላጎታቸውን እንዴት ሕዝብ ላይ እንዲጫንላቸው የሕወሃት ሰዎች የሚያደርጉትን ምሥጢራዊ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ነው። ዜናው ፋና ላይ ሶስቴ ተቀያይሮ መጨረሻ ላይ ያለ ብሩክ ስም ወጣ። ኢዜአ ሲያወጣው ደግሞ የመጀመሪያውን እትም እንደያዘ ቀርቶ ምሥጢራቸውን አንኳ አስተባብረው ለመምራት አቅቷችው፡ ከብሩክ ስም ጋር ወጣ።

ዋናው ቁም ነገር፡ አሁንም የመሬቱን ፓሊሲ የሚመሩትና የሚያጽድቁት – ‘እንደ ካዛንችሱ መንግሥት’ ሁሉ – በ2005 ምርጫ ማግሥት መሬት ዘረፋውን በቀጥታ የመሩት ግለሰቦች ናቸው – የከተማ ልማት፡ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ይትባረክ መንግስቴ፡ የሕወሃት የስለላ ድርጅት (Information Newtwork Securtiy Agency – INSA) ተወካዮች፣ የፋና ኃላፊዎች፣ ወዘተ ናቸው።

(ሐ) የኤኮኖሚ ምዝበራ። ከምንጊዜውም በላይ በተጠናከረ መልኩ ትግራዊ ባለሃብቶች (ከሃገር ውስጥና ከሃገር ውጭ) በሕወሃት አስተባባሪነት በተለያየ መንገድ ከፍተኛ ገንዘብ ብድርና ሠፋፊ መሬት እየተሰጣቸው፡ የሃገሪቱን ሃብትና ንብረት በመቆጣጠር የሃብትና የፖለቲካ የበላይነታቸውን ሥር እንዲሰድ በማድረግ ላይ ናቸው። ይህ ሁኔታ፡ አሁን ተባብሶ፡ ብድርም የለም ተብለው ትግሬ ያልሆኑት ኢትዮጵያውያን በትዕግሥት ሲጠብቁ፡ ልማት ባንክም ይሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሕወሃት ሰዎች ግን ከፍተኛ ብድር በዘር መለያነት እየተለካ እየሰጡ ናቸው!

በተጨማሪም፡ የተለያዩ የመደጋገፍ እንቅስቃሴዎች በየቀኑ ይካሄዳሉ። ከብዙ በጥቂቱ ለምሳሌ፦

    * የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ (ከአርከበ እቁባይ ጋር ሆነው የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን መሬት በማዘረፍ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱት የሕወሃት አባል) የመንግሥት ንብረት ግዥ ቦርድ ሰብሳቢ እንደመሆናቸው፡ አብዛኞቹ እዚህ “መንግሥት የሚጋጥበት” ቦታ ላይ ነገደ ሕወሃቶች በተናጠል ሃገሪቱን እንዲግጡ እየተደረገ ነው። ለምሳሌ እንዴት ነው

አቶ ግርማይ ገብረአረጋዊ (የአግታ ሥራ አስኪያጅ)

    ከቻይና ለዩኒቨርስቲዎች የሚገዙትን አውቶቡሶች የጨረታ አሸናፊ የተደረጉት፣ ለዚያውም በተጠየቀው ወቅት ሁሉንም አውቶብሶች ማቅረብ እንደማችይሉ እየታወቀ?

* እንዴት ነው የእነኩሪፍቱና ሃገሪቱ ውስጥ በሙሉ የሪዞርት ሥፍራዎች ባለቤቶች፡ እነሙሉጌታ ተስፋ ኪሮስ ወዘተየእነኩሪፍቱ ሪዞርት እንዲህ መሬት በየቦታው እየተመረጠ የሚሰጣቸው? ሌሎች ኢትዮጵያውያን ምክንያቶች እየተፈለጉና በተለይም በታክስ ስም እየተገፉና የነበራቸውን ለሕወሃት አባላት እንዲሸጡ እየተደረገ መሆኑ ሕወሃቶች የማይታወቅ ከመሰላቸው ተሳስተዋል!

* የመለስ ዜናዊ ቤተስብ ኩባንያ ኦርኪድ የምርት ገበያን የአባልነት ወንበር በሃሰት ጨረታ ስም በ1.6 ሚሊዮን ብር በመግዛት፡ ሌሎችን በር እየዘጉባቸው ያሉት?

* ተከስተ ስብሃት፡ የስብሃት ነጋ ልጅ በጥቂት ብሮች የኢትዮጵያ የእህል ጎተራን 4000 ስክዌር ሜትር ሥፍራ ለአራት ዓመታት በብር 600፣000 ለማስታወቂያ ሊከራይ የቻለው? ይህ በጠቅላላ የሕወሃት አስተዳደር ሥር ያለው (ጸሐፊና ተላላኪ ሳይቀር) የኢትዮጵያ ጎተራና የኢትዮጵያ የስብል ድርጅት የሚያስተዳድረው ይህ ሥፍራ ሌሎች ጠያቂዎች ተከልክለው? ቀደም ሲል ለምንድነው የተከለከለው? አንደኛ ለተወሰኑት ዋጋውን በማሰወደድ የተደረገው ነገር ጭምጭምታው ተሰምቷል። ሁለተኛ ደግሞ ደጋግመው ለጠየቁት፡ ገና አልተወሰነም ሲባል ተከርሞ፡ በአካባቢ ዕድሳት ስም በመጨረሻ እንዲከለከሉ ተደረገ! እስከ መቼ ድረስ ነው የሕወሃት ሰዎች ለትግሬዎች ተመራጭነት ዕድል ስጥተው ሊሎች ኢትዮጵያውያንን ሲያራቁቱ በዝምታ ሕዝቡ የሚመለከተው?

* አህዱክስ ቢሾፍቱ ላይ የምግብ ማምረቻ ሰሞኑን መመረቁን ስምተናል። ነገሩ Vasari Investments Group ከተሰኘ የእንግሊዝ ኩባንያ ጋር ተባብሮ ሲሆን፡ በአሁኑ ወቅት ማቋቋሚያው $36 ሚሊዮን ሲሆን፡ ይህንንም ሁለቱ ወገኖች ወደ $120 ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ ስምምነት አለ። የዛሬዎች ከበርቴዎች፡ ሁኔታው የተመቻቸላቸው የሕወሃት ሰዎች ስለሆኑ፡ የሚኖረውን የገንዘብ ወደውጭ ሽሽትም እንደሚያባብስው አያጠያይቅም። በዚህም ሆነ በዚያ እየተመዘበረ ያለው ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው!

* የሕወሃቶች ተአምር ስለማያልቅ፡ በአዳማ ከተማ ኦሮሚያ ውስጥ በአንድ ኪሎ ሽሮ መንገድ ዳር ምግብ መሸጥ የጀመሩት ወይዘሮ ሰላም ተክላይ በ12 ሚሊዮን ብር ዘመናዊ ሆቴል አሰርተው ባለፈው ቅዳሜ አስመረቁ ይለናል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት። ኢዜአ ያልነገረን ግን፡ ስለሴትዮዋ ግንኙነቶች ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ፡ ዛሬ የሕወሃት የደህንነቱ፡ የጦሩና የፖለቲካ ካድሬዎች ቀድሚያ ግብር ካልበሉ፤ እንዲሁም ከሌሎች ድርጅቶች የመጡት ትርፍራፊ ሰብሳቢዊችና አስገባሪዎች ቅንጣቢ ካልወሰዱ፡ ንግዱም፡ ምርቱም ልውውጡም ከንቱ ልፋት ነው! ቅንጣቢዎች ተደማምረው ዘረፋ ሰልሚሆን፡ ንጹሃንና ትጉህ ሃገር ወዳድ አምራቾችና ነጋዴዎች ተስፋ ቆርጠው፣ ኤኮኖምስቶች Disincentive በሚሉት ሁኔታ ምክንያት ዕለታዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ትልልቅ ሃሣቦችን ይሸሻሉ!

ወይዘሮ ሰላም ተከላይ ይህን ሁሉ ተቋቁመው ከሆነ ባለ 12 ሚልዮን ሆቴል ገንብተው በተጨማሪ ባለ 50 ሚሊዮን ሆቴል መፍበርኪያ ሊያቋቁሙ የተዘጋጁት፡ በሰማይም በምድርም ተአምር ተደርጎ ተወስዶ – የቫቲካኑ ፓፓ ፍራንሲስ የድሃ ወዳጅ ናቸውና – ስለወይዘሮ ሰላም ተክላይ ተአምር ተነግሮ የቅዱሳንነት ማዕረግ እንዲሰጣቸው መጠየቅ ይገባል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ራሷ የወንበዴዎች ዋሻ ሰለሆነች እግዚአብሔርም ውስጧ ላሉት ‘ካህናት’ ከላይ እስከታች ጆሮውን እንደማይሰጥ ግልጽ ከሆነ ስንብቷል!

ሜክሲኮ ለምንድነው የወጣቶች ደም ሳይቀር የሚፈሰባት ሃገር የሆነችው? መንግሥትና ፖሊስ ከሕዝቡ ጋር ሳይሆነ ከአድንዛዥ ዕጽ/ኮኬን ነጋዴዎች ጋር እጅና ጓንት ስለሆኑ ነው። ገና ከንጋቱ በሥልጣን ላይ ከሰባ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የሃገሪቱ መሪ ፓርቲ (Partido Revolucionario Institucional, (PRI) – Institutional Revolutionary Party) ከጉበኞች፡ ዘራፊዎችና ወንበዴዎች ጋር በጥቅም በመተሳሰሩ ነው። ለምሳሌ በቅርቡ 43 መምህራን ኮሌጅ ተማሪዎች ለምንድነው በፖሊስ ተውሰደው (በከንቲባውና ፖሊሲች – ሃሜት እንደሚያሰማው፡ የፕሬዘደንቱ ሚስት እጅ አለበት እየተባለ) ደብዛቸው የጠፋው? እነዚህ ከደሃ ቤተሰብ የመጡ – የዛሬዎቹ ተማሪዎች የነገው መምህራን – የበሰበስውን ሥርዓት ጥቅም ሰለማያስጠብቁ ነው የሚል ትንታኔ ማንበቤ ትዝ ይለኛል።

ሃገርና መንግሥት ወንበዴና ሽፍቶች ሲሆኑ፣ ሕዝብ ምን አማራጭ ይኖረዋል? የዛሬይቷን ኢትዮጵያ ሕወሃቶች የነገዋ ሜክሲኮ እንዳያደርጓት እያንዳንዱ ኢትዮጵያ ዛሬ ነው ሊታገላቸው የሚገባው!

* ባለፈው መጋቢት ወር ጋሞጎፋ ውስጥ፡ አልጌ በተባለ የገበሬ ማኅበር ውስጥ ባለሃብቶች ከፖሊስ ጋር መጥተው ገብሬዎቹን መሬታችሁን ለቃችሁ የፈለጋችሁበት ድረሱ ተባሉ። አብረው ከፖሊሶች ጋር የመጡት ሃብታሞች ትግሬዎች ናቸው። ባለሃብቶቹ የፈለጉት ግለስቦቹን አስነስተው በሥፍራው ላይ ትምባሆ ለማምረት ነበር። ስው ሃብቱን መጠበቅና ማስጠበቅ አለበት። መሬታችንን አንሰጥም በማለታቸው ገበሬዎቹን ፖሊስ ደበደባቸው። በኃይለ ቃል ተናገራቹ በተባሉት ላይ ተኩስ ተከፍቶ አንድ ሰው ሲሞት፡ ሰባት ሰዎች ክፉኛ ቆስለዋል። ፖሊስም ተጠያቂ አልሆነም፤ ገብሬዎችም መሬታቸውን ማዳን አልቻሉም። ይህ የዘረፋ ሥር በግልጽና በተደጋጋሚ የታየው፡ ሃገሪቱ በዘር በተደራጀ ዘራፊ ቡድን በመያዟ ነው።

* ሪፓርተር በሚያዝያ 29 ቀን 2007 ዕትሙ ቀድሞ በአዲስ አበባ አስተዳደር የመሬት ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት አቶ ቃሲም ፊጤ በመሬት ማጭበርብር ወንጀል ተከሰዎ ለጊዜውም ቢሆን እሥር ሁሉ ገብተው ነበር። ከስንት መጉላላት በኋላ፡ ነጻ ናቸው ተብለው ተፈቱ። ወዲያው የከንቲባው አማካሪ ሆነው ተሾሙ። አሁን ደግሞ ሪፖርተርን ጭምር እስኪገርመው ድረስ፡ የኦሮሚያ ክልል የከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ ኃላፊ ሆነው መሾማቸው ተነገረ። ሕጉ ነጻ ያለውን ግለሰብ ወንጀለኛ ነው ለማለት መረጃው ባይኖረንም፡ አቶ ቃሲምን ሕወሃት ለዚህ ሥፍራ ከአቶ አባይ ፀሐየ በኦሮሞች ላይ የሐዋሣ ድንፋታ በኋላ፡ ጥርጥራችንን አበራክቶታል። ሕወሃትም የተንኮል ፖለቲካውን ያውቀዋል፡ ኢትዮጵያውያንም ሕወሃት ሊበላት ያሰባትን ቆቅ ወንም ጅግራ በግልጽ እያያት ነው!

* የሕወሃት የንግድና የአገልግሎቶች ድርጅቶች ወደ ድርጅቱ (ሕወሃት) ገንዘብ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ናቸው። ለምሳሌም ያህል ከሕዳሴ አባይ ግድብ እስከ ሱካር ፋብሪካዎች፡ መንገድ ሥራ ያለአንዳች ጨረታ ምን ያህል ሃገራችንን እየጋጡ እንደሆነ ጠጋ ብሎ መመልከት ያስፈልጋል – ለምሳሌ መሰቦ ሲሚንቶ በውድ ዋጋ በማቅረብ፡ ሱር ኮንስትራክሽን፡ ኢዛና ያለጨረታ በሚያገኟዋቸው ኮንትራቶች ወዘተ ሌላውን ሕዝብ መንገድ እንደተዘጋበት ከመገንዘብ ይልቅ፡ ሰነፍ፡ ደደብ፡ ኋላቀር አድርገው እንደሚመለክቱት እየታየ ነው።
የተ.መ.ድ. (UNDP) ጥናት የኢትዮጵያ ዕድገት የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ብቻ ነው የሚጠቅመው አለ

2014 የተ.መ.ድ. (UNDP) ሪፖርት የኢትዮጵያን የኤኮኖሚ ዕድገት የተቀበለው ቢሆንም፣ አሁን ደግሞ ባለፊት 15 ዓመታት የኢትዮጵያ ድሆች ቁጥር 25 ሚሊዮን ሲሆን፣ ይህም እስካሁን ምንም ለውጥ አላሳየም ይላል። ይህ አሁን ተመድ የደረሰበት ድምዳሜ ለኢትዮጵያውያን ሕይወታቸው ነውና ምንም አዲስ ነገር አይነግራቸውም። ይህ የተመድ ሪፖርት አሁን ግልጽ ያደረገው፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቦቿ በኤኮኖሚ ዕድገቷ ሁሉም ተካፋይ አይደሉም የሚለውን ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ኢትዮጵያ ሁሉም እኩል ተጠቃሚ ከሚሆንበት የዕድገትና ልማት ፖሊሲ ጎዳና ከወጣች እጅግ በመሰንበቷ ነው የሚለው አመለካከት በተዘዋዋሪ መንገድ ሠፍሯል።

በአዲስ አበባ የተመድ ተወካይ፡ ይህንን ሲያብራራ እንዲህ ይላል፦

    “We launch this report as part of helping the inclusiveness of the country’s economy and the Human Development Index of the country, which showed a slight increase although the rank it holds still remains at 173 out of 187 countries … Gain from the country’s growth is not equal among different groups.”

ከሪፖርቱ ውስጥ ጠቅሶ ተወካዮ ያወጣው ክፍል እንዲህ ይላል፦

“However, because of high population growth, the absolute number of the poor (about 25 million) had remained largely unchanged over the past 15 years”.

በዚህም ምክንያት ምንም ያህል፡ ስለዕድገትና ድህነት ቅነሳ ቢወራም፡ ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ ሃገሮች ጤነኛና አዳጊ መሆኗ አጠያያቂ ነው። መንግሥት ውስጥ የተሠገሠገው ሽፍታና ወንበዴ ከካንሥር የካፋ የጥፋት ኅይል አለው!
መደምደሚያ

የሌብነት ባህሪ፡ የተጠናወተው፡ ጥጋብና ጉልበተኛነት የሚሰማው ሕወሃት ገና የከፋ ሁኔታ በሃገራችን ላይ ሊያመጣ ይችላል!

የግለሰብ ነጻነት ማለት፡ ግለሰቡ ሙሉ ችሎታውንና ተሰጦውን ተጠቅሞ ባለበት ኅብረተስብ ውስጥ በሚፈልገው መንገድ ሕይወቱን ለመምራት መቻል ነው። ይህ የመብቶች ክምችት፡ የንብረት ማፍራትን፡ መለወጥን መብቶች የሚያጠቃልል እንደመሆኑ፡ መንግግሥት የሚባለው አካል ደግሞ የግለስቡንና ቤተስቡን ሕይወትና ንብረቶቻቸውንን የመጠብቅ ግዴታዎች አለበት። ችግሩ ግን ዛሬ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ወንበዴዎችና ሽፍቶች የሚፈነጩበት የወሬ በሎች ካምፕ ተደርጓል! ጨዋታ ሆኖአል።

መንግሥት ራሱ በሕግ የሚተዳደርና፣ ከሕግ ውጭ ታክስ እንዳይጭን፡ ንብረቶችን እንዳይዘርፍ ለሕግ የሚገዛበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ከዚህም በተጨማሪ፡ የንብረቶችን አስተዳደር በሚመለከት፡ ሕወሃትና ጭፍሮቹ ውስጥ የተሰገሰጉት ዘራፊዎች የሕግን ቀዳዳ በመጠቀም፡ ደምና ዘር ቆጥረው ከእነርሱ ጋር ያልተዛመደውን የሚዘርፉበት ቀዳዳ መዘጋት አለበት።

መንግሥት የሚባለው አካል ይህንን ማድረግ ካልቻለ፡ የሰዎች ንብረት እየተደበደቡ ሲዘረፉ ተመልካች ወይንም አበራታች ከሆነ፡ ሽፍቶቹና ወበዴዎቹ ያሉት ራሱ ወንበዴው የሕወሃት መንግሥት ውስጥ ሰለሆነ ለማንም ሃገር ቢሆን አደጋው እጅግ ከፍተኛ ነው!ኢትዮጵያውያን ይህንን ዛሬ ሊያደርጉ ካልቻሉ ሃገራችን ወደ አደገኛው ሜክሲኮ በቅጽበት ልትቀየር ትችላለች!

ሜክሲኮ ለምንድነው የወጣቶች ደም ሳይቀር የሚፈሰባት ሃገር፡ መንግሥትና ፖሊስ ከሕዝቡ ጋር ሳይሆነ ከኮኬን ነጋዴዎች ጋር እጅና ጓንት የሆኑት? ገና ከንጋቱ በሥልጣን ላይ ከሰባ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው Partido Revolucionario Institucional, (PRI) Institutional Revolutionary Party )ከጉበኞች፡ ዘራፊዎችና ወንበዴዎች ጋር በጥቅም በመተሳሰሩ ነው። ለምሳሌ በቅርቡ 43 መምህራን ኮሌጅ ተማሪዎች ለምንድነው በፖሊስ ተውሰደው (በከንቲባውና ፖሊሲች – ሃሜት እንደሚያሰማው፡ የፕሬዘደንቱ ሚስት እጅ ባለበት – ደብዛቸው የጠፋው? እነዚህ ከደሃ ቤተሰብ የመጡ የዛሬዎቹ ተማሪዎች የነገው መምህራን – የበሰበስውን ሥርዓት ጥቅም ሰለማያስጠብቁ ነው የሚል ትንታኔ ማንበቤ ትዝ ይለኛል።

ሃገርና መንግሥት ወንበዴና ሽፍቶች ሲሆኑ፣ ሕዝብ ምን አማራጭ ይኖረዋል? የዛሬይቷ ኢትዮጵያን ሕወሃቶች የነገዋ ሜክሲኮ እንዳያደርጓት እያንዳንዱ ኢትዮጵያ ዛሬ ነው ሊታገላቸው የሚገባው!

ለነገሩማ ሕወሃት ጤነኛ መንግሥት መመሥረት ቢችል ኖሮ፡ የዜጎችን ደህነንት ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባሩ ሊያደርግ በተገባው ነበር። ባለፈው ጊዜ ኢትዮጵያዉያን በሊቢያና ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም የመን አደጋ በደረሰባቸው ወቅት፡ እንደ መንግሥት ኃላፊነቱን መረከብ ባለመቻሉ፡ እንደውም ይባስ ብሎ፡ ከባለጌነቱ የተነሳ፡ የእነሱን ሥቃይና ሞት የዘራፊ ፖለቲካና ቁማር መጫወቻ ደረገው።

ይህ የሚያሳየው፡ በመንግሥታዊ ሃላፊነቱና በዜግነት ግዴታው ይህንን ሊማድረግ  የማይችል መንግሥት – ጥላቻ፡ ንቀትና ትዕቢት ያሰከረው አስተዳደር ሰለሆነ – ለሰው ልጅ ከበሬታ የሌለው ሰብዓዊነቱ ተሟጦ የደረቀበት ድርጅት ብቻ መሆኑ ለዕይታ እንኳ ሕወሃት መንግሥታዊ ተቋም አለ የሚያስብል እንቅስቃሴ እንኳ ማድረግ እንዳቃተው አሳየ።
&nbps;

*Updated material

&nbps;

Updated.

%d bloggers like this: