በምርጫው በሕወሃት ቅጥረኞች ከተፈጸሙት የድምጽ ሌብነቶች ጥቂቱ: መረጃው ሲያፈጥበት፥ ማጅራት መችው ምርጫ ቦርድ “አጣራለሁ” አለ

1 Jun

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

ከአዘጋጁ

በምርጫው ዙሪያ የተፈጠሩት አሳፋሪ ተግባሮች፡ ሃገሪቱ ያለችበትን የአመራር ዕጦት፣ የሕወሃትን የሥልጣን ርሃብና በኢሕአዴግ በኩል ደግሞ የኃይለማርያምን የአመራር ብቃት ድህነት አመላካች ነው።

የእነርሱ ችግር የራሳቸው ነው! እነዚህ ሰዎች ግን ሃገራችንን ወደ ገደል ሲገፏት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዝም ብሎ መመልከቱ፡ ለልጆቹና ለመጭው ትውልድ ግድ የለኝም ማለት ስለሆነ በታሪክ ፊት ያስወቅሳል! ዘረፋቸውም ሊያበቃ ይገባል!

ይህ ችግር ሃገሪቱን ወደከፍተኛ አዘቅት ሳይከታት በፊት፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተገፈፈውን መብቶቹን ለማስመለስ፡ ከዚህ የወንበዴና ሽፍታ አስተዳደር ጋር ላለመተባበር ሁሉን ጥረት፡ መሣሪያ እስከማንሳት የሚደርስ ትግል ለሚደረግ መዘጋጀት ይኖርበታል!

ቆማጣ ቆማጣነቱን እንዲገነዘብ ካልተደረገ፡ ገበታው ለማንም አይበጅም!
 

– I –
 

ታዋቂ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ባልሥልጣኖች በድምጽ ሌብነት ተጠርጥረዋል!

ከአንድ ሺሕ በላይ መራጮችን ያስተናገዱ የምርጫ ጣቢያዎች ከሕጉ ተጣርሰዋል ተባለ

የተሻሻለው የምርጫ ሕግ በአንድ የምርጫ ጣቢያ መመዝገብና መምረጥ ያለበት መራጭ ከአንድ ሺሕ በላይ መሆን የለበትም ቢልም፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በርከት ያሉ የምርጫ ጣቢያዎች ከአንድ ሺሕ በላይ ነዋሪዎችን በማስመረጥ ሕጉን

መጣረሳቸው ታይቷል፡፡ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፣ ‹‹እኛ የምናውቀው በሁሉም ምርጫ ጣቢያ አንድ ሺሕና ከዚያ በታች መራጭ መመዝገቡንና መምረጡን ነው፡፡ የተባለውን ስህተት አጣራለሁ፤›› ብሏል፡፡

ይኼንኑ ችግር የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ጊዜያዊ ሪፖርቱ ጠቁሞታል፡፡ የሪፖርተር ዝግጅት ክፍል ያሰማራቸው ጋዜጠኞችም በአንድ የምርጫ ጣቢያ ከአንድ ሺሕ በላይ መራጮች መሳተፋቸውን በማስረጃ ማረጋገጥ ችለዋል፡፡

የሪፖርተር ጋዜጠኞች ከጎበኟቸው የምርጫ ጣቢያዎች መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ የተወዳደሩበት በኦሮሚያ አርሲ ዞን ምርጫ ጣቢያ ኢተያ 01-2ሀ-1 ማሳያ ነው፡፡

አቶ አባዱላ ከላይ በተገለጸው የምርጫ ጣቢያ 1,214 ድምፅ በማግኘት አንደኛ ደረጃ ሲይዙ፣ የኦብኮ ተፎካካሪያቸው ደግሞ 10 ድምፅ አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ምርጫ ጣቢያ ብቻ 224 መራጮች ከሕጉ በተቃራኒ ተሳትፈዋል፡፡

በፓርላማው የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በተወዳደሩበት በስልጤ ዞን ዱና ምርጫ ጣቢያ በብቸኝነት ተወዳድረው 1,459 ድምፅ አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ምርጫ ጣቢያ ከሕጉ በተቃራኒ 459 መራጮች ተስተናግደዋል ማለት ነው፡፡ ወ/ሮ ሙፈሪያት በተወዳደሩበት ሌላ ምርጫ ጣቢያ በቅበት ምርጫ ክልል ሸ/ገሬም ቁጥር 0-1 ምርጫ ጣቢያ ብቻቸውን ተወዳድረው 1,370 ድምፅ አግኝተዋል፡፡ ይኼ ማለት በምርጫ ጣቢያ ከሕጉ በተጣረሰ መልኩ 370 መራጮች ተሳትፈዋል፡፡

በተጨማሪም በወላይታ ሁለገብ ምርጫ ክልል በቦዲቱ ቆርኬ ምርጫ ጣቢያ ከመድረክ ዕጩ ጋር የተወዳዳሩት የኢሕአዴግ ተወካይ አቶ አማኑኤል አብረሃም 1,182 ድምፅ ሲያገኙ፣ የመድረክ ተፎካካሪያቸው አንደ ድምፅ አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ የምርጫ ጣቢያ 183 መራጮች ያላግባብ ተስተናግደዋል፡፡

ሌላው በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን ስቄ 02 ምርጫ ክልል የኢሕአዴጉ አቶ ዮሴፍ ዳኤሞ 1,051 ድምፅ ያሸነፉ ሲሆን የመድረክ፣ የሰማያዊና የቅንጅት ተፎካካሪዎቻቸው ደግሞ አንደ ቅደም ተከተላቸው 171፣ 19፣13 ድምፆች አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ የምርጫ ጣቢያ 254 መራጮች ያላግባብ ተሳትፈዋል፡፡

በደሴ ከተማ ሮቢት ክፍለ ከተማ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው በሚወዳደሩበት ምርጫ ጣቢያ 22 ላይም 1,049 መራጮች ተመዝግበው የነበረ መሆኑን ሪፖርተሮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቱን ቦርዱ ይፋ ባደረገበት ወቅት ስለጉዳዩ የተጠየቁት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር፣ ‹‹አንድ ምርጫ ጣቢያ የሚያስተናግደው አንድ ሺሕ መራጮችን ብቻ ነው፡፡ እኛ የምናውቀው በአንድ ምርጫ ጣቢያ ከአንድ ሺሕ በላይ መራጭ አለመመዝገቡን ነው፤›› ብለዋል፡፡

የምርጫ ሕጉ በአንድ ምርጫ ጣቢያ ከአንድ ሺሕ በላይ መራጭ መመዝገብ የለበትም እንደሚል የገለጹት ዶ/ር አዲሱ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ 45,795 ምርጫ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ የተደረገውም በዚሁ ሥሌት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ከአንድ ሺሕ በላይ ያስተናገዱ ምርጫ ጣቢያዎችን ማጣራትና መመርመር ይኖርብናል፡፡ በመሆኑም ይኼንን ጥያቄ በተመለከተ ይኼ ነው ብለን የምንሰጠው መልስ የለም፤›› ብለዋል፡፡

የተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ዓ.ም. በአንቀጽ 22(6) ላይ ‹‹እያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ የሚያስተናግደው የመራጮች ብዛት ከ1,000 መብለጥ የለበትም፤›› በማለት ይደነግጋል፡፡
 

– II –
 

መድረክ የምርጫው ውጤት በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠየቀ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተከናወነው አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ መሠረታዊ የሆኑ ሕገ መንግሥታዊና ሌሎች የምርጫ ሕጎችን በጣሰ ሁኔታ የተከናወነ በመሆኑ፣ ይኼንን የሕግ ጥሰት የሚያጣራ ገለልተኛ የሆነ አጣሪ አካል እንዲቋቋም ጠየቀ፡፡

ፓርቲው ይህን ጥያቄ ያቀረበው ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡

በዕለቱ መግለጫውን የሰጡት የወቅቱ የመድረክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የፓርቲው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲናና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ናቸው፡፡

‹‹ምርጫው የአገሪቱን ሕገ መንግሥትና ያሉትንም ሕግጋት ሁሉ የጣሰ ነው፡፡ ስለሆነም ወገንተኛ ያልሆኑ ዜጎች ያሉበት ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ፣ በምርጫው ሒደት የተከሰቱት የሕግ ጥሰቶች እንዲያጣራ መድረክ አበክሮ ይጠይቃል፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ከምርጫው ዕለት ቀደም ብሎ በከፍተኛ ሁኔታ መሠረታዊ የሕገ መንግሥት፣ የምርጫ ሕግጋትና ሌሎች የሥነ ምግባር ጥሰቶች ተፈጽመዋል ብለዋል፡፡

ለአብነትም ያህል ሲጠቅሱ፣ ‹‹ለመድረክ 303 የፓርላማ ተወዳዳሪዎችን አዘጋጅተን ያቀረብን ቢሆንም፣ ምርጫ ቦርድ ግን ዕውቅና የሰጠልን ለ270 ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱንም የሚያስረዳን አካል አልነበረም፤›› በማለት መድረክ መጉላላት የጀመረው ከምርጫው ዕለት ቀደም ብሎ እንደነበር አውስተዋል፡፡

ሌላው ፕሬዚዳንቱና ሌሎች የመድረክ አመራሮች ያነሱት ነጥብ ደግሞ፣ ከምርጫው ቀደም ብለው የተከናወኑት የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫና የምርጫ ቅስቀሳ በችግር ውስጥ መከናወናቸውን ነው፡፡

‹‹የምርጫው ዕለት ሲቃረብ ደግሞ ዕጩ ተወዳዳሪዎቻችን ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የዘንድሮ ምርጫ የምርጫ ሕጎችን፣ የሥነ ምግባር ደንቦችንና ሕገ መንግሥቱንም ጭምር የጣሰ የምርጫ ሒደትና አፈጻጸም ያሳየ መሆኑን መድረክ ገምግሟል ብለዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ፓርቲው ደርሷል፤›› በማለት አክለው አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የፓርቲው አመራሮች የታሰሩ አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን መንግሥት እንዳፈታ ጠይቀዋል፡፡
 

– II –
 

የመኢአድ ምክትል ፕሬዚዳንት በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ተከሰሱ

-የኮበለሉ መኮንንና አክራሪነትን ሰበኩ የተባሉ ሼክም ክስ ተመሥርቶባቸዋል

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዚዳንት መሆናቸው የተገለጸውና አድራሻቸው በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ማክሰኝት ከተማ መሆኑ የተጠቀሰው አቶ ዘመነ ምሕረቱ ታከለ፣ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ተከሳሹ በሰው ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፈራረስ ዓላማ ካለውና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ግንቦት ሰባት ድርጅት ጋር አብረው ለመሥራት መስማማታቸውን፣ ክስ የመሠረተባቸው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስፍሯል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ መስከረም 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ በሚገኘው የመኢአድ ጽሕፈት ቤት ውስጥ አባላቱን በመሰብሰብ ‹‹የወያኔ መንግሥት መውደቂያው ደርሷል፡፡ አንድ የጦር አውሮፕላን፣ 12 የጦር ጄኔራሎች መንግሥትን ከድተው ወደ ኤርትራ ገብተዋል፡፡ ኢሕአዴግን በጦር ካልሆነ በሰላማዊ መንገድ ከሥልጣን አይለቅም፡፡ የሕዝብ እምቢተኝነትን በመፍጠር የወያኔን መንግሥት መጣል አለብን፡፡ በ2007 ዓ.ም. የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ አይካሄድም፡፡ ወደ ምርጫው አንገባም፡፡ ሌላ አማራጭ መጠቀም አለብን…›› በማለት ሕጋዊ አማራጮችን ትተው የኃይል አማራጮች ለመጠቀም ሲቀሰቅሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቦምብ አወራወርና መሣሪያ መፍታት የሚችል በማነጋገርና በጥምቀት በዓል ላይ ተልዕኮ መፈጸም የሚችል ሰው ሲያፈላልጉ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ በአጠቃላይ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የሽብር ዓላማን ለማራመድ በማሰብና የሽብርተኝነትን ድርጊት ለመፈጸም ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴርና ማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸውን የክስ ሰነዱ ያብራራል፡፡

ከመኢአድ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር በአንድ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው፣ አድራሻቸው አዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ውስጥ መሆናቸው የተጠቆመው አቶ ጌትነት ደርሶ አዱኛ ናቸው፡፡ እሳቸውም የግንቦት ሰባት ድርጅት አባል በመሆን እንደ አቶ ዘመነ ምሕረቱ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም መንቀሳቀሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ተከሳሹ ከድርጅቱ ጋር አብሮ ለመሥራት በመፈለግ ወደ ኤርትራ በመሸጋገር የግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራር ከሆኑት ዶ/ር ክፈተው አሰፋ ጋር በመገናኘት፣ ስለድርጅቱ ዓላማ ፖለቲካዊ ሥልጠና መውሰዳቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ በወታደራዊ ሥልጠና የመሣሪያ ተኩስ፣ የዒላማ ተኩስ፣ መከላከልና ማጥቃት በድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮችና በኤርትራ መንግሥት ወታደሮች መሠልጠናቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡ ተከሳሹ ለድርጅቱ አባላትን እንዲመለምሉና ወደ ኤርትራ ወታደራዊ ሥልጠና መስጫ ካምፕ እንዲልኩ የፌስቡክ አካውንት Fasil@gmail.com የሚል አድራሻ እንደተሰጣቸውም ክሱ ያብራራል፡፡ በአጠቃላይ የሽብር ድርጅቱ አባል በመሆናቸው፣ በማንኛውም መልኩ በሽብርተኝነት ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወንጀል መከሰሳቸው የክስ ቻርጁ ያስረዳል፡፡

በተመሳሳይ የክስ መዝገብ ክስ የተመሠረተባቸው ሌላው ተጠርጣሪ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነዋሪ መሆናቸው የተገለጸው አቶ መለሰ መንገሻ የተባሉ ግለሰብ ሲሆኑ፣ ራሱን የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ብሎ በሚጠራው ቡድን ውስጥ አባል ሆነው የተገኙ መሆናቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ጠቁሟል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በሰው ሕይወትና አካል ላይ ጉዳይ ለማድረስ መንቀሳቀሳቸውን፣ በትጥቅ ትግል ሥልጣን ለመያዝ ከሚንቀሳቀስ ቡድን ጋር ማበራቸውን፣ በኤርትራ አውሃጅራ አካባቢ ለሚንቀሳቀሰው የሽብር ቡድን ከፍተኛ አመራር ከሆኑት ግለሰብ ጋር በተለያዩ ጊዜያት በስልክ በመገናኘት አባላትን ይመለምሉ እንደነበር በክሱ ተካቷል፡፡ ተከሳሹ የኢትዮጵያ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሚበዙበት አካባቢ እንዴት ጥቃት መፈጸም እንዳለበት ለሽብር ድርጅቱ አመራሮች ገለጻ በማድረጋቸው፣ በሽብር ተግባር ላይ በመሳተፍ ወንጀል መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ግንቦት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ሌላው ክስ የመሠረተው የአየር ኃይል ባልደረባ በሆኑት ምክትል መቶ አለቃ አንተነህ ታደሰ ዘውዴ በተባሉት ተጠርጣሪ መኮንን ላይ ነው፡፡

ምክትል መቶ አለቃው ወደ ኤርትራ እንዲኮበልሉ ምክንያት የሆናቸው ቀደም ብሎ የአየር ኃይል ባልደረባ የነበረውና ባልታወቀ ምክንያት በጥቅምት ወር በ2007 ዓ.ም. ወደ ኤርትራ መሄዱ በተጠቀሰው ምክትል መቶ አለቃ ዳንኤል የሸዋስ ጋር በፌስቡክ በመገናኘት መሆኑን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ “Doni Yeshu Sweet” በሚል አድራሻና በተለያዩ ስልኮች ይገናኙ እንደነበርና ታኅሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ከደብረ ዘይት አየር ኃይል በመነሳት ወደ ኤርትራ ጉዞ እያደረጉ መንገድ ከሚያሳያቸው ሌላ ሰው ጋር ታኅሳስ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ወሮታ ከተማ ላይ መያዛቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ወንጀልም መከሰሳቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በተለያዩ የክስ መዝገቦች ክስ ከመሠረተባቸው ውስጥ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ቶንጎ ወረዳ ሻንቦላ ከተማ ሻንቦላ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ ነዋሪ መሆናቸው የተጠቀሰው ሼክ መሐመድ አብዱል ቃድር የሚባሉ ተጠርጣሪ ናቸው፡፡

ተከሳሹ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደርና ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት የእስልምና ሃይማኖትን እንደ ሽፋን በመጠቀም፣ በኃይል እስላማዊ መንግሥት ለማቋቋም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ሼክ ሐመድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቶጎ ወረዳ ጎሬ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ በሚገኙ መስጊዶች በመዘዋወርና ሙስሊሙን ማኅበረሰብ በማሰባሰብ፣ ‹‹እኛ የካዋርጃ እምነት ተከታይ መሆን አለብን፡፡ ለመንግሥት አትታዘዙ፡፡ ግብር አትክፈሉ፡፡ ጤና ጣቢያ ሄዳችሁ እንዳትወልዱ፡፡ ወላጆች ልጆቻችሁን ትምህርት ቤት አትላኩ፡፡ የእኛን አስተምህሮ የማይከተል ካፊር ነው፤›› ብለው በግልጽ በመናገር፣ ኅብረተሰቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረው ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

‹‹የሻንቦላና የአካባቢው ነዋሪዎች በአጠቃላይ መመራት ያለብን በሸሪዓ ሕግ ወይም እስላማዊ መንግሥት መሆን አለበት፤›› በማለት በመቀስቀስና የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድ በማሴር፣ በማዘጋጀትና በማነሳሳት ወንጀል ሼኩ መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡
 
/ሪፖርተር
 

ተዛማጅ ጽሁፎች

    ምርጫ 2007ን ለመዝረፍ በሕወሃት/ኢሕአዴግ በከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች የተደረጉ ወንጀለኛ ዝግጅቶች – በፓርቲው ውስጣዊ መረጃ ላይ የተመሠረተ ትንታኔ
    የሽፍታ/ወንበዴ መንግሥት በኢትዮጵያ

 

%d bloggers like this: