ከቴፒ እሥረኞች በማስፈታትና መሣሪያዎች በመንጠቅ ያመለጠው ወጣቶች ቡድን ተጨማሪ የሕወሃት ወታደሮችን መግደሉና የቆሰሉት ሆስፒታል እንደሚገኙ ታወቀ! ጨካኙ የሕወሃት ጦር የአንድ ተፋላሚ ሬሣ መንገድ ለመንገድ ሲጎትት ውሏል!

11 Jun

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

ሰኔ ፬ ቀን ፳፻፯ ዓ/ም (ኢሳት ዜና): ሰሞኑን የቴፒ ወጣቶች ቡድን በአንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ የወሰደውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ ሶስት ፖሊሶች ከተገደሉና በርካታ እስረኞች ካመለጡ በሁዋላ፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ታጣቂዎች መሽገውበታል ወዳለው አካባቢ በመሄድ ውጊያ የከፈቱ ሲሆን፣ ወጣት ታጣቂዎች አስቀድመው ዝግጅት አድርገው በመቆየታቸው በርካታ ወታደሮች መሞታቸውንና መቁሰላቸውን ምንጮች ገልጸዋል።

የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት በርካታ ወታደሮች ሙትና ቁስለኛ ሲሆኑ፣ ቀላል የመቁሰል አደጋ ያጋጠማቸው በአማን ሆስፒታል ተኝተው ሲታከሙ፣ ከባድ ቁስለኞችና ሟቾች ደግሞ በሄሊኮፕተር ተወስደዋል። መካለከያ ሰራዊቱ የደረሰበትን ጉዳት ከህዝብ ለመደበቅ አማን ሆስፒታልን በልዩ ሁኔታ ሲያስጠብቅ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል።

የመከላከያው አዛዥ መገደሉንም ምንጮች አክለዋል።

በደረሰው ጉዳት የተበሳጩት ወታደሮች የቡድኑን ታዋቂ ተዋጊ የሆነውን ተካ ጣመን ከገደሉ በሁዋላ አስከሬኑን መንገድ ላይ እየጎተቱ መንገድ ላይ ጥለውታል።

ለሟቹ አድናቆታቸውን ወይም ሀዘናቸውን ሲገልጹ ታይተዋል የተባሉ የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች ተይዘው መታሰራቸውንም ምንጮች ገልጸዋል። ሮዛ ሙራ የተባለች ነዋሪ “ጀግና ሞተ” በማለት በመናገሩዋ ወደ እስር ቤት የተወሰደች ሲሆን፣ ከሁለት ቀን እስር በሁዋላ በማስጠንቀቂያ ተለቃለች። ሌሎች ነዋሪዎች ግን አሁንም በእስር ላይ ናቸው።

ከግጭቱ በሁዋላ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አዝመራውና እና የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሾሎ ከግጭቱ ጀርባ እጃቸው አለበት በሚል ተጠርጥረው በቁም እስር ላይ ናቸው። ወታደሮች ከታጣቂዎች ጀርባ አሉ ያላቸውን ባለስልጣናት ለመያዝ እየተወያዩ ነው።

ባለፉት 3 ቀናት ተጨማሪ ወታደር ወደ አካባቢው የተላከ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች የላኩት ማስጠንቀቂያ ነዋሪዎች እጅ መግባቱንና መነጋጋሪያ መሆኑንም የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።
መንግስት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር በአካባቢው ያሰፈረ ሲሆን፣ ውጥረቱ አሁንም እንዳለ መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

የቴፒ ወጣቶች የመብት ጥያቄዎችን ካነሱ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖአቸዋል። የገዢው ፓርቲ ንብረት የሆነው ሬዲዮ ፋና እስር ቤት ሰብረው እስረኞች እንዲጠፉ ያስደረጉ አምስት ሽፍቶች ተገድለዋል በማለት ዘግቧል።

ተፋላሚዎቹ በበኩላቸው ሁለት አባሎቻቸው፥ እንዲሁም ከሕወሃት በኩል ደግሞ 33 ወታደሮች መመገደላቸውን ይናገራሉ።

%d bloggers like this: