በሕወሃት የአፈና ኃይሎች ተደብድቦ የሞተው ወጣት ሳሙኤል አወቀ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ ተፈጸመ፣ ቀባሪዎቹ ደብረ ማርቆስ እንዳይገቡ ታግደዋል

16 Jun

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

የወጣት ሳሙኤል አወቀ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ ሰኔ 9/2007 ዓ.ም የትግል አጋሮቹ፣ ጓደኞቹና ዘመዶቹ በተገኙበት በጎንቻ ሲሶነሴ ወረዳ ሰቀላ ቀበሌ ግንደወይን አርባይቱ እንሰሳ ቤተ ክርስቲያን ከቀኑ 11፡30 ላይ ተፈፅሟል፣ ነገረ ኢትዮጵያ እንደዘገበው፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ የምስራቅ ጎጃም ዞን ፀሐፊና በ2007 ዓ.ም ምርጫ የፓርቲው ዕጩ ተወዳዳሪ የነበረው ወጣት ሳሙኤል ሰኔ 8/2007 ዓ.ም ምሽት ላይ ወደ ቤቱ እየገባ በነበረበት ወቅት በሁለት ግለሰቦች ከፍተኛ ድብዳባ ከተፈፀመበት በኋላ ሆስፒታል ውስጥ ሕይወቱ ማለፏ ታውቋል፡፡

ወጣት ሳሙኤል ከቀድሞው አንድነት ጀምሮ ሲታገል የቆየ ሲሆን የሰማያዊ ፓርቲ መስራች አባል ነው፡፡ በአካባቢው የሚፈፀሙ በደሎችን ለሚዲያ በማጋለጥ ሲያበርክተው ከነበረው ሚና ባሻገር በፓርቲው በነበረው ጠንካራ እንቅስቃሴ ምክንያት በተደጋጋሚ እስርና ድብደባ ተፈፅሞበታል፡፡

Samuel Awoke

ከመሄዱ በፊት በፌስ ቡክ ገጹ ላይ እዚህ የሚታየውን የመሰናበቻውን ፎተግራፍ የለጠፈው ክፉኛ እያሳደዱት መሆናቸውን በማወቁ ነበር!

ይህ አልበቃ ብሉ፣ ከአንድ ሰዓት በታች በሆነ ጊዜ ውስጥ ዛሬ ነገረ ኢትዮጵያ እንደዘገበው፣ የሳሙኤል አወቀ ስርዓተ ቀብር ላይ ደርሰው ወደ ደብረማርቆስ ሲመለሱ የነበሩት ለቀስተኞች ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ ወደ ደብረማርቆስ እንዳይመለሱ ታግተዋል፡፡

ለቀስተኞቹ በመኪና እየተመለሱ በነበረበት ወቅት ከቢቸና ወደ ደብረማርቆስ 80 ኪሎሜትር አካባቢ የምትገኝ የትመን የተባለች ቦታ ላይ ፖሊሶች ያስቆሟቸው ሲሆን “በዚህ ሰዓት መንቀሳቀስ አትችሉም” በሚል የሾፌሩን መንጃ ፈቃድ ከቀሙ በኋላ ለሚሊሻ አስረክበዋቸው ሄደዋል፡፡

ለቀስተኞቹ የታገቱበት ቦታ ከመኖሪያ አካባቢ የራቀና ጫካ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለቀስተኞቹ አሁንም ድረስ በበርካታ የሚሊሻ አባላት ተከበው ይገኛሉ ብሏል ነገረ ኢትዮጵያ፡፡

በመጨረሻም፡ ሳሙኤል ለደብረማርቆስ ሕዝብ ያሰተላለፈው መልዕክት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፦

    “ውድ የደብረማርቆስ ከተማ ኗሪዎች ፤ ሰማያዊ ፓርቲን የመረጣችሁ ከ25’0000 በላይ መራጮች(ኮረጆውን) እርሱት እና በተጨማሪም በ31 ዩኒቨርስቲ የምትገኙ ከ14,000 በላይ ሰማያዊ ፓርቲን የመረጣችሁ ሌሎች ደጋፊዎች እና የኢሕአዴግ አባላትም የማያፍረው ብአዴን / ኢሕአዴግ ድምፅ መቀማቱ ሳያንስ በ21/08/2007 ዓም አፍነው ደብድበው ከሞት መትረፌ ቆጭቷቸው እሰር ቤት ለመወርወር ያለመከሰስ መብቴን እንኳን ተዳፍረው የሀሰት ክሰ እየፈጠሩ ነው!!!” በስልኬ እደተደወለም ያለፍላጎቴ ደሕንነት እያስገደደኝ ይገኛል!!!!! ተገደልሁም ታሠርሁም ፤ ታፈንኩም ነፃነት አይቀርም እና ለማሰረጃነት የደሕንነቶችን ስም፤ ፎቶግራፍ ፤ እና አድራሻ እንዲሁም በሐሠት ምሰክርነት እና ከሳሽነት የተደራጁ አካላት እና ዋና ተወካዮች የደብረማርቆስ ከተማ 04 ቀበሌ አመራሮች እና ፖሊስ ለታሪክ አሰመዘግባለሁ ማንኛውም የምከፍለው ዋጋ ለሀገሬ እና ለነፃነት ነው ከታሠርሁም ሕሊናዬ አይታሰርም ከገደሉኝም ትግሌን አደራ በተለይ የኔ ትውልድ አደራ !!!!” አገራችን የወያኔ ዘረኞች ብቻ መፈንጫ መሆን የለባትም ትግላችን የነፃነት ጉዟችን ጎርባጣ መድረሻችን ነፃነት ታሪካችን ዘላለማዊ ነው!!!! (ከሳሙኤል አወቀ ዓለም – የሰማያዊ ፓርቲ የደብረ ማርቆስ የሕዝብ ተወካዮች እጩ ተወዳዳሪ)”


 

%d bloggers like this: