የሕወሃት አስተዳደር የጠየቀው የ$11.4 ቢሊዮን የ2008 ፌዴራል በጀት ከሃገሪቱ አቅምና ገቢዋ አንጻር እጅግ ከፍተኛ ነው (ክፍል 2)

7 Jul

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

ክፍል ሁለት

I. የ2008 በጀት ይዘት

የ2008 (2015/16) በጀትን በተመለከተ ቀደም ሲል በክፍል አንድ በቀረበው ጽሁፍ እንዳነሳሁት፣ በ’ፌዴራል መንግሥት’ በጀትነት ለ2008 ዓ.ም. ብር223.4 ቢሊዮን ($11.4 ቢሊዮን) በኢትዮጵያ ስም ተጠይቋል። ለአዲሱ በጀት ትርጉማዊነት፡ የሚጠበቀው የታክስ ገቢ ብር 141,208,500,000 ($6.8 ቢሊዮን) ሲሰበሰብ ሲሆን፣ ከ2007 ክንውን ግምት ጋር ሲነጻጸር 22.2 በመቶ ዕድገት ማሳየት አለበት ይላል ገንዘብ ሚኒስቴር፡፡

በዛሬው ዕለት ዋና የፊስካል ዓመቱን የፌደራል በጀቱን በማጽደቅ ሥራውን የጀመረው አዲሱ ‘የሕዝብ ምክር ቤት’ ቋሚ ኮሚቴዎች ስብሳቢዎች – በከናከኗቸው ጉዳዮች ላይ ለመተንፈስ ይመስላል – “በምክር ቤቱ በሚፈጠሩ የተለያዩ መድረኮች ላይ ህዝቡ በቀጥታ ተሳታፊ ከሆነ በአስፈጻሚውም ሆነ በፈጻሚው አካል ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያስችላል” በሚል አስተያየት የአሠራሩን አንድ ፓርቲ ስብስብ የሚለውን ነቀፌታ ለመቋቋም መጣራችውን አመላክቷል።

ለዚህም ምስክርነት ሲሰጡ፡ በተጨማሪ የሚከተለውን መልዕክት ሲያስተላልፉ ሲሉ ተደምጠዋል፦

  “ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የምርምር ማዕከላትም በፓርላማው ተሳትፎ ከማድረግ ባሻገር በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ምክረ ሃሳቦችን የሚያቀርቡበት አሰራር መፈጠር አለበት” ያሉት ቋሚ ኮሚቴ ስብሳቢ “ቋሚ ኮሚቴው፣ የሚከታተላቸው ተቋማት፣ የመንግስት ፈጻሚና አስፈጻሚ አካላት የመንግሥት በጀት ለተገቢው አላማ እንዲውል ሕዝቡ ከወኪሎቹ ባሻገር በቀጥታ ተሳታፊ እንዲሆን እድል ይፈጥራል። ይህም በአንዳንዶች ዘንድ “ፓርላማው የአንድ ፓርቲ ስብስብ ስለሆነ ውጤታማ አይሆንም የሚለውን ሃሳብ ውድቅ እንዲሆን ያደርገዋል”።

ለእነዚህ ግለሰለብ ‘የሕዝብ ተወካዮች’ ያልታያቸው፡ ወይንም ግድ የሌላቸው፡ ርዕስ መስተዳድሩ መጥቶ ቀደም ብሎ ተዘጋጅቶ የተሠጠውንና የሸመደደውን ዲስኩሩን ካሰማ በኋላ፡ የምክር ቤቱ አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሚል ስም ሬኮርድ ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ፣ ምክር ቤቱ ያላንዳች ማሻሻያና ክርክር ብር 223.4 ቢሊዮን በዛሬው ዕለት ከታክስ ከፋዩ የሚሰበሰብ ለሕወሃት አስተዳደር አጽድቋል።

2008bejut ከላይ ከተጠቀሰው ታክስ ገቢ በተጨማሪ፣ ታክስ ካልሆኑ ምንጮች (የካፒታል ገቢን ጨምሮ) ብር 15,852,300,078 ($767 ሚሊዮን) ጋር በድምሩ ብር 157,060,800,078 (80.2 በመቶ ወይንም $8 ቢሊዮን) ገቢ ይሰበሰባል የሚል ግምታቸውን የገንዘብና ኤኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ ለፓርላማው ሰኔ 2/2007 ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ከሃገር ውስጥ የሃገቷን ዓመታዊ ዕድገት (GDP) 1.8 ከመቶ የሚሆን ገንዘብ በብድር ይወሰዳል፤ እንዲሁም ከውጭ ብድርና ዕርዳታ ደግሞ ብር 39.0 ቢሊዮን ይገኛል ተብሎ ቢተመንም፣ ከየትም ገንዘብ ተገኝቶ ሊሽፈን የማይቻለው ቀዳዳ ብር 27.6 ቢሊዮን ስፋትና ጥልቀት፡ ወይንም የበጀት ጉድለት (budget gap) አግጦ ይታያል፡፡

የዚህ በጀት ስሌት አዘጋጆቹ እንደሚሉት፣ በሃቅ ለፓርላማውና ለኢትዮጵያ ዝሕብ እየተናገሩ ነው ብለን ከተቀበልን (የማይታሰበውና የማይሆነው!)፣ እንዲሁም ገንዘቡ ከተለያዩ ምንጮች ለመገኘት ከቻለ፡ በአራት ዋና ዋና ፕሮግራሞችና አስተዳደራዊ ድጋፍ እንደሚከተለው እንደሚከፋፈል ነው የገንዘብ ሚኒስትሩ የገለጹት፦

  ሀ.  ለካፒታል ወጭ ብር 84.3 ቢሊዮን (ከበጀት ድርሻ 37.7%)

  ለ.  ለዘላቂ ልማት ግቦች ብር 12.0 ቢሊዮን (ከበጀት ድርሻ 5.4%)

  ሐ.  ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት በጀት ዴጋፍ ብር 76.8 ቢሊዮን (ከበጀት ድርሻ 34.4%)

  መ. ለመደበኛ የመንግሥት ወጭ ብር 50.3 ቢሊዮን (ከበጀት ድርሻ 22.5%)።

የዚህን የ$11.4 ቢሊዮን በጀት 37.7 ከመቶ የሚይዘው ገንዘብ፥ ለካፒታል በጀት የሚውል ሲሆን፡ የሚከናወኑት የልማት እንቅስቃሴዎችም የመንገድ ሥራ፣ ትምህርት፣ የግብርና፣ የውሃ፣ የጤና እና የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራሞች እንደሆኑ ተጠቁሟል። በተጨማሪም፣ ከዚሁ በጀት ውስጥ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጦችን ለማረጋገጥ “ከፍተኛ ትርጉም ላላቸው የማኑፋክቸሪንግ፣ ኤክስፖርትና የከተማ ልማት ሥራዎች ከፍያ” ገንዘብ ተይዟል ይላሉ፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ዓላማዎችና ግቦች በትክክልና በጥንቃቄ ሥራ ላይ ከዋሉ፡ እጅግ ጠቃሚ ስለሆኑ፡ በሃሣብ ደረጃ ምንም እንከን የላቸውም። ነገር ግን የጥሩ በጀት መለኪያዎችን ያሟላሉ ወይ? እነዚህም፡ የፕሮግራም በጀቱ ዓላማና አፈጻጸሙ የሃገሪቱ ፖለቲካ ሁሉን አቀፍነት፥ የኅብረተስቡ ተጠቃሚነት፥ የተመሠረተውም በግለስቡ ዜጋ ደህንነት (wellbeing)፡ በዜጎች እኩልነትና በአስፈጻሚው ወገን ለገንዘቡም ሆነ ለፕሮግራሙ ተጠያቂነት ላይ መመሥረቱ ነው። በተረፈ ችግር ሲያጋጥም – ሁልጊዜም የትም ሃገር ያጋጥማል – በጥሩ ሕግ ተፈጻሚነት ላይ የተመሠረተ የፕሮግራም በጀት አፈጻጸም በተግባር እየታየ ሊስተካከልና ሊሻሻል በቻለ ነበር፥ እንደኛ ሃገር መሰተዳድራዊ መመሪያ ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትና ሃስተኝ ፕሮፓጋንዳ የሕይወት እስትንፋሱ መሠረት ባይሆን ኖሮ!

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ ሱፊያን አህመድ (ምንጭ፡ ሪፖርተር)

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ ሱፊያን አህመድ (ምንጭ፡ ሪፖርተር)

የገንዘብና ልማት ሚኒስትሩ ሱፍያን አህመድ የአስተዳደሩን የ2008 ዓ.ም. አዲስ በጀት ጥየቃ (proposed budget) በሕገ መንግግሥት አንቀጽ 77 (3) መሠረት ለፓርላማ ሲያቀርቡ ባደረጉት ንግግር፣ አሁን በሚጠናቀቀው በጅት ጭምር በመጀመሪያው አምስቱ ዓመት ዕቅድ አማካይነት የተገኘውን ውጤት ከምናውቀው ውጭ እንዲህ ሱሉ ነበር በመኩራራት ያሠመሩበት፦

  “በአጠቃላይ ተግባራዊ ለማድረግ የተያዙ ዋና ዋና የኢኮኖሚና የልማት ግቦች አብዛኞቹን ማሳካት የተቻለበትና በሀገሪቱ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈቱ ታላላቅ የልማት ውጤቶች የተገኙበት እንደሆነ የዕቅዱ የእስከ አሁኑ ትግበራ ግምገማ አመልክቷል”። በተጨማሪም፡ ሚኒስትሩ “በአጠቃላይ በአራቱ ዓመታት የተመዘገበው ዕድገት በዕቅድ በመሠረታዊ አማራጭ የተያዘውን የኢኮኖሚ ግብ ያሳካ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል” ይሉናል፡፡

ፀጥታ! ዐባይ ፀሐዬ አስቸኳይ ሥራ ላይ – የሕወሃት/ኢሕአዴግ ሥራ  አስፈጻሚ ኮሚቴ ዝግ ዝበስባ ላይ! (Credit:https://www.facebook.com/photo.php?fbid=679080905551746&set=p.679080905551746&type=1)

ፀጥታ! ዐባይ ፀሐዬ አስቸኳይ ሥራ ላይ – የሕወሃት/ኢሕአዴግ ሥራ
አስፈጻሚ ኮሚቴ ዝግ ዝበስባ! (Credit:https://www.facebook.com/photo.php?fbid=679080905551746&set=p.679080905551746&type=1)

በቅርቡ እንዳየነው ከሆነ፡ በ2008 ከፍተኛ ገንዘብ ስለተጠየቀበት በጀት ገንዘብ ምንም እንኳ በአንድ በኩል የገንዘብ ሚኒስትሩ በፓርላማ ከላይ በተጠቀስው ንግግራቸው አንድ የድል መግለጫ ዐይነት ዲስኩር ቢያሰሙንም፡ እንዲሁም፥ በሌላ በኩል ደግሞ በሃሰተኝነታቸው፡ በዘረኝነታቸው፡ መግረፍንና መግደልን ለሁሉም ችግር መፍትሄ አድርጎ በመውሰድ የሚታወቁት የመስተዳደሩ ዋና አማካሪ ዐባይ ጸሐዬ፣ ታማኒ ይመስል፥ አዲሱ በጀት የመጀመሪያውን መሠረት ሰለሚጥልለት GTP II፥ “መጭው አምስት ዓመታት ፈጣን፣ ዘላቂ፣ መሠረተ-ሠፊና ፍትሃዊ የገቢ ክፍፍልን ያረጋገጠ ዕድገት” የሚታይበት ዘመን ይሆናል ብለው እንደተለመደው መደስኮራቸው፡ መጭው ካለፈው እንደማይሻል ምልክት ሠጥተውናል። በሌላ አባባል፡ ካለፈው ባለመማር፥ አዲሱን የአምስት ዓመታት ፕላን ካለፈው በከፋ ሁኔታ የካድሬዎች ዕድር ሲያደርጉትም ተመልክተናል!

ለምን ይሆን ሕወሃት/ኢሕአዴግ ወደ ስንኮፉ የተመለሰው? ካለፈው መጋቢት ወዲህ መላውን የሕወሃትን አስተዳደር እንደመብረቅ የመታውና አሁን ሁለቱም ባለሥልጣኖች አፈቀላጤ ሆነው የቀረቡበት ምክንያት፡ በዓለም ዙሪያ ክብደት በሚሠጣቸው ተቋሞችና ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ እየቀረቡ ያሉት ትንተናዎችና ዳታዎች፣ አሁንም በኢትዮጵያ ድህነት የተስፋፋ መሆኑን በማጋለጣችው ነው። በተጨማሪም፥ የዚህ ጽሁፍ የመጀመሪያ ክፍል አንድ መንደርደሪያ ያደረግሁት የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) የ15 ዓመቱን የተባበሩ መንግሥታት የልማት ግቦች (MDGs) አፈጻጸም ግምገማ በኢትዮጵያ ላይ አካሂዶ፡ ጥቆማውም፡ የሃገሪቱ ተስፋዋና ጥረቷ ከአጀማመሯ ድህነትን አስወግዶ ጠንካራ ኤኮኖሚ መመሥረት ቢሆንም፡ አሁን የሚታየው ጥቂቶች የከበሩባት ሃገር መሆኗ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዕድገቷም አብዛኛውን ኢትዮዮጵያውያንን አግላይ መሆኑን (non-inclusive growth) መጠቆሙ አሸማቋቸዋል – የውጭ ዕርዳታን ይጎዳልና።

ስለሆነም፥ የ2008 በጀትንትም ሆነ የአምስቱን ዓመት የልማትና ዕድገት ዕቅድ ራሱ በአንድ ጊዜ ለዚህ መልስ የሚሠጡ መሣሪያ አድርገው መጠቀማቸው፣ ይህ ግዙፍ በጀት – ዜጎች መሠረታዊ መብታቸውን የሚያሰክብሩባቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (civil society organizations) በጸረ-ሽብር ስም በሕግ በተደመሰሱባቸው ሃገር – ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት በጀት ሕዝባዊ ባለቤትነት (stakeholders) እንደሌሉት አረጋጋጭ ነው!ይህ ሁኔታ ከበረሃ ተመላሹን ሕወሃትን ቢያንስ ቢያንስ በርዕዮተ ዓለም ደረጃ ገላጭ እንዳይሆን መከላከል ከመፈለግ የመነጨና ለዚያ መልስ ለመስጠት የተደረገ ካባድ መሣሪያ ተኩስ ነው!

ለማንኛውም አሁን በሃገሪቷ በሠፈነው የዘረኞች ፖለቲካ፣ ለሕግ የበላይነትና ለሰው ልጆች እኩልነት ለማመን ጠባብ ዘረኝነቱ በሚያስቸግረው የሕወሃት አሰተዳደር አማካይነት ሁሉን አቀፍ ዕድገትን እንደ መብት የሚመለከት ልማት፥ ፍትህንና እኩልነትን ለማምጣት ነው የምንሠራው የሚለው አባባል ሕዝባችን ከዘንዶ ማርና ወተት እንዲጠብቅ ከማጓጓት አይለይም!

ስማቸውን ከላይ የጠቀስኩት ሁለቱ ባለሥልጣኖች ከሚሉትና በዚህ በጀት ዝግጅት፣ አቀራረብና ገለጻ መካከል የምትታየው ድል አድራጊዋ ኢትዮጵያ ሳትሆን፡ በችግሮች የተተበተበች ሃገር ናት። ለእኔ ግልጽ ሆኖ የሚታየኝ – አሁንም የገንዘብ ሚኒስትሩ እንዳሉት – የዕቅዱና በጀቱ (program budget) ፍጹም ጋብቻ ሳይሆን፣ አለመጣጣማቸው ነው። ለዚህ ነው በዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ በተወሰኑ ፕሮግራሞችና በጀቶች፥ እንዲሁም ዝግጅቶችና አፈጻጸሞች ማስተባበር ኃላፊነቶች በማገልገል ካገኘሁት ልምድ በመነሳት፥ ይህ ለምን እንደ ተሰማኝና የኢትዮጵያ በጀት ችግሮች – አዲሱን በጅት ጨምሮ – ምን እንደሆኑ ለመጻፍ የመረጥኩት (በተከታታይ ጽሁፎች)።
 

II. ይህን ያህል ከፍተኛ የታክስ ገቢ ሙሉ ለሙሉ መሰብሰብ ይቻል ይሆን?

በጀቱ የጠየቀው በጣም ከፍተኛ ገንዘብ ከመሆኑ አንጻርና የሃገሪቱ ኤኮኖሚ በመቀዛቀዙ፡ እንዲሁም በአስተዳደሩ ውስጥ በሠፈነው ግድ የለሽነትና የመንግሥታዊው መዋቅር ፖሊሲና ሥራ አፈጻጸም ደካማነት – ካለፈው ልምድ በመነሳት – ለጥያቄው የሚሠጠው አጠር ያለ መልስ ጥርጥር ላይ የሚያሠምር ነው።

የ2007 ገቢን በተመለከተ፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በገጹ ላይ እንዳሠፈረው ከሆነ፡-

  ♪♪♪ ሀገራችን ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመቆም እያደረገች ባለችው በዚህ ከፍተኛ እርብርብ ወቅት ባለስልጣኑ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ሲሆን♪♪♪

  ♪♪♪ በ2007 በጀት አመት በአጠቃላይ 134.2 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ [አቅዶ] በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለመሰብሰብ ከታቀደው 32.5 ቢሊየን ብር ላይ 32.7 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 100.64 በመቶ ያሳካ መሆኑንና አፈፃፀሙ ከ2006 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 29 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጿል፡፡ ♪♪♪

ሆኖም፣ ይህ የአንድ ዓመት ሩብ ሥዕል፥ ከባለሥልጣኑ ያለፉት ዓመታት ልምድና ከዋናው ኦዲተር ጽሕፈት ቤት የተገኙት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፥ መሥሪያ ቤቱ ዕቅድ አውጥቶ እንዳሰበው የታክስ ክፍያውን ሙሉ በሙሉ የሰበሰበት ጊዜ በሬኮርዱ ላይ አይታይም።

የሚከተለው ከሪፖርተር የተገኘ የፓርላማው ኮሚቴ ሊቀመንበርና የገቢዎችና ግምሩክ ሥራ አስኪያጅ ልውውጥ ይህንን ያጠናክራል።

አቶ ተሾመ እሸቱና አቶ በከር ሻሌ (ፎቶ፡ ሪፖርተር)

አቶ ተሾመ እሸቱና አቶ በከር ሻሌ (ፎቶ፡ ሪፖርተር)

ይህንንም በተመለከተ፡ በፓርላማው የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ የተደረገውን ውይይት ዝርዝር ባናውቀውም፡ በኮሚቴው ስብሳቢ አቶ ተሾመ እሸቱና በጉምሩክ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ መካከል ስለነበረው መፋጠጥ ሁኔታውን ገሃድ ያደርገዋል። የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌ የተቋማቸውን የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሰኔ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ካቀረቡ በኋላ በአንድ በኩል “የፌዴራል ዋና ኦዲተር በተቋማችን ላይ የሚያደርገውን ኦዲት ተከትሎ የሚላክልን የኦዲት ግኝት ለሥራ አፈጻጸማችን ትልቅ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎልናል፤” ይላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የፓርላማ ኮሚቴው ሊቀመንበር የባለሥልጣኑ የፓርላማ ሪፖርት ትክክል ሆኖ፣ታዲያ ለምን “ኦዲተሩ የሠጧችሁን ምክርና ጥቆማ ተግባራዊ ማድረጋችሁን በገሃድ የሚያሳይ መረጃ ለምን እንዳላካተቱ” በግልጽ ጠይቀዋል።

ከዕሰጥ አገባው በኋላ ነው፡ የባለሥልጣኑ ኃላፊ፡ ችግሩን “በፖሊሲ አስተዳደር ቦታ ላይ ተቀምጦ ማየትን ይጠይቃል፡፡ ግብር የተጣለበት ከፋይ ቅሬታ አቅርቦ ሲከራከር፣ የተጣለው ግብር ለረዥም ጊዜ ሳይሰበሰብ ይቀራል፡፡ ይህ በኦዲት ቋንቋ ያልተሰበሰ ሒሳብ ነው…ሌላው [ደግሞ] አምራች ኩባንያዎችን ለመደገፍ የታክስ ክፍያ ጊዜያቸውን እያሰፋንላቸው እንሄዳለን፡፡ ይኼንን በማድረጋችንም ባለሀብቶችን እየደገፍን የመንግሥትን ግብር እያስከፈልን ነው” ሲሉ ሰለ ግብር አሰባሰቡ ሁኔታ ተጣራሽና የማይታረቁ ሃሣቦችን አሰምተዋል፡፡

የፓርላማው ተወካይ ደግሞ “ምናልባት የወሰድነውን ዕርምጃ ብንዘረዝር ከፓርላማው ክርክር ይገጥመናል ወይም ሪፖርቱ እንዳይረዝም ብዬ ነው የሚል ምላሽ ይቀርብ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከፋኝ ተብሎ ሕግ አይጣስም፡፡ የከፋን ቀን ሕግ ጥሰን መሄድ አንችልም” በማለት መልሰውላቸዋል – ሪፖርተር እንደዘገበው

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በዜጎችና በታክስ ባለሥልጣኑ መካከል ያለው መካሰስና መራገጥ ሲትታሰብ፡ እነዚህ ሁሉ የፍርድ ቤት ውዝግቦች እያሉ፡ የታክስ ገቢዎቹን እንደታሰበው መሰብሰብ መቻሉን ማውሳት፡ እንደቤት ማፈረስ ወይንም መሬቶችን መዝረፍ ሁሉ፡ ለነገ ግድ የለንም ዛሬ ሁሉን መዳጥና መጨፍለቅ እንችላለን የማለት ያህል ነው!

በሌላ በኩል ደግሞ፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ ሱፊያን አህመድ ሰኔ 2/2007 አዲሱን በጀት ለመጠየቅ (Budget Proposal) ለፓርላማ ባድረጉት ንግግር አዳማጩን ለማረጋጋት ይመስላል የሚከተለውን ማለታቸው ይታወሳል፡-

  በአምስቱ ዓመት የልማት ዕቅዱ “የመጀመሪያ አራት ትግበራ ዓመታት የሃገር ውስጥ ገቢ በየዓመቱ በአማካይ በ29 በመቶ እያደገ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተለይም የታክስ አሰባሰቡ 33 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በ2006 በጀት ዓመት የተሰበሰበው ሃገራዊ የመንግሥት ገቢና ዕርዳታ መጠን ብር 158 ቢሊዮን የነበረ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ በበጀት ከታወጀው ዕቅድ አፈጻጸሙ 96.7 በመቶ ነበር፡፡ በ2006 የተሰበሰበው የታክስ ገቢ በአሃዝ ደረጃ በ2002 ከተሰበሰበው አንጻር ከሁለት ዕጥፍ በላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡”

ለነገሩ በ2006 ዓ.ም. የተስበሰበው ገንዘብ መጠን፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ እንዳሉት 96.7 ከመቶ ሳይሆን – የገቢዎችና ግምሩክ ባለሥልጣን የሰበሰበውን የታክስ ገንዘብ ልክ የሚያውቅ ከሆነ – 91.4 ከመቶ ነበር። ምናልባትም፡ የዘገየ የታክስ ክፍያ በኋላ በመምጣቱ አብሮ ተደማምሮም ከሆነ፡ ገቢነቱ የሚመዘገበው በ2006 ዓ.ም. እንዳለ ሆኖ፣ ገንዘቡ ግን ለተባለው የበጀት ዓመት በወቅቱ መምጣቱ አስፈላጊነትና የበጀቱን አዘገጃጀት ስሌት ስናስታውስ፡ ከአጠቃቀምና በጀት አፈጻጸም አንጻር፡ ያ ገንዘብ እንደሌለ ነው መታየት ያለበት!

የዓለም ገንዝብ ድርጅት (IMF) ጥቅምት 2014 ላይ በጽሁፍ ለመንግሥት እንዳሳወቀው፡ በገቢ ያልተሸፈነው በጀት ስፋት (tax gap) በአንጻራዊነትና ከገቢ አንጻር ሲታይ እጅግ ዝቅተኛ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት፡ ተሸካሚው አናሳው የግል ሴከተሩ በመሆኑ (ባንኮች፡ የግል የንግድና የምርት ሴክተሩ)፡ ለመንግሥት ታክስ ከፋዩ ሕዝብ 12.5 ከመቶ ብቻ ሆኖ፡ ከኬንያ 23.0 ከመቶ፡ ታንዛንያ 17.0 ጋር ሲወዳደር፡ የኢትዮጵያ የታክስ መሠረት ጠባብ መሆኑን ያስገነዝበናል።
 

III. ሕጋዊ አስተዳደር ከበጀት ጋር ያለው ተዛምዶ

የሕገ መንግግሥቱን አንቀጽ 77 (3) ተፈጻሚ ለማድረግ – ማለትም የ2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፊስካል ዓመት ከመጀመሩ በፊት የፌዴራል መንግሥቱ በጀት በፓርላማ በጥሩ ጊዜ ተፈቅዶ ሥራ ላይ እንዲውል ለማስቻል – በሕወሃት የተሠየመው ርዕስ መሰተዳድር ማክሰኞ ሰኔ 30/2007በፓርላማ ተገኝቶ በቀረበው አዲስ ዓመታዊ የበጀት ጥያቄ ላይ ‘በሕዝብ ተወካዮች’ ለሚነሱ ጥያቄዎች ‘ማብራሪያ’ ሠጥቷል። ምክር ቤቱም እንደተለመደው ያንን አዳምጦ የተጠየቀውን በጀት በአንድ ድምጽ ይሁንታ ሠጥቶታል።

ገዥው ፓርቲ በጀት ጠያቂ መንግሥት፥ በፓርላማም በጀት ፈቃጅ እርሱ በመሆኑ፥ ያላንዳች ውጣ ውረድ፥ መሻሻሎች፡ አዳዲስ ሃሣቦች ስይካተቱና የፕሮግራም ለውጥ ወይንም ቅናሽ ሳይደረግ ጸድቋል።

የኢትዮጵያ የበጀት አቀራረብ፡ በተለይ ከፓርላማ ጋር የሚደረገው አስመሳይ ውይይት፡ በሕግ የሚተዳደሩ ሃገሮች ከሚያደርጉት ልምድ የተቀዳ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስኪሰለቸው ሰምቶታል። ችግሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥያቄና መልሱ በቅርጽ ብቻ እንዲወሰን በመደረጉ፥ ዋናው ቁም ነገር የኅብረተሰቡ አስተያየትና ፍላጎት ፌዝ እንደሆነ ቀርቷል፡፡ ይህንንም ከሚያሰኙ ምክንያቶች መካከል ዋናው ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ በላይነትና ተጠያቂነት አለመኖሩ ስለሆነ፣ ይህም የዛሬው አሠራር ለሃገራችን ዕድገትና በሕዝባችን እኩልነት ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ እየታወቀ፡ በዚህ ጽህፍ በተጨባጭ እንደምናሳየው፡ አሠራሩን ሕወሃት ለፖለቲካ ማታለያና ለገንዝብ ዘረፋ ሲጠቀም የኖረበት ዘዴ ነው፡፡

ከሁሉም አሳዛኙና አሳፋሪው የብቃት ጉድለት ማሟያው ነው። እንደተለመደው፡ ርዕሰ መሰተዳድሩ ፓርላማ ሲደርስ የተደጎሰ ጥያቄና መልሶችን በጽሁፍ ሽክፎ ነው የመጣው። የፓርላማ አባላት ከአንድ ሣምንት በፊት ጥያቄዎቻቸውን በጽሁፍ ለርዕሰ መስተዳድሩ ጽሕፈት ቤት እንዲልኩ፡ ላለፉት አያሌ ዓመታት ሕወሃት በአስገዳጅ ውስጠ ደንብ ተግባራዊ አስደርጎ እንደ ቅጥፈት መሣሪያው ሲጠቀምበት የኖረው ዛሬም ተግባራዊ ሆኖአል።

ርዕስ መሰተዳድሩ የመጣው ይህንን የተዘጋጀለትን የጥያቄዎች መልሶች ይዞ ነበር። እርሱም ሁሉን አዋቂ፡ በሕዝቡ ስም ሁሉንም በቅርብ የሚከታተል፡ ብልህና ምሁራዊ ለመምሰል መልሶቹን ሸምድዶ ቲአትረኛ ይሆናል። ይህም እውነተኛ መንግሥታዊ አሠራር ከመሆን ይልቅ፡ በእርግጥም የኢትዮጵያን ፓርላማ በሁለንተናዊ መልኩ፥ የሕዝብን ፍላጎትና ጥቅም ለራሳቸው የግል ጥቅሞች አሳልፈው የሸጡ ሸምዳዳ ተዋንያን የተሰበሰቡት የቲአትር መድረክ አድርጎታል።

ምን አለበት አንድ ባለሥልጣን አሰፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ፡ መልሱን በማያስታውሰው ወይንም በማያውቀው ጉዳይ ላይ – በዴሞክራቲክ ሃገሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንደሚደረገው ሁሉ – የዚህ መልስ ለጊዜው በቅርብ የለም። በሚቀጥሉት ቀናት በዝርዝና በጽሁፍ ለአባላቱ እንዲሠራጭ ይላካል ቢባል – ለዚያውም በጀት በመፍቀድና ባለመፍቀድ መብት ለሌለው ቤት? ይህ በአሠራር ደረጃ ግልጽነትን ሳይፈነጥቅ፡ ሕዝቡንስ መልካም ምሣሌ ከየት አግኘው ነው የሚባለው?

እንዲያውም፣ በሌለው የሕግና የፋይናንስ ዕውቀቱ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው የሕውሃት አስተዳደር፡ በጀቱን እንደፈለገው አዘዋውሮ ሊጠቀምበት ይችላል በማለት ከምርጫው ጥቂት ቀደም ብሎ በሚድያ የሰጠው መገለጫ ምን ያህል አስተዳደሩ ሕገ ወጥ መሆኑን በተጨባጭ አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ጫና ከ$30 ቢሊዮን በላይ መሆኑ ይነገራል። በሌላ በኩል ደግሞ፡ በIMF ስሌት፣ የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ 28.9 ከመቶ ከሃገር ውስጥ ገቢ (GDP) – መስከረም 2014) ነው። ስሌቱ እንደሚያሳየው፡ እጅግ ከፍተኛ ድርሻ ይገሸልጣል። የሃገር ውስጥ የመንግሥት ዕዳ ደግሞ በያዝነው ዓመት 23.4 ከመቶ ከሃገር ውስጥ ገቢ (GDP) እንደሆነ በIMF ተመልክቷል።

የኔ አመለካከት ፕሮግራም ተጠናቆ ከጽደቀ በኋላ፡ በጀት ዝግጅቱና አፈጻጸሙ ከፕሮግራም ጋር ባለው ትሥሥር ምክንያት እጅግ አድካሚ ቢሆንም፡ ውጤቱ ሲሰምር አሰገራሚና እንደ ቆንጆ ሙዚቃ አርኪ የሣይንስና አርት ቅንጅት ስሜት ይፈጥራል። ትሥሥሩና ፈትልነቱ (sophistication) ትርጉም አዘል ከመሆኑ የተነሳ፡ አጠቃላይ ጥንካሬው በተለያየ መልኩ ይገለጻል፤ እንዲሁም አንድ ቦታ ላይ የሚከሰት ድክመት/ስህተት፡ ሊሎችም ውስጥ ክፍተት ያሳያል። የዚህን ‘ሙዚቃዊ’ ድርሰት ጉልህነት ለማየት የበጀቱን ዓላማ፡ የሚፈለጉትን ግቦች፡ ሳይንሱንና ‘ድርሰቱን’ – ከተፈለገም ሎጂኩን – አትኩሮ ማየት ያሻል።

አንድ መንግሥታዊ በጀት፡ አንድ ኅብረተስብ በወኪሎቹ አማካይነት ሊያከናውን የፈለጋቸው ግቦችና ዓላማዎች በገንዝብ የሚተመኑበት የመርሃ ግብር መተግበሪያና መግለጫው ነው።

ስለሆነም፡ መላውን ኅብረተሰብ አቀፍ ፖለቲካ፥ ሕጋዊነትን፣ ተገቢው መንግሥታዊ መዋቅር፣ ዓላማውንና ግቡን የሚያውቅ አስተዳደር ባለበት ሥፍራ፥ የመንግሥት በጀት በመንግሥት እጅ ትልቅ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ኑሮንና የሕዝብን አስተሳሰብ መቀየሪያ መሣሪያ ነው። የሃገርን ሃብት ዕቅዳዊና ስልታዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም ብሔራዊ ሁለንተናዊ አስተዳደርን ፍሬያማ ለማድረግ እንደሚረዳ ከሃገሮች የዕድገትና ከበጀት የ300 ዓመት ታሪክ መገንዘብ ይቻላል።

በጀት የሕዝብንና የሃገር ደህነንትን ለመጠበቅ ያስችላል። የሃገርን ሃብት ዕቅዳዊና ስልታዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም፣ በጀት ብሔራዊ ደህነነትንና ሁለንተናዊ አስተዳደርን ፍሬያማ ለማድረግ ይጠቅማል። ይህም የኅብረተስብ ዕድገት በየጊዜውና በየደረጃው እየዳበረ እንዲሄድ ለማድረግ ምቹ ብሔራዊ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ግለስቦች፡ ማኅበራትና ድርጅቶች በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኑሮ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በገሃድም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳታፊ (derivative incentives and benefits) እንዲሆኑ መንግሥታዊ በጀት ይረዳል። በልዩ ትኩረቱ፡ እንደኛ ዐይነት ሃገር ውስጥ አንዳንድ ታላላቅ የኅብረተስብ ችግሮችን ለመቀነስ ወይንም ለመፍታት ይረዳል – ምንም እንኳ በጀት በውስኑነቱ ምክንያት፡ ሚናው መፍትሄ ለኳሽ (catalytic) ብቻ ቢሆንም።

በሌላ አባባል፣ ለሕግ ተጠያቂነትና ከተጽዕኖ ነጻ የሆነ የሕዝብ ተሳትፎ ባለበት መንግሥታዊ አስተዳደር፣ በጀት ሃገር ለመገንባት ሁኔታ ይፈጥራል። የሕዝብ ኑሮና ሃገር እንዲሻሻል፣ ዕውቀት በማስፋፋቱ ትኩረት የሚሠጠው መሣሪያ ነው። አንድ ሃገር ሰለወደፊቱ ጠንካራ፡ ብሩህና ምቹ ተስፋ እንዲኖራት በጀት ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ተቀርጸው ተግባራዊ ይደረጉበታል። አንድ ሃገር ከሌሎች ጋር ተወዳድራ በብቃት የራሷን ቦታ እንድትይዝ፡ ተከታዩ ትውልድም የተሻለች ሃገር ወራሽ እንዲሆን መንግሥታዊ በጀት በተለያዩ መስኮች ወጣቱ ትውልድ በዕውቀትና ብስለት ዳብሮ ለዚህ እንዲዘጋጅ ለማድረግ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ መነቃቃትንና ብቃትን ይፈጥራል።

በተመሳሳይ መንገድ፡ መንግሥታዊ በጀት የሕዝብን ኑሮ ወደ ተሻለ ደረጃ ለመለውጥ የማስቻሉን ያህል፡ ለቡድን ጥቅሞች ተማራኪ መሣሪያ በሚሆንበት ወቅትና ሥፍራ – ስሙ መንግሥታዊ በጀት ቢሆንም – የሃገርን ደህንነት ማፍረሻ፥ የሕዝብን ነጻነት ማውደሚያ መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ጠቃሚ ነው።

የሕዝብ ድምጽ በማይሰማበት፡ አንድ ፓርቲ ለ25 ዓመት ሃገሪቱን በብቸኝነት በሚያሰተዳድርበት በራሳቸው ፈቃድ የተደራጁ መንግሥታዊ ያልሆኑ ሕዝባዊ ድርጆትች (stakeholders) በሌሉበት ሃገር፡ አባዛኛው የኢትዮጵያ በጀት ምን ዐይነት ተግባር ላይ እንደሚውል ገና ግልጽ የሆነና የሚያስተማምን ሥዕል የለም።

ምንም እንኳ፡ ባለፈው ምርጫ መብታቸውን ተገፈው – ፖሊስ የፍርድ ቤትን ውሳኔዎች የሚሽርባት ኢትዮጵያ ውስጥ – ያለአግባብ እስካሁን በእሥርና በድበደባ የሚሠቃዩት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚፈጸምባቸው ግፍ ጥግ የነካ ሆኖ ሳለ፡ የሕዝብ ግጭት በስፋት አለመነሳቱ ብቻ፡ ኢትዮጵያ ነገዋ ሰላም ነው የሚለው ግምት ተላላነት መሆኑም፡ ምናልባት ይህ የብዙዎቹን ላብ የሚያቋትተው በጀትም፡ ነገር ምስክርነት ይሰጥ ይሆናል!

አ! ሳልረሳው፥ ጥቂት ደቂቃዎች ይህንን ጽሁፍ ለአንባብያን ከመልቀቄ በፊት የሚከተለውን ፋና ላይ አነበብኩ፦

  አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2007 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሁለኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ዘመን ለስራ እድል ፈጠራ 21 ቢልዮን ብር መመደቡን የፌደራል ጥቃቀንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ…በሁለተኛው የእቅድ ዘመን በተለይ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶች የእድሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ገልጸዋል…የተመደበው በጀት አሁን በከተሞች የሚታየውን የ16 ነጥብ 5 በመቶ የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ ያስችላል።”

 

እኔም ለዜናው የነበረኝ መልስ ይኸው ነበር…

@EthiObservatory ‏@EthiObservatory በለው! ሕወሃት አዲሱን የ$11.4 ቢሊዮን ፌዴራል በጀት ካሁኑ መቀንጠብ ጀመረ! http://www.fanabc.com/index.php/news/item/8822…
 

ይቀጥላል…
 

%d bloggers like this: