ለረዥም ጊዜ ግጭትንና ጦርነትን ሲመኝ የኖረው የሕወሃት አስተዳደር ሊያገኘው ይሆን? በኤታ ማዦሩ በኩል “ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ” በአስቸኳይ መሣሪያ ግዥ ያስፈልገኛል አለ

9 Jul

በከፍያለው ገብረመድኅን – Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

በእንግሊዝኛ ቋንቋ አንድ አሰገራሚ ተረታዊና ምክር አዘል አባባል አለ። ለኔ እንደገባኝ በአማርኛ ሳስቀምጠው፡ ስለምትመኘው ነገር ጥንቃቄ አድርግ ይላል። በእንግሊዝኛው – “Be careful what you wish for.” ይላል። የሕወሃት ባለሥልጣኖች ይህንን አባባል ያውቁት አንደሆን አላውቅም። ከአያያዛቸው ሳየው ግን፡ ባለፉት 24 ዓመታት ካሳዩን ባህሪያቸው የሚያውቁት አይመስልም!

የቋንቋ ባለሙያዎች ይህ አባባል (adage) ሥረ መሠረቱ ከየትና እንዴት እንደተጀመረ እስካሁን እርግጠኛ ባይሆኑም፡ የRandom bits አዘጋጅ፣ James Love፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ አባባሉንና ምክንያቱን ጀርመናዊው ፖለቲከኛና ፀሐፊ Johann Wolfgang von Goethe (1749-1832) እንደሰጠን ጽፈዋል።

Goetheም ያለው፦

“Beware of what you wish for in youth, because you will get it in middle life.”

በ1944 ዓ.ም. ይህ በFleming MacLiesh ተሻሽሎ፣ የለም Goethe ያለው – “Beware of what you wish for in youth, lest you achieve it in middle age” ነው ተባለ። ሲያብራሩትም፡-

And you agree, and go on still desperately wanting all the things you want now in your youth. Learn the hard way ማለት ነው ይላሉ።

ይህንን አባባል ዛሬ ጭንቅላቴ ውስጥ ያመጣው፡ ኢሣት ምሽት ዜና ላይ “ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የጦር መሣሪያ ሊገዛ ነው” የሚል ዜና በመስማቴ ነው።

አንዱ ያስገረመኝ ነገር፡ ለፎርማሊቲ ያህል፣ ሕውሃት ራሱ በጀት ጠያቂ መንግሥት፣ እንዲሁም በፓርላማም ራሱ በጀት ፈቃጅና አጽዳቂ በሆነባት ሃገር፡ ማክሰኞ ሐምሌ 8/2015 ፓርላማው ለሕወሃት አሰተዳደር ለ2008 የብር 223.4 ቢሊዮን በጀት በፈቀደበት ማግሥት ዜናው መምጣቱ ነው። መንግሥት ነኝ ባዪም፡ ባለሥልጣኖቹም ስለፕሮግራም በጀት ያላቸው ጥምዝምዝና ሕግን መከተል የሚጠየፍ አስተሳሰባቸው ስለሚያናድደኝ፡ ለምን ካለኝ ዕውቅትና የሥራ ልምድም፣ ሰለበጀት ምንነትና አፈጻጸም አስተያየቴን አልጽፍም በማለት አርብ ሐምሌ 3/2015 “የገንዘብ ሚኒስትሩ የዓመቱ ባለ ልማት ያሉት የ2007 በጀት ከፍተኛ ገንዘብ ለተጠየቀለት 2008 በጀት ጥሩ መሰናዶ መሆኑ አጠራጣሪ ነው (ክፍል 1)” በሚል ርዕስ የመጀመሪያውን ለአንባብያን አቀርብኩ። ባገኘሁት ያንባብያን ብዛት በጣም ትደስቻለሁ።

አከታትዬም ሐምሌ 7/2015፡ አሁን በኢትዮጵያ ስም ሕወሃት የጠየቀው በጅት ብዛት፡ ለድርጅታቸው ዘረፋ ስለሚውል፡ የገንዘቡ መጠን ስላሳሰበኝ የሕወሃት አስተዳደር የጠየቀው የ$11.4 ቢሊዮን የ2008 ፌዴራል በጀት ከሃገሪቱ አቅምና ገቢዋ አንጻር እጅግ ከፍተኛ ነው (ክፍል 2) በሚል ቀጣዩን ጽሁፍ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ለአንባብያን ይፋ አደረግሁት።

በዚህ አርዕስት ላይ ገና የሚመጡ ሌሎች ሁለት ወይንም ሶስት ተከታታይ ክፎሎች ይኖራሉ። በዚሁ ሣምንት መጨረሻ ላይ፡ በጀቱ ኢትዮጵያን ለማሳደግና ለማልማት ወይንስ ሕወሃትን ለማድለብ ለሚለው፡ ተጨባጭ ምሣሌዎችን አቀርባለሁ!

ዛሬ ከደረስንበት፡ ከሁሉም ደግሞ እጅግ ያስገረመኝ፡ ማክሰኞ፡ ኢትዮጵያ የ$11 ቢሊዮን በጀት በሕወሃት መዳፍ ላይ አስቀመጠች፤ ማክሰኞ ማምሻውን፣ ፋና እንደዘገበው፡ “በሁለኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ዘመን ለስራ እድል ፈጠራ 21 ቢልዮን ብር መመደቡን የፌደራል ጥቃቀንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ…” የሚል ዜና አየር ላይ ተበተነ! ይኼ ገንዘብ የኢትዮጵያ ልጆች (ከሕውሃት ውጭ) ሥራ ለማስያዝ እውነትም ረድቷል ብሎ የሚያምን ካለ፣ ካለፈው ዓመት በጀት ውስጥ ተፈጸመ ያሉትንና ወደ ሰላሳ ቢሊዮን ብር የወጣበት ፕሮግራማቸው፡ እንዴት የሥራ አጡን ቁጥር የመቀነሱን አዝማሚያ የሚያሳይ ማስረጃውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያቅርብ!
 

ድንገተኛ የጦር በጀት? እስካሁን የተሠጠውን ገንዘብ አዛዦቹ ምን ገዙበት?

ይህ ብቻ አይደለም፤ ከየቀዳዳው በአንድ ጊዜ አዲሱን በጀት ለማሠላቀጥ የተዘጋጁት ሁሉ መስፈሪያቸውን ይዘው ከተፍ አሉ! የአሳሳቢ ነገሮች አመጣጥና ፍጥነታቸውም ያንኑ ያህል አስገራሚ ነው! የመጨረሻው ምጽዓት ደርሶ፡ የዮሐንስ ራእይን የማነብ እስኪመስለኝ ድረስ፡ በአንድ በኩል አዲሱ በጀት የከፈታቸው ሠፋፊ ጉሮሮዎች ታዩኝ! በሌላ በኩል ደግሞ ሃገራችንን – በሰለለ ነገር ግን ደፈር ባለ ግፊት – አለመረጋጋት የመፈታተኑ ምልክቶች ፈርጠም ማለታቸው አንደሻማን ተሰሙኝ!

ለአንድ ወዳጄ ረቡዕ ዕለት ከቀትር በኋላ ቡና እየጠጣን፣ የሃገራችን ሁኔታ በጣም እንዳስፈራኝ ነገርኩት። እርሱም እንደዚያው ዐይነት ሥጋት አዕምሮው ውስጥ እንደሚመላለስ ነግሮኝ፡ ምንም ማድረግ በማንችለው ሁኔታ ውስጥ ሆነን የጀመርነውን ሳንቋጨው ተውነው።

(Credit: ESAT TV)

(Credit: ESAT TV)

ነገር ግን እነዚህ ጫፍጫፋቸው የሚዳስሱንየነገሮች ዑደት አልቆሙም። በአውሮፓ ሰዓት አቆጣጠር በዚያኑ ዕለት ማምሻውን አምስት የዞን 9 ጦማርያንና ጋዜጠኛ መፈታትን ሰማሁ። ከዕራት በኋላ፣ በኢሳት አማካይነት ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ የቴሌቪዥኑን መስኮት ሞልተወት፡ ያ ሁሉ ገንዘብ ይህን ሁሉ ዓመት ሲፈስለት የኖረው የሕወሃት ጦር ምንም የረባ መሣሪያ እንደሌለው ተናገሩ ተብሎ ዜናውን ስሰማ፡ የዋናው ኦዲተር ጽ/ቤት ሠራተኞች የመከላከያ ሚኒስቴርን በሩን እንኳ እንዳይረግጡ መከልከላቸውና ከሞላ ጎደል ጂኔራሉ ይህንን ማድረግ የቻሉበት ሁኔታ ትዝ አለኝ።

ነገርን ነገር ያመጣዋል እንደሚባለው፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው ላይ በሚያዝያ ወር ሂስ በተደረገበት ጊዜ ወ/ሮ ሙፍያት ከሚል በግለስቡ ላይ የሠነዘሩትም አቃጨለብኝ።

ወ/ሮ ሙፈሪያት መከላከያና ደህንነቶች የሂሣብ መዝገቦቻቸውን ኦዲተሮች አይመለከቱም ብለው በር መዝጋታቸውን አስታውሰው፣ እርሳቸው የፊናንስ ሕጉንና ደንቡን ለማስከበር ጥረት ሲያደርጉ፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ውስጥ የተቀመጠው ሰው፡ ለጅቦቹ አሳልፎ እንደጣላቸው ምርር ብለው እንደሚከተለው ነበር ያሰሙት፡

  “በመንግሥት በጀት እና ፋይናንስ እገዛ ማድረግ እና ሥራ እንዲሠራ መደገፍ ሲኖርብህ፡ አትገድፍም፤ የመከላከያ ገንዘብ አወጣጥን በተመለከተ በከፊል በኦዲተር እንዲጣራ ከተስማማህ በሁዋላ፣ በግልህ ሽረህ በእኔ ላይ ዛቻ እንዲደርስብኝ አስደርገሃል” ነበር በሰውየው ላይ ያላቸው ቅዋሜና ሂስ።

ለካ ሃገሩቷ ውስጥ ነገሮች እንዲህ ከፍተዋል አልኩኝ የጂኔራሉን የፊት ሁኔታ ልብ ብየ ስመለከት፣ ምን እንደሆኑ ባላውቅም – ከግንቦት 7 ጦር እወጃ ውጭ። ከአሁኑ የተሸበሩ፡ የደነገጡ የመሰሉብትን ምስልና የሃገሪቷን ሁኔታ ከሕዝቡ ስሜት ጋር ሳነጻጽር፣ እያንዣበበ ያለው አደጋ፣ ከምን ጊዜውም በላይ የከፋ እንደሆነ ተሰማኝ።

ሰኔ 2/2015 ለፓርላማ የሕወሃት በጀት ጥያቄ (proposed budget) ሲቀርብ፣ በወቅቱ ከተሰላው ከነበረበት ብር 27.6 ቢልዮን ጉድለት በተጨማሪ፡ የልማት መ/ቤቶች አሁን ከተበጀተላቸው የሥራ ማስኬጃ የሚስጡት – በዜናው እንደተነገረው – ከ15 ከመቶ ወደ 20 ከመቶ ከፍ እንዲል መጠየቁ፡ የበጀት ጉድለቱን ከእጥፍ በላይ እንደሚገፋው ገመትኩ!

ዳሩ ግን፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ ራሳቸው ቤተኛ ያልሆኑበት በጀት፣ በፓርላማ በተፈቀደ ማግሥት የተለየ የመከላከያ ስሌት ሲመጣ መስማት፣ ከጀርባ ሆኖ ሲገፋ የነበረው የሕወሃት አስተዳደር፡ መጋረጃውን መጥላቱን አመላካች ብቻ ሳይሆን፡ በጀቱ የተመሠረተበት ሎጂክ ራሱ መቀየሩን ይናገራል!

በዚህም አሳፋሪ ድርጊት፣ ፓርላማውም እንደሚሏቸው ‘የሕዝብ ተወካይ’ አባሎች ያሉበት ቤት ሳይሆን፡ የአሻንጉሊቶች መንደር መሆኑን ያረጋገጠ ይመስለኛል!
 

መከላከያ የራሱን በጀት፣ የፌደራል መንግሥቱ በጀት በጸደቀ ማግሥት ይዞ ቀረበ

ታዲያ ይህ ሲያሳስበኝ የነበረው የ$11 ቢሊዮን የበጀት ተራራን በተመለከተ ጽሁፌን ሳዘጋጅ፡ መጀመሪያ በአዕምሮዬ ሳብላላቸው የነበሩት ጥያቄዎች፡

  (ሀ) ይሄን ሁሉ ገንዘብ መስብሰብ (በአብዛኛው በማስፈራራት) የኤኮኖሚውን ጉሮሮ አይዘጋውም ወይ?

  (ለ) ሃገሪቱስ ለሕወሃት ድርጅቶች፣ በዝርያ የተሳሰሯቸው የእነርሱ ነጋዴዎችና ሸቃዮች ሲሳይ የሚሆነውን ይህን ሁሉ ገንዘብ ከቀጥታ ታክስ፡ ከሽያጭ፡ ከብድርና ከዕርዳታ ይገኝ ይሆን ብዬ ሳስብ፣ የደረስኩበት መደምደሚያ ገንዘቡ አይገኝም ነው

ከበፊቱ ይበልጥ፣ ለራሴ ማጨብጭብ አይምሰልብኝ እንጂ፡ አሁን ገንዘቡን ማግኘት እንደማይቻል እርግጠኛ ሆኛለሁ!

አንደኛ፡ በጀቱ የተዘጋጀበትን የሃገሪቱ ዕድገት 11.2 ከመቶ ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ የለም። ይህንንም በክፍል አንድ እንደማይሆን፡ ራሱ የዓለም ገንዘብ ድርጅት (IMF) የደረሰበት ድምዳሜ ትክክለኛነት መጥቀሴ ይታወሳል።

ሁለተኛ፡ አማካይ የዋጋ ዕድገት 8.0 በመቶ ሆኖ መቀጠል አለበት ብለናል በክፍል አንድ – የገንዘብ ሚኒስትሩም፡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም እንዳሳሰቡት! ዳሩ ግን በጀቱ ከመጽደቁ አንድ ቀን ቀደም ብሉ፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ የበጅት ጥያቄያቸውን ባቀረቡ በ27 ቀናት ልዩነት፡ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ መ/ቤት ሰኞ ሐምሌ 7/2015 የሰኔ ወር ዋጋ ግሽበት ከ9.4 ወደ 10.4 ከመቶ ከፍ ማለቱን፡ የምግብ ዋጋ ግሽበቱም ከ10.1 ወደ 12.4 ከመቶ ከፍ ማለቱን ለሮይተርስ ገልጿል።

የሚያሳዝነው፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባሉት ዕጥረቶች ምክንያት (ምግቦች፡ ሸቀጦች፡ ወዘተ.) የግሽበቱ ሁኔታ እየባሰበት እንጂ የሚቀንስበት ሎጂክ በገሃድ አይታይም!

ሶስተኛ፡ በጽሁፌ ክፍል አንድ ካሰፈርኳቸው ነገሮች መካከል፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት የሰላምን አስፈላጊነት፡ አልያ ለበጀቱ መሳካት አስፈላጊ ሁኔታ እንደማይኖር እንደሚከተለው ጠቁሜያለሁ፦


  “ሸ. በሃገሪቱ ሰላም መስፈን በተለይም በየአካባቢው የሚካሄዱ ግጭቶች ከቁጥጥር ወጥተው የሕወሃት አስተዳደር በየሥፍራው ወታደራዊ ኃይል መጠቀሙ ምክንያት የሚፈጠረው አለመረጋጋት ኤኮኖሚው ላይ ተጽእኖ የማይፈጥር ከሆነ – እንዲያውም በዛሬው ዕለት ለምሣሌ፡ የአርበኞች ግንቦት 7 ጦር ሐምሌ 2 ቀን 2015 ከሕወሃት አስተዳደር ጋር የጦርነት ይጀመር “ፊሽካው ተነፍቷል” በማለት በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል!”

በተጨማሪም፡ እንዲህ በማለት ነበር በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አደገኛ ሁኔታ የገለጽኩት፡


  ቀ. በታክስ መጠን መብዛት፥ በጥሬ ዕቃ ዕጦት ወይንም በፖለቲካዊ ቂም በቀል ወይንም በመብራትና ውሃ ችግር ምክንያት የሚወድቁት/የሚዘጉት የንግድ ወይንም አምራች ድርጅቶች ችግር ሊቀነስ ካልቻለ፡ ዛሬ እንደሚታየው የሃገሪቱ በዜጎቿ አማካይነት ለዜጎቿ የሥራ ዕድሎች ማስፋፋት መቻሏና የውጭ ንግዷንም ማዳበሯ አሁን እንደሚታየው ከቀጠለ የበጅቱ ሙሉ ለሙሉ መሳካት የማይታሰብ ነው

  በ. ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተባብሶ የሚታየው በኅብረተስቡና በአስተዳደሩ መካከል ያለው ሆድና ጀርባ መሆን፡ በይበልጥ ወጣቱን ማስከፋቱ ሰለሚታይ፡ እነዚህ ሁኔታዎች ውጥረታቸው ከተባባሰ በሰላምና መረጋጋት ላይ እንዲሁም በኤኮኖሚው ላይ ሊኖረው የሚችለው ጉዳት [ግልጽ ነው]

  ተ. በሃገር ውስጥ፡ በሕዝብ በኩል ያለውም ቅሬታ በሙስና፡ በአገልግሎቶች አሠጣጥ፥ በዘረኝነትና በመሬት ዘረፋ ዙርያ ያለው ችግር የኢትዮጵያ ኤክኖሚ የወደፊቱ መቅሠፍት እንደሚሆን የመልካም አስተዳደር ባለሙያዎች ደጋግመው አሰምተዋል።”

ሕዝቡ መንግሥት ይጠብቀኛል ከማለት ይልቅ፡ ዛሬ ትልቁ ጠላቱ አድርጎ የሚመለከተው ዘረኛውን የሕወሃትን አስተዳደር ነው! ይህንንም፡ ከምን ጊዜውም ይበልጥ፡ ያለፈው ምርጫ ዐይንና ቅጥ ባጣ ሌብነት የሕዝብን ድምጽ መዘረፍ ከማረጋገጡም በላይ፣ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ሃገሪቱን ከሰሜን ኮሪያ ጋር ማመሳሰላቸው፡ ኢትዮጵያ የደረሰባትን የአመራር ኪሣራ ለዓለም ገሃድ አድርጓል!

በመሆኑም፥ ማንም አይነካኝም! ማንም አይደፍረኝም! ሲል የነበረው ሕወሃት በጥጋቡ የናፈቀው የደም መፋሰስ እየተቃረበለት ነው! ለ24 ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ በጥላቻው፣ በንቀት ሲያስገርፍ፡ ሲያሳስር፡ ሲገድል ቆየ። መንግሥታዊ አመራር ጠፍቶ፡ ከወንበዴ ለመሸሸ ልጆቻችን ስደትንና በረሃን መረጡ። በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ እነርሱ ሲታረዱና በቁም ሲቃጠሉ፡ የሕወሃት ሰዎች በየመ/ቤቱና ኤምባሲው ተሰይመው በዜጎቻችን ደም ንግድ መወንጀል ደረጃ ላይ ደረሱ!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ ሆኖ ሳለ፡ የሕወሃት ሰዎች ግን ይህንን ጨዋነት መለየት፡ መቀበልና ማክበር ሲገባቸው፡ ውርደት ሰጡት። ልጆቹን ማሠርና መገደል የደም ጥማታችውን አጋለጠ! በደርግ ላይ እንዳደረገው (ያውም የደርግ አባሎች ሃገርን ሳይዘርፉ፡ ለራሳቸው በየአካባቢው ቪላዎች ሳያሰሩ፣ የሃገርን ድንበርና ልዕልና ሳይቸበችቡ)፡ ሕዝቡም ፊቱን ከሕወሃት አዞረ!የጥፋት ጉድጓዳቸውን ከሚቆፍሩላችው ጋር ማበርን መረጠ!

ኤርትራውያን ሰደተኞች አዲስ አበባ ውስጥ ሰላምዊ ሰልፍ እንዲያደርጉና ኤርትራ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንድትባረር እንዲጠይቁ የሕወሃት የፖለቲካና የዲፕሎማቲክ መሃይምናን ሞከሩ! በአንጻሩ ግን፡ የሕወሃቶች ድንቁርና፡ ሕዝቡ በሕገ መንግሥቱ የተሠጠውን መብት እንኳ በመጠቀም ጥያቄዎቹን በሰላማዊ ሠልፍ እንዳያሰማ፡ ከወጣም የሚደበደብትና፡ የሚሰባበርበት የሚገደልበት ሁኔታ ሆኖ ለሌቹ ተቆርቋሪ መስሎ መቅረቡ እንቆቅልሽ ነው!

የኛ ወገኖቻችን ከሳዑዲ አረብያ መባራራቸውን በዓለም ዙርያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ተሰልፈው ሲያወግዙ፡ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ የሳዑዲ ኤምባሲ ፊት ለፊት በመሰለፋቸው፡ የደረሰባቸው ድበደባና እሥራት አይዘነጋንም! የሕወሃት ባለሥልጣናት ወላጆች ባንዳ ሆነው ያገለገኩትን ወገኖቻችንን የፈጀውን ግራዚያኒ በኢጣልያ ከሮም ወጣ ብሎ ሃውልት ስለተሠራለት ተቃውሞ በማሰማታቸው፡ አዲስ አበባ ላይ ዜጎቻችን እንደእባብ ተቀጠቀጡ!

ከላይ ከብዙ በጥቂቱ ለማንሳት እንደተሞከረው፣ በተለያዩ ደርጊቶቹ፡ ሕወሃት ለኢትዮጵያውያን ጠላትነቱን በማያጠራጥር መንገድ አረጋግጧል!

ሕወሃት ለራሱ እንኳ የሚፈልገውን ማወቅ ስላልቻለ፡ በሃገራችንም ላይ ዘረፋው ሰለተበራከተ፡ ኢትዮጵያውያን ሰላምን ከጠላ፡ ጥጋቡን መቆጣጠር ካቃተው ኃይል ጋር በጋራ ምንም ስለሌላቸው፡ በኃይል መወገዱን የሚመርጡበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

ሰለሆነም፡ በሠይፍ ሌሎችን ለማጥፋት የመዘጋጀቱን ያህል፡ ለእርሱም በተለይ የኢትዮጵያ ወጣቶች በፊናቸው የናፈቀውን ለመሰጠት በቁርጠኝነት ተነሰተዋል!

በ2008 ኢትዮጵያ ኤቨረስትን የሚያህል ፌዴራል በጀት መጫኗ ሳያንሳት፣ የመከላከያው ተጨማሪ የብር 24 ቢሊዮን ጥያቄ ሲቀርብለት፣ የርዕሰ መስተዳድሩን አመራር የያዘው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የተቀመጠው ግለሰብም፣ «እኔ ሰለ ጦርነት ምንም ዐይነት ኖሃው (ዕውቀቱ) የለኝም፣ የግዥ ፍላጎቱን አጸድቃእሁ፣ እናንተ ብቻ ይሆናል የምትሉትን አቅርቡልኝ» አለና እርፍ እለው– ግደታውን በሚገባ ለመወጣት ያህል አምስት ወይንም ስድስት የካቢኔ አባላት እንዲሁም የፓርላማው የመከላከያና ደኅንነት ኮሚቴው ሰብሳቢ ያሉበት አንድ ኮሚቴ ባስቸኳይ ጉዳዩን ይመልከተውና የውሳኔ ሃሣብ ይቅረብልኝ እንኳ ሳይል!

ሃገራችን ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይጠብቃት!
 
*Updated.
 

One Response to “ለረዥም ጊዜ ግጭትንና ጦርነትን ሲመኝ የኖረው የሕወሃት አስተዳደር ሊያገኘው ይሆን? በኤታ ማዦሩ በኩል “ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ” በአስቸኳይ መሣሪያ ግዥ ያስፈልገኛል አለ”

 1. shimeles July 11, 2015 at 07:32 #

  Hello sir! thank you for effort to inform us down here in Ethiopia. we are reciving information that Ginbot 7 is intensifying the war against the weyane and captured a couple of places? could you write on this area?

  Like

Comments are closed.

%d bloggers like this: