$11.4ቢ በጀት እንደጸደቀ ተጨማሪ $1.2ቢ ጄኔራል ሣሞራ ለመሣሪያ ግዥ መጠየቃቸው ‘ሕዝቡን አስፈቅደው’ ኤርትራን ለመቅጣት ወይስ ዜጎችን? ለዛውም ጦሩ በ24 ዓመታት በጀቶቹ ምን እንደገነባ ሳይነግሩን ይህ ገንዝብ መነሻ ነው አሉ! (ክፍል 3)

24 Jul

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

ክፍል ሶስት
 

መንደርደሪያ: የሥጋት ጊዜና በቅጽበት በውጥረት ወቅት ወደ ጦርነት በጀትነት የተለወጠው በጀት

የ’መንግሥት’ በጀት ላይ ይህንን ውይይት ስንጀምር (ክፍል 1) እና (ክፍል 2)፡ በሕወሃት ላይ እንዳሁኑ ዐይነት የጦርነት ከፍተኛ ሥጋት አላንዣበበም ነበር – ምንም እንኳ በዛ ያሉ መሣሪያ ያነገቡ ኃይሎች ሃገሪቱ ውስጥ መኖራቸው ቢታወቅም። ይህንን ውይይት ለመጀመር ምክንያት የሆኑኝ ሁለት ነበሩ። አንደኛው ከፍተኛ የሆነው የ$11.4 ቢሊዮን በጅት መዘጋጀቱና መጸደቁ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከብዛቱ አንጻር፡ ይህ ገንዘብ ለኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት ከመዋሉ ይልቅ፡ እንደ ወትሮው ለሕወሃት ድርጅትች ሲሣይ መሆኑ፣ መመዝበሩ አሳስቦኝና አስቆጥቶኝ ነበር/ነውም።

አሁን ደግሞ፡ በሕወሃት የጦር ኃይሎችና የሕወሃት መመዝበሪያ የሆኑት የኤኮኖሚ ድርጅቶች ከግጭቱ ዒላማዎች መካከል መሆናቸው፣ እንዲሁም በእነዚህ ሁኔታዎች በጀቱ ወደ ጦርነት በጀት መለወጡ፡ የውይይታችንን ሂደት ቀያይሮታል። መረጃ ማግኘቱ አስቸጋሪ ቢሆንም፡ በተቻለ መጠን፡ በምናውቃቸውና በሚገኙት መለኪያነት በበጀቱ ላይ ውይይቱን እንቀጥላለን – ውይይቱ፥ የጦርነቱ ዓላማና በዚሁ የታሸው አየር አካል ናቸውና።

  አዲሱ የሲቪል በጀት ወደ ጦርነት በጀት መቀየሩና ኢትዮጵያን ከዘረኛ አገዛዝ ለማላቀቅ የሚነፍሰው የጦርነት አየር የዛሬይቷን ኢትዮጵያ ለሕወሃት የትናትናዋ የማድረጉ ሥጋት እያየለ ይመስላል!
  ሕወሃት በኢትዮጵያ የፈጠረው የሕግና መዋቅራዊ ምደረ በዳነት በሁሉም ረገድ ያስከተላቸው ጠንቆችን የሚቀለብስ ሁኔታ እንዲፈጠር ግፊቱ እየተጠናከረ ነው!
  አርበኞች ግንቦት 7 ጦርነት ካወጀበት ዕለት ጀምሮ የሃገራችን አንድ ቁጥር መወያያ ይኸው ብቻ ሆኖአል! ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አሥመራ መውረዱ ከተነገረ ጀምሮ በሕወሃት ዙሪያ ምጽዓት እየተጠበቀ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያኖች ነገን በላቀ ተስፋ መጠበቅን “ሀ” ማለት ጀምረዋል!

በእኔ አመለካከት፣ ሕወሃት እስካሁን ከወሰዳቸው ፖለቲካዊና ስትራቴጂካዊ የፖሊሲ እርምጃዎችና ውሳኔዎች ሁሉ ትክክለኛው፣ ኢሣት ቀንደኛና አደገኛ ጠላቱ መሆኑን በውል ለይቶ ማወቁ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት – ሙሉ ለሙሉ ባይሳካለትም – ድህነት በተንሰራፋባት ሃገር፣ በዕርዳታ የተለገሠን ገንዘብና ብሔራዊ አንጡራ ጥሪትን እያፈሰሰ፣ ኢሣትን ሊያፍነውና ሊያጠፋው በተደጋጋሚ ሲሞክር ቆይቷል፤ ከኪስ በማይወጣ ክፍያ የሕወሃት ባለሥልጣኖች የአፈና ቀቢጸ ተስፋቸውን እንደቀጠሉበት ነው ይባላል!

ይህ ለምን እንደሚሆን ለማወቅ ዜጎች የሚከተለውን ጥያቄ መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ምንድነው ሕወሃት የሚደብቀው? ዜጎች እንዳያውቁ የሚፈልጋቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? መልሱ ሊገኝ የሚችለው የሚከተሉት ግንዛቤ ሲያገኙ ነው። የሚደበቅ ነገር ለመኖሩ ማስረጃ ካስፈለገ፡ ሕወሃት በሃገር ውስጥም ያሉትን የሕዝብ መገናኛ መሣሪያዎችን በመዝጋትና ጋዜጠኞችን ወደ ማሠርና ማሳደድ ባልሄደ ነበር።

አንዱ ዋናው ኢሣት እንዳይሰማ የሚፈለግበት ምክንያት፡ ተቃዋሚዎች የዘረኛውን አስተዳደር ምንነት ስለሚያጋልጡ፡ በተለይም የግንቦት 7ን እንቅስቃሴ፡ እንደሌሉ፣ ነገሮችም እንዳልሆኑ ለማስመሰል ነው። ቢችልማ ኖሮ ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 18/2015 ስለተነገረው፡ ዋና የግንቦት 7 አመራሮች – ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ – የመሣሪያ ትግሉን ከሜዳ ለማስተባበር ከሰሞኑ ኤርትራ እንደገቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳይሰማ ለማድረግ በቻለ ነበር።

ኢሣት የሕወሃት እጅ ሰባሪ በመሆኑ፡ ነገሮች ዌንዲ ሼርማን አዲስ አበባ ላይ ስለ ‘ሕወሃት ዲሞክራሲያዊው መንግሥት’፣ እንዲሁም ግንቦት 7 ላይ ሕወሃት ያስተላለፈውን የአሸባሪነት ፍርጃ አሜሪካ መቀበሏን በመውረግረግ ይፋ ማድረጋቸው እንደ ደሰኮሩትና በኋላ እንደካዱት ሳይሆን፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘረኞች ትዕግሥቱ እንደተሟጠጠ ለማየት፣ ይህንን ሰበር ዜና አስተርጉመው እንዳነበቡት/እንደሚያነቡትና ስቴት ዲፓርትመንትም ይህንኑ ተገንዝቦ ሰሞኑን ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ከአዲስ አበባ ከመግባታቸው በፊት ተገቢውን መረጃና ምክር እንደሚሰጣቸው ተስፋ አደርጋለሁ!

ኢሣት ባይኖር ኖሮ – እንዲሁም በመለስተኛ ደርጃ ኢትዮጵያዊ ድህረ ገጾች ባይኖሩ ኖር – ዴሞክራሲ ተገርፎ በተሰቀለባት ሃገር፡ በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎትጓች ችግሮቹ፣ የመብቱን ረገጣዎች ጉዳይና ትክክለኛ ምኞቶቹ፣ የሃገሪቱን ሃብትና ንብረት ላይ በሕወሃት ሰዎችና ድርጅቶች በኩል የሚፈጸሙት ዘረፋዎች እንዴት ይታወቁ ነበር? በሌላ ደግሞ የሕወሃት ቅጥፈቶቹስ እንዴት ለዓለም ይፋ ይሆኑ ነበር?

እንደሚታወቀው ዛሬ በኢትዮጵያውያን የተለያዩ ጥረቶች የሕወሃትና ጋሻ ጃግሬዎቹ ማንነት ከምን ጊዜውም በላይ ለዓለም ኅብረተሰብ ግልጽ ሆኖአል፤ ምንም እንኳ ዛሬ ለዓለም ሕዝብና ለኢትዮጵያዉያን ጭምር ክፉኛ እየተደሰኮረ ያለውና ትኩረት የሳበው የሃገሪቱ ኤኮኖሚ ዕድገት ቢሆንም፡፡

እሱም ቢሆን፡ ቀደምት ተጠቃሚዎቹ ራሳቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የበኸር ልጅ አድርገው ከሰየሙት ጋር እኩል የዕድገቱ ተቋዳሽ ላይሆን፡፡ የ2008 በጀትም የተሰላው ለሃገር ዕድገትና ልማት ሳይሆን፡ ለሕወሃት ድርጅቶች እንደመሆኑ፣ በአጠቃላይ በዋናነት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንና በብረታ ብረት ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን በኩል የቅርጫ ክፍፍሉ ይፈጸማል። ስለሆነም የኤኮኖሚ ዕድገትና ልማት ዲስኩሩ ሁሉ ሰለ ሕወሃቶች ኑሮ መደላደል መሆኑን ግልጽ እንዳደረገለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይገነዘባል።

ኢሣት ባይኖር ኖሮ – በየቦታው ስለሚካሄዱት የሕዝብ ቁጣዎችና አመጾች – ሕጻናት ሳይቀሩ ሕወሃት ለዚያ መቀጣጫ ማድረጉ – ከመሬት ቅርምት ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ፥ ደቡብና ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ወዘተ እንዲሁም በትግራይ የሕወሃት መስፋፋት ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ በጎንደር፥ አፋርና ወሎ ውስጥ በግንባሩ ካድሬዎች የሚፈጸሙት ወንጀሎች እንዴት ይሰሙ ነበር?

በኦጋዴን የሕወሃት ጦር አዦች በንግድ ጥቅማ ጥቅሞች ዘረፋ ውስጥ መግባታቸው፣ ሕዝቡን ማሠቃየታቸውና ደሙን በየጊዜው ማፍሰሳቸው፣ ለሃገር ደህንነትና አንደነት ደንታ እንደሌላቸው እንዴት ይሰማ ነበር? አመራሩ ዛፉና ቅርንጫፎቹ ሁሉ – እያንዳንዱ የቀበሌና ወረዳ አስተዳዳሪ የአገዛዙ ጋሻ ጃግሬ በመሆን – የኢትዮጵያ ሕዝብ በየአካባቢው በተለያዩ የሕወሃት ፊውዳል ‘መኳንንት’ መዳፍ ሥር መውደቁን ከተደጋጋሚ የሕዝቡ ስሞታዎችና ምሥክርነቶች በኢሣት በአየር በተለቀቁ ዜናዎችና ከሰብዓዊ መብቶች ዘገባዎችም ለማወቅ ተችሏል!

የቅርብ ሣምንት ምሣሌ ቢያስፈልግ፣ በሕወሃት በግፍ የተጨፈጨፉትን ለመታደግና ሃገራችንን በዘረኝነት ፖለቲካ ባርነት ቀንበር ሥር የጣላትን ሥርዓት ለማንበርከክ፡ ሐምሌ 2/2015 አርበኞች-ግንቦት 7 ጦርነት ማወጁንና መጀመሩን፥ ኢትዮጵያውያን በየት በኩል ይሰሙ ነበር?

ሕወሃት እንደ ገዥ ‘ፖለቲካ ፓርቲነቱ’ – እንደሚጠበቅበት – ለነጻነት፣ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሰብዓዊና ዜግነታዊ እኩልነትና የሃገር ልማት የቆመ ሳይሆን፤ ባለፉት 24 ዓመታት እንደታየው – የሽፍታ ሥርዓት በመመሥረት፣ የሕዝብ ሃብት በመዝረፍ የገነባቸው የዜና ማሠራጫዎች እንደሆኑ፣ በሃሰተኛ መሠረት ላይ ለቆመው አገዛዛቸው፣ ከሃሰት ማሠራጨትና ፕርፓጋንዳ ውጭ ለሕዝባችን ጥቅሞችና በሃገራችን ለዴሞክራሲ ግንባታ የፈየዱት ፍሬና ወቅት ባለመኖሩ፣ ሊያወርዳቸው የተዘጋጀውን ኃይል ከማጥልላት ውጭ፣ የዚህን የጦርነት ዝግጅት መታወጅ ዜና እንኳ ሊነግሩት አልደፈሩም!

የእነዚህ ሁኔታዎች አስከፊነት ገሃድ እየሆነ በመምጣቱ፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ አልገዛም ባይነት በአጭር ጊዜ ሊሸጋገር እንደሚችል፡ ከሕወሃት ይልቅ ባዕዳን ደጋፊዎቹ ይህንን በቀላሉ ሊገንዘቡ ስለሚችሉ፡ እስካሁን ሲያገኝ የኖረውን ወፍራምና ጭፍን የኤኮኖሚ፡ የፖለቲካና ዲፕሎማቲክ ድጋፉን በአጭር ጊዜ ውስጥ እያመናመነው እንደሚመጣ ምልክቶች እየታዩ ነው።

በቅርቡ ‘የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች’ በፓርላማ አጸደቁት የተባለው የ$11.4 ቢሊዮን በጀትም፣ ለሃገር ልማትና ዕድገት ሣይሆን፣ በቅጽበት ወደ ጦርነት በጀት መለወጡ ኢትዮጵያውያን ከሕወሃት ‘ጦር ምንም የረባ መሣሪያ የለኝም’ ጥያቄ ሊገምቱ ይችላሉ!

ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች ሁሉ፡ ሕወሃት ራሱን እንጂ ሌላ ማንንም ተጠያቂ ማድረግ እንደማይችል፡ ከወዲሁና – ሌላው እንኳ ይቅር ቢባል – የተለመደውንና ምርጫን ወደ ሌቦች ሠርግ መቀየር ባህሪውን እንኳ ብንል ረሳው – የግንቦቱ 2015 ምርጫ ከሁሉም የከፋ፣ የሕዝብና የሃገር ንቀት በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተጠናከረ ክንድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለሕወሃት የማያዳግም ትምህርት ይሰጠዋል የሚል ጠንካራ ግምት አሳድሮብኛል!

ይህም ትምህርት በመጭው ተተኪው ኃይል ውስጥ ሠርጾ በመግባት፡ ሃገሪቱን ከዚህ ዐይነት ቅንጥብጥብ ያልተረጋጋ፣ በደም የተለወሰ ምዕራፍና የሥልጣን ብልግና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊገላግላት ስለሚገባ፡ በሣምንት ውስጥ ይሁን፣ በዓመት፣ ሁለት፥ ሶስት ወይንም በአሥር ዓመት ሕውሃት የሚገረሰሰው፡ ተተኪዎቹ መጥፎና አሳፋሪ ድርጊቶቹን በሚገባ ሊመረምሯቸው ይገባል – በእነርሱም በኢትዮጵያ ምድር ሁለተኛ እንዳይደገሙ!

ይህ ከላይ የተነሳንበትም የ$11.4 ቢሊዮን በጀት ትርጉም የለውም፤ አይኖረውም። ምክንያቱም በቀናት ልዩነት አስተዳደሩ በፍርሃት በራደና የያዘውን ይዞ ለመቆየት በሚያደርጋቸው ጥረቶች ምክንያት በተከታታይ የአፈጻጸም ባህሪው ወደ ጦርነት በጀት እየቀየረው ነውና!
 

  I. የዜጎች የብሔራዊ በጀት የኛነት የት ነው የሚጀምረው? በጀት የልማት መሣሪያ የመሆኑን ያህል ለመንግሥታዊ ወንጀሎችም ምቹ ምንጭ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ በግልጽ ያሳያል

ከአሥራ ስድስት ቀናት በፊት ከሕወሃት አስተዳደር የጦር እምብርት ሾልኮ ኢሣት እጅ የገባው ዜና ያልተጠበቀና ድንገተኛ ነበር። አስገራሚው ነገር፣ ወቅቱ፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ – ለስም ቢሆንም እንኳ – ለመጀመሪያ ጊዜ 23.4 ቢሊዮን ብር ($11.4 ቢሊዮን) በጀት ያጸደቀችበት ማግሥት ነበር።

ለነገሩ በጀቱ ገና ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት በብር በተከታታይ ዋጋው መውደቅና (ከሃገሪቱም ኢኮኖሚ መዳከም ሁኔታ አንጻር) በተለይም ዶላር መጠናከርና እንዲሁም ከኢትዮጵያ ገንዝብ አንጻር ሌሎቹ የውጭ ገንዘቦችም በመጠናከራቸው፡ በጀቱ ከጸደቀ ወር ባልሞላ ጊዜ በገበያ የውጭ ምንዛሪ ዐይን አንጻር ምንዛሪ ዋጋው በፍጥነት ወርዷል። ይህም አንድ ራሱን የቻለ አሳሳቢ ችግር ነው።

የዜናው ይዘት፣ የሕወሃት ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሣሞራ ዩኒስ – ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው በተገኘበት – ከፍተኛ ምሥጢራዊ ስብሰባ ላይ፡ ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖችና የጦር አዛዦቻችው ለመጀመሪያ ጊዜ የተናዘዙት፣ “ጦራችን ከጊዜው ጋር እየዘመነ አይደለም፤ የታንኮቻችን አቅም ያረጀ ነው፤ ተዋጊ አሮፕላኖቻችን ከገበያ የወጡ ናቸው፣ መቀያየሪያ ዕቃዎቻቸው (ስፔር ፓርትስ) ከገበያ እየወጡና እየጠፉ ነው” የሚለው ትርጉሙና ምንነቱ ያስነሷቸው/የሚያስነሷቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች አሉ፡-

  (ሀ) ሕወሃት ጦር መጣሲባል ነው እንዴ የጦር መጋዘኑን የሚፈትሸውና የጦርነት ዝግጅቱን የሚያረጋግጠው?

  (ለ) ፈትሾ በቅጽበት ባዶነቱን ማመኑ – ለስሙ ‘የኢትዮጵያ ጦር ኃይል’ ቢሆንም – ዝግጁ አለመሆኑን በተዘዋዋሪ መናዘዙ ከ24 ዓመታት የጦር ግንባታ በኋላና – ዋናው ኦዲተር በተደጋጋሚ ለኢትዮዮጵያ ሕዝብ ያለተጠያቂነት በመከላከያ ሚኒስቴር የሚፈሰውንና እስካሁን በሃገሪቱ የፋይናንስ ሕግና ደንብ መሠረት ያልተወራረዱትን ሂሣቦች እንዳሳወቁት ሁሉ – አሁን የጄኔራሉ መሣሪያ የለኝም ኑዛዜ ከምን የመነጨ ነው?

  (ሐ) በአሜሪካ የመረጃ ምንጮች መሠረት ለመሣሪያ መግዥያ በዓመት ሕወሃት $330 ሚሊዮን ያህል እንደሚያጠፋ የሚነገርለት፡ ለ24 ዓመታት በበጅት እየተያዘ የጦሩን አቅዋምና ዘመናዊነት ለመጠበቅ እየተባለ በምሥራቅ አውሮፓ ሃገሮች በተለይም ሩስያ፣ ዩክሬን፣ እሥራኤል፣ ሰሜን ኮሪያና ወዘተ ውስጥ ሕወሃት ሲያባክን የኖረው ገንዘብ የማንን ደህንነት ለመንከባክብ ነው? ወይንስ አይዘርባጃን ውስጥ እነጄነራል ክንፈ ዳኘው የሚፈጽሟቸው መመላለሶች የማንን ደህንነት ወይንም ሕሙማን ለመጎብኘት እንደሆነ እንዳሳሰበን ቀደም ብለን ጥያቄ ማንሳታችን ይታወሳል!

ጄኔራል ሣሞራ ዩኑስ እነዚህን ጥያቄዎች ማን ወንድ ደፍሮ ይጠይቀኛል ብለው ሊሆን ይችላል (ወይንም ተደናግጠው) አሁን በገሃድ የሕወሃትን ጦር ምሥጢር በመሣሪያ ቁጥር የዘባተሉት። በዚያም ባላሰቡበት ሁኔታ የሕወሃትን ጦር ገበናውን አጋልጠው እርቃኑን አስቀሩት!

በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የሚቀመጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው (ጠቅላላ ሚዲያ)

በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የሚቀመጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው (ጠቅላላ ሚዲያ)

ቢቻል እነርሱን መስሎ፣ አልያም ጠንካራና ታማኝ ቀኝ እጃቸው ሆኖ መስተዳድሩን እንዲመራ ሕወሃት የሰየመው ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው፣ ለጄኔራሉ ጥያቄ እዛው በሥፍራው የሠጠው ምላሽ፡ ኢትዮጵያ ባፍንጫዋ ብትደፋ ግድ የሌው ግለሰብ በመሆኑ፣ ሕወሃት የታወቀበትን ዘራፊነት በማስታወስ ለሃገሪቱ ግደታውን ለመወጣት እየሞከረ ነው እንዲባል እንኳ፣ አምስት ወይንም ስድስት የካቢኔ አባላት እንዲሁም የፓርላማው የመከላከያና ደኅንነት ኮሚቴው ሰብሳቢ ያሉበት አንድ ኮሚቴ ባስቸኳይ ጉዳዩን ተመልከተው የውሳኔ ሃሣብ እንዲቀርብልኝ አደርጋለሁ አልነበረም ያለው!

ሐምሌ 9/2015 ባቀረብኩት ጽሁፌ “ለረዥም ጊዜ ግጭትንና ጦርነትን ሲመኝ የኖረው የሕወሃት አስተዳደር ሊያገኘው ይሆን? በኤታ ማዦሩ በኩል “ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ” በአስቸኳይ መሣሪያ ግዥ ያስፈልገኛል አለ” እንደገለኩት አጅግ ሸቆጥቋጣ፣ አሳፋሪና ብሔራዊ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ፦ “እኔ ሰለ ጦርነት ምንም ዐይነት ኖሃው (ዕውቀቱ) የለኝም፣ የግዥ ፍላጎቱን አጸድቃእሁ፣ እናንተ ብቻ ይሆናል የምትሉትን አቅርቡልኝ” አለና እርፍ እለው!

በነገራችን ላይ፣ በ2004 ሂሣብ ኦዲት ላይ፡ ዋናው ኦዲተር በመከላከያ ቢሮ በኩል 3.5 ቢሊዮን ብር ከመጉደሉም በላይ፣ በሃገሪቱ የፊናንስ ደንብ መሠረት መከላከያ ሂሣቡን ለመዝጋት እንኳ አልቻለም/ፈቃደኛ አልነበረም ማለታቸው ይታወሳል። በ2005ም ዋናው ኦዲተር ብር 86.4 ሚሊዮን በሥራ ማስኬጃ ተይዞ የፊናንስ ደንቡ በሚያዘው መሠረት ሳይወራረድ ቀርቷል ነበር ያሉት። በ2006 መከላከያ ብር 97.1 ሚሊዮን የተጠራቀመ ውዝፍ የተገኘበት መሥሪያ ቤት ከመሆኑም ባሻገር፡ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ አሉታዊ የኦዲት ትችቶች ተስጥተውበታል። ለምሣሌም ያህል:

  (ሀ) በ2004/5 የኦዲተሩ አጠር ያለዘገባ ውስጥ እንደተመለከተው፣ ብር 3.2 ሚሊዮን የሠራዊት ደመወዝና በበጀት ዓመት የተቀጠሩ በዝውውር የመጡ በጡረታ የተገለሉ እና በተለያየ ምክንያት የተሰናበቱ የሠራዊት አባላት እና የተወሰኑ ዓመታት በማገልገላቸው ማበረታቸ የተሰጣቸው አባላት ስም ዝርዝር ጭምር ለኦዲት ተጠይቆ መ/ቤቱ ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ የተጠቀሰውን የሠራዊት ደመወዝ ወጪ ትክክለኛነት ማረጋገጥ እንዳልተቻለ በጽሁፍ ለፓርላማ ቀርቦ ምንም እርምጃ ሳይወሰድ መቅረቱ ይታወሳል።

  በኋላ የመከላከያን ምሥጢር ለመጠበቅ በሚል ሰንካላ ምክንያት ሁለቱም ሂሳባቸው (ክደኅንነት ጋር) ኦዲት እንዳይደረግ የጠየቁና፣ ጥያቄያቸውን ለብቻ ለጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው ሲያቀርቡለት፡ በምሥጢር ከእነርሱ ጋር የተስማማና ሥራውን የሚሠሩትን ሠራተኞች ግን ለተኩሎች ተንኮልና ጥርስ ያጋለጠ ሃላፊ መሆኑን ነው በግለስቡ ላይ የተካሄደው ግለሂስ ያጋለጠው። በማስረጃነትም ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ያሰሙትን ሂስ እዚህ ላይ ተጭነው ማንበብ ይችላሉ።

  ከምንወያይበት ጋር የተያዘ ባይሆንም፡ በነገራችን ላይ የሕወሃትን ምንነትና የጀሌዎቹን ታማኒነት በአጠቃላይ መለካት እንዲያስችል፡ ያለፈውን ምርጫ ታማኒ እንዳይሆን ካደረጉት ባለሥልጣን ተመራጮች መካከል ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አንዷ ናቸው። በምርጫ ሕጉ መሠረት፡ አንድ የምርጫ ጣቢያ ከአንድ ሺህ መራጭ (ድምጽ) እንዳይኖር ሕጉ ቢደነግግም፡ የምርጫ ኰርጆ ሙሉ በሚለው የፓርቲው ውስጣዊ መመሪያ መሠረት፡ እርሳቸውም እንደ ሌሎቹ ከፍተኛ ካድሬዎች ሁሉ፡ የአንድ ሺህ ድምጽ ጣራን በርቅሰው በ1,459 ድምጽ ነው የተመረጡት!

  (ለ) በ2004 መከላከያ ብር 19.4 ሚሊዮን ያለማስረጃ በማውጣቱ በዋናው ኦዲተር ተጠያቂ መደረጉ አስቆጥቶት ነበር፡፡

  የፌዴራል ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ (ከጽ/ቤቱ ገጽ)

  የፌዴራል ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ (ከጽ/ቤቱ ገጽ)

  (ሐ) በ2007ም በወቅቱ ያልተከፈሉ ሂሣቦች በማለት በመከላከያ ላይ ዋናው ኦዲተር ያቀረቡት ነቀፌታ ብር 330.1 ሚሊዮን መድረሱ የመ/ቤቱ የገንዘብ አወጣጥ ቁጥጥር የሌለበት መሆኑን አስገንዝቦናል። በተጨማሪም፡ ያለፈቃድ በመንግሥት ወጭ በ800 ሺህ ብር ያህል ግዥ ተፈጽሞ፡ የተገዛው ንብረት የመንግሥት ሆኖ ያለመመዘገቡ ትክክል አለመሆኑ ተገልጾ፡ ጉዳዩ እንዲስተካከል ጥያቄ ሲቀርብለት አሠራሩን ካለማሻሻሉ ውጭ፡ በዋናው ኦዲተር ሥራ ላይ መ/ቤቱ ቅሬታውን አሰምቷል።

ታዲያ ለዚህ መሥሪያ ቤት ነው፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው – በዐይነ ሕሊና ሲማተር – ‘እኔ ስለጦርነትና የሚያሰፈልጋችሁን ስለማላውቅ፡ “ችግር የለም! የሚመስላችሁን የገንዘብ ጥያቄ ሠርታችሁ አምጡልኝ፤ እኔ ፈርማለሁ፣ እናንተም ጭልፋችሁን ይዛችሁ ቅረቡ!” ያላቸው።

የኢትዮጵያ ሕዝብም ሕወሃትን እርግፍ አድርጎ የተፋው፡ እነዘህን መሰል ነገሮችን በመገንዘብ ነው። በዚህም ምክንያት፡ ሕወሃቶች ምንም እንኳ የራሳቸውን ካድሬዎች ብቻ በየቦታው ቢሰገስጉም፡ ለሃገራቸው ደህንነት በቆሙ ዜጎች ምክንያት፡ የትም ቦታ ምሥጢሩ ሊጠበቅ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በምሥጢር የያዙት ነገር ሁሉ ባላሰቡበት መንገድ እየወጣ እንጂ፥ እንደ አጀማመራቸው ቢሆንማ ሁሉም ነገር ተበልቶ ካለቀ በኋላ ዜጎች ኢትዮጵያን ለመቅበር ብቻ ነበር ምናልባትም ምሽቱ ላይ እንዳሁኑ ሊጠሩ የሚችሉት!

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት በመጠኑም ቢሆን፡ የመንግሥት ኃላፊነት በተለይም የሕዝብ ንብረቶችን ባለቤት የለሽ ይዞታና አጠቃቀም ሁኔታ – ሌሎች የባሱ ብኩንና የሃገር ሃብት አብካኝ የሕወሃት መሥሪያ ቤቶች ቢኖሩም፡ መከላከያን ብቻ በምሣሌነት በማቅረብ – በኢትዮጵያ የበጀት አጠቃቀምንና አፈጻጸምን በሚመለከት (እነርሱን ብቻ የሚመለከት ከሆነ) ተጠያቂነት ፈጽሞ ያለመኖር ሁኔታ ለማሳየት ተሞክሯል።

ሌሎች የሉም ለማለት አይደለም የሉም ለማለት አይደለም። ይህም የሚያሳየው፡ የሕወሃት ፖሊሲና አስተዳደር የነካቸው መሥሪያ ቤቶች በመሉ ተበክለዋል። ለምሣሌም ያህል በተደጋጋሚ ስለ ትምህርት ይነገራል፡ የዩኒቨርሲቲዎችን ቁጥርም፡ ሕወሃት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ወደ 41 ከፍ ለማድረግ ዝግቶች መጠናቀቃቸው ይነገራል። መታየት ያለበት፡ የሕወሃት ኤኮኖሚ የተመሠረተው በግንባታ ላይ ነው – መንገዶች፡ ሕንጻዎችና ሌሎች መሠረት ልማቶች።

ይህም የሚሆንበት ምክንያት፡ የሕወሃት ሰዎችና ድርጅቶች የሚከብሩትና የእነርሱን ብሄረስብ የበላይ እንዲሆን በየዘርፉ የግንባታ ሥራዎችና ለሃገር ልማት ኮንስትራክሽን በሚል ሽፋን በግንባታ ሥራዎችና በኮንስትራክሽን ኮንትራቶች ሰጭነትና ተቀባይነት በሚደረጉ ዘረፋዎች ነው – የሱር ኮንስትራክሽን ሣንባ የሚተነፍሰው ገንዘብ ነው። ይህም በዓመት እስከ ብር 30 ቢሊዮን ሥራ ላይ ያውላል። በተመሳሳይ መንገድ ለግንባታዎች ቀዳሚ ሲሚንቶ አቅራቢው መሰቦ ነው። ይህም ተጫራች በሌለበት ሁኔታ የአባይ ግንባታን ብቸውን ይዞ ከርሟል – ሌሎችም በየመስካችው።

የሚሠራው ሥራ ጥራት ያለው ቢሆን አንድ ነገር ነው – በዚህ ረገድ ግን በፖለቲካ ድርጅቱ ብሔራዊ ምርጫ አስተዳደርና በሕወሃት የንግድ ድርጅቶች መካከል ሃቅና ጥራት ብርቅ ናቸው።

የኢትዮጵያ መንገድ ሥራ በዓለም ባንክ ግምገማ በጥርጥር የሚታይ ነው። አንዴም ከSatisfactory አልፎ አያውቅም።

በዓለም ባንክ ባለሙያዎች በኩል ለረዥም ዘመናት በተማሩ ኢትዮጵያውያን አመራርና ምዕራባውያን ዕርዳታ በንጉሡ ዘመነ መንግሥት የተቋቋመው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መዋቅር የተፈተነና እንደ መዋቅር እጅግ ጠንካራ ለመሆኑ ተቀባይነት አለ። ነገር ግን፡ የሕወሃት ዘረኝነትና ብልግናና የጨረታ ሕግ አለማክበርና ሥራን በጊዜ አከናውኖ የማቅረብ ችሎታና ተጠያቂነት ባለመኖሩ የድርጅቱን የማስፈጽም ብቃት የሕወሃቶች አመራር አበላሽቶት፡ እነርሱም ለረዥም ዓመታት ያስተዳደረውን ግለስብ በብጣሽ ደብዳቤ አባረውታል

ለከፍተኛ ትምህርት የሚሠሩት ግንባታዎች፣ ሕወሃት እንደ ድርጅት ለትምህርት አሳቢ ነው ብሎ የሚያስብ ካለ ስህተተኛ አመለካከት ነው። ለዩኒቨርስቲ ተብለው የሚሠሩት ሕንጻዎች ኮሾ ናቸው፤ ለትምህርትም ሆነ ለተማሪዎች ጤነኛ ኑሮም ምቹ አይደሉም።

ለምሳሌም ያህል በ2007 ዘገባቸው ከጥቂት ወራት በፊት ዋናው ኦዲተር እንዳመለከቱት፡ ውሃ የለሽ፡ ሥራ ማስኬጃ የለሽ፣ በአስተዳደርም፡ መህራንና የኮሌጆች አስተዳዳሪዎች በቂ ደሞዝ የማይከፈላቸው ዩኒቨርሲቲዎች፡ ከትምህርትና ዕውቀት ምንጭነት ይልቅ፡ የሙስናና የተንኮል እንዲሆኑ ሁኔታዎች እያስገደዱ ነው።

“አሶሳ፡ ደብረማርቆስ፡ ጎንደር፣ ዋቻሞ፣ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች የሰበሰቡት የውስጥ ገቢ ብር 72,072,130.37 ባቀረቡት ዓመታዊ የገቢ ሂሣብ ሪፖርት” ውስጥ ሳይካተት ቀርቷል፡፡ እንዲሁም መቐሌ ዩኒቨርሲቲ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሳያውቀው የራሱን የገቢ ደረሰኝ በማሳተም እስከ ብር 12,879,067.34 ገቢ የሰበሰበ መሆኑ ታውቋል፡፡ መቱ፤ ሚዛንና ዋቻሞና በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ተገኝቶባቸዋል፡፡

መምህራን በቂ ደሞዝ ስለማይከፈላቸው፡ ውስጥ ለውስጥ በሚደረግ ስምምነት የወር ያህል ውሎ አበል የትም ሳይጓዙ አንዳንድ ቦታ እንደሚከፈል፡ ለተባባሪ ድጋፍ ሠጭ ሠራተኞችም ደጎስ ያለ ትርፍ ሰዓት ክፍያ እንደሚፈጸም ታውቋል። ይህንንም ዋናው ኦዲተር በ2006 ዘገባቸው አሳውቀዋል። በዚህ ረገድ ይህንን በመሰለ ሁኔታ፡ ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች (ጅማ፡ ባህር ዳር፡ ዲላ፡ ሃዋሳ፡ አርባ ምንጭና ዋቸሞ) ብር 41.3 ሚሊዮን ማጥፋታቸውን ዋናው ኦዲተር በመረጃነት አሳውቀዋል።

በ2006 ዓ.ም. እንደሆነው፡ እነዚህ በቂ ቁሳቁስ ለመግዛት ገንዘብ ያልተመደበላቸው ዩኒቨርሲቲዎች፡ ዕቃዎቹ አስፈላጊ ሆነው በመገኘታችው፡ እስከ ቢሊዮን ብር ድረስ ከሃገሪቱ የፋይናንስ ሕግና ደንብ ውጭ ከበጀታቸው ለማጥፋት መገደዳችውን ኦዲተሩ (ምክንያቱን ሳይገልጡ)፣ ጉድለቱን ለፓርላማ ቢያቀርቡም፡ ይህ እንደ ችግር በሚዲያም ሆነ በፓርላማ ለመነሳቱ ምንም ምልክት የለም።

በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ካድሬዎችና የስለላ ድርጅቱ ተወካዮች ከዩኒቨርሲቲው የሕወሃት ባለሥልጣኖች የተማሪዎችን አልጋ ወደ ማከራየትና ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን ሰመ-ትምህርት ሚኒስትር ተብየው መቀሌ ላይ የሕወሃት 40ኛ ዓመት ሲከበር ለጋዜጠኞች አምኖ እስከ አሁን ምንም እርምጃ አለመወስዱ፡ ስለዘራፊዎቹ ማንነትና ጥንካሬ፣ የደህንነትና የፖለቲካ ጉልበት ለማንም ኢትዮጵያዊ ምስክርነት ይሰጣል።

ይህ ሁኔታ፡ አጠቃላይ ሥዕሉን በሙሉ ባይቀርጽም፣ ሃገሪቷ በየፈርጁ ያለችበትን የብኩነትና ዘረፋ ሁኔታ በሚገባ ይሥላል።

በአጠቃላይ፡ የሃገሪቱ የሕወሃት አስተዳደር ሲታይ፡ በተለይም በሃገሪቱ የፈጠረው የመርህ፡ የፖለቲካና አስተዳደራዊ ምድረ በዳነት በኢትዮጵያ የበጀትና የፕሮግራም መቆራኘንትን በማገዱ የሃገሪቱ አሠራርና ሁኔታ ብልሹ፣ እንዲሁም እያንዳንዱ የኤኮኖሚ ዘርፍ እንደፖለቲካው ሁሉ በሙስና የተጨማለቀና ለመጥፎ አስተዳደር ክፉኛ የተጋለጠ ነው።
 

  II. የዜጎች በተለያዩ ድርጅት የመሰባስብ መብት በተነጠቀበት፡ የመናገርና የሙያ ነጻነት በሌለበት ሁኔታ ‘የመንግሥት ሌቦችን በማጋለጥ ‘ኦዲተሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ይከፍላሉ
  አንድ ሃገር የሕዝቡ አንድነት ከላይ በተጠቀሱት ሕወሃት በፈጠራቸው መከፋፈሎችን ችግሮች ምክንያት እየላላና እየተናጋ በሄደ መጠን፡ ስለተሳካ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሰብና መናገር ይችላል ወይ?

ከውስጥም ሆነ ከውጭ ያለበትን ግፊት ያዳፈነና፡ የታዛቢዎችን ዐይን ሁሉ ያደበዘዘ መስሎት፡ ሕወሃት ሥልጣን እንደያዘ በሃገር ውስጥ የነበሩትን ወይንም ነጻነት አለ ብለው ብቅ ብቅ ያሉትን ጥቂት መሠረታዊ ድርጅቶችን (መምህራን፡ ሠራተኞች፡ ገበሬዎች: ሴቶች፡ ወጣቶች ወዘተ) በራሱ ድርጅቶችና ቧለሙዋሎቹ በመተካቱ፣ ከውስጥ ያለው ተሟጋችነት ለእርሱ ብቻ እንዲሆን አድርጓል! ከ2005 ዓ.ም. በኋላማ ሃገሪቱ በሙሉ እያንዳንዱ የመንግሥት ወይንም መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የሚመራው በሕወሃት ሰዎች ብቻ ሆኖአል – አንዳንድ የሥልጣን ቦታዎች ላይ ከጀርባ አጥንት ጠንካራነት፣ የአዕምሮ ንቃትና ብቃት ይልቅ የሆድ ስፋት ያላቸው እየተመረጡ ለናሙና መሃሉ አንጠባጥቦ ቢጠቀምባቸውም!

ከሁሉም የከፋው ደግሞ ከጭቃ ጠፍጥፎ የሰው ሕይወት መተካት ይችል ይመስል፣ እያንዳንዱ የሕወሃት ካድሬ እንደፈለገ የመግደል፣ የማፈንና ሕዝብን የመጨፍጨፍ ሥልጣን ራሱን ማከናነቡ ነው! በሕዝብ ስም የተደራጁት ማህበራት አፋቸውና አዕምሮአቸው ተሸብቦ፣ ዛሬ ምንም ማለት አይችሉም። ይህም ማለት፣ ለምሣሌ ዛሬ የኢትዮጵያ ሠራተኞች መሪዎች፣ እንዲሁም ሌሎች ሥርዓቱ የዘራቸው ትክሎች (civil society organizations) በሕልማቸውም ሆነ በልባቸው ከኢትዮጵያ ሠራተኞች፡ ተማሪዎች፡ ገበሬዎች፣ ሴቶች፡ ምሁራን፡ ወዘተ ፍላጎትና ጥቅም በላይ ቅድሚያ የሚሠጡት ለሕወሃት የፖለቲካና የኤኮኖሚ ጥቅሞችና ፍላጎቶች እንዲሆን አድርጓል። ይህ አስተሳሰብና አሠራር ዛሬ ፋፍቶ፡ ሕወሃት ስህተቱን እንኳ እንዲያርም ደፍሮ የሚነግረው ካድሬ በመካከላቸው የለም!

በማዳበርያ ግዥ የሚታሠሩት፥ የሚሠቃዩት፥ ከይዞታቸው የሚባረሩት የሚገደሉት የገበሬ ማኅበራት አባላት ተገቢ ፍርዳቸው ሆኖ ነውን? ማኅበራቱን ከአመራራቸው ጭምር ‘መንግሥታዊ’ አስተዳደሩ እንደ ንብረት ቆጥሮ ከነአባሎቻቸው ስለወረሳቸው አይደለምን?

አጠር ባለ አገላለጽ፥ እስከዛሬ የኢትዮጵያ ‘መንግሥት’ በጀትም እንዲሁ በአንድ ደብዛዛ መነጽር የሚታይ – ‘መንግሥት’ ባለው ብቻ ምንነቱ የሚገለጽ – የቁጥሮች መንደር እንጂ፡ የሃገርና የሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት መገለጫና ማርኪያ መሣሪያ አይደለም። በዚህም ምክንያት፡ በጀት ሕዝቡን፡ ፍላጎቱንና ጥቅሙን ይወክላሉ ተብለው በሕዝብ ስም ሕወሃት ያቋቋማቸው የሕዝብ ጥቅም ጠባቂዎች እንኳ በቅርብ የሚያዩትና የሚያስከብሩት የሕወሃትን ጥቅሞች ብቻ ነው!

ይህም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሕዝቡ ያሉበትን የቤተሰቡንም ሆነ የማኅበረሰቡን ችግሮች የቅርብ ቤተሰብ አጀንዳ ብቻ አድርጎት ነበር። ከኢሣት መቋቋምና የመሣሪያ ትግል ከተጀመረ ወዲህ እንኳ ሕዝቡ ለወደፊቱ አማራጭ የሚያይበት መስኮቶችን እንደሚያገኝ እየተሰማውና ደፈርም እያለ ጥያቄዎቹን በቃላት ማስቀመጥ ጀምሯል!

‘መንግሥታዊ’ አስተዳደርን በተመለከተ፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ ችግር፡ ከላይ ከተነሱት በተጨማሪ፡ ፕሮግራምና በጀት በሚገባ አለመቆራኘታቸው ነው። ከላይ በተጠቀሱት ችግሮች ምክንያት፡ ፕሮግራሙ አንድ ነገር ይላል፣ ገንዘቡ ሌላ ቦታ ይጠፋል። ውጤቱ፡ ለሃገርና የሕዝብ ጥቅሞች በተግባር የሚፈጸም ፕሮግራም የለም ማለት ነው! ይህም፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ በጀት የአስተዳደር፥ ሕወሃት ቁራ – ዘራፊና ትልቁ በሽታ – እንዲሆን ሁኔታውን አመቻችቶለታል (የዚህን ሥዕል በክፍል አራት እንመለከተዋለን)፡፡

በሌላ አባባል፡ በተለይም ‘መንግሥት’ ራሱን መቆጣጠር አለመቻሉ፣ ወይንም ኅብረተስቡ ውስጥ ይህን ‘መንግሥት’ የሚባለውን የሃገሪቱ ጉልበተኛን ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይል አለመኖሩ (ውክልና ያለው መዋቅር፡ ሕግና ዳኝነት)፣ በጀቱ ለዘረፋ የተጋለጠ እንዲሆን አድርጎታል። ይህም ማለት ‘መንግሥት’ የሚባለውን የታጠቀና ሕግን መርገጥ የሚወደውን ጉልበተኛ መቆጣጠር በሚችል/በሚያስችል ተከባሪ ብሔራዊ ሕግ፣ የማይበገር ተጠያቂነት፣ መዋቅራዊ ውክልናና ቁጥጥር በሃገራችን እንዳይዳብር ሁሉንም ነገር ለራሱ በሚያመቸው መንገድ መለስ ዜናዊ ሃገሪቱንና ፖለቲካዋን በክሎ – በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መሣሪያነት የሕወሃትን የበላይነት መሥርቶ – በ’መንግሥት-መሰል ለራሱ የማፊያ ቡድን ጥቅም የሚያመች አስተዳደር ሥር ኢትዮጵያን ተብትቧት ሄዷል!

ይህንንም ቀዳሚ የጭቆና ካህንና ሕዝብ ከፋፋዩ መለስ ዜናዊ፡ በ2012 መጀመሪያ ላይ ከሌሎች የውጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በጋራ ባሳተመው መጽሐፍ (Good Growth and Governance in Africa: Rethinking Development Strategies – Editors Stiglitz et.al) ውስጥ፣ በሕይወቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሃቅ በራሱ ምዕራፍ ውስጥ እንደገለጸው፣ በተለይም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ካለው ርዕዮተ ዓለማዊ አቋም የተነሳ፡ መንግሥታዊ አስተዳደር (State) ልዕልና የሚያጣው የኢኮኖሚው አመራር በግል ዘርፉ እጅ ሲወድቅ የሚከተለው አደጋ ነው ይላል።

“የግል ዘርፉ” የሚለው አመለካከት ሠፊና አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በሥራ መስኩ፡ በገቢውና በሕይወት ዓላማውና ግቡ ጭምር ማካተቱ ለሕወሃት ጠቅሞታል።

እንደሚታወሰው፥ መጽሐፉ የተዘጋጀውና የታተመውም በ2012 መጀመሪያ ላይ መለስ ሊሞት ከግማሽ ዓመት ያህል ጊዜ ሲቀረው እንደመሆኑ፡ ለአንዴ በሕይወቱ እውነት ልናገር ብሎ ነው መሰለኝ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመራር ብሔራዊ ስምምነት የመፍጠር ችሎታው መንማና መሆኑን ታሪክም እንደመሰከረበት መዝግቧል! ይህንንም በሚመለከት ያሰፈረውና በሃገራችንም በተግባር የታየው እንዲህ ይላል፡፟ –

  “…[D]evelopmental state ought to be autonomous from the private sector. In the absence of state direction of the economy, it would be the private sector that would provide overall economic guidance to the economy…As clear as the need for a developmental state based on national consensus is, it appears to be contradicted by historical experience.”

መለስ ዜናዊ ይህን አሁን ከመሸ በኋላ መናዘዙ፡ በፊት የፈጸማቸውን ለማረም አይመስለኝም። በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዳደራዊ አሠራር ምንም የሚታረም ነገር የለውም! ስለዚህም፡ ሕወሃት የያዘው ዐይነት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ውስጡ በዘረኝነት ማለትም፡ በትግራዊ የበላይነትና የግል ጥቅም ላይ የተመሠረተ በመሆኑ – ለትግራይ ጥቅም ብሎ ሳይሆን – ለራሱ ጥቅም የፈበረከው ስለሆነ፡ አጥፊ የፖለቲካ ሥርዓት በመሆኑ – ለኢትዮጵያ ደህንነት ሲባል – ይህንን መገረሰሱ አፍታ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም!

በዚህ ሁኔታ ውስጥ፡ ብሔራዊ በጀቱም ለታሰበለት ዓላማ ሊውል ስለማይችል፡ ተሸራርፎ እየተበላ፡ ለስሙ አንዳንድ ነገሮች ለሕዝቡ ተሠሩ እየተባለ፡ ባዶ የዕድገት አመላካች ቁጥሮች ብቻ ይለጠፉበታል። በበለጸጉት ሃገሮች፡ የከተማ አልሚዎች (Developers) አካባቢውን ለማልማት ኮንትራት ወሰዱ ወይንም መሬት ገዙ እንደተባለ፡ ትልልቅ ሕንጻዎች ይሠራሉ፤ የሚቀጥለው ነገር ድሆች ክዚያ አካባቢ ይፈናቀላሉ።

በዚያ አካባቢም የመሬት ዋጋ ሰማይ ይሰቀላል – ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ እንደ ሆነው ሁሉ። ዞሮ ዞሮ አልሚዎቹ ሳይውል ሳያድር ከፍተኛ ገንዘብ ያካብታሉ!የሕወሃትም የልማትና ዕድገት ዓላማ ከዚህ የተለየ አይደለም! በአብዛኛው አፍሪካ እንደሚታየው – ኢትዮጵያን ጨምሮ – ዕድገት ‘ይሆናል’ እንጂ ‘ሆኖአል’ የሚባል ነገር የለም!

በመሆኑም፡ ፖለቲካው፡ ሕጉ፡ ፍርድቤቱና ዳኞቹም በሕወሃት ኪስ ውስጥ ሆነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከድህነትና የኤኮኖሚ ጭቆና መላቀቅ መቻሉ በጣም አጠራጣሪ ነው – ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ለ2008 ከፍተኛ በጀት ($11.4 ቢሊዮን) ብትመድብና ከውጭም እስከ ዛሬ በታሪኳ አይታ የማታውቀው የውጭ ዕርዳታ ለሕወሃት አስተዳደር ተሳክቶለት እንዳለፉት ዓመታት ከፍተኛ ገንዘብ ቢፈስለትም!

እነዚህን አንቀጾች ሳሰፍር ትዝ ያለኝ በግንቦት 2010 ዓ.ም. ጋዜጠኛና ደራሲ Helen Epstein በNew York Review of Books ላይ “Cruel Ethiopia” በማለት የጻፉት አርቲክል ነው። በለጋሽ ሃገሮችም ይሁን በኢትዮጵያ አስተዳደር በኩል ራሳቸው የሚፈልጉትን ማድረግ እንጂ፡ በተለይ ሕዝቡ መንግሥታዊ ከበሬታን በማያገኝባት ኢትዮጵያ ውስጥ በልማትና ዕድገት ስም ምን ያህል አስተዳደሩ ሕዝቡን ዝቅ አድርጎ እንደሚመለከተው ነው!

  “The Western Renaissance helped to democratize “the word” so that all of us could speak of our own individual struggles, and this added new meaning and urgency to the alleviation of the suffering of others. The problem with foreign aid in Ethiopia is that both the Ethiopian government and its donors see the people of this country not as individuals with distinct needs, talents, and rights but as an undifferentiated mass, to be mobilized, decentralized, vaccinated, given primary education and pit latrines, and freed from the legacy of feudalism, imperialism, and backwardness. It is this rigid focus on the “backward masses,” rather than the unique human person, that typically justifies appalling cruelty in the name of social progress.”

በጀትን ትርጉም የሚያሳጣው፡ ለሕወሃት ሰዎች ዕድገት የግለሰቡ ሕይወት መለወጥ፣ የኅብረተስብ ማደግና በጋራ መበልጸግ ሳይሆን፡ ከላይ በተጠቀሰው መንገድ አስተዳደሩን የያዙት ሰዎች ከአልሚዎች (የራሳቸው ሰዎች) ጋር እየተመሣጠሩ፡ በዕድገትና ልማት ስም፡ እነርሱ ብቻ ሲፋፉ ይታያሉ። ይህ የዛሬው የኢትዮጵያ ሪአሊቲ ነው! ለዚህ ምስክሩ፡ ስለልማት ብዙ ማውራት የሚወደው የሕወሃት ዜና አገልግሎት ፋና ሚዲያ (ብሮድካስት) እንደመሆኑ፡ የሚያሳየው የሕዝብን ልማት የሚገለጽ እመርታ ስለሌው፡ አብዛኛውን ጊዜ የዜና አርዕስቶቹ፡ “ሊደረግ ነው” እንጂ “ይህ ተከናወነ/ ተፈጸመ የለም!”
 

III. አስተዳደሩና የኢትዮጵያ ሕዝብን የማይሳስተው የበጀት መለኪያ

  ሕወሃቶችና ተክሎቻቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ዝቅተኛና ደንቆር አድርገው ይመልከቱት እንጂ፥ ሕዝቡ በታክስ ስም በከፈላቸው ገንዘቦች፡ ምን እየተደረ እንደሆነ ጥሩ ዕውቀት አለው።

ጥያቄው፡ የዜጎች የብሔራዊ በጀት የኛነት የት ነው የሚጀምረው? ትክክለኛ የሕዝብን የሃገር ጥቅሞችን የሚጠብቅ ፖለቲካ፡ ተጠይቂነትን በየደረጃው ያጠናክራል። ስለሆነም፡ ተጠያቂነት ባለበት አሠራር፡ በጀት ወንጀልን ለመዋጋት የሚጠቅመውን ያህል፣ ተጠያቂነት በሌለበት አሠራር፡ መንግሥታዊ ወንጀሎችንም ያመቻቻል – ለምሣሌም ያህል የመሬት ቅርምትና የሕዝብ ንብረት ገፈፋ።

ዋናው ቁም ነገር፣ ከላይ ለተነሳው ጥያቄ፡ የተማረው፡ ያልተማረው ኢትዮጵያዊ፡ ፖለቲከኛ ወይንም ሃገረኛ፣ እያንዳንዱ ሰው መልሶቹን ጥርት አድርጎ ያውቃል! ይህም በዜግነታችን በግል ስናየው ሁኔታው ያስደስታል። አማንያንም፡ በሃይማኖት እንደተነገረው “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ”(ሉቃስ ወንጌል 20፡ 17) የሚለው አዕምሮአቸው ውስጥ እንዲመላለስ ማድረጉ አይቀርም!

ወላጅ ለልጁ ትምህርት ቤት መኖሩን ሲያይ፣ ልጁ ከቤት ወጥቶ/ታ መመለሱ(ሷ)ን ብቻ ሳይሆን፡ ተምሮለት/ተምራለት ያየ ቤተሰብ ልጆቹ ዕውቀት ማግኘታቸውን ያያል፣ ትምህርት ቤት አለ ይላል። በተመሳሳይ መንገድ፣ ሕዝብ በጤና ጉዳዮች፡ በመንገድ ሥራዎች፡ በግብርናና ውሃ አገልግሎቶች፡ ወዘተ… መስኮችም ተጠቃሚነቱንና በከፈለው የታክስ ገንዘብ ምን እንደ ተደረገ ያያል።

ፖሊስና ወታደር የሕዝብ ወገን መሆናቸውን አውቀው የሕዝቡን ሰላምና ደህንነቱን ሲጠብቁለት፡ የሃገር ዳር ድንበር ሲያስከብሩና ሕገ መንግሥቱን ከማናቸውም ፓርቲዎች ፖለቲካ ነጻ በሆነ መንገድ በተግባር መከበሩን ሕዝቡ ሲያይ፥ መንግሥት በፍትሃዊነት ሲያስተዳደርና ሲመራ፡ ሕዝብ ከ’መንግሥት’ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ለዜጎች እኩልነትና የጋራ ብልጽግና ሥራ ምን ጊዜም ተባባሪ ይሆናል። ስለሚከፈለው ታክስ ቅሬታ አይሰማውም፤ በፖለቲካም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱት ቅሬታዎች ምክንያት ክፋት ወይንም ተንኮል ወይንም መንግሥት እንዲደፋ አይተጋም። በአጭሩ፡ ይህ ተሠርቷል/አልተሠራም ለሚሉት ጥያቄዎች ሕዝቡ መልሶቹን ከሕወሃት ሳይሆን (አይታመንምና)፡ በቀላሉ ከዕለት ዕለት ሕይወቱ ማስረጃ ያገኛል።

በሌላ አባባል፡ ለዚህም ተብሎ በታክስ ስም ለሕወሃት አስተዳዳር የተከፈለው ገንዘብ በበጀት ተከፋፍሎ፡ ከላይ የተጠቀሱት ‘መንግሥታዊ’/የሕዝብ አገልግሎቶች ተግባሮች በሥነ ሥርዓት መከናወናቸውንና ያም ግንዛቤ በከተማዎች፡ በቀበሌ፡ ወረዳና ዞን ደረጃ፡ ገንዘቡ በሚገባ ሥራ ላይ መዋሉን ሕዝብ ምሥክርነት የሚያገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ ነው።

በአንጻሩ ደግሞ፡ ሕዝብ ያልተሠራ ነገር ሲያይ ቅሬታ ይኖረዋል። ሆኖም፣ በሃገራችን ያለው ‘መንግሥታዊ’ አስተዳደር በተለይም በዴሞክራሲና በብሔረሰቦች እኩልነት ስም ዘረኝነትና ብልግና በባለጌው ሕወሃት አስተዳደር እንደሚፈጸም ስለሚያውቅ – በጋራ ፍላጎት ድርጅቶች አማካይነት እንዳየጠይቅ እንኳ፡ ሕወሃት እንደመጥ እነዚህን የሲቪል ሶሳይቲ መዋቅሮችን አጥፍቶአቸዋል። በዚህም ምክንያት ሕዝቡ በልቡ ሲያደባ ነው የኖረው። የትኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ዛሬ ሕወሃትን በሃሰተኛነቱ ምክንያት ለማመን የማይቸገር?

ይህ በግንባሩ በሙሉ የሠረጸው የሃሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ፍቅር ደግሞ፡ ከፖለቲካ፡ ፍርድና ዳኝነት አንጻር የመጥፎ አስተዳደር ውጤት ብቻ ሳይሆን፡ ኢትዮጵያን በመጥፎ ሕግ፡ ድንብና ፖለቲካ ላይ የተመሠረተ አሠራር፡ በመጥፎ በጀት የገንዘብ አጠቃቀምና አስተዳደር ብልግናና የፖለቲካ ወንጀል ያለተጠያቂነት የሚፈጸምባት ሃገር አድርጓታል – በጀት ለፖለቲካ ሙስና፣ ጉቦና አፈና ይውላልና!

አፈና ደግሞ ወደ ግድያና ዘረፋ ያመራል። እንዲሁም፡ አፈናና ዘረፋ ወደ ሰብዓዊ መብቶች ጭቆናና ስብዓዊነትን ወደ ማዋረድ ወንጀል ያመራሉ – የኢትዮጵያ ታሪክ ላለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት በየቀኑና በየአጋጣሚው በተደጋጋሚ እንዳሳየን ሁሉ (ድንበራችን ለሱዳን ጥቅም መገፋቱ፡ ሊቢያ በታረዱት ወገኖቻችንን ሰቆቃ በመበሳጨት ሃዘናቸውን ለመግለጽ ሠልፍ የወጡት ዜጎቻችን ጭምር አዲስ አበባ ውስጥ ሕወሃት ያደረሰባቸው ጉዳት፣ ጭካኔና ውርደት፣ ደቡብ አፍሪካ በቁም ለተቃጠሉት ዜጎቻችን ያሳየው ጀርባ ሠጭነት፣ ገንዘብ ለማግኘት ማናቸውም ኢትዮጵያ ዛሬና ነገ የሚያስፈልጓትን ሁሉ ለራሱ መውሰዱ ወይንም ለባዕዳን መቸርቸሩ…) በቀላሉ የሚታዩ ወይንም የሚዘነጉ አይደሉም። እነዚህ ሁኔታዎች አደገኛ እንደ መሆናቸው፡ ኅብረተስብን እርስ በእርሱ ያናቁራሉ፣ ለጦርነቶችም ምክንያት ይሆናሉ። ሰንበት ሲልም፡ ፖለቲካው ለጥቅሙ ድንበር ዘለል ግጭቶችን መተዳደሪያው ያደርጋቸዋል።

የሕውሃትን ይዘትና ማንነትም በመግለጽ ረገድ፡ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ፓርላማ ልዑካን ቡድን (NATO) በጥቅምት 2010 መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያን በጎበኘት ወቅት (ከሬኮርዱ ለማየት እንደሚቻለው፣ ትግራይና አዲስ አበባን ብቻ ነበር የጎበኙት)፡ ትግራይ ውስጥ ብዙ ተዟዙራል። ከዚያም ከፍተኛ የሕወናት ባለሥልጥኖችንና በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ አንዳንድ ምሁራንን አነጋግሮ ከተመለሰ በኋላ ስለ ሕወሃት አደረጃጀትና አሠራር የጻፈው ሪፖርት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል:-

  “The government rules in a kind of commando fashion rather than building up strong governance institutions. This leads to a personalization of politics which raises important questions about the long-term sustainability of the current order.”

በዚያን ወቅት ይህንን የጻፉት ሰዎች ትንቢታቸው ተፈጻሚ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰናል – ሰሜን ኮሪያዎች እንደሚያደርጉት በሙት መሪ ስም ለመገዛት!

የጦር ቃል ኪዳኑ ልዑካን ኢትዮጵያን የጎበኘው፡ የአምስቱ ዓመት ልማት ፕላን ዝግጅት እንደተጠናቀቀ ቢሆንም፡ በወቅቱ ከሩቁ በትንቢታዊነት አምስት ዓመታት ቀደም ብሎ የደረሰበት ድምዳሜ ትክክለኛ ከመሆኑ ባሻገር፣ ያደረገው ትንበያ መስመር ይዟል።

ስለአምስቱ ዓመት ዕድገትና ልማት ፕላን – የእነርሱ የጥቅምት 2010 ግምገማ ትክክል ብቻ መሆኑ ሳይሆን – ዛሬ የተደረገ መምሰሉንና ሕወሃት በዕድገት ቁጥር አጭበርባሪነት ብዙ ሊያምታታ እንደሚችልና ይህም የሃገሪቱን ዕድገትና የኤኮኖሚ ፖሊሲዋን አጉጓል እንደሚያደርገው ነበር የሚከተለውን ትንበያ ያደርጉት፦፡

  “Unless Ethiopia experiences a very large increase in productivity, its current savings rate will be insufficient to underwrite the kind of growth it anticipates. Simply put, the numbers do not add up. There are concerns that if the country is unable to meet the targets laid out in the plan, the regime will be tempted to fudge the numbers and claim that achievements have been made when they have not been. This could distort economic and development policy.”

ናዚዎችም እስከዛሬ በተጨማሪ ተጠያቂ ከሚደረጉባቸው ወንጀሎች መካከል፡ ሙሰኝነት፡ ጉበኝነትና የሕዝብን ገንዘብ አላግባብ መጠቀም መሆናቸውን በ1987 እና 1999 ለሕዝብ ይፋ የተደረጉት (declassified) የናዚ ባላሥልጣኖች ላይ በ1945 ዓ.ም. በእንግሊዝና አሜሪካ ወታደራዊ አስተዳደሮች የተደረጉት ምርመራዎች መረጃዎች ያሳያሉ።

ለነገሩ፡ ሃገራችን ሕግ የማይከበርባት ሆና ነው እንጂ፣ አፈናና ዘረፋ በተናጠልም ሆነ በድምራቸው፡ ሁለቱም ዛሬም በብሔራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወንጀሎች ናቸው – ለምሣሌ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጾች 16-18, 28። ሌላው ዓለም (መንግሥታት፡ የተለያየ ዓላማ ያላቸው ድርጅቶች ወዘተ) በኢትዮጵያ የሕወሃትን አስተዳደር በሰብዓዊ መብቶች ረገጣ፡ በመናገር፡ መጻፍ፡ ማንበብና በሃይማኖትና መሰብሰብ ነጻነቶች ገፈፋ፡ ኢትዮጵያውያን ላይ ሰቆቃ (torture) በመፈጸም፡ በሃብት፡ ንብረትና መሬት ዘረፋ በሕዝብ መገናኛ መንገዶች በሙሉ ክስና ስሞታ በየጊዜው ሲያሰማ ከርሟል። ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ሌሎች ሃገሮች በዘመነ ሶሻል ቴኮኖሎክጂ (social media) ይሀ እንደምናየው ተስፋፍቶ ሕወሃትንና መሰሎቹን ከማጨለም ባሻገር፡ የምሥጢር ቋት እንኳ አሳጥቷቸዋል።

ይህ በእነርሱ ላይ የተቃጣው ክስና ስሞታ፡ ተጠፍጥፈውና ተጋግረው ሊበስሉ ያልቻሉት የሕወሃት ካድሬዎችና ቅጥረኞቻቸው ኃጢያቶቻቸውን ለመሸፋፈን እንደየሚያሰሙት፣ ኒኦ ሊበራሊዝም ወይንም የውጭዎቹ የኢትዮጵያ ጠላትነንትና በሃገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት አባዜ ምልክት አሰመስለውት በየቀኑ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያሰለቻሉ።

ሃቁ ግን፡ በዓለም ውስጥ የሰብዓዊ መብቶችና እያንዳንዱ ዜጋ ሊሰማው የሚገባ የደህንነት ስሜት (sense of security) እንዲጠናከር፡ በወል በተፈረሙ ዓለም አቀፍ የስብዓዊ መብቶች ስምምነቶች፣ ደንቦችና ሕጎች ደረጃ መደረግ የሌለባቸው ነገሮችን በሕጎቹና ደንቦቹ ተሳታፊ የሆኑ መንግሥታት በሌላው ሃገር መፈጸሙን ሰለማይቀበሉት ነው። ይህም International Covenant on Civil and Political Rights አንቀጽ 41 (a) ላይ እንደሚከተለው ተቀምጧል፦

  “If a State Party to the present Covenant considers that another State Party is not giving effect to the provisions of the present Covenant [ለሰብዓዊ መብቶች መሻሻል ማለት ነው], it may, by written communication, bring the matter to the attention of that State Party. Within three months after the receipt of the communication the receiving State shall afford the State which sent the communication an explanation, or any other statement in writing clarifying the matter which should include, to the extent possible and pertinent, reference to domestic procedures and remedies taken, pending, or available in the matter;

የሕወሃት አስተዳደር በንጉሡ ዘመን የወጣውንና ደርግ አልፈርምም ያለውን የ1966 ዓ.ም. ኮንቬንሽን ሕወሃት እንደመጣ ተንደርድሮ ቢፈርምም፡ ሕጎቹን በደንቡ ተፈጻሚ የሚያስደርጉትን ፕሮቶኮሎች በተለይም የ1976 ዓ.ም.ፕሮቶኮል (Optional Protocol to the International Covenant on Civil and Political Rights) አለፈርምም እንዳለ ቀርቷል። እንደማስታውሰው ከሆነ፡ በሕወሃት አስተዳደር ሥር ያለችው ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ግንቦት 6/2014 ሃገሪቱ በአምስት ዓመት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ የሰብዓዊ መብቶቿ አከባበር ለምርመራ በቀረበበት ወቅት፣ ፕሮቶኮሉን እንድትፈርም የውጭ መንግሥታትና ሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶች ከፍተኛ ግፊት የተደረገው ነበር (በ Universal Periodic Universal Review – UPR May 6, 2014)።

ይህንንም በተባበሩት መንግሥታት የስብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መድረክ ላይ በንግግር፡ አከታትሎም በደብዳቤ ኢትዮጵያ እንደማትፈርምና እንደማትቀበለው ሕወሃት ግልጽ አድርጓል። አሁንም ባለመፈረም እያጋጠመው ያለውን ተከታታይ ክስ፡ ስሞታና ወቀሳ ከዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ማምለጥ እንዳልቻለ እየታወቀ፣ ለምን ይሆን ሕወሃት መፈረሙን ላለመቀበል የወሰነው?

አጭሩ መልስ፡ ሕግጋቱ ሌሎች ሃገሮች እንደሚያደርጉት ሁሉ፡ ዜጎች በሃገራቸው መንግሥት ላይ በፍርድ ቤት፡ አለያም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግሥታት አካሎች ውስጥ ክስ ማቅረብ ያስችላቸዋል!፡ ሕወሃት የፈራው ችግር ምንደነው? Optional Protocol to the International Covenant on Civil and Political Rights በፈራሚዎቹ ላይ የሕግ አሰገዳጅነት አለበት፣ የሚከተሉት አንቀጾች እንደሚያመለክቱት፦

  Article 2

  Subject to the provisions of article 1, individuals who claim that any of their rights enumerated in the Covenant have been violated and who have exhausted all available domestic remedies may submit a written communication to the Committee for consideration.

  Article 3

  The Committee shall consider inadmissible any communication under the present Protocol which is anonymous, or which it considers to be an abuse of the right of submission of such communications or to be incompatible with the provisions of the Covenant.
  Article 4

  1. Subject to the provisions of article 3, the Committee shall bring any communications submitted to it under the present Protocol to the attention of the State Party to the present Protocol alleged to be violating any provision of the Covenant.

  2. Within six months, the receiving State shall submit to the Committee written explanations or statements clarifying the matter and the remedy, if any, that may have been taken by that State.

 

            ይቀጥላል………….
 

%d bloggers like this: