አፋርና ሶማሌ ክልሎች ለግብርና ኢንቨስትመንት ሰፋፊ መሬቶችን ለማዕከላዊ መንግሥት እንዲያሰረክቡ ተወሰነ!

25 Jul

የአዘጋጁ አስተያየት፡

  ይህ አስፈላጊው የሕግና መዋቅራዊ ሁኔታ ሳይኖር፡ መሬት ያላግባብ ከሕዝብ እየተሰባሰበ (እየተፈናቀለ) የሚፈጸመው በእውነትም ለሃገራችን ልማትና ዕድገት ቢሆን ኖር፥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተደሰተ ነበር። ነገር ግን በሌሎቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች እስከዛሬ እንዳየነው ከሆነ፡ ቀዳሚ ተጠቅሚዎቹ የሕወሃት ባለሥልጣናት፡ ቅጥረኞቻቸው፡ የእነርሱ ልጆች፣ ጓደኞቻቸው ናቸው። ከዚያ ካለፈም፡ ዞር ብለው በራሱ በሕወሃት አስተዳደር የሚስቁበት ባዕዳን ናቸው የኢትዮጵያን መሬት ተጠቃሚ የሆኑበት።

  ከሁሉም የከፋ፡ ሕዝባችን በፖሊስና በሚሊሽያ እየተደበደበ፡ በላዩ ላይ ቤት የሚያፈርስበት አስተዳደር፡ አረመኔ ነው!

  ባለፈው መጋቢት ወር በጋሞ ጎፋ፣ አልጌ ገበሬ ማህበር አካባቢ ያሉት የገበሬ ማህበር አባላት መሬታቸውንና ማሳቸውን ለቀው እንዲወጡ ሁለት የሕወሃት ብሄረሰብ ባለሃብቶች ከፖሊስ ጋር መጥተው በድንገት መሬታቸውን እንዲለቁ ሲጠይቋቸው፡ ገበሬዎቹ ንብረታቸውን ለቀው እንደማይሄዱ ቢገልጹ፡ ፖሊሶች ገበሬዎቹን ከመደብደብ ባሻገር፣ ተኩስውባቸው አንድ ሰው ሲገድሉ ሰባቱን ክፉኛ አቁስለዋቸውል።

  የሕዝቡን ጥቅም ጠባቂ መንግሥት በሌበት ሃገር፡ የእነዚህም ግለሰቦች ደም በከንቱ መፍሰሱ፡ ለአስተዳደሩ ስሜትም አልሰጠውም – ምናልባትም ፖሊሶቹን መዳልያ ሠጥቷቸው ሊሆን ይችላል!

  ሕወሃት የፈለገው፡ መሬቱ በአባያታ ሃይቅ አካባቢው ሆኖ፡ ለትምባሆ ምርት ምቹ ነው ስለተባለ፡ ሕወሃት (እና ቅጥረኞቹ) ዘመዶቹ የውጭ ምናዛሪ ለማግኘት እንዲችሉ (ምናልባትም አንዳንዶቹ ባለሥልጣኖች ወይንም ሚስቶቻቸው/ቅምጦቻቸው የጥቅም ተቀራማች እንዲሆኑ) በገበሬዎቹ ላይ መፈናቀል ብቻ ሳይሆን የጥይት እሩምታ አዘነቡባቸው!

  አሁንም አፋርና ሶማሌ ለሕወሃት ሰዎች ጥቅም ብዙ እንግልትና የመሬት ምዝበራ ይደርስባቸዋል። ይህም ሳይመጣ ለነገሩ ክፉኛ የተጎዱ ዜጎች ያሉባቸው አካባቢዎች ናቸው!

  የሃገራችን ዋናው ችግር፡ የፌዴራል አስተዳደርና ተፈጻሚ ሕግ በሌለበት፥ በሌሎች ሃገሮች እንደሚደረገው የሰብዓዊ መብቶች መከበር በክልል ደረጃ ትኩረት የሚሠጠው አለመሆኑ፥ ማናቸውንም ሁኔታ በቅርብ ማዕከላዊው መንግሥት ተከታትሎ የማያስተካክልበት አሠራር ለመልካም አስተዳደር ምንም አስገዳጅ ሁኔታ አይኖርም! በዚህም ምክንያት መዋቅሩ፡ የሌቦችና በጥቅም የተሳሰሩ የሚበለጽጉበትና በሥልጣን እንዲባልጉ ሁኔታ የሚያመቻች በመሆኑ፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስብዓዊ መብቶች፥ በመሃይምናን ወረዳ (ከዚያም በላይ ያሉት) አስተዳዳሪዎችና ካድሬዊች ይረገጣል። ችግር እንኳ ሲፈጠር፡ እነዚህም የሚያዙትና የሚቀጡት፡ የሕወሃትን (የራሳቸውንም) ጥቅሞችና ፍላጎቶች የነኩ እንደሆነ ብቻ ነው።

  ለምሣሌም ያህል፣ የአራት ኪሎው የቀበሌ ባለሥልጣን ነፍሰ ገዳዩ ግርማ ከበደ ‘ጸረ-አብዮተኞች’ እያለ ሰውን ከየቤቱ እያወጣ በሌሊት ሲረሽን፣ ደርግ የእርሱ ደህንነት የተጠበቀ መስሎት፥ ምንም አላለም ነበር። “አላርፍ ያለች ጣት…” እንዲሚባለው አንድ ቀን ሳይቸግረው በቀን ቢሮአቸው ድረስ ሄዶ፡ የመንግሥቱ ኃይለማርያም አጎት የሆኑት አቶ ዐሥራት ወልዴ – ያን ጊዜ የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በኋላም በሞስኮ አምባሳደር – ላይ እጁን በማሳረፉ፣ በእርሳቸው ምትክ – ‘የፍየል ወጠጤ’ ተዘፍኖበት – እርሱ ራሱ ተረሽኖ፣ ደርግ ቀይ ሽብርን ለመቀነስና ለማቆምም ምክንያት ሆኖታል!

  ዛሬም፣ በየክልሉ ያለው ዘረፋና የመብት ረገጣ ሊቆም የሚችለው፣ ሕወሃት ውስጡ የተሰገሰጉት ሌቦች ላይ እርምጃ ወስዶ ዐይኑን ወደ የክልሎች ሲያዞር ነው! የመልካም አስተዳደር ጅምር ይሆናል፤ የሃገር ልማት ተገቢውን ትኩረት ያገኝ ይሆናል – ምንም እንኳ በሕወሃት ሰዎች በዜጎችና በሃገራችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ውንብድናና ወንጀል ተወዳዳሪ ባይኖረውም!

  የእነጓዶች አረከበ ዕቁባይና ስብሃት ነጋ ወዘተ ልጆች (ሣሚ አርከበ እቁባይና ተከስተ ስብሃት)ና የነእነ ጓድ ቀ፣ በ፣ ወዘተ ሚስቶችና ቅምጦች በየቦታው ሁሉን ገፈታትረው በትዕዛዝ የይስሙላ ጨረታ የሚከፈትላቸው፣ ወይንም ሌሎች የሕወሃት ነገድ ያልሆኑት ምንም በቀላሉ መግዛት ወይንም መከራየት በማይችሉባት ሃገር፡ ያለፉት 24 ዓመታት ምዝበራ አልበቃ ብሎ አሁንም ለልማት እየተባለ መሬት ማሰባሰቡ፣ ሕዝብን ማሠቃየቱ ዓላማው የእነማንን ኑሮ ለማድለብ እንደሆነ ኢትዮጵያውያን አይጠፋቸውም!

  በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ውስጥና ዙርያ የተኮለኮሉት የሚፍጽሟቸው የደላልነት ሥራ፡ ‘መንግሥትና’ በእጁ ያሉት ሥልጣኖች በከበሬታ የማይታዩበት ሃገር ውስጥ ሆኖአል ኢትዮጵያውያን የሚኖሩት!

  አዲስ አበባ ሕወሃቶች መሬቱን ከኦሮሞች ዘርፈው፡ የመሬት ዋጋ ሰማይ ተሰቅሎላቸዋል፤ ያንን በጨረታ ወይም በቤት ሥራ ወዲያ ወዲህ እያገላበጡ ‘ዘላቂ’ የተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ አድርገውታል -ከቶኪዮና ኒውዮርክ በባሰ ዋጋ! የሶቭየት ዳቻ ይመስል፡ እነርሱም አዲስ አበባና መቀሌ ቪላዎቻቸውን ኮልኩለው (ካሊፎርኒያ ስታንዳርድ ይባላል አሉ)፤ አሁን ደግሞ ሃዋሳና ባህር ዳር ላይ ዐይናቸውን መጣል ጀምረዋል ይላል የሕዝቡ መረጃ!

  ዛሬ ዩኒቨርሲቲ የሚማረው ተማሪ፡ ለአንድ ሺህ ዓመት ገንዘብ ቢያጠራቅምም (ጥያቄው የእርሱ ወይንም የአርሷ ያን ያህል መኖር ሳይሆን፡ ከወር ወርስ መድረስ ይቻላል ሆኖ) ቤት ሊገዛና ከቤተሰቡ ጋር ተደስቶ የሚኖርበት ጣራ ምንጊዜም አይኖረውም/አይኖራትም – ሕወሃቶች ግን ሳይኖራቸው ጠመንጃ በማገላበጥ ብቻ በሃገር ሀብትና ንብረት የመሬቱ ከበርቴዎች ሲሆኑ! ይህ ወበዴው ሕወሃት በዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመ ግፍ ከመሆኑም በላይ፡ የመጭውንም ትውልድ ኑርና ሕይወት እንደ እንጦርጦሮስ ከወዲሁ አመሰቃቅለውታል! ይህም ራሱን የቻለ ወንጀል ነው!

  እዚህ ላይ ሕወሃት እንደእርሱ ዐይነት አዋቂ እንደሌለ 24 ዓመታት ሙሉ ጥሩንባ በኢትዮጵያውያን ላይ ሲነፋ ከርሟል። ታዲያ ለምን የራሱ የፖሊሲ ድንቁርና፡ ችግርና ብልግና እስካሁን እንዴት አልታየው አለ – ለዛውም በግፍና ዘረፋ ያካበቱትን ሃብት በዚህች ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም ለመባላት እንኳ ላይችሉ?

 
====================

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

አፋርና ሶማሌ ክልሎች ለሰፋፊ እርሻዎች የሚውሉ መሬቶችን ለፌዴራል መንግሥት ሊያስረክቡ ነው፡፡ መንግሥት ከእነዚህ ክልሎች መሬት ለመረከብ ያቀደው ከአምስት ዓመት በፊት ቢሆንም፣ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች መሬት የተያዘው በጎሳ መሪዎች በመሆኑ መረከብ አልቻለም፡፡

የአፋር ክልል ለግብርና ልማት የሚሆን መሬት ከጎሳ መሪዎች በመረከብ ለአልሚዎች እንዲውል ማድረግ የሚያስችል አዋጅ፣ ደንብና መመርያ አዘጋጅቷል፡፡ ክልሉ በአሁኑ ወቅት መሬቱን በመለየት ላይ ሲሆን፣ በአዲሱ በጀት ዓመት ያዘጋጀውን የክልሎችን መሬት በውክልና እንዲያስተዳድር ኃላፊነት ለተሰጠው ግብርና ሚኒስቴር ያስረክባል ተብሏል፡፡

በሶማሌ ክልልም እንዲሁ መሬት የተያዘው በጎሳ መሪዎች ቢሆንም፣ በክልሉ መንግሥት ለልማት የሚሆን መሬት መኖሩ ተረጋግጧል፡፡

ከክልሎች መሬት እየተረከበ ለባለሀብቶች የሚያቀርበውን የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ የሚመሩት አቶ አበራ ሙላት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኤጀንሲው በሚቀጥለው ዓመት ከሁለቱ ክልሎች መሬት መረከብ ይጀምራል፡፡ መሬቶቹን ወደ ልማት ለማስገባት ማነቆ የነበሩ ችግሮች በመፈታት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በእነዚህ ክልሎች በተለይም በአፋር ክልል የነበረው ችግር መንግሥት ያወጣው የመሬት ፖሊሲ ተግባራዊ ባለመሆኑ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው ቢልም፣ በአፋር ክልል አብዛኛው መሬት የተያዘው በጎሳ መሪዎች ነው፡፡ ይህ አሠራር መንግሥት ለአልሚዎች የሚያቀርበው መሬት እንዳይኖረው አድርጓል፡፡ የግል ባለሀብቶች ከጎሳ መሪዎች መሬት ተከራይተው ወደ ሥራ ሲገቡ፣ ባንኮች ብድር ስለማያቀርቡላቸው ከፍተኛ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ክልሎች በተለይ ለሜካናይዝድ እርሻ የተመቹ ከመሆናቸውም በተጨማሪ አዋሽ፣ ገናሌ ዳዋና ዋቢ ሸበሌ ወንዞች ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱባቸው በመሆኑ ጥጥ፣ ሸንኮራ አገዳና ሰሊጥ በስፋት ሊለማባቸው ይችላል፡፡

አቶ አበራ እንደገለጹት፣ ከእነዚህ ክልሎችና ቀደም ሲል መሥሪያ ቤታቸው ከቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ከጋምቤላና ከደቡብ ክልሎች የተረከባቸው መሬቶች በተለይ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ፕሮጀክቶችን ብቻ ለሚያቀርቡ ባለሀብቶች ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን መሥሪያ ቤታቸው ትኩረት የሚያደርገው ከዚህ በፊት ሰፋፊ መሬት ተረክበው በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ያልገቡ ባለሀብቶችን በመደገፍ ወደ ልማት ማስገባት ነው፡፡

መንግሥት 3.5 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ከክልሎች ተረክቧል፡፡ ከዚህ ውስጥ 2.3 ሚሊዮን ሔክታር ለአገር ውስጥና ለውጭ ኩባንያዎች ተሰጥቷል፡፡ ይህንን መሬት የወሰዱ 86 አገር በቀልና የውጭ አገር ኩባንያዎች ናቸው፡፡ መሬት ከወሰዱ ኩባንያዎች መካከል የሳዑዲ ዓረቢያ፣ የቻይና፣ የቱርክና የህንድ ኩባንያዎች ይገኙበታል፡፡ ነገር ግን ለኢንቨስተሮቹ ከተሰጠው 2.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ ወደ ልማት የገባው 840 ሺሕ ሔክታር መሬት ብቻ ነው፡፡

አቶ አበራ መሬቱን የማልማት ብቃት የሌላቸው ኩባንያዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ የማልማት አቅም ያላቸው ኩባንያዎችን ዳግም በመደገፍ ወደ ልማት የማስገባት ዕቅድ ተነድፏል ብለዋል፡፡
 
/ሪፖርተር
 

ተዛማጅ ጽሁፎች፡

  Building food security in Ethiopia work in progress; new phase of PSNP agreed for 2015 -2020

  The state of hunger & malnutrition in Ethiopia

  Forced relocations in Ethiopia bring hunger, hardship — Human Rights Watch reports; urges donors not to allow use of their funds

%d bloggers like this: