‘ድርቅ ገባ፣ እንስሳት እያለቁ ነው’ ሲባል ጠ/ሚ ተብየው ከካይሮ መልስ ቃለ መጠይቁ የሃገራችን “ፈጣን ዕድገት ዓለም ዓቀፍ ትኩረትን እየሳበ ነው” ብሎ ያልተጠየቀውን መዘላበዱ የተለመደው ሃሰቱ ድርቅን ያቆማል ብሎ ይሆን? ወይንስ በሥልጣን ለመቆየት ፕሮፓጋንዳዊ ማደንዘዥያ?

9 Aug

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

ውሸታምነት በሳል የአመራር ችሎታን የተካ ይመስል፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ውስጥ የተቀመጠው ግለሰብ በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያሰማው ቅጥፈት ብዙ ዜጎችን የሚያሳፈር ከሆነ ሰንበት ብሏል። አልፎም በአሁኑ ወቅት ድርቅን በመሸፋፈን፣ በዜጎች አኗኗርና ሕይወት ላይ አደጋ ወደሚያስከትልበት ደረጃ የተሸጋገረ ይመስላል!

የድርቅ አደጋ ሃገራችን ላይ ማንዣበቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነገር ከጀመረ ሰንብቷል። ከወራት በፊት በዚህ ብሎግ እንደገለጽነው ችግሩ አሳሳቢነት፡ ከሃገሪቱ ቆዳ ስፋት አንጻር የሸፈነው ነገር ነበር ያሳሰበን በዚያን ጊዜ ባወጣነው ካርታ እንዳሳየነው። የሕወሃት ባለሥልጣኖች ግን ስብሰባ አድርገው እነርሱም ችግሩን ሳያነሱት ቀርተዋል። እንዲያውም ከስብሰባው በኋላ በሰጡት መግለጫ “በኢኮኖሚ መስክ የህዝቡን ተጠቃሚነት ማዕከል በማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን የገመገመው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በመስኖ ሥራ የአርሶ አደሩ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እድገት የተመዘገበበት እንደሆነ አረጋግጧል”በማለት አልፎታል! ዛሬ ግን ችግሩ ብዙ ጉዳት የሚያስከትልበት ደረጃ ላይ ደርሷል!

The state of 2015 Belg production in Ethiopia (credit: fews.net)

The state of 2015 Belg production in Ethiopia (credit: fews.net)


 
ቅጥፈት የለመደበት ነገር ስለሆነ፡ አሁንም በሃገራችን ድርቅ ገባ ሲባል፡ ውሸትና ባዶ ፕሮፓጋንዳ መፍትሄ የሚሆኑ ይመስል፣ ከካይሮ ጉዞው መልስ የሕወሃት ማታለያና የማደናገርያ መሣሪያ በሆነው በፋና በኩል “ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ባለው ዕድገት ዓለም ዓቀፍ ትኩረትን እየሳበች መጥታለች” በሚል ርዕስ የተለመደውን ሃስት በሕዝባችን ላይ አርብ ነሐሴ 1/2007 ሲረጭ ነበር።

ነገር ግን፡ እጅግ አሳሳቢው የድርቁ ሁኔታና የእንስሳት በብዛት መሞትና ቀጥሎም የዜጎች ሕይወት በስፋት አደጋ ላይ መውደቁ ምንም እንዳልመሰለው፣ በግምት ሳይሆን ባነሳቸው ነጥቦች ግልጽ ተደርጓል!

ለነገሩ መሪዎች – በዲፕሎማሲ ተለምዶ እንደሚታየው – ለሥራ ጉብኝት ሂደው ወይንም በሌላ መንግሥት ጋባዥነት ውጭ ሃገር ሄደው፡ ሲመለሱ፥ በአየር ማረፍያ ወይንም በአንድ ሁለት ቀናት ውስጥ በቢሮዋቸው የጉዞዋቸውን ጭብጥ ለሕዝባቸው ያካፍላሉ። ከመረጃነቱ ባሻገር፥ ይህ ለአንድ ሃገር ሕዝብ እንደ ማስተማሪያም ነው! በዚህም መሠረት፡ ስለተጋበዙበት ሃገርና ስላከናወኑት ተግባርና ውጤቱ ለሕዝባቸው መረጃ የሚሰጡበት አጋጣሚ ነው።

በዚህ 36 የዜና አንቀጾች በያዘው የፋና አምድ እንደተመለከተው፣ ግለሰቡ ስለሄደበት የስዌስ ካናል ምረቃ ምንነትና ለምን የሚሉትን ጥያቄዎች አንዴ እንኳ አልነካም!

ይባስ ብሎ፡ አንዴ ኦባማን በመጥቀስ ወይንም ስለፈጣኑ የኤኮኖሚ ዕድገት እስክስታ በመውረድ፡ ሃገሪቷ ላሉባትና ሕውሃት እያባባሳቸው ላሉት የሃገሪቱ የኤኮኖሚ፡ የሰብዓዊ መብቶች፡ የዲሞክራሲና የፖለቲካ ችግሮች በሃሰት ማድበሽበሺያ አድርጎት እርፍ አለው!

ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው ሲናገር፣ ጉራም ገፍተር እያደረገው፡ ካይሮ የሄደው፡ ፕሬዚደንት አል ሲሲ “አራቴ ካልመጣህ” የምረቃው በዓል አጉል ይሆንብናል (በሽፍንፍን መንገድ) ብሎ ከጋበዘው በኋላ፣ ከካይሮ የስዌዝ ካናል መስፋፋት ምረቃ ላይ ተገኘቶ ሲመለሰ፣ ለጋዜጠኞች (በፋና ብሮድካስት) በሠጠው መግለጫ፣ “ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ባለው ዕድገት ዓለም ዓቀፍ ትኩረትን እየሳበች መጥታለች” በማለት መዓት ነገሮችን ሲነካካ፡ በሃገራችን ላይ እያንዣበበ ስላለው ድርቅ፡ ሰለብዙ እንስሳት በየአካባቢው መርገፍና የምግብ ዋጋ ክፉኛ ማሻቀብ መንግሥታዊም ሆነ አስተዳደራዊ ደንታም እንደሌለው በገሃድ አሳይቷል!

ሃገሪቱ ላይ ለ24 ዓመታት የተጋረጠባት ችግሮች እየተባባሱ፣ አሁን ደግሞ የድርቅ ችግር መስፋፋቱን ተከትሎ ጥልቅ በሆነ መንገድ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ፡ ወደዚያው እንደተለመደው ቅጥፈቱና ባዶ ፕሮፓጋንዳው ዘሟል!

በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኘው የአደጋ መካላከልና ዝግጁነትና የምግብ ዋስትና ዘርፍ በ2015 የሕወሃት አስተዳደር ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር 3.2 ሚሊዮን ብቻ ናቸው ብሎ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በአሥር በመቶ ቀንሶ ካቀረበ በኋላ፣ ከስምንት ወራት በላይ ከራሱ ገጽ እንኳ ጠፍቶ ከርሞ፡ ኢሣት የድርቁን ዜና ሣምንቱን ሙሉ ማስተጋባት ሲጀምር፣ አንዳንድ መረጃዎችን (ከውጭ የተገኙ) ሰሞኑን መለጣጠፍ ጀምሯል።

የሚያሳዝነው ግን ዕርዳታ የሚሹት ወገኖች ምንም ጠብ አላለላቸውም! በመሆኑም፡ የተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያ ከፍተኛ አደጋ እንደሚያጋጥማት ይተነብያል – በተለይም በመንግሥት በኩል በቂ ዝግጅት ባለመደረጉ! ከሰኔ ጀምሮ የገንዝብ ዕጥረት በመኖሩ፣ ዕርዳታ በተቻለ ፍጥነት ማድረስ አለመቻሉን ጠቁሟል።

እንዲያውም በድርቅ የተጠቁት ወረዳዎች ቁጥር በጠቅላላ ወደ 348 ከፍ ሲል (ክፍተኛ አንድ 97 – High priority I –፣ ከፍተኛ ሁለት – High priority II – 191፣ እና ከፍተኝ ሶስት –High priority III– 60)፣ የዕርዳታ ፈላጊዎቹ ቁጥር በዝቶ የሕወሃት አስተዳደርን ገጽታ እንዳይበላሽ አሁንም ሐምሌ 15 ለለጋሾች በተሰጠው የዕርዳታ ፈላጊው ሕዝብ ቁጥር ከ3.2 ሚሊዮን እንዳይበልጥ ተደርጓል!

በዚህም ምክንያት ከግንቦት ጀምሮ ከ348 መካከል፣ 97 ወረዳዎች ክፉኛ ለአደጋ የተጋለጡ በመሆናቸው ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጣቸው የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል። የእነዚህ ወረዳዎችም የክልል ክፍፍል እንደሚከተለው ነው፡-

  ኦሮሚያ 41

  ሶማሊ 15

  አፋር 13

  አማራ 13

  ትግራይ 7

  ደቡብ 6

  ጋምቤላ 2

እንደዚህ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥም መቻሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀድም ብሉ ትንበያ ይደረጋል። የዓለም ሕብረተሰብ ሊያደርግ የሚችለው፡ የተባበሩት መንግሥታት በOCHA (Office for the Coordination of Humanitarian Assistance) አማካይነትና በFAO ሥር ባለው በGIEWS (global information and early warning system on food and agriculture)፣ የአሜሪካ መንግሥት ደግሞ በUSAID በ1985 በተቋቋመው ዘመናዊ የሳተላይት ቴክኖሎጂዎችን በሚጠቀመው፡ በFEWS.net (the Famine Early Warning Systems Network) አማካይነት መረጃ በነጻ ያከፋፍላሉ። በተጨማሪም፡ ሃብታም መንግሥታት በግል በሚያካሂዷቸው ጥናቶች፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሚያካሂዷቸው operational ምርምሮችና ጥናቶችም ወዘተ፥ መረጃዎች ቀደም ብለው ይሰባሰባሉ።

(Credit: OHA)

(Credit: OCHA)


 
ለምሳሌም ያህል፣ FEWS.net ከጥር 2015 ጀምሮ የበልግ ዝናብ ሁኔታ ዘንድሮ መፎ እንደሚሆንና ኢትዮጵያን ከላይ እስከ ታች ለሁለት ክፍሎ ከትግራይ በሰሜን እስከ ደቡብ የምሥራቁ ክንፍ ብዙ አደጋ እንዳዣበበት ከላይ ባለው በመጀመሪያው ካርታ አማካይነት አሳውቆ ነበር። ይህ ብሎግም እዚያ የትንበያ መረጃ ላይ ተመሥርቶ በሰኔ ወር Failed Belg rains worsen Ethiopia’s food insecurity on wider basis; food prices escalate as TPLF stumbles by its lack of appropriate policies or money to feed the nation በሚል ርዕስ የራሱን ጹፍ ማቅረቡ ይታወሳል።

በተመሳሳይ መንገድ፣ ለምሣሌም ያህል FAO GIEWS ካለፈው ዓመት ሐምሌ 2014 እስከ ጀምሮ የነበረውን ወርሃዊ የሳተላይት መረጃ ለኢትዮጵያ ሐምሌ 2015 አስተላልፏል።

የተ.መ.ድም የሰብዓዊ ዕርዳታ ዘርፎች ብዙ ሣምታዊና ወርሃዊ መረጃዎች ሲያከፋፍሉ ቆይተዋል። የእነዚህም ዓላማ አንድ ነው። ተጎጅ ሃገሮች ቀድም ብለው በራሳቸው አቅም ክልል አስፈላጊውን እርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲወስዱ ለማስቻል ነው። ዛሬ ግን እንደፒላጦስ እጃቸውን አጣጥበው፡ እኛ የችግሩ ምንጭ አይደለንም፤ ዋናው ወንጀለኛ ኤልኒኖ ነው ሲሉ ይደመጣሉ!

በማንኛውም ሃገር ላይ የሚደርሰው አደጋ ከባድ ከሆነ፡ ዕርዳታ የሚያስተባብሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አሉ። ይህም በመሆኑ ለኢትዮጵያ መረጃው መፍሰስ የጀመረው ቀደም ብሎ ሲሆን፡ በአስተዳደሩ የተወሰደው እርምጃ ግን አጥጋቢ አለመሆኑን የተ.መ.ድ. ባለሙያዎች አልደበቁም።

ለምሳሌም ያህል የሚፈለገው ዕርዳታን ዕርዳታ በወቅቱ ባለማስተባበራቸው፡ በዚህም ምክንያት ዕርዳታ ባለመኖሩና በአስቸኳይ ባለመድረሱ፡ የሚከተሉት የዕርዳታ ዕጥረቶች ከሰኔ ጀምሮ መከሰታቸው ተገልጿል

  *   በምግብ ዕርዳታ በኩል የ51 ከመቶ ቀዳዳ (resource gap)

  *   በተመጣጠነ ምግብ (nutrition)፡ በኩል 41 ከመቶ ቀዳዳ (resource gap)

  *   በውሃ አቅርቦትና በተያያዥ የንጽህና ችግሮርች (WASH) 83 ከመቶ ቀዳዳ (resource gap)

  *   በግብርና 77 ከመቶ ቀዳዳ (resource gap)

  *   በጤና 84 ከመቶ ቀዳዳ (resource gap)

  *   በትምህርት 39 ከመቶ፡ቀዳዳ (resource gap)

 

በየመንገዱ ዳር በድርቅ የሚያልቁት እንስሳት ከፊል ገጽታ (Credit: ECADF)

በየመንገዱ ዳር በድርቅ የሚያልቁት እንስሳት ከፊል ገጽታ (Credit: ECADF)

አዲስ አድማስ በቅዳሜ ነሐሴ 8/2015 እትሙ ስለድርቁ አሳሳቢነት የሚከተለውን ምስክርነት ስጥቷል፡ –

  “ባለፉት ሁለት ወራት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው የዝናብ እጥረት የድርቅ አደጋ እንዳይከሰት ስጋት የፈጠረ ሲሆን ግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የዝናብ እጥረት ቢኖርም የድርቅ አደጋና የምግብ እጥረት ስጋት የለም ብሏል፡፡ በአፋር ክልል ግን ሁኔታው ተባብሷል፡፡ በየቀኑ እስከ 100 የሚደርሱ ከብቶች በመኖና በውሃ እጥረት እየሞቱ መሆኑን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡ የአፋር ክልልን አቋርጠው ወደ ጅቡቲ ወደብ ከሚጓዙ ሹፌሮች አንዱ ለአዲስ አድማስ እንደገለፀው፤ በመንገድ ዳርና ዳር በርካታ በጎችና ፍየሎች ሞተው ይታያሉ፡፡”

በሃገሪቱ የምግብ ዋጋዎች መናርም በከፍተኛ ደረጃ መሰተዋሉን የFAO መረጃ አረጋግጧል – ከዚህ በታች የተቀመጠው የአዲስ አበባ የቅይጥ ጤፍ የጅምላ ዋጋ ከጥር 2000 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 2015 አጋማሽ ድረስ የደረሰበትን የዋጋ ጣራ መመልከት ይቻላል!

የአዲስ አበባ የቅይጥ ጤፍ የጅምላ ዋጋ ከጥር 2000 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 2015 (Credit: FAO)

የአዲስ አበባ የቅይጥ ጤፍ የጅምላ ዋጋ ከጥር 2000 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 2015 (Credit: FAO)

እነዚህ የተጠራቀሙት ምክንያቶችና ታማኝ የሆነ አመራር ዕጦት ሃገሪቷን ለክፉ ነገር እያጋለጣት እያለ ነው፡ በውሸትና ሃስተኝ ፕሮፖጋንዳ የሌለውን ያለ ለማስመስል ብዙ ማጭበርበሮች በጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው የሚፈጸሙት። እስቲ ወደ ኋላ መለስ ብለን አንኳር የሆኑትን ቅጥፈቶቹን ለመመልከት እንሞክር።
 

ኢትዮጵያ በስንዴ ምርታማነት ከፍተኛ ውጤት አገኘች

በጥቅምት 2013 ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው አርሲ ሙኔሳ፣ ዲገሉና ጢጆ ወረዳዎች የሞዴል አርሶ አደሮችን የእርሻ ማሳ ከጎበኘ በኋላ “[ጠቅላይ ሚኒስትሩ] ባዩት ሁሉ በእጅጉ ተደምመዋል” ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ለሕዝብ አሰነብቧል። ዋናው ፍሬ ነገሩ በሃገራችን የእርሻ ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ በመድረሱ፡ አርሲ ውስጥ ገበሬዎች እስከ 111.5 ኩንታል/ሄክታር ስንዴ ማምረት ጀምረዋል በሚል፣ አካባቢውን ከጎበኘ በኋላ ነው “ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ስንዴ ሻጭ እንጂ ስንዴ ለማኝ አትሆንም”፤ “አፍሪካን እንመግባለን” ማለቱን ነበር ኢዜአ በወቅቱ የዘገበው።

ነገር ግን አንዴ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት በሚል ሳቢያ፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ነጋዴዎች የሚፈጥሩትን የአርቲፊሺያል የምግብ እህል ዕጥረት ለማቆም በሚል ሽፋን ኢትዮጵያ ቢያን በዓመት ሁለት ሶስት ጊዜ ስንዴ ከውጭ ማስገባቷን እንዳባባሰች ናት! በሃገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት እያለ፡ ባለፈው ጥቅምት ብሔራዊ ባንክ ሌሎቹን ፍላጎትችን ዘግቶ እህል ከውጭ ለማሰመጣት $600 ሚሊዮን መመደቡ ይታወሳል። ከዚያም ወዲህ ሌላ የግዥ ትዕዛዝ ተላልፏል!

በአጠቃላይ፡ ከ2009/10 እና 2013/14 የበጀት ዓመቶች 17.7 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በብር 15.5 ቢሊዮን ተገዝቶ ወደሃገር ገብቷል። የሚገርመው ነገር ምርታማነት ጨምሯል እያለ ሕወህትና ቅጥረኞቹ ሲደሰኩሩ፡ በውድ ዋጋና በብድር ወደሃገር የሚገባው ስንዴም ጨምሯል – እንደ ሃሜታው ከሆነ የሕወሃት ካድሬዎች በደቡብ ሱዳን በኩል ስንዴ፡ ስኳርና ዘይት ወደደቡብ ሱዳን በክንትሮባንድ እንደሚያሸጋግሩ ይነገራል!

ይህ ገጽም የግለስቡን ሃስተኛነት በተደጋጋሚ በመታዘብ፡ በየወቅቱ ለሕዝብ ሲያጋልጥ ቆይቷል። በነገራችን ላይ፡ የዚያን የአርሲን የምርት ባዶነት ዜና ባዶነት ይህ ገጽ ካጋለጠ በኋላ ዜናው ከኢዜአ ሰርቨር ተሠርዟል። ደግነቱ በወቅቱ ኮፒ ይዘን ስለነበር፡ ሕወሃት ቢያሠርዘውም፡ ኮፒው ግን በእጃችን ስለሚገኝ ከዚህ በታች በገጻችን ላይ ያለውን ቅጂ ሊንክ ለአንባብያን አቅርበነዋል

በተጨማሪም የሚገርመው ግለሰቡ – ኢዜአ እንደዘገበው – ለስድብና ለማሳጣት ችኩል በመሆኑ፣ የተበላሸ ፖለቲካ ደራሲ ሆኖ ሃገር ማመሱን አንዱ ‘የአመራር’ ዘይቤው አድርጎታል። ያን ጊዜም ስንዴ ተገኘ ብሎ የተናገረው ያንኑ ኢዜአ እንደሚከተለው አትቶታል፦

  “ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጉብኝታቸው ወቅት አስተያየታቸውን ለመስጠት ቀዳሚ ነበሩ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ከአነስተኛ ማሳ ላይ ከፍተኛ ምርት ማግኘት አይቻልም ለሚሉ ወገኖች አርሶ አደሩ ተግቶ በመስራት ይህን አፍራሽ አስተያየታቸዉን ዉድቅ አድረጎታል። የተገኘዉ ከፍተኛ የምርት ውጤት የአገሪቱን የግብርና ፖሊሲ ትክክለኛነት እንደሚያረጋግጥም አጽእኖት ሰጥተዉ ተናግረዋል።”

ይህ ብቻ አይደለም።
 

ኢትዮጵያ ከምግብ ዕርዳታ ተመጽዋችነት ከግንቦት 2014 ጀምሮ አቆመች ብሎ አወጀ

ግንቦት 20/2013 ሕወሃት አዲስ አበባን የያዘበት በዓል ሲከበር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው ከአዲስ አበባ ስታዲዮም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረገው ንግግር ከዛሬ ጀምሮ ኢትዮጵያ በምግብ ምርት ራሷን በመቻሏ ኢትዮጵያ የእህል ዕርዳታ አትሻም፤ አትቀበልም ማለቱ ይታወሳል። ለማስታወስም ያህል፣ ከተናገራቸው የሚከተለው ይገኝበታል፦

  “በዋና ዋና ስብሎች ምርት በ1983 ዓ.ም. 50 ሚሊዮን ኩንታል ያመርት የነበረው የህገሪቱ የእርሻ ምርት ዛሬ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ 250 ሚሊዮን ኩንታል በማምረት በሃገር አቀፍ ደረጃ በሁለት አሥርታት ጊዜ ውስጥ …በምግብ ራሳችንን ችለናል።”

በወቅቱ ግለሰቡ ለባለሙያዎች ስላቅና ለሕዝብ ትችት መጋለጡ ይታወሳል። በቅርቡም ፕሬዚደንት ኦባማ ኢትዮጵያ ውስጥ አጽዕኖት ካሳረፉባቸው ነገሮች አንዱ በምግብ ራስን መቻል ነው። በዚህም ረገድ ፕሬዚደንቱ ፋፋ ፋብሪካን ከጎበኙ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ በምግብ ራስን የመቻል አስፈላጊነት ትርጕሙ ግልጽ በሆነ መንገድ ለኢትዮጵያ እንደሚከተለው አንስተውታል፡-

  “…[W]ith Power Africa and all the initiatives that we’re putting forward, is to make sure that we are not in the business of just donating, but we’re in the business of creating entrepreneurs, opportunity, and capacity locally, so that over time, Africa –– we want Ethiopia not only to be able to feed itself –– we want eventually Ethiopia to be a food exporter as well.”

ከግንቦቱ የስቴዲየሙ ንግግር በኋላ፡ ይህ ገጽም The state of Ethiopian agriculture, prospects and pitfalls አቅርቦ ነበር። አንዱ መከራከሪያ ነጥባችን፡ ሃገራችን ውስጥ ካሉት ከ700 በላይ ወረዳዎች፡ 300 ያህሉ በምግብ ራሳቸውን አይችሉም ተብሎ በSafety Net program መደገፋቸውን በማስታወስና ለእነዚህም ከውጭ የምግብ ዕርዳታ እንደሚገባ፡ ወይንም ገንዘብ ለሕወሃት እየተሰጠ እህል እንደሚገዛ በማስታወስ ነበር።

በተጨማሪም በቅርቡ Productive Safety Net Project (PSNP) እስከ 2020 ዓ.ም. ድረስ የዕርዳታ ስምምነት ከዓለም ባንክ ጋር መፈራረሙ ይታወቃል። እዚህ ላይ ሊታወስ የሚገባው፡ የገንዘብና ልማት ሚኒስትር ሱፍያን አህመድ ሰኔ 2/2007 በፓርላማ የ2008 በጀትን ሲያስተዋውቁ ካደረጉት ንግግር ውስጥ –አሁን ካለው በምርት፡ ብድርም ሆነ በዕርዳታ የማይለበደው የብር 24 ቢሊዮን የበጀት ቀዳዳ (ጉድለት)መኖሩን ወደጎን ትተነው – ሃገራችን ምን ያህል በምጽዋት የምትኖር መሆኗን በመጠኑም ቢሆን የሚከተለውን ፍንጭ ሰጥተዋል፡ –

  “ከልማት አጋሮች በብድርና በዕርዳታ ይገኛል ተብሎ የተገመተው አጠቃላይ ገቢ ብር 38,693,999,465 ሲሆን’ ከዚህ ውስጥ ብር 24,558,091,510 በብድር’ እንዲሁም ብር 14,135,907,955 የሚሆነው ደግሞ በዕርዳታ መልክ የሚገኝ ነው፡፡ በቀጥታ ወደዯ መንግሥት ትሬዠሪ ቋት ከሚገባው የመሠረታዊ አገልግልቶች ድጋፍ ብር 6,676,272,000 በብድርና ዕርዳታ የሚገኝ ሲሆን’ ከዚህ ውስጥ ብር 1,074,372,000 የሚሆነው በዕርዳታ የሚገኝ ነው፡፡ ቀሪው ብር 5,601,900,000 ደግሞ በብድር መልክ ይገኛል ተብሎ የታቀደ ነው፡፡ ከጠቅላላ የውጭ ብድርና ዕርዳታ ውስጥ ብር 13,061,535,955 የሚሆነው በፕሮጄክቶች ዕርዳታ መልክ የሚገኝ ሲሆን፣ ቀሪው ብር 18,956,191,510 ፕሮጀክቶች የሚገኝ ብድር እንደሚሆን ተገምቷል፡፡”

በሌላ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ውስጥ የተቀመጠው ግለሰብ እንዳለው የማይሆንበት ምክንያት፡ በቢል ጌትስ የሚደገፈው የአፈር ምርምር ሥራ በዚያን ወቅት ባለመጠናቀቁ፡ እንዴት ይህ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ እንዳልሆነ ለማስታወስም ሞክረናል። ለምሳሌ በዚያን ወቅት መመርመር ከሚገባቸው 360 ወረዳዎች አፈሮች፡ መካከል በጽሁፋቸን እንደገለጽነው፣ የተጠናቀቀው የ162 ወረዳዎች ብቻ ነበር!

ያልነው አልቀረም። ኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት ርሃብ እንዳዣበባት የምትኖር ሃገር ናት – ሃገሪቱ ለመከተል በተገደደችው መጥፎ የአመራር ፖሊሲ፡ ሙስና፡ የመሬት ዘረፋ ችግሮችና ተገቢው በሕግ የሚከበር የመሬት ስሪት አለመኖሩ ቀዳሚ የችግሮች ምንጮች ናቸው!

ከሁለት ዓመት በፊት አርሲ ላይ ስለስንዴ ምርታማነት ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው ሲናገር የስጠው ምክንያት የሚከተለው ነበር፡

  “በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመኑ ግብርናውን ከወቅቱ ገበያ ስርአት ጋር የተሳሰረ ለማድረግ ዘመናዊ አሰራርን መከተሉ የተሻለ ተጠቃሚነትን ስለሚያረጋግጥ ሁሉም አርሶ አደሮች የሞዴል አርሶ አደሮችን ፈለግ መከተል እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ማርያም አሳስበዋል” ይላል ኢዜአ

ካለፈው ባለመማሩ፡ ዛሬም የተናገረው ተመሳሳይ ነበር:

  “አቶ ኃይለማሪያም እንዳሉት የአገሪቱን የመጀመሪያ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማሳካት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በቀጣዩ ዕቅድ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን አርሶ አደር ሞዴል አርሶ አደር ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ይሰራል፡፡”

ስለድርቁ ግን አንዳችም ትንፍሽ አላለም!

በአሜሪካ የሚደገፈው The Famine Early Warning Systems Network (fews.net) ሚያዝያ ላይ ቀደም ብሎ ማስጠንቀቂያ በመሰጠቱ፡ አስፈላጊውን ዝግጅት ከማድረግ ይልቅ – በሃገሪቱ በሠፊው የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም መፍትሄ ከመሻት ይልቅ – ሕወሃትና ቡችሎቹ ወደመደበቅና መሸፋፈን በማድላት ላይ ናቸው! ሌላው ቀርቶ የአሁኑ ድርቅ አፋርንም ከፊል አማራንና ትግራይን ማዕከላዊና ምሥራቅ ኦሮሚያን አንዲሁም ደቡብንና ሶማሌ ክልልን እንደሚያጠቃ መጠኑንም ድርጅቱ ተንብዮ ነበር።

ዜጎች እኩል ተጠቃሚ የማይሆኑበት ባለሁለት አሃዝ ዕድገት ሃገር ውስጥ ባለቤትነቱ እንዳይጎሳቀልበት – ዜጎች ሲታረዱና ሲቃጠሉ ደንታ የሌለው የሕወሃት አስተዳደር – እንስሳት በድርቅ ሲረግፉ ፍንክች ይላል ብሎ መጠበቅ የዋህነት መሆኑ ባያጠራጥርም፣ ብዙውን ሕዝብ ለረሃብ ሊያጋልጠውና ሊሸፋፍን ችላ ብሎ መመልከቱም ራሱን የቻለ ተላላነት ነው!

በነገራችን ላይ፡ ላለፉት ወራር ለምን ይሆን ወተት አዲስ አበባ ውስጥ የጠፋው? የሕወሃት አስተዳደር ሹምባሾች ድርቁ ሣርና ግጦሽን በማሳጣቱ ነው ይሉናል! ለመሆኑ ስንቶቻችን ነን አስተዳደሩ የኢትዮጵያን ከብቶች እያስራበ፡ ግጦሽ ወደሱዳንና መካከለኛው ምሥራቅ እንደሚልክ የምናውቀው? ይህንን አስመልክቶ የአሜሪካው Feed the Future በተዘዋዋሪ መንገድ ነካ አድርጎታል፡ The Ministry of Finance sets VAT on livestock feed – despite a critical feed shortage in Ethiopia, and the practice of exporting raw oil crops which is depriving the country of substantial quantities of oil cake feed.

በ2004/05 ኢትዮጵያ ብር 10 ሚሊዮን ግምት ያለው የእንስ ሳት መኖ ለውጭ ገበያ አቅርባለች፡ ማዕከላዊ ስታቲክስ ኤጀንሲ እንደዘገበው
 

Related articles:

  በመጭው ዓመት ኢትዮጵያ ከ6.5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ በግዥ ከውጭ ታቀርባለች – የምግብ ዋጋ ግሽበት 6.3% ሆኖ – ቁጥሩ ጤና ነውን?

  Ethiopia to become wheat exporter – ‘thanks to 1 x 5 system, instead of wheat beggar’ – PM Hailemariam!

 

%d bloggers like this: