ኖክ ኦይል ሊቢያን በብር450ሚ ገዛው፤ ለመሆኑ ኖክ የሚድሮክ ብቻ ወይንስ ሕወሃት ሰዎችም የጥቅም ተጋሪ ሆነው ሃገሪቱን በቁሟ እየቸበቸቡ ነው? የኖክ ስፋቱን መመልከቱ ብቻ ይበቃል!

13 Aug

የኖክ ሥር አስኪያጅ አቶ ታደሰ ጥላሁንና የሕውሃቱ ካድሬ አቶ አብነት ገብረመስቀል (ፎቶ ሪፖርተር)


 
Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

    *   የቡታጋዝ ዴፖና ሲሊንደር ማምረቻ ሊገነባ ነው

    *   የሞተር ቅባቶች ማቀነባበሪያ ሊያቋቁም ነው

አገር በቀል የነዳጅ ኩባንያ የሆነው ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) በጂቡቲ የሚገኘውን ኦይል ሊቢያ በ450 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ገዛው፡፡

ነሐሴ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋሽንግተን ሆቴል የኖክን ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አስመልክቶ በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጥላሁን፣ በጂቡቲ ቶታልና ኦይል ሊቢያ ለሽያጭ መቅረባቸውን ጠቅሰው ኖክ በሁለቱም ኩባንያዎች ላይ ተገቢውን ጥናት ካካሄደ በኋላ፣ ኦይል ሊቢያ ጂቡቲን ለመግዛት መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ ቶታል ጂቡቲን አንድ የፈረንሣይ ኩባንያ ገዝቶታል፡፡

አቶ ታደሰ ኖክ ከኢትዮጵያ ተሻግሮ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች (ጂቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያና ኡጋንዳ) ለመንቀሳቀስ ያቀረበውን ዕቅድ የኩባንያው ባለቤትና የቦርድ ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲ ማፅደቃቸውን ገልጸው፣ ይህንንም ለማሳካት በጂቡቲ ቅርንጫፍ ለመክፈት ላለፉት ሁለት ዓመታት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል፡፡

አቶ ታደሰ ለሪፖርተር እንደተናገሩት የጂቡቲው ኦይል ሊቢያ ጂቡቲ ውስጥ ስድስት የነዳጁ ማደያዎች፣ በጂቡቲ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከፍተኛ መጠን ያለው የአውሮፕላን ነዳጅ ማጠራቀሚያና መሙያዎች ባለቤት ነው፡፡ እነዚህን ንብረቶችና የኩባንያውን ጽሕፈት ቤት በአጠቃላይ ኖክ በ450 ሚሊዮን ብር ጠቅልሎ ገዝቶታል፡፡ በጂቡቲ የሚገኘው የኦይል ሊቢያ የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች ለአገሪቱ የሚያስፈልገውን 50 በመቶ ፍላጎት እንደሚያሟሉ፣ የአቪዬሽን ዲፖው በበኩሉ 70 በመቶ የገበያ ድርሻ እንዳለው አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

የግዢው ርክክብ እንደተፈጸመ የማደያ ጣቢያዎቹን ወደ ኖክ ዓርማ የመለወጡና ደረጃቸውን በኢትዮጵያ ከሚገኙት የኖክ ጣቢያዎች ጋር ተመሳሳይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ከፍተኛ በጀት መመደቡንና ቅድመ ዝግጅቱ መጀመሩን አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ማደያዎቹም በደረጃቸውም ሆነ በሚሰጡት አገልግሎት ዓለም አቀፍ ደረጃን እንደሚይዙ ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህ የኢንቨስትመንት ውሳኔ የተደረገው በኩባንያችን የቦርድ ዋና ሊቀመንበር በክቡር ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲ መመርያ ሲሆን፣ በተመሳሳይም በጎረቤት አገሮች ማለትም በደቡብ ሱዳን፣ በኬንያና በኡጋንዳ ገበያ ውስጥ ለመግባት ሒደቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሙሉ ድጋፍ ስለሰጡ እንቅስቃሴው በአጭር ጊዜ ይጀምራል፤›› ብለዋል፡፡

ኖክ ከ11 ዓመታት በፊት በ100 ሚሊዮን ብር ካፒታል 11 የነዳጅ ማደያዎችን በመክፈት ሥራውን የጀመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የነዳጅ ማደያዎቹ 150 ሲደርሱ ካፒታሉ ወደ 1.2 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ የኩባንያው አጠቃላይ ዓመታዊ ሽያጭ 30 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ በዓመት ከ177 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር እንደሚከፍልና ከ10,000 በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ የነዳጅ ሥርጭት ገበያ ውስጥ ከ40 በመቶ በላይ የገበያ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

ኖክ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ዘመናዊ የአቪዬሽን ነዳጅ ዴፖ በመገንባትና ዘመናዊ የአውሮፕላን ነዳጅ መሙያ ማሽኖች በመግዛት፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለሌሎች ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች አውሮፕላኖች ነዳጅ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህን አገልግሎት ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በጅማ፣ በአሶሳና በጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያዎች እየሰጠ ሲሆን በሰመራና በደሴ ተጨማሪ ዴፖዎች በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

በዱከም ከተማ በ50,000 ካሬ ሜትር ላይ ያስገነባው የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ ለአዲስ አበባና አካባቢው የሚደረገውን የነዳጅ አቅርቦት አስተማማኝ እንዲሆን እንዳስቻለ ያወሱት አቶ ታደሰ፣ በዚሁ ዴፖ ውስጥ የኢታኖል ማደባለቂያና የቡታ ጋዝ ማጠራቀሚያ፣ የሲሊንደር መሙያ ተቋም በከፍተኛ ወጪ አስገንብቶ ሥራ ላይ ማዋሉን አስታውሰዋል፡፡

ኖክ በአገሪቱ የሚታየውን የቡታ ጋዝ እጥረትና የዋጋ ንረት ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የቡታ ጋዝ ሲሊንደር ለመሙላት እስከ 500 ብር የሚያስወጣ በመሆኑ፣ አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ቡታ ጋዝ ከመጠቀም ታቅቧል፡፡ እንደ አቶ ታደሰ ገለጻ፣ የቡታ ጋዝ ዋጋ ሊንር የቻለው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ቡታ ጋዝ በአነስተኛ መርከብ የሚጓጓዝ በመሆኑ ነው፡፡ ጂቡቲ የሚገኘው የቡታ ጋዝ ዴፖ የማጠራቀም አቅሙ 700 ሜትሪክ ቶን ብቻ ነው፡፡ ወደ ጂቡቲ ወደብ የሚመጣው ቡታ ጋዝ በአነስተኛ መርከቦች በመሆኑ፣ ይህም የማጓጓዣ ወጪውን ከፍተኛ እንዲሆን ስለሚያደርገው ኢትዮጵያ ውስጥ የመሸጫ ዋጋውን ያንረዋል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ኖክ በጂቡቲ ወደብ ከፍተኛ መጠን ያለው ዘመናዊ የቡታ ጋዝ ዴፖ ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡

Abinet Gebremeskel

አብነት ገብረመስቀል በሕወሃት ስብሰባ ላይ

የኖክ ኩባንያ ባለድርሻና የቦርድ አባል የሆኑት አቶ አብነት ገብረ መስቀል ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከሞሮኮ ዘመናዊ የቡታ ጋዝ ማጠራቀሚያ፣ ማራገፊያና መሙያ ጣቢያ ግዢ በ20 ሚሊዮን ዶላር ተፈጽሟል፡፡ ሼክ አል አሙዲ በሞሮኮ ኮራል ሆልዲንግስ የተሰኘ ግዙፍ ኩባንያ ባለቤት ሲሆኑ ሳሚር ኦይል ሪፋይነሪ የተባለ ኩባንያም አላቸው፡፡ ጂቡቲ የሚተከለው የቡታ ጋዝ ዴፖ የተገዛው ከሳሚር ኩባንያ ነው፡፡ የቡታ ጋዝ ዴፖ መሠረተ ልማት በቅርቡ በመርከብ ተጭኖ ወደ ጂቡቲ እንደሚጓጓዝ አቶ አብነት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወደ ሞሮኮ ለጉብኝት በሄድኩበት ወቅት የቡታ ጋዝ ዴፖውን ተመልክቼ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጋዝ ችግር ስለማውቅ ለምን ወደ አገራችን አንወስደውም ብዬ አሰብኩ፡፡ ሳሚር ሁለት የቡታ ጋዝ ፋሲሊቲ ስላላቸው አንዱን ሸጠውልናል፤›› ብለዋል አቶ አብነት፡፡

ይህ ግዙፍ መሠረተ ልማት ጂቡቲ ላይ ከተተከለ ኢትዮጵያ ውስጥ የናረውን የቡታ ጋዝ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ማውረድ እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኖክ የቡታ ጋዝ ሲሊንደር ማምረቻ ለማቋቋም ማቀዱን አቶ አብነት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የሲሊንደር ማምረቻው የት ቦታ እንደሚቋቋም ገና በጥናት እንደሚወሰን የገለጹት አቶ አብነት፣ ለሲሊንደር ማምረቻውና ለቡታ ጋዝ ዴፖ ግንባታና ተከላ በአጠቃላይ 35 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ኖክ የሞተር ዘይትና ቅባቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ኩባንያው እስከዛሬ ሲያከፋፍል የነበረው ሼቭሮን የተሰኘው የአሜሪካ ኩባንያ ምርቶችን ሲሆን፣ በራሱ አቅም የሞተር ዘይትና ቅባቶች ማምረቻ አዲስ አበባ ላይ በማቋቋም የኖክ ብራንድ ምርቶችን በማምረት በኢትዮጵያ፣ በጂቡቲ፣ በኬንያ፣ በደቡብ ሱዳንና በኡጋንዳ ገበያዎች ለማከፋፈል ማቀዱን የገለጹት አቶ ታደሰ አስፈላጊው ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኩባንያቸው ከአገር በቀልነት ወደ ድንበር ተሻጋሪነት ሲለወጥ በተጓዳኝ ውስጣዊ አደረጃጀቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ በመከለስና በማሻሻል ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራር ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ታደሰ፣ ለዚህም ማሳያ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ተከላና የነዳጅ መግዣ ኤሌክትሮኒክ ካርድ መሠረተ ልማት ዝርጋታን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡

ኖክ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴና የነዳጅ ስርቆትን የሚቆጣጠር የነዳጅ ማመላለሻ ቦቴዎች መቆጣጠሪያ (Fleet Management and Cargo Tracking System) መሠረተ ልማት ለመዘርጋት በመስኩ ሰፊ ልምድ ካለው ግሎባል ትራኪንግ ቴክኖሎጂ ከተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር ውል ገብቶ ሥራውን በማቀላጠፍ ላይ እንደሚገኝ አቶ ታደሰ ገልጸው፣ በቅርቡ የምረቃ ሥነ ሥርዓት እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የጥሬ ገንዘብ ልውውጥን የሚያስቀር ዘመናዊ የሆነ የኤሌክትሮኒክ ካርድ ግብይት ሥርዓትን በመዘርጋት ላይ ነው፡፡ በተለያዩ የአፍሪካና የካረቢያን አገሮች የኤሌክትሮኒክ ካርድ ግብይት ሥርዓት በመዘርጋት ከሚታወቅ የሞሪሺየስ ኩባንያ ጋር ውል በመግባት ሥርዓቱ ተዘርግቶ መጠናቀቁን የገለጹት አቶ ታደሰ፣ የሙከራ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረው በመጪው ጥቂት ሳምንታት በይፋ ተመርቆ ሥራ እንደሚጀምር አስረድተዋል፡፡ ሁለቱ መሠረተ ልማቶች ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚመረቁ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የድፍድፍ ነዳጅ ማጣሪያ ግንባታን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ድፍድፍ የነዳጅ ሀብታቸውን ለአሜሪካ ሲሸጡ የነበሩ የምዕራብና የሰሜን አፍሪካ አገሮች አሜሪካ በነዳጅ ራሷን በመቻሏ ፊታቸውን ወደ እስያ ማዞራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እነዚህ አገሮች ምርታቸውን በእስያ የሚሸጡት ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር በመፎካከር ነው፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ በኬንያ፣ በታንዛኒያና በኡጋንዳ ነዳጅ እየተገኘ ነው፡፡ በኢትዮጵያም መገኘቱ አይቀርም የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ተባብረው ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ከምሥራቅ አፍሪካ የኢነርጂ ተቋማት ጋር መነጋገር ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ኖክ ኢትዮጵያ ውስጥ ነዳጅ በሚወጣበት ክልል የነዳጅ ማጣሪያ ለመገንባት ፍላጎት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

በነዳጅ ፍለጋና ምርት የመሰማራት ሐሳብ እንዳላቸው ተጠይቀው የነዳጅ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ ንግድ ዘርፎች እንዳሉት፣ ከፍተኛው የነዳጅ ፍለጋና ምርት፣ መካከለኛው የነዳጅ ማጣራት፣ የታችኛው ደግሞ የነዳጅ ምርቶችን ማከፋፈል ሥራዎችን እንደሚያካትት አስረድተው፣ የኖክ ክህሎት በመካከለኛውና ታችኛው ዘርፍ በመሆኑ በነዳጅ ፍለጋ ሥራ የመሰማራት ውጥን እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ ኖክ በአዲስ አበባ ያለውን የነዳጅ ጣቢያዎችን እጥረት ለመቅረፍ 15 ማደያዎችን ለመገንባት በማቀድ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ቦታ ጥያቄ ማቅረቡን ያስታወቁት አቶ አብነት በበኩላቸው፣ አስተዳደሩ ቦታውን ከሰጣቸው በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ አሥር የነዳጅ ማደያዎችን ለመገንባት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኖክ እ.ኤ.አ. በ2004 ዓ.ም. የተመሠረተ አገር በቀል የነዳጅ ኩባንያ ሲሆን፣ ሼክ አል አሙዲ ከፍተኛ ባለድርሻና የቦርድ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ የቦርድ አባል የሆኑት አቶ አብነትና የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ የባለቤትነት ድርሻ አላቸው፡፡
 
/ሪፖርተር
 

%d bloggers like this: