ሕወሃት የቴፒ ቡና ተክል ልማት ድርጅትን ለታደለ አብርሃ “ግሪን ኮፊ” በብድር ሸጠ: ከለገሬጂና ለገደንቢ አለመማር ወይንስ ጎሣዊ የጥቅም ትስስር?

17 Aug

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ አምስተኛ ቡና አምራች ብትሆንም፡ አብዛኝውን ራሷ ጠጥታ ስለምትጨርስ፡ ሕዝቡና ከድህነት ማለቀቅ አልቻለችም። የአየር መለዋወጥና ሃብታሞችና ፖለቲከኞች ቡናውንና መሬቱን ሲቀራመቱት ችግሩ የከፋ ይሆናል (ፎቶ ጄኒ ዊልያም/RBG Kew)

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ አምስተኛ ቡና አምራች ብትሆንም፡ አብዛኝውን ራሷ ጠጥታ ስለምትጨርስ፡ ሕዝቡና ከድህነት ማለቀቅ አልቻለችም። የአየር መለዋወጥና ሃብታሞችና ፖለቲከኞች ቡናውንና መሬቱን ሲቀራመቱት ችግሩ የከፋ ይሆናል (ፎቶ ጄኒ ዊልያም/RBG Kew)


 
በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

የኢትዮጵያ ቡና ብዙ ዐይነት አደጋ እያንዣበበት መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎች አሉ። በአንድ በኩል ቡናውን እንደ ተፈጥሮ የኅብረተሰቡ የጋራ ሃብት አድርጎ መቁጠርና መንከባከብ ሲገባ፡ ተገቢው ፖሊሲና አመራር ባለመኖሩ፡ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ አምስተኛዋ ቡና አምራች ሃገር መሆኗ ቢነገርም፡ ኢኮኖሚስቶች ደግሞ የሃገሪቱ ችግር አብዛኛውን ቡና እራስዋ የምትጠጣ በመሆኗ ከድኅነት መላቀቅ አለመቻሏን ይናገራሉ። በቡና ላይ የሚዞርበት ሟርት በዚህ ብቻ አያበቃም።

የቢቢሲ የዜና መጽሔት Saving coffee from extinction በሚል ርዕስ ግንቦት 24/2015 ላይ እንደዘገበው፣ ተወዳጁ የኢትዮጵያ አረቢካ ቡና በአየር ለውጥ ምክንያት አደጋ ላይ ነው ይላል።

የእንግሊዝ ሮያል ጋርደንስ (UK’s Royal Botanic Gardens, Kew) ጥናትን ጠቅሶ፡ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት አስፈላጊው የመንከባከብ እርምጃ ካልተወሰደለት ቡናው የሚወደውና ተመቻችቶ የሚያድግበት አካባቢ እስከ 85 ከመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ይተነብያሉ። በዚህም መሠረት ሃገሪቱን በመምራት ካለው ኃይል ጋር ሳይንቲስቶቹና ዓለም አቀፍ የቡና ኢንዱስትሪ ተወካዮች 25 ሺ ኪ/ሚ የቡና አካባቢዎችን በ2012 ጎብኝተው በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝ መንግሥት ዕርዳታ ከኢትዮጵያ ጋር በመመካከር ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።

አረቢካን ለመንከባከብ ከሚወሰዱት እርምጃዎች መካከል፡ በንእግሊዝ ባለሙያዎቹ ምክር መሠረት፡ ወደ ደጋው አካባቢ ቡናው ሊዘምት የሚችልበትን መንገድ ማስላትና መምከርን ይጨምራል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ በታች የሠፈረው የአዲስ አድማስ ዜና የሚነግረን የሕወሃት አስተዳደር፡ የቴፒን የተፈጥሮ አረቢካ ቡና ተክል ልማት ድርጅትን ለግሪን ኮፊ ባለቤት ለአቶ ታደለ አብርሃ በከፊል ብድር መሸጡን ነው።

ሃገራችንን የያዘው አስተዳደር ግራ የተጋባና ግራ የሚያጋባ ሆኖ፡ በየወረዳዎች ፋርማሲዎች ለመክፈት በሚዘጋጅበት በሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ ወቅት ይህንን ድርጅት በብድር መሸጡ፡ ቀናና ለሃገር ጥቅም ተብሎ የተደረገ መሆኑ አጠራጣሪ ነው!

ሃገራችን በዞረባቸው ‘መሪዎች’ መሣሪያነት ለገሬጂ የወርቅ ማዕድንን ይዛ መቆየት ሲገባት፡ ዛሬ ለሚድሮክ አሳልፋ በመሰጠቷ በዋጋ ከመጎዳቷ በላይ፡ ሚድሮክ ብቸኛ ወርቅ ወደውጭ ላኪ በመሆኑ እንደ ነጋዴነቱ የዓለምን የወርቅ ዋጋ ውጣ ውረድ እያየ ሆነ የሚያቀርብው። ስለዚህም ሃገሪቱ የምትጠብቀውን የውጭ ምንዛሪ እንኳ በሚፈለግበት ወቅት የማታገኝበት መሆኑ በ2013 በገሃድ ታየ!የአስተዳደሩ ሥራ፡ “መቼ ይሆን ዓሊወርቈን ወደ ገበያ የሚያወጣው” ተብሎ በር በር ማየት ሆነ!

ከዚያ በቂውን ትምህርት ያልተማሩት የሕወሃት ባለሥልጣኖች፡ አሁን ደግሞ የዚህ ዐይነት የቡና መሬት ለአንድ ወዳጅ በብድር ውሰድ ብለው አስተላለፉለት።

ለነገሩ መንግሥት ባለቤት ሆኖ የሚሠራቸው የንግድና የልማት ሥራዎች አይሳኩም። ለዚህም ዋናው ምክንያት የመንግሥት ተቀጣሪ የራሱ አድርጎ ሰለማይሠራና ነጋዴውም በምቾት ነገሮች እያማለለ ሙስና ባህር ውስጥ ሰለሚያሰምጠው ነው!

ስለሆነም መንግሥት ከእንዲህ ያለ የንግድና የልማት ሥራዎች መውጣቱን ብደግፍም፡ ቴፒ ላይ ግን ትልቅ ቅሬታ አለኝ።

አንደኛ አንድ አስተዳደር/መንግሥት በባለቤትነት ከቆየ በኋላ፡ በሽያጭ ማስተላለፍ ያለበት የውቅቱን የዋጋ ሁኔታ አይቶ መሆን አለበት። መንግሥት በብድር ሠጠ የሚባለው ነገር በተለይ በሕወሃት አስተዳደር ከኋላው ክፉኛ የሚሸት ነገር አለበት – ሙስናና የዘር ሃረግ ቆጠራ! ሁሉም ጊዜ እንዲህ ዐይነት ሽያጭ የተደረገላቸው የአስተዳደሩ ብሄረስብ ሰዎች ናቸው!

ዜጎች የሚጠይቁት፡ ለምን እነርሱ ብቻ በሃገሪቱ ሃብት ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው! የትኛው የኢትዮጵያ ሕግ ነው ይህንን የሚደግፈው? ዛሬ ባይቻል፡ ነገ በዚህ ላይና በተመሳሰሉት ላይ ተቃውሞ መነሳቱ ካለመቅረቱም በላይ፡ ወደኋላ መለስ ብሎ ሃገሪቷ ያጣችውን/የተዘረፈችውንም ማስመለስ አስፈላጊነት ሕጋዊ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል!የሰሞኑን ተከታታይ ቺሌ በቀድሞ ጂነራሎች ላይ እየወሰደች ያለችው የሕግ እርምጃ ልብ ሊባል ይገባል!

ከዚህ ዐይነት የመንግሥት ከገበያ መውጣት (divestment) አሠራር አንጻር፡ በብድር የሕዝብ ሃብትና ንብረት ማስተላለፍ ኃጢአትም ነው! የDeregulation እና state divestment አሰቸኳይ የብድርና ዕዳ ክፍይ አጣዳፊነት እስከሌለ ድረስ፡ እንደ አሁን ዐይነት እርምጃ መወሰዱ ትክክል አይደለም። ሎጂኩ መንግሥት ተራበ፡ ገንዘብ ቸገረው ነው እንዲሀ ዐይነት እርምጃ የሚያስወስድ። ያ አለመሆኑ የሚታየው፡ አስተዳደሩ የቴፒ ሽያጭ ገንዘብን አልፈለገውም፡ በብድር ስለሠጠው!

ጆን ኬሪና ታደለ አብርሃ (ፎቶ አዲስ ፎርቹን)

ጆን ኬሪና ታደለ አብርሃ (ፎቶ አዲስ ፎርቹን)

ለዚህ ነው ለአቶ ታደለ አብርሃ – ምንም እንኳ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ጋር ግንቦት 2014 ላይ ቡና አብረው ቢጠጡም፡ ኢትዮጵያ ሃብቷን ዝም ብላ ትወርውር ወይንም ጥቂቶች ይጠቃቀሙበት የሚል ሕግ የለም!
 

ከአዲስ አድማስ የተገኝው የዚሁ የቴፒ የቡና ልማት ዜና

ግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ፤ የመንግሥት ይዞታ የነበረውን የቴፒ ቡና ተክል ልማት ድርጅት በአንድ ቢ. ብር ጠቅልሎ መግዛቱን አስታወቀ፡፡

ቅዳሜ ረፋድ ላይ በሂልተን ሆቴል በተደረገው የሽያጭ ውል ስምምነት፣ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገ/መስቀልና የግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ አብርሃ ውሉን ተፈራርመዋል፡፡

አቶ ታደለ በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፣ ግሪን ኮፊ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት የቴፒ ቡና ተክል ልማት ድርጅትን ድርሻ 51 በመቶ በመያዝ፣ መንግሥት ደግሞ ቀሪውን 49 በመቶ ይዞ በሽርክና ለመሥራት ተስማምተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ 12 ሺህ ሄክታር ስፋት ያለውን የእርሻ ልማት፣ በ1 ቢሊዮን ብር እንደገለፁት አቶ ታደለ፤ የፊርማ ሥነ – ሥርዓቱ የተፈፀመው የዋጋውን 35 በመቶ፣ 265 ሚሊዮን ብር ባንክ አስገብተው ሲሆን ቀሪውን 65 በመቶ በ5 ዓመት ውስጥ ከፍለው ለማጠናቀቅ መስማማታቸውንም አስረድተዋል፡፡

12ቱ ሺህ ሄክታር መሬት ባረጁ የቡና ዛፎች የተሸፈነ ስለሆነ፣ ከ8-9 ሺህ ሄክታሩን የተሻለ ምርት በሚሰጡ አዳዲስ ዝርያዎች መተካቱን ጠቁመው፣ ቀሪውም በየዓመቱ 1000 ያህል ሄክታር በአዲስ ምርታማ ዝርያ ይተካል ብለዋል፡፡ ከእርሻ ልማቱ አጠገብ የጋምቤላ ክልል ይዞታ የሆነውን 3ሺህ ሄክታር መሬት ክልሉን ጠይቀው ስለፈቀደላቸው አዲስ ፕሮጀክት ቀርፀው እንደሚያለሙትም አቶ ታደለ አክለው ገልፀዋል፡፡

ከእርሻው የሚገኘውን የቡና ምርት ኤክስፖርት በማድረግ 20 ሚሊዮን ዶላር እንደሚገኝ የጠቀሱት ባለሀብቱ፤ እርሻው ለማር ምርት አመቺ በመሆኑ በዓለም ተወዳጅ የሆነውን ኮፊ ሀኒ የተባለ የማር ዓይነት በአነስተኛ መሳሪያ እያዘጋጁ ወደ ውጭ ሲልኩ ቆይተዋል፡፡ አሁን በብዛት (50 እና 60 ኮንቴይነር ኮፊ ሀኒ) ወደ ውጭ በመላክ ከ4-5 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ፋብሪካ እየገነቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የቴፒ ቡና እርሻ ልማት በረከት ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች እያመረቱ ለመላክ አቅደዋል፡፡ ብዙም ባይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ፓልም ኦይል የሚገኘው በቴፒ እርሻ ልማት ብቻ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ታደለ፤ ለሙከራ ከማሌዢያና ኢንዶኔዢያ የተለያየ ዝርያ አምጥተው በ120 ሄክታር መሬት ላይ በመትከል ምርቱ ደርሶ አይተውታል፡፡ በአነስተኛ መሳሪያ እያዘጋጁ በየወሩ አንድ መኪና ዘይት ለተለያዩ ድርጅቶች የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ወደ ዘይት ከመለወጡ በፊት ያለውን ድፍድፍ፣ የሳሙና ፋብሪካዎች በጥሩ ዋጋ በሰልፍ እንደሚገዙና በየወሩ አንድ መኪና ድፍድፍ እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡ የፓልም እርሻውን ወደ 10,000 ሄክታር ለማሳደግ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ኩባንያ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፣ የእርሻ መሬት ለማግኘት ከክልሉ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም አቶ ታደለ ገልፀዋል፡፡
በቴፒ እርሻ ልማት ውስጥ ባሉ 6 እርሻዎች፣ 16ሺ ሰራተኞች ተቀጥረው እንደሚሰሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
 
*Updated.
 

%d bloggers like this: