ጸረ-ኢትዮጵያዊ ኃይሎች፣ ጠባቦች፣ ሸፍጠኛ ታሪክ በራዦችና የፖለቲካ ቸርቻሪዎች ሕወሃት ውስጥ ተጠናክረው ወጥተዋል – ሌሎቹ ድርጅቶች ለሕወሃት ባለውለታ መሪዎች ጋር ቀጥለዋል!

26 Aug

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

ረዘም ላለ ጊዜ፡ ሕወሃት በአዲስ አበባና የመቀሌ ቡድን መከፋፈሉ ሲነገር ቆይቷል። እሳት የሌለበ ጭስ አይኖርም እንደሚባለው፡ ይህም አለምክንያት አልነበረም። አባይ ወልዱን እንደአባ ጨጓሬ ይጠሉት የነበሩት የሕወሃት ሰዎችም ሆኑ ሌሎቹ፡ በራሱ በትግራይ ውስጥ ከሚታየው አፈናና ዘረፋ ውጭ ሕወሃት ይህንንም በሌሎች አካባቢዎችም አስፋፍቶ ድርጁቱንና የሃገሪቱን ዘለቄታ አደጋ ላይ ጥሏታል የሚል ሥጋት ላይ ተመሥርተው ነበር።

አሁን እንደምናየው፡ በሃገሪቱ ላይ ያንዣበበው አደጋ አስተባብሮአቸዋል። ታሪክ ምስክር ከሆነ በ1966 ዋዜማ የታየው የለወጥን አሳማሚነት ለመቀነስ የተድረገውን የእንዳልካቸውን ካቢኔ መልካም ገጽ ለኢትዮጵያውያን ለማሳየት የተደረገውን ይመስላል ። ነገር ግን ደህንነቱ የበላይነቱ ስለተሰጠው፡ አሁንም ሕወሃት በቡጢው ለመግዛት የሚያደርገው ዝግጅት አሠራር ነው።

በሌላ አባባል፡ እነዚህ መጡም ቀሩ፡ ለነገሩ ለተጨቋኙ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕወሃት የትም ቦታ ሕወሃት የኢትዮጵያ ቋሚ ጠላትና ዘራፊ የወንበዴ ቡድን ነው።

ለማንኛውም በጠባብነት፡ ሸፍጠኝነትና ሙስና አፍቃሪነታቸውና ጸረ-ኢትዮጵያ አመለካከታቸው የታወቁት ሰዎች በተለይም እነ አርከበ እቁባይ፡ ስብሃት ነጋ፡ ብርሃነ ገብረክርስቶስ፡ ጸጋይ በርኸና መስፍን ሥዩም ወደ ድርጅቱ መራጭና ተመራጭ አባልነታቸው መመለሳቸው፡ ድርጅቱ በጥቃት ፊት እንሰባሰብ ያለ ይመስላል እንጂ፣ ጉባዔው በተለያዩ ንዑሳን ቡድኖች መካከል ያለውን የፖለቲካም ሆነ የጥቅም ሹክቻቸውን እንዳላሰወገደ ነው!

ከሥረ መሠረቱ ስንነሳ፡ ምላጩ ዲክቴተር መለስ ዜናዊ እነዚህን ግለሰቦች ለምን አሰወገዳቸው ለሚለው፡ መልሱ፡-

  አንደኛ ዲክቴተሮች ከእነርሱ የሚስተካከል ምላጮችን ስለማይፈልጉ ነው የሚለው መልስ ለግንዛቤ ይረዳል። ቀዳሚ ተሰላፊ በዚህ ረገድ አረከበ እቁባይ ብቻ ነው! ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ እዚህ ውስጥ ሊሰለፍ ቢችልም፡ በአንድ ጊዜ ብዙ ቦታ ለመሆን ዘወትር መሻቱ፡ ሙስናና አፍቅሮተ ሴት ሰብዓዊና ፖለቲካው ሚዛኑን ለረዥም ጊዜ ዘውሮበት ችግር ውስጥ መኖሩ ይታወቃል!

  ሁለተኛ፡ በቤተስበ ግጭትም ሆነ በአፉ ለከት ማጣት መለስ ስብሃት ነጋን አይፈልገውም ነበር! ከጊዜ ወደጊዜ በተለይም በጸረ-ኢትዮዮጵያዊና አፍቅሮተ ኤርትራዊነቱ – መለስ የሚያምንበት ቢሆንም – የስብሃት አፉ ቦታና ወቅት የማይመርጥ በመሆኑ ከጥቅሙ ይልቅ ጎጂነቱ ለመለስ ጉልህ ሰለነበረ በዚህ ምክንያት ያባረረው ሰው ነው!

  ሶስተኛ፡ ጸጋይ በርኸ የስለላው ወገን በመሆኑ፡ ድርጅቱ በመሉ የስለላ ክንፉን ማቀፉንና የጌታቸው አሰፋን አመራር ዘላቂነት ያሳያል። በነገራችን ላይ ጸጋይ የሚታወቀው ላለው ጭንቅላት ሳይሆን፡ ለጌታቸው አሰፋ ባለው ታማኝነትና በመልዕክተኛነት የማስተባበር ችሎታው ነው ይባላል።

  አራተኛ፡ ሥዮም መስፍን ሙስና ውስጥ በጣም የተጨማለቀ፣ ጠባብበነት ማዕከሉ የሆነው፡ ከብቃት ይልቅ ተላላኪነት ክብ ያስገኘለት ሰው መሆኑን ሕወሃቶችም ለወዳጆቻቸው ያንሾካሽካሉ! ውጭ ጉዳይ ውስጥ በዚህ የታወቀ ነበር። የደቡብ ሱዳን ሁለቱም ወገኖች የግለሰቡን ደካማነቱ ሳያበቃ የዞረበት መሆኑን በተደጋጋሚ ሲናገሩ፣ ተሳስተዋል ማለት ባይቻልም ‘በኢትዮጵያ በኩል’ ይህ ስህተት ነው ብሎ ምላስ የዘረጋ ባለሥልጣን እንኳ አልነበረም! ሥዩም ምቾት ይወዳል፤ ሰው እንደሚያከብር ያሳያል! በዲፕሎማሲና ፖለቲካ ኦርቢት ውስጥ ግን የሥልጣን ያዡ ሜጋፎንና ለቡድንና ለሃገር ሽክም መሆኑ ይከብዳል! 35 ዓመታት ያህል በድርጅትና የመንግሥት ዲፕሎማሲና ፖለቲካ ውስጥ ቢኖርም የራሱን አስተሳሰብ ያነጸባረቀበት ጊዜ ቢኖር – ጠቃሚና በሳል የፖለቲካ ሃሣብ ሣር ውስጥ የወደቀ መርፌ ስላልሆነ እስካሁን መታየት ነበረበት!

  ለመለስ ግን ንቆ እስኪታዘበው ድረስ ጠቃሚ ቱልቱላው ነበር!

  መለስ ግን እነዚህን ሰዎች በማንኪያው ሲያንደባልላቸው ለኢትዮጵያ አስቦ ሳይሆን፡ የራሱን ሥልጣን ለማጠናከር ነበር! ዛሬ ደግሞ በእነርሱ መመለስ ሕውሃት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጠብመንጃና የምዝበራ ሥልጣኑን ሊያጠናክርባቸው ወስኗል!

  ሁሉም ዕውር በሆነበት ሃገር ዐይኑ የሚያይ የሚመስለው የመኖሩን ያህል፡ ከመለስ ሞት በኋላ አዋቂያን ነን የሚሉት የሕወሃት ሰዎች ብዙ ናቸው። ሥዩም መስፍንም መጀመሪያ እንደሄደ ድምጹን አጥፍቶ ቆይቶ፣ ቻይና ውስጥ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከመሆነ ይልቅ የቻይና አምባሳደር እስኪመስል ድረስ በቴሊብቪዥናቸው ሰለቻይና ማንነት እንዲገልጽ ብዙ ጊዜ ተጋባዥ ሆኖአል።

  አሁን ደግሞ ሕወሃት ውስጥ በዲፕሎማሲው አንቱ የሚባል ባለመኖሩ፡ ሥዩም መስፍን የደቡብ ሱዳኖች አስታራቂ እንዲሆን ሕወሃት በኢጋድ ላይ ባለው የበላይነት፡ ሊቀመንበሩ እንደዱብዳ ወርዶበታል!

  እንግዲህ ዛሬ እነዚህ ግለሰቦች ናቸው እንደገና ኢትዮጵያን የሚያንገላቷት የሚግጧት! መታወቅ የሚኖርበት፡ ፊት ለፊት የዚህ የዚያ ጉዳይ ኃላፊ ባይባሉ እንኳ፡ ሕወሃት ብዙ ነገር የሚሠራው በስተጀርባ ስለሆነ፡ የእነዚህ ግለሰቦች ተጽእኖም ተግባራዊ የሚሆነው ከኋላ ነው!

  አቶ ዳዊት ገብረእግዚአብሄር (ፎቶ ሪፖርተር)

  አቶ ዳዊት ገብረእግዚአብሄር (ፎት ሪፖርተር)

  ሌላ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ነገር ባለሃብቱ ዳዊት ገብረእግዚአብሄር የፈጠረው አተካሮ ነው። የመቀሌን ቡድን ብዙ የመታው ቢሆንም (በነስብሃትና አርከበ ተጋፋፍቶ)፡ ከላይ እንደተገለጸው፡ ለሕወሃት ሰዎች ወቅቱ ብዙ የተጠሉና የተነከሱበት በመሆኑ፡ ለጊዜው ጦር ክተት ሰለታውጀ፡ እርሱም ሰላሙን መቀበል ይኖርበታል፡ የቅሰቀሳው ዘመቻ ብዙ ገንዘብ ቢያሰወጣውም! በነገራችን ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው የሚገባ ዳዊት ገብረ እግዚአብሄር – እንደ ብዙዎቹ የሕወሃት ሰዎችና ከአንዳንዶቹም የከፋ – ጠባብና ጸረ-ኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ነው!

 

ፎቶ ሪፖርተር

ፎቶ ሪፖርተር

በሪፖርተር፡ – በመተካካት ተሸኝተው የነበሩት የሕወሓት ነባር አመራሮች ተመለሱ

ከነሐሴ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በመቐለ ሰማዕታት አዳራሽ እየተደረገ ባለው 12ኛው የሕወሓት ጉባዔ፣ በመተካካት ተሸኝተው የነበሩ የሕወሓት አመራሮች በጉባዔው እንዲመረጡና እንዲመርጡ ተወሰነ፡፡ አዘጋጅ ኮሚቴው የጋበዛቸው ያለ ድምፅ እንዲሳተፉ ነበር፡፡

ከ1,650 በላይ ጉባዔተኞች በታደሙበት ጉባዔ የተገኙ አንድ ተሳታፊ ከዚህ ቀደም ተገፍተው የወጡ ያሏቸው ነበር አመራሮች በድምፅ እንዲሳተፉ ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ፣ በጉዳዩ ላይ የመከረው ጉባዔ በጭብጨባ በሙሉ ድምፅ ጥያቄውን ተቀብሎታል፡፡ በዚህም መሠረት ዶ/ር አርከበ እቁባይ፣ አቶ ስብሃት ነጋ (አቦይ)፣አምባሳደር ሥዩም መስፍን፣ አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ፣ አቶ ፀጋዬ በርኼን ጨምሮ 17 ነባር አባላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ጉባዔው በእስካሁኑ ቆይታው በአንደኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ በመልካም አስተዳደርና በመተካካት ላይ ተወያይቷል፡፡ በመልካም አስተዳደር እጦት ክልሉ እየተጠቃ እንደሆነ በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ በተለይ በአንድ የሃይማኖት አባት የቀረበው የመልካም አስተዳደር እጦት ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ የሕወሓት አመራሮች ድርጅቱ ቀድሞ አንግተውት የነበረውን ዓላማ እንደረሱ በአጽንኦት ገልጸው፣ ፍትሕ በገንዘብ እየተገዛ የክልሉ ሕዝብ የማያውቀው አዲስ ባህል በመጎልበቱ ይህንንም እንደሚዋጉት አመልክተዋል፡፡ ‹‹እሳት ያልፈራ ሕዝብ እናንተን የሚፈራ ይመስላችኋል?›› ሲሉም ጥያቄአቸውን አቅርበዋል፡፡ መተካካትን በተመለከተም ወደ መገፋፋት በመቀየሩ ያለ ዕድሜና አቅም ማነስ ዶ/ር አርከበና አምባሳደር ብርሃነ እንዲወጡ መደረጉን ተችተዋል፡፡ እንደ ድሮው መገማገምና አንዱ አንዱን ተጠያቂ ማድረግ በመሸፋፈንና በመጠባበቅ መቀየሩም ተገልጿል፡፡

የሕወሓት ሊቀመንበርና የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ዓባይ ወልዱ የቀረበውን ቅሬታ ተቀብለው፣ የተሠራ ነገር ቢኖርም ትልቅ ዳገት እንደሚጠብቅ ገልጸዋል፡፡ የአመራር አባላት ራሳቸውን ማጥራትና ወደ ራሳቸው መመልከት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር አርከበ በጉባዔው ንቁ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን፣ ሕዝቡ ቅሬታ እያቀረበ ያለው በፍትሕ አካላትና በፓርቲው አባላት መሆኑ አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ጉባዔው ዛሬ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ የሥራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም የቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን ይመርጣል፡፡

11ኛው የብአዴን ድርጅታዊ ጉባዔ በባህር ዳር በድርጅቱ ሪፖርት ላይ ተወያይቷል፡፡ ጉባዔው በክልሉ የተመዘገበውን የኢኮኖሚና ዕድገትና የግብር ምርት ውጤታማነት የገመገመ ሲሆን፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ 10.4 በመቶ በመድረሱ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ መቻሉ ተገልጿል፡፡ የመጀመርያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ መልካም አስተዳደር፣ ትምህርት፣ ጤናና ሌሎች መስኮችም በግምገማው ተካተዋል፡፡

መልካም አስተዳደርን በተመለከተና በሥራ ፈጠራ ጉድለቶች መኖራቸውን የገመገመው ጉባዔው፣ የክልል ከፍተኛ አመራሮችም ለችግሩ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ አውስቷል፡፡ የድርጅቱ ጉባዔ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የብአዴንና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን፣ የድርጅቱን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር በመምረጥ ማክሰኞ ምሽት ተጠናቋል፡፡ ማክሰኞ ምሽት የተመረጡት እነማን እንደሆኑ ግን አልታወቀም ነበር፡፡

ኢሕዴድ በአዳማ ከተማ 8ኛ ጉባዔው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል፡፡ በጉባዔው በክልሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ለማምጣት የሚችሉ አዳዲስ ሐሳቦች እንደ ግብዓት ሲሰባሰቡ እንደነበር ተገልጿል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በክልሉ የ11.2 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብና የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማፋጠን የሚያስችሉ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ተብሏል፡፡

የኦሕዴድን ድርጅታዊ ህልውና ይፈታተናሉ የተባሉት ትምክህትና ጠባብነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የተንዛዙ አሠራሮችና ፍትሐዊነት የጎደላቸው አመራሮች በጉባዔው ወቅት መነሳታቸው ታውቋል፡፡ ላለፉት ሦስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የኦሕዴድ ጉባዔ ማክሰኞ ምሽት ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ እየተጠበቀ ነበር፡፡

የደኢሕዴን ጉባዔ በሐዋሳ ማክሰኞ ነሐሴ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ተጠናቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሊቀመንበር ሆነው እንዲቀጥሉ ሲመረጡ፣ የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለምክትል ሊቀመንበርነት ተመርጠዋል፡፡ ጉባው በሦስተኛ ቀን ውሎው የመጀመርያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ገምግሞ፣ በምግብ እህል ራስን መቻል ላይ አበረታች ውጤት መገኘቱን ተወያይቶበታል፡፡

አበረታች የተባሉ ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ ይቀራቸዋል የተባሉት ላይ ደግሞ በተጠናከረ ሁኔታ ርብርብ እንዲረደረግ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ የጤናና የትምህርት ዘርፍ ተደራሽነታቸው መልካም መሆኑ ተወስቶ፣ የጥራት ጉዳይ ግን እንዲታሰብበት ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ጠባብነት፣ ብልሹ አሠራርና ሙስና በድርጅቱ ውስጥ ቦታ እንደማይኖራቸው ውሳኔ ላይ መደረሱ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የደኢሕዴንና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባላትም ተመርጠዋል፡፡ የተሟላ ዝርዝር ግን ማግኘት አልተቻለም፡፡

በተያያዘ ዜና የብአዴን ነባር ታጋይና ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ አዲሱ ለገሠ በክብር መሰናበታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ አቶ ዮሴፍ ረታም እንዲሁ ተሰናብተዋል፡፡ የደኢሕአዴን ሊቀመንበር፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆን ያገለገሉት ዶ/ር ካሱ ኢላላ እንዲሁ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት በክብር መሰናበታቸው ተገልጿል፡፡
 

%d bloggers like this: