ለምንድነው የሃገራችን ባለሥልጣኖች ባለጌ ሆነው ሕዝቡን ማዋረድ መብታቸው ወይንም የሥልጡንነታችው ምልክት የሚመስላቸው? ደኢህዴን ከላይ እስከታች በመረጃ ሲጋለጥ – መደመጥ ያለበት!

27 Aug

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

ከኢሣት የተገኘው ዜና እንደሚያመለክተው፣ በታደለ ቱፋ የተጻፈውን የጋሞን ህዝብ ማንነት የሚያንቋሽሸውን መጽሃፍ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው የሚመመራው የደቡብ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች የገንዘብ ደጋፍ በማድረግ አስጽፈውታል በሚል ምክንያት፣ በአርባ ምንጭና በተለያዩ የጋሞ ወረዳዎች የተቃውሞ ሰለፎች መደረጋቸውን ተከትሎ፣ በከፍተኛ አመራሩ እና በታች አመራሩ መካከል ያለው አለመግባባት ይፋ ሆኗል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደሴ ዳልኬ – ኢሣት እንደዘገበው – የጋሞ ጎፋ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የደኢህዴን ባለስልጣናት እጃቸው አለበት በሚል የሚያናፍሱት ወሬ ትክክል አይደለም በማለት፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች ጥፋታቸውን እንዲቀበሉ ጫና አድርገዋል። የወረዳ አመራሮች በተለይም የጨንጫ እና የአርባምንጭ የወረዳ አመራሮች ሂሳቸውን ወይም ጥፋታቸውን ለመቀበል ዝግጁ ካልሆኑ፣ የጥገኞች አስተሳሰብ አራማጆች ተብለው እንደሚፈረጁ በፕሬዚዳንቱ ተነግራቸዋል።

ማዳመጥ ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ ይክፈቱ
 
የወረዳ አመራሮች ከመጽሃፉ ጋር በተያያዘ “ህዝቡ ከአመራሩ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኗል” ቢሉም፣ የክልል መሪዎች” ሊቀበሉት ፈቃደኞች አልሆኑም። ፕሬዚዳንቱ መጽሃፉን ደኢህዴን እንደላስጻፈውና እንዲያውም ሁሉም የድርጅቱ መሪዎች ደራሲውን ማውገዛቸውን ገልጸዋል።

 ንጉሠ ነገሥት ተብየው ሕገ መንግሥቱን ሳይሆን ዙፋናቸውን ብቻ ለማስከበር ቀና ደፋ ሰለሚሉ፡ ጓደኞቻቸውና ጭፍሮቻቸውም ይህንን የፈረደበት ሕዝብ በየቀኑ እንርገጥህ ነው የሚሉት (credit: article.wn.com).


ንጉሠ ነገሥት ተብየው ሕገ መንግሥቱን ሳይሆን ዙፋናቸውን ብቻ ለማስከበር ቀና ደፋ ሰለሚሉ፡ ጓደኞቻቸውና ጭፍሮቻቸውም ይህንን የፈረደበት ሕዝብ በየቀኑ እንርገጥህ ነው የሚሉት (credit: article.wn.com).

የሚያስገርመው ነገር፡ ሕግን በመጣስ ረገድ አቶ ደሴ የራሳቸው ዲክቴተርነት (ከጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው የኮረጁት) በጉልህ በኢትዮጵያ ሕዝብ መሰማቱ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲህ ያለ ጸረ-ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብና አነጋገር በዚህ ዘመንና ወቅት እጅግ ይዘገንናል!

እርሳቸው እንደሚሉት ከሆነ፡ ግለሰቡ ሕጉ ፈቅዶለት ቢፈታ እንኳ፡ እርሳቸው እንደማይፈቱት ተናግረዋል። ይኼ ከፊውዳልም ፊውዳል አስተሳሰብ አይደል እንዴ?

ሃገሪቱስ በየቀኑ እየተዋረደች ያለችው ለዚህ አይደል እንዴ? ልጆቻችን ሃገራችን ውስጥ ሆነን – ለዚያውም ሥራ እንኳ በሌለበት – ተነስተው በረሃና ባህር እያቋረጡ ጉዳት ላይ እየወደቁ ያሉት?

ትዕዛዙ ከየትም ይምጣ ከየትም፡ ይህ በየቀኑ አዲስ አበባና ሌሎችም አካባቢዎች የሚታየው የሕግ መጣስ ጓደኛቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየውና ቀጣሪዎቹ የፈጽሙት አይደለምን? ይህስ ዜጎችን በግፍ በሸብርተኝነት ስም አሥሮ ማጉላላት ሕገ ወጥነትና ወንጀል አይደለምን?

ኢህአዴግ ባለስልጣናት ከህግ በላይ ወይም ከፍርድ ቤት በላይ መሆናቸውን አስመስከረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕወሃት/ኢሕ አዴግ የሚባለውን የጠብራሮች፡ የዘረፋ፡ የወንጀልና የሙስና ፖለቲካ ድርጅት ለምን እንደሚጠላቸው ይህ እንኳ ትምህርት ይሆናቸው ይሆን? ለአንድ ጊዜ ቆም ብለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ዐይነት ፍዳ ውስጥ እንደሆነ ለማየት ይረዳቸው ይሆን?

ድህነትና ርሃብ በሠፊው በተንሰራፋባት ሃገር፣ ዋናው የሕዝባችን ችግሮች አባባሹ፡ ጠግበው ግሣታቸውን መቆጣጠር ያቃታቸው ባለሥልጣኖች ናቸው!

የሃብታሙ አያሌውና የእሥር ጓዶቹ ሁኔታ (ሌሎችም ያልታወቁ እሥር ቤት ተዘግቶባቸው ሲቀጠቀጡ የሚኖሩት ኬዝ ጭምር) ከዚህ ጋር ያለው ዝምድና እንዳለው ለአቶ ደሴና የወንጀል ተባባሪዎቻቸው (ትዕዛዝ ሰጭዎቻቸው ጭምር) ይታያቸው ይሆን? ፍርድ ቤት አላግባብ ነው የታሠሩት ነጻ ናቸው ብሎ ካሰናበታቸው በኋላ፡ በተለይም እሥር ቤቱ ሃብታሙን ያለፈው አርብ ነሐሴ 21/2015 መልቀቅ ሲገባው፣’መለያየት ሞት ነው’ የሚል ይመስል፡ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ጥሶ እሥሩ ቀጥሏል መንግሥትና ዳኝነት በሌለባት ሃገር!

ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ልምን አይታያቸውም?

የሕወሃት/ኢሕአዴግ ሰዎች በፖለቲካ ሽንገላ የተሰሉ እንደመሆናቸው፡ ለሃገርና ለወገን የሚያስቡ ይመስል፡ አቶ ደሴም – ኢሣት እንደዘገበው – እንዲህ አሉ:-

“ይህ አንድ መጽሃፍ እርስ በርስ እንድንጠራጠርና እንዳንተማመን ካደረገን፣ እስከዛሬ አብረን የተጓዝነው ጉዞ የውሸት ነበር፡፡” ሲያብራሩም፡ መጽሀፉ የድርጅቱን መዋቅር እንዲፈትሹ እና የደኢህዴንን የድርጅት ጥንካሬና በአመራሩ መካካል ያለውን መተማመንና መደጋገፍ እንደገና እንዲመረምሩ እንዳስገደዳቸው ገልጸዋል።

ፕሬዚደንት ደሲ ዳልኬ (ፎቶ፡ ከደአሕዴን)

ፕሬዚደንት ደሲ ዳልኬ (ፎቶ፡ ከደአሕዴን)

የአቶ ደሴ ዳልኬ ሃቀኝነታቸውና ትልቅነታቸው መለኪያው፡ ተሳስቻለሁ ብለው፡ ሲያንገላቱና ሲያፋጁት የነበሩትን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ ነው! ቀጥለውም፡ የፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲከበር ከፍተኛ ትግል አካሂደው፡ በየምክንያቱ ((በዘር በመከፋፈል፡ እርስ በእርስ በመናናቅ፡ በሃዋሣ ከተማነት ዙሪያ የደማውና የሞተው ሕዝብ ቁጥር ያስከተለው ውጥረት ውስጥ ለውስጥ አሁንም ስለሚንተከተክ ወዘተ) የደቡቡ የሃገራችን ክፍል በከንቱ የሚሠቃየውን ሕዝብ ከእሥር ለቆ፣ አበረታቶ መደገፍና መንከባከብ ነው!

የመሬት ምዝበራውን ማቆም ነው! ወጣቶችን ቀንና ማታ ማሳደዱ መቆም አለበት!ብዙ ወጣቶች እስከዛሬ በጥርጣሪና መታወቂያ የላቸውም በሚል ሚያዝያ 2014 የታሠሩት እስካሁን በእሥር ላይ ናቸው!

በመጨረሻም የክልሉን ፕሬዚደንት ሳላስታውሳቸው የማላልፈው፡ የሳይንስ ሰው በመሆናቸው፡ ከደቡብ ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ፍሰሀ ጋረደው ጋር በመተባበር፡ ከምርጫው አንድ ሁለት ወር ቀድም ብለው ወንጀል ሲፈጸም፣ ፍርድ ቤቶችን ወደጎን በመተው ከሚመስሉዎት ዳኞች ጋር በመሆን ዳኝነት በስልክ እንዲሰጥ መስማማቶን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)ሚያዝያ 3/2007 መዘገቡ ነበር ብዙዎቻችን ያስደነገጠን!

በዚህም ምክንያት The Ethiopia Observatory (TEO) ላይ “ኢትዮጵያ ውስጥ እስርና ፍርድ በስልክ ተጀመረ! በምርጫው ጊዜ የሕወሃትን ክንድ ለማጠናክር የታሰበ ዝግጅት ይመስላል!” የሚል ጽሁፍ ሚያዝያ 12 ለማውጣት ተገደን ነበር!

እንዲህ ደንበርበር ያለዜና ሲጠቀስበት፣ ኢዜአ ከስርቨሩ ላይ ዜናዎች መሠረዝ መጀመሩን ስለደረስንበት፣ እኛ ለታሪክ ምስክርነት የዚህን ዜና ኮፒ በፋይላችን ይዘነዋል። ዋናው ሃሣቡ ሕዝቡ ወንጀል ተፈጽሟል ብሎ ሲያምን፡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከመምጣት ይልቅ ባለበት ሆኖ በስልክ መስመር /8595) ቢደውል፡ ወንጀለኛ በአንድ ቀን ውስጥ ፍርድ እንዲያገኝ ለማስቻል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ዝግጅት ማድረጋቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ይህ ምን ታስቦ እንደመጣ እናውቃለን! በምርጫው ወቅት ካድሬዎች በመደዋውል የሚፈልጉትን ለማሣሣር የተዘጋጀ ዘዴ ነው። እንድጋጣሚ ሆኖ፡ የደቡብ ክልል ብዙ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የተደበደቡባትና ከታሠሩባቸው ግንባር ቀደሞቹ መካከል መሆኗ ይታወሳል!

ያመልጣቸውና ክልሉ የሚታወቀው፡ (ሀ) ከቀበሌ ጀምሮ ሕዝቡ በጥለቀት የተደራጀ መሆኑንና የወንጀል መከላከል ኮሚቴ አሰራር መኖሩን ይናገራሉ (ለ)ሕዝቡ የማኅበረሰብ ወንጀል መከላከያ ኃይል በየደረጃው መቋቋሙን ያስረዱናል። ወንጀልን ከሕዝብ ጋር ተባብሮ መዋጋት እጅግ ጠቃሚ አሠራር ነው!

በጸረ-ሽብር ሕጉ እንደታየው፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕወሃት ሕግጋትን ደንቦች ለተራው ሕዝብ የተዘጋጁ፡ ባለሥልጣኖች ላይ ተፈጻሚነት የሌላቸውና በከሰረው ፖለቲካ ምክንያት ንጹሃን የሚሰቃየበት በመሆኑ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደኅንነት ፋይዳ አይኖረውም!

ማን ጠበቀ፡ ለምሣሌ፡ እንደ አቶ ደሴ ዳሌ የተማረ ስው በሕግ መንግግሥቱ አንቀ 19 መሠረት፡

    “የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲይምኑ አይገደዱም። በማስገደድ የተገኘ መረጃ ተቀባይነት አይኖረውም።”

ታዲያ፣ ክቡር አቶ ደሴ ዳሌ ለሕግ እስረኞች ይህ የሕግ ጠለላ መኖሩን እያወቁ፡ ለምን ይሆን እርሳቸው ከሥራ ባልደረቦቻቸው፡ በሥልጣን ማስፈራራት፡ በፖለቲካ የውስጥ አሠራርና በግለ ሂስ ማስፈራሪያነት ይህንን መብት ለመግፈፍ የመረጡት?

በመጨረሻም፣ ቴክኖሎጂ ዲሞክራሲን የሚደግፍ ፕሮግሬሲቭ ኃይል በመሆኑ፡ ዲክቴተሮች በሥውር አንድ ነገር ሠርተን አይታወቅብንም የሚለውን አስተሳሰብ ሊቀይሩት ይገባል – ሕዝባቸው ላይ እየተፉ ዘመነ ጥፋትን የሚጠብቁ ካልሆነ በስተቀር!
 

%d bloggers like this: