ሕወሃት መራሹ ኢሕአዴግ መቀሌ ላይ በወሰደው የፖለቲካ ውሳኔ ምክንያት ሃገራችን አንድ ግዙፍ እርምጃ ወደኋላ ትራመዳለች

31 Aug

በከፍያለው ገብረመድኅን – Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

መቀሌ በመካሄድ ላይ የነበረው አሥረኛው የኢሕአዴግ ስብሰባ “ሕዝባዊ አደራን በላቀ ዕድገትና ትርንስፎርሜሽን” ፖለቲካዊ፡ ኢኮኖሚያዊ፡ ማኅበረ ስብዓዊ፡ ድርጅታዊ፡ ልማታዊ፡ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ተግባራት አፈጻጸሞችን ከገመገመ በኋላ፥ እንደ ተጠበቀው ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው በያዘው ድርጅታዊ ሊቀ መንበርነትና አስተዳደራዊ አመራር ከአቶ ደመቀ መኮንን ጋር በሥራቸው እንዲቀጥሉ ወስኗል።

በዚህ ጽሕፈት ወቅት ሙሉ የጉባዔውን ውሳኔዎች ማግኘት ባይቻልም፡ ከሕውሃት ዜና አውታር እንደተመለከትኩት፡ ዋነኛው የጉባዔው ውሳኔ “ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በስኬት ለማጠናቀቅ ርብርብ በማድረግ የኢትዮጵያ ህዳሴን ዕውን ለማድረግ በላቀ ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ” እንደሚገባ ከመወሰኑ ባሻገር፣ ትኩረት ባገኙት ጉዳዮች ዙርያ ሌሎች ሁለት ውሳኒዎችም ይታያሉ፦

      (ሀ) ከመሬት አስተዳደር፣ ንግድና ፍትህ ጋር ተያይዞ የሚፈጸመውን የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ለማስወገድ ህዝቡ እንዲታገል ማድረግ የሚያስችል ርብርብም እንደሚደረግ

ስምምነት ላይ ተደርሷል

(ለ) የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታትም የሞት ሽረት ትግል ይደረጋል ብለዋል

ካለፉት ስበሰባዎች ሁሉ አሥረኛውን ጉባኤ አነጋጋሪና በጣም አሳዛኝ የሚያደርገው፣ ገዥው ፓርቲ ምን ያህል በሕዝብ የተጠላ መሆኑን መገንዘቡ ብቻ ሳይሆን፡ ሕገ መንግሥቱ በደነገገው መሠረት ሕወሃት መሩ ኢሕአዴግ አንዴም በብቃት ሃገሪቱን ለማሰተዳደር አለመቻችሉን ተገንዝቦ፥ ቢቻል ሁሉንም ነገር እንደ አዲስ ቢጀምር ምን ያህል ይደሰት እንደነበረ ከጉባዔው ውይይቶች ለመገንዝብ መቻሉ ነው!

ሌላው ቀርቶ የጉባዒው ታሳታፊዎች የሆኑት ካድሬዎች ድርጅታቸው ሙሰኛ፡ ጉረኛና በባዶ ፕሮፓጋንዳ የሚደነፋ የኪራይ ሰባሳቢዎች መረብ መሆኑን በግልጽ በጉባዒው ላይ መናገራቸውን ከረድዋን ሁሴን የነሐሴ 24/2007 ለጋዜጠኞች የተሰጠ መግለጫ “የመልካም አስተዳደር ችግር ሁሌም ችግራችን ነው እያልን ከመቀጠል ይልቅ ልማቱን በማፋጠን ችግሩን ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅረፍ መሠራት እንደሚገባው” ነው ጉባኤው ላይ የተነሳው” ማለቱ ነው።

ያም ሆኖ ሃገሪቷ ምንም ዐይነት ችግር ያላንዣበባት ይመስል፡ የድርጅቱ ሊቀመንበር ጉባኤውን ሲከፍት በተለመዱትና በታወቁት የመቀባባት ባህሪና አስተሳሰቡ፡ የሚከተለውን በጉባኢው መክፈቻ ላይ መናገሩ ችግራችንን ለመፍታት እንኳ አለመዘጋጀታችንን የሚያሳይ፣ ነገ ሃገራችን የምትጎዳበትና የምትጸጸትበት አሳዛኝና አሳፋሪ ዕውርነት ነው!

“10ኛውን ድርጅታዊ ጉባዔያችንን የምናካሂደው የህዳሴ ጉዟችንን አጠናክረን ለማስቀጠል ወሳኝ ወቅት ላይ ሆነን ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጉባኤዎች ቁልፍ ትኩረት ሆኖ የነበረውን የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ፈፅመን ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለመተግበር በዝግጅት ላይ ባለንበት ታሪካዊ ወቅት ላይ የሚካሄድ ጉባዔ ነው። የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም በትልቁ ከማቀድ ጀምሮ የአይቻልምን መንፈስ በመስበር ለቀጣዩ የህዳሴ ጉዟችን ከጥንካሬዎቻችንም ሆነ ከድክመቶቻችን በርካታ ልምዶችና ትምህርቶች የተገኙበት ነው፡፡ እቅዱ ከምንጊዜውም በላይ በልማት ሃይሎች ማለትም በድርጅት፣ በመንግስትና በህዝቡ የተደራጀ ንቅናቄ በመፈጸሙ በእቅድ ዘመኑ በአማካኝ ባለሁለት አሃዝ ዕድገት በማስመዝገብ ፈጣኑን የኢኮኖሚ እድገት ማስቀጠል ችለናል። በአገር ደረጃ በምግብ እህል ራሳችንን የቻልነው በዚሁ የእቅድ ዘመን ባደረግነው ከፍተኛ ርብርብ ነው። በዚህ አጋጣሚ እቅዱን ለመፈጸም በግንባር ቀደምትነት ለተንቀሳቀሱ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና ፈጻሚ አካላት እንዲሁም የልማቱ ዋነኛ ተዋናይ ለሆነው ህዝባችን በኢህአዴግና በእራሴ ስም የላቀ ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡”

ለመሆኑ፡ ከላይ ከተቀመጠው ከጉባዒው ሊቀመንበር ንግግር ውስጥ ስንቱ ዕውነትና ስንቱ ገለባ ነው? እግዚአብሔር በሚያውቀው ብዙ ባምጥም ከላይ ከተጠቀስው ንግግር ውስጥ የስንዴ ስባሪ የምታህል ዕውነት ማየት አልቻልኩም! ለምሣሌ፣ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ለሃገራችን የሚያስፈልገውን ውጤት አስገኝቶልናል ሊለን ነው የሚዳዳው? ባለሁለት አሃዝ ዕድገት ከተገኘ፡ በትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ መሳካት ነው ሊለን ነውን? ሌላው ቢቀር፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው አማካሪ አርከበ እቁባይ አይደለምን ምንም ውጤት ያለበት ሥራ አለመሠራቱን ነሐሴ 10/2015 – ሪፖርተር እንደዘገበው – ወድቀቱን ኦፊሴል ማህተም ያደረገበት?

በምግብ ራስን ስለመቻል (Food Security) ጠቅላይ ሚኒስትር ተበየው በተደጋጋሚ የሚናገረው – እኔም በተደጋጋሚ ለማስረዳት እንደሞከርኩት – ሃስተኛ መረጃ ነው! ኢትዮጵያ በምግብ ምርት ራሷን የቻለች ሃገር አይደለችም። መለስ ዜናዊ ያደርግ እንደነበረው አሁንም ይህም ግለሰብ የሚናገረው ራስ መቻል ጠቅላላ ምርቱን በሕዝብ ቁጥር በማካፈል ስለ Food Self-sufficiency ነው።

ይህ በብዙ ሁኔታዎች ከፍተኛ ምርት ካለበት አካባቢ ወደሌለበት ትራንስፖርት በማድረግ ራስ መቻልን ቢፈጥርም፡ በኢትዮጵያ ግብርና ሴክተር ደካማነት ምክንያት፡ ሃገራችን ይህንን በምግብ ራሷን እንደመቻል አድርጋ ልትወሰድ አትችልም! ይህ የሆነበትም ምክንያት ሃገራችን በየዓመቱ የምታደርገው የውጭ ምግብ ሸመታ ብዛት ይታያል IFPRI ያቀነባበረው ከ2005 ጀምሮ ያለውን ሃገር ውስጥ ገቢ የእህል ዳታ በሠንጠረዥ ያሳያል እዚህ ይጫኑ። ስሞኑን ድንገተኛ በድርቅ ወደተጎዱት አካባቢዎች ምግብ ማድረስ ተፈልጎ ከሃገር ውስጥ ባለመገኘቱ በውጭ ዕርዳታ ገንዘብ ሃገሪቷ ያላንዳች ጨረታ ከውጭ የታዘዘው ምግብ እህል እስካሁን ሃገራችን አለመግባቱን ማስታወሱ ይጠቅማል!

በምግብ ምርት ራሷን ባለመቻሏ፡ በየዓመቱ የምታደርገው የውጭ ምግብ ሸመታ ብዛት ይታያል! በምግብ ራስን መቻል ትልቅ ነገር ነው። ፍትሃዊ ክፍፍል ወይንም ለምግብ በሩ (access to food) በምንም መልክ ባልተቆለመመበት ሁኔታ ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው አንዳለው ማለት ይቻል ይሆናል – በብዙ ጥንቃቄ! አልያ ነገሮች ሁሉ፡ የሃገሪቱን ምርት በአጠቃላይ ደምሮና በሕዝብ ቁጥር አካፍሎ ይህንን ያህል አምርተሃል፣ ወይንም የሃገሪቱ የምርት ዕድገት (Gross domestic production – per capita) ይህን ያህል ግብር መክፈል አለብህ ወይንም በነፍስ አከፍ ያንተ ድርሻ $568 (ዓለም ባንክ) አድርሰንልሃልና ‘ምናባክ እያልክ ጩኸት የምታሰማው’? ብሎ እንደመወራጨት ይቆጠራል!

ለማንኛውም፡ የዓለም የምግብ ድርጅት ላይ አንዴ ሳይሆን፡ ሶስት ጊዜ የዓለም ርዕሳነ ብሄር ተሰብስበው (የመጨረሻው ጊዜ 1996 World Food Summit (WFS)) food security ምን ማለት እንደሆነ ማብራራታቸውና ዓለም አቀፍ መግባባት የተገኘበት ስምምነት መኖሩን –ኢትዮጵያም ፈራሚ መሆኗ ይታወሳል።

በአጭር አገላለጽ food security አለ ማለት የሚቻለው፡ እንደ የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት አገላለጽ መሆኑን ብዙ ግለሰቦች እንዳደረጉት ሁሉ
እኔም ለማስታወስ ሞክሬ ነበር! በዚያም አተረጓጎም መሠረት፦

    “Food security exists when all people, at all times, have physical, social and economic access to sufficient, safe and nutritious food which meets their dietary needs and food preferences for an active and healthy life. ሁሉም ዜጎች፣ በሁሉም ጊዜ ለምግብ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምግብ የማግኘት ዋስትና ችሎታ ሲኖራቸውና፡ ይህም ምግብ የተመጋቢነት ፍላጎታቸውንና ምርጫቸውን ጭምር በማርካት ንቃት ለተላበሰና ጤነኛ ሕይወት አስተዋጾ ሲያደርግ ነው ይላል!”

ሌላው ቅጥፈት፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ዐይነት ምርጫ ሳይኖረው ሕወሃት-መሩ ኢሕአዴግ ከላይ በሚጭነበት ትዕዛዝና አንድ ለአምስት ተከርችሞ የልማቱ ዋነኛ ተዋናይ ተደርጎ መገለጹ የነጻነቱ ምሣሌ ሳይሆን፡ ከዶሮዋና መጫኛ ምሣሌ ተለይቶ የሚታይ ጉዳይ አይደለም!

ከላይ እንደተመለከተው ሁሉ፡ ቀጥሎ የተጠቀሰው ስለድርጅቱ የፖለቲካዊ ክንውኖች የሚናገረው ክፍል ከታጀለበት ሃስትና ቧልት በተጨማሪ፡ እጅግ የከፋና በፖለቲካ በተከፋፈለች ሃገር በሌላው ቁስል ውስጥ እንጨት ስደድበት በመሆኑ፡ ንግግሩና ፖሊሲው የሚከተለው አቅጣጫ አሁም በዝርፍያ ትክክለኝነት ላይ በመመሥረቱ የሃገራችንን የወደፊት አደጋ ጠቋሚ ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፦

    “10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤያችን አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ በስኬት በተካሄደበትና ህዝቡ ለድርጅታችን ከፍተኛ ኃላፊነት በሰጠበት ማግስት የሚካሄድ መሆኑ ሌላው ጉባኤውን ታሪካዊ የሚያደርገው ጉዳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ህዝባችን በምርጫው ያስተላለፈውን ውሳኔ እና ከውሳኔው በስተጀርባ ያስተላለፋቸውን መልዕክቶች በአግባቡ ይረዳቸዋል። ህዝቡ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤትነት መብቱን ተጠቅሞ የሰጠው ውሳኔ ኢህአዴግ ባስመዘገባቸው ስኬቶችና እና በእስካሁን ያልረካባቸው ጉዳዮችም ኢህአዴግ ከህዝባዊ እና አብዮታዊ ባህሪው ተነስቶ ሊፈታቸው ይችላል የሚል እምነት አሳድሮ ያስተላለፈው ውሳኔ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መራጩ ህዝብ ሊመራውና ሊያገለግለው የሚችለውን ፓርቲ በባዶ የተስፋ ቃል ብቻ ሊሸነግለው ከሚፈልገው ፓርቲ የለየበት በሳል ውሳኔ ያስተላለፈበትም ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ በአገራችን መገንባት የተጀመረው የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አሸናፊ ሆኖ የወጣበት በመሆኑ የህዳሴ ጉዟችንን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠል ያስቻለ የህዝብ ውሳኔ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የጥላቻና የቂም በቀል የዜሮ ድምር ፖለቲካ እየከሰመ ሂዶ የተረጋጋ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ ከ2002ቱ ምርጫ ቀጥሎ ዳግም መሰረቱን ያጠናከረ በሳልና በአርቆ አስተዋይነት የተሰጠ የህዝብ ውሳኔ ነበር፡፡”

የደርጅቱ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው በሽንገላ ሲያጠቃልሉም እንዲህ ይላል፦

    “ድርጅታችን ባለፈባቸው የትግልና የስኬት መንገዶች ሁሉ መላ የሀገራችን ህዝቦች ከጎኑ በመሰለፍ ወሳኙን ሚና ተጫውተዋል። በዚህም ለዘመናት ወድቀን ከነበረበት የድህነትና የኋላቀርነት አረንቋ እና ተጠፍረን ተይዘን ከነበርንበት አስከፊ የድህነትና የመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ እጦት ወጥመድ ደረጃ በደረጃ እየተላቀቅንና እየወጣን የህዳሴ ጉዟችን በማፋጠን ላይ እንገኛለን። ከፊት ለፊታችን የሚጠብቀን መድረክም የልማት ሃይሎችን የተደራጀ ንቅናቄ በእጅጉ ይጠይቃል፡፡ የአገራችን ህዝቦች የጀመሩት የህዳሴ ጉዞ ከዳር የሚደርሰው በእነሱው ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ባለቤትነት በመሆኑ ከተለመደውም በጠለቀና በነቃ የዜግነት ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚገለጽ በመሆኑ ይህንኑ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ድርጅታዊ ጥሪያችንን በአክብሮት እናቀርባለን፡፡ ድርጅታቸው ኢህአዴግም በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው የመሪነት ሚናውን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ማስተላለፍ የሚጠበቅበት በመሆኑ ይህንን ተልእኮውን በብቃት እንደሚወጣ ለማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡ የጉባኤው ተሳታፊዎችም የሀገራችን ህዝቦች ከኛ የሚጠብቁትን መሪነት መወጣት በሚያስችለን ደረጃ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ እምነቴ የፀና ነው፡፡”

ለምንድነው ሕዝበ ካድሬው ዘንድሮ ደፈር ብሎ መናገር የጀመረው?

ከላይ በተነሱት ችግሮች፡ በገዥና በተገዥ መካከል መተማመን በመጥፋቱ፡ ሕወሃት-መሩ ኢሕአዴግ 24 ዓመታት ሙሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሲገባ የኖረው ቃል ኪዳንና ያስገኛቸው ውጤቶች ሲገመገሙ፡ በተለይም ከሰው ልጆች ደህንነትና ነጻነት አንጻር ከታዩ፡ ብቁ መንግሥታዊ አስተዳደር በሚፈለግባቸው አካባቢዎች ሁል ድርሽ እንዳይል የሚታገድ ድርጅት ነው!

ከነዚያ ርዕዮተ ዓለማዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ባሻገር፡ በድርጅቱ ውስጥ የተሰገሰጉት ኃይሎች ከሃገር በላይ ራሳችውን የሚያስቡ፡ የወገኖቻቸው ችግር የማይሰማቸው፡ ፖሊሲ ማለት ሃሰትና ፕሮፓጋንዳ ብቻ ሆኖ የሚታያቸው፥ ለዘረፋና ለራስ ጥቅም የተዘጋጁ ጨካኝ ጩልሌዎች በመሆናቸው ነው!

ይህ ከላይ ያስቀመጥኩት ፍርድ እጅግ ጠንካራ ነው። እናንተም ከውጭ ሆናችሁ ወደ ውስጥ ራሳችሁን ብትመለከቱ፣ ሃቀኛ ከሆናችሁ ይኸው ነው የሚታያችሁ እንጂ የተለየ አይሆንም!

የኢትዮጵያን ሕዝብ ዝቅ አድርጋችሁ ነው የምትመለከቱት! በመሆኑም በየጊዜው ያላንዳች የሕግ አግባብ ሃብቱንና ንብረቱን ስትዘርፉ፡ መንገድ ላይ ይዛችሁ ወይንም የግለስቡን በር ሰብራችሁ ከቤት ወስዳችሁ ስትገርፉና ስታሰቃዩ፡ ይህን ማድረግ ሰለምንችል እናደርጋለን ነው የምትሉት እንጂ (ጉልበት ስላላችሁ)፥ አንድም ቀን የምናደርገው ነገር ከሕጉ ጋር አይጻረርም ወይ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቃችሁ አታውቁም! አትፈልጉምም!

ይህም ሁኔታ የሕዝባችንን ልብ ሰብሯል! አሳዝኗል! እናንተን የማያይበትና እናንተን ማየት ወደ ማይችልበት መሄድ ቢችል ደስታው እጥፍ ድርብ እንደሚሆን ይገምታል! በዚህም ምክንያት ብዙ ወገኖቻችን – ሲችሉ በአውሮፕላን አልያም በእግርና በባሀር እያቆራረጡ – ሃገራቸውን ሲሸሹ፡ እናንተ ስለስው ነጋዴዎችና አመላላሾች በመደስኮር፡ የችግሩ ምንጭ የሕወሃት/ኢሕአዴግ አስተዳደር እንዳልሆነ ለማመልከት በየስብሰባው ሁሉ በአጽዕኖት ስታሰሙ ኖራችሁ! በዚህ ሁኔታ ስንትና ስንት ዜጎችን አጣን?

ማጣፈጫ እንዲሁንላችሁ፣ ገሚሱን የግዛት ዘመናችሁን ሃገሪቱ 11 ከመቶ እያደገች ነው እያላችሁ ባዶ ፕሮፓጋንዳችሁን ቸበቸባችሁ። ሆኖም በገጠር ያለውን ድህነት ለጊዜው እንርሳውና አፍንጫችሁ ሥር በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የረሃብ አለንጋ የድሃ ልጆችን እየገረፈ፥ ውሃ እንኳ አጥተው በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ ራሳቸውን ስተው መውደቃቸው ለናንተ ስሜት የሰጣችሁ ቀን የለም!

ሕዝቡ በኤኮኖሚ ችግሮች ተወጣጥሯል፤ በተመጣጣኝ ዋጋ ምግብ ለመግዛትና ቤተሰብን ለመመገብ አለመቻሉ፡ የውሃና መብራት ዕጦትና የመልካም አስተዳደር አለመኖር ዋና ዋና ችግሮች ከመሆናቸውም በላይ፣ በሥልጣን በባለጉ የተለያዩ ዐይነቶች ፖለቲካዊ ብስናቶች (ዘረኝነት፡ ጠባብነት፡ ትምክህትና ከኔ በላይ ማን) ማግሣት የተጠናወታቸው ባልሥልጣኖች የሕዝቡን ሕልውና ትርጉም ሲያሳጡት ከርመዋል።

የዘንድሮው ጉባኤ ትኩሳቱ ሞቅ ያለ በመሆኑ፡ በአቶ ረድዋን አገላለጽ – ከላይ እንደተመለከተው – ሕዝቡ እሮሮውን መቀሌ ድረስ ይዞ የሄደ ይመስል “መልካም አስተዳደር ችግር ሁሌም ችግራችን ነው እያልን ከመቀጠል ይልቅ ልማቱን በማፋጠን ችግሩን ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅረፍ መሠራት እንደሚገባው” ነበር የጠየቀውትርጉም፦ እናነትና ቤተሰቦቻችሁ ዘረፋችሁን ስለማታቆሙ፡ ለኛም ትንሽ እንዲተርፈን ኤኮኖሚውን አሳድጉልን ነው የሚሉት!

ቀደም ሲልም የአባል ድርጅቶቹ ስበሰባዎች በተለያዪ አካባቢዎች ተካሂደው፡ ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ በተለይም የመልካም አስተዳደር መጥፋትን አስመልከተው አስልቺ ዲስኩሮችን አሰምተዋል፤ ድርጅታዊ ውሳኔዎችን አስተላልፈዋል። ልቡንና ጆሮውን የዘጋ ድርጅት፡ በተለያዩ ጊዜ ኢሕአዴግ ባደረጋቸው ስብሰባዎች፡ የካድሬዎቻቸውንና የባለሥልጣኖቻቸውን ብልግናና ስግብግብነት ስለሚያውቁም ይሆን፡ ዛሬ ዝሕቡ እይጉረመረመ ነው በተባለባቸው ችግሮች ዙሪያ በዛ ያሉ ውሳኔዎችን ቢያስተላልፉም፣ ዞሮ ዞሮ የኅብረተሰባችን ችግሮች ሊቀረፉ አልቻሉም። በአሁኑ ደፍጣጭ አሠራር አይችሉም!

ለምሳሌም ያህል አራተኛው የኢሕአዴግ ጉባኤ አዲስ አበባ ላይ በተደረገበት በ1993 ዓ.ም.የተላለፈው ውሳኔ፡ “ሙስናን፣ ጠባብነትን፣ ጎጠኝነትን፣ የኢ-ዴሞክራሲያዊነት እና የኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያዎችን በፓርቲው አመራርና አባላት ውስጥ እንዋጋለን የሚለው ከዛሬው ባልተናነስ ዋነኛው ነበር

ስድስተኛው የድርጅቱ ስብሰባ በ1999 መቀሌ ላይ ሲካሄድ የተላለፈውም ውሳኒው “በመልካም አስተዳደር ዘርፍና በምጣኔ ሃብት እድገት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣትና የአመራር ብቃትን ከፍ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ትኩረት እንዲሰጣቸውም ነበር የተወሰነው። ይህም ሥልጠና እስከዛሬ ድረስ ቢካሄድም፡ በአመራር ደረጃለውጥ ለማምጣት ባለመቻሉ ብቻ፡ በሃገራችን ችግሮቹ ተባብሰው፡ ዛሬም ባለሥልጣኖቹ በተሰባሰቡ መጠን ገዥው ፓርቲም ስብሰባውን ሲያካሄድ ያለመታከት ስለእነዚሁ ችግሮች – ከላይ አቶ ረድዋን እንዳሉትና እንደ አምስተኛው የ1997ና 2005 በተካሄዱት የባህር ዳር – የሞኝ ለቅሶ መላልሶ አስመስሏቸውል። ምሥክር ቢያስፈልግ፡ በተለይም የ2005 የባህር ዳር ጉባዔ ሰነዶች ስለ ሙስና፣ ኪራይ ሰብስቢነትና አስተዳዳራዊ ችግሮች ብዙ ውይይቶች መካሄዳቸውን የሚጠቁም ስለሆነ፡ በቅርብ መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል።

እንኳ ደስ ያለን! (ፎቶ ፋና)

እንኳ ደስ ያለን! (ፎቶ ፋና)

ኢትዮጵያ ለምድነው ለምንድነው ጥሩ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግ ከችግሮች መላቀቅ ያልቻለችው?

እንደ ሣይንሱና ደንቡ ከሆነ፡ ኢትዮጵያን ያጋጠሟት ችግሮችን ለመፈታት ተገቢውን ርዕዮተዓለም፡ ራዕይ (Vision) ይዞ ፖሊስዎችን ቀርጾ፡ መዋቅሮችን መሥርቶ ወይንም አስተካክሎ ወደ ሥራ ለመግባት መዘጋጀት ነበር ቀደምቱ ተግባር መሆን ያለበት።

ሕወሃት-መሩ ኢሕአዴግ ከበረሃ ጀምሮ ይዞ የመጣውን ብሄረሰብ ላይ የተመሠረተ ርዕዮተ ዓለም አሳይቶናል። እስከዛሬ እንዳየነው ከሆነ፡ ለእነርሱም አለበጃቸውም፡ ሃገሪቷንም ምንም አልፈየዳትም።

የዚህ ውድቀታቸው ምክንያት፡ ሕግ መንግሥት ቀርጸው፣ ሕገ መንግሥታዊ መርሆች ርዕዮተ ዓለማቸውንም ጭምር እንዲመራው ፈቃደኝነት ለማሳየት እስከዛሬም ባለመቻላቸው ነው። ርዕዮተ ዓለማቸው ገደብ የሌለውን ሥልጣን ስለሚሻ፡ ይህም ለዘረፋ ጭምር ስላመቻቸው፡ ሕውሃት-መሩ ኢሕአዴግ በሥልጣን ላይ ወደ ወንበዴነት ተቀይሯል!

በእነዚህ የተወሳሰቡ የፖለቲካ፡ ኢኮኖሚ፡ ማኅበረሰባዊ ችግሮች ምክንያት ሕወሃት ሶስቱና አስፈላጊ ሁኔታዎች – ማለትም የተጋ ኢኮኖሚማኀበራዊ ፍትህና ግለሰባዊ ነጻነቶችን ተግባራዊ በማድረግ፣ ዕድገቷን ለማቀጣጠል ዝግጁ አልሆነም! በምትኩ፡ የዜጎች ሕይወት የለወጠ ይመስል መሬታቸውን በመዝረፍ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በድንጋይ ላይ ድንጋይ በመጫን ዕድገት ነው ይለናል። ይኸ ለቱሪዝም ገቢ የሚደረግ የሃገሮች እሽቅድምድም ነው!

ዘይትና የከበሩ ማዕድናት የሌላት ሃገራችን በሰው ሃብት ልማት በመጎልበት የነገዋ ከሌሎች ግንባር ቀደምት ሃገሮች እኩል ተፎካካሪ እንዳትሆን ተሰጦዋንና ዕድሎቿን ሁሉ ተዘርፋለች። ባለንበት ዓለም ማደግና መበልጽግ ዑደታዊ (cyclical) በመሆኑ፡ አንዱን ድረጃ አንድ ሃገር ስትስት፡ የሚቀጥለው የዕድገት ዑደት ውስጥ በምቾት ለመሳተፍ አስቸጋሪ ይሆናል። ስለሆነም ምንም ስለሌለን አሁን በቱሪዝም መስክ ተሰማርታለች ሃገራችን፡ ምንም እንኳ የጠበቀችውን እስካሁን ባታገኝም!

በመሆኑም፡ ዛሬ እንደሚታየው ከሰሃራ ደቡብ ሃገሮች ጋር ኢትዮጵያ ስትወዳደር፡ ለምሳሌም ያህል፦

    (ሀ) ወደ ውጭ በሚላኩ የምርት ዐይነቶች ጥራትና ብዛት ለምሣሌ በኢትዮጵያ ቡና ላይ ጃፓን ከስድስት ዓመት በፊት የጣለችውን ማዕቀብ በቅርቡ ካነሳች በኋላ በኢትዮጵያ ቡና ጥራት አለመደሰቷን በቅርቡ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል። በሌሎች ምርቶችና በሌሎች ገበያዎችም ላይ ለምሳሌ የቅባት እህሉች፡ ኦፓል (ትንሽ ቢሆንም)፡ ወዘተ ተመሳሳይ ችግሮች እየታዩ ነው! የሃገሪቱ ምርት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ሲጨምር፡ በመሃል የገቡ ደላሎችና ነጋዴዎች ምዘበራ እያካሄዱ ቢሆንም፣ በማኅበር የተደራጁ የኦፖል አምራቾች ኑሮአችን ተሻሽሏል በማለት በቅርቡ ለውጭ ሚዲያ መግለጫ ቢሰጡም

(ለ) በሚሰበሰበው የውጭ ምንዛሪ ብዛት (ሌላ ቀርቶ ትኩረት በተሠጠው በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አምስት ዓመታት ውስጥ ገቢው ከ3.2 ቢሊዮን ለመብለጥ አለመቻሉ። ለዚህም በቅርቡ አንድ ጉባዔ ላይ አረከበ እቁባይ “በ3.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንዴት ይህን ዕድገት ማስቀጠል ይቻላል?” በማለት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ችግርን ለማጉላት ያነሳው ጥያቄ መሠረታዊ ነው!

(ሐ) በካሪኩለም በተወሰነው የትምህርት ዘመን ውስጥ ኢትዮጵያ ጥራት ያለው የሰው ኃይል ከማፍራት ይልቅ፡ ከክፍል ክፍል እየተገፋ፡ ባላገኘው ውጤት እየአዘለለ ትምህርቱ መጨረሱ፡ የዘመናችን ትውልድ ዕውቀትን የተቀናጀ ሳይሆን፡ እንደ ካድሬዎች ለብለብ ብቻ ሆኖአል

(መ) ግብርናው ካገኘው ግብዓት አንጻር አጥባቢ ውጤት አግኝቶ ሕዝቡን ከመመገብ አልፎ ለኢንዱስትሪ ምርት የሚሆን ምርት (raw materials) ማመረት በለመቻሉ አምራቹም ገቢው እንደሚገባው ሊጨምር አልቻለም፤ በቂ ምርት በሌለበት አካባቢ ደግሞ በቂ ገቢ ስለማይኖር ድህነት የማይጋፉት ባለጋራ ሆኖአል

(ሠ) ፖለቲካውና ድርጅታዊ አሠራሩ ሁሉ ነገር ውስጥ የእርጎ ዝንብ በመሆንና ነጻነትን ማፈኑ በሃገሪቱ ውስጥ የዕውቀትና ፈጠራ ብልጭታ እንዳይዳብር አድርጓል

(ረ) የሕግ በላይነት መጥፋቱ በፍርድ አሰጣጡ የኅሊና ነጻነትና መዋቅራዊ ደህንነት ከሕጋዊ ዳኝነት ከፉኛ መለያየቱ በአስተዳደሩ ላይ እምንት በማጥፋቱ፡ ዘረፋን በሃገራችን ውስጥ አጠናክሮታል

(ሰ) የሚዲያው መታፈንና የባለሥልጣኖች ከሕግ በላይ መሆን ሃገራችን ውስጥ ድንቁርናን ከማሰፋፋቱም በላይ፡ ዘረኛነቱንና ሃገራችንን በኅይል የተያዘች ሃገር ከማድረጉም በላይ ሃብትና ንብረቷን ክፉኛ ለዘረፋ አጋልጦታል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተቀየሱት የአምስት ዓመታት ዕቅዶች፡ ልዮ ልዩ ፕሮግራሞች ፍሬቢሶች ቢሆኑ ያስገርማልን?

በሕወሃት መሩ ኢሕአዴግ አስተዳደር፡ ማንኝውም ችግር ሲከሰት፡ የችግሩ ምንነት ግንዛቤ ሳያገኝ ዘሎ ኮሚቴና ቡድን በማቋቋም ባለሟያዎች ዕውቀታቸውን ፈትነው የተሻለ ሃሳብና አማራጭ እንዳያቀርቡ ዘወትር በፍርሃት፡ ጥርጣሬ ውስጥ የሚኖረው ፖለቲካ – አንዳንዴም በድንቁርና ሌላ ጊዘም በፍራት እንዳይሠሩ ያደርጋቸዋል።

ከ1929-1932 ድርሰ የቆየው የዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ (Great Depression) ወቅት የፕሬዚደንት ሩዝቬልት አስተዳደር ችግሩ በጎላ በ100 ቀናት ውስጥ አያሌ እርምጃዎችን (The New Deal) በመውስድ ለመፍታት ቢሞክርም – የታውቀው ኤኮኖሚስት ሚኒስኪ (Hyman P. Minisky Stabilizing An Unstable Economy – 1986) እንደሚተነትነው – ፖሊሲው ቀናና አስፈላጊ መሆኑ ቢታወቅም፡ በወቅቱ – መይናርድ ኪነስ (Maynard Keynes) እስከመጣ ድረስ – ስለኤኮኖሚ ያለው ግንዛቤ ያልዳበረ በመሆኑ፡ ርዕዮተ ዓለምን፡ ፖለቲካውን፡ ሕግን፡ ፖሊሲን፡ መዋቅርንና ዕውቀትን አዋህዶ ለመሥራት ችግር አጋጥሞ እንደነበር ያሳያል።

ኪነስ የኤኮኖም ዕይታውን ካበረከተ በኋላ ግን የዓለምን የኢኮኖሚ ድቀት በመቀየር ብዙ ሃገሮች የሃገራቸውን የኢኮኖሚ ዕድገት አቅጣጭ ለመቀየር ችለዋል።

ምንድነው ኪነስ ይዞ የቀረበው? ታዋቂነቱ ሲጎላ የጻፋቸውን ሁሉ የሚያነቡ መበራከት ጀመሩ። ከነዚያም መካከል አንዱ ጥናቱ Essays in Persuasion (1931) ሲሆን ጠቃሚ ሃሣብ ይሠነዝራል።

እኔ እዚህ የምጠቅስው ሕውሃት መራሹ ኢሕአዴግ ተግባራዊ ለማድረግ ብቃቱም ሆነ ፍላጎት አለው ብዬ ሳይሆን፡ ዛሬ በዕልልታና በከበሮ ትግራይ ውስጥ ያስተላለፉት ውሳኔ የኢትዮጵያን መድኅን ማምጣት እንደማይችል ስለምገምት ነው።

ኪነስ ያለው እንደሚከተለው ነው፦

“The political problem of mankind is to combine three things: Economic Efficiency, Social Justice, and Individual Liberty. The first needs criticism, precaution, and technical knowledge; the second, an unselfish and enthusiastic spirit which loves the ordinary man; the third, tolerance, breadth, appreciation of the excellences of variety and independence, which prefers, above everything, to give unhindered opportunity to the exceptional and to the aspiring. The second ingredient is the best possession of the great party of the Proletariat. But the first and third require the qualities of the party which, by its traditions and ancient sympathies, has been the home of Economic Individualism and Social Liberty.”

ከመቀሌ የመጣው ውሳኔ ግን ከዚህ ጋር አይራመድም። ስለሆነም ሃገራችን ከአምስት ዓመት በኋላ ጨቋኝ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ሆና ለምን አምስተኛው የሁለት ዓመት ዕቅድ የሚፈለገውን ውጤት ሳያስገኝ ቀረ ለሚለው አሁን ባለው ወይንም በሌላው አረከበ እቋባይ ገለጻ ሰጥቶን ወደ የቤቶቻችን እናቀናለን!

ወይንም ትክክለኛ ግንዛቤ ያጣው የኢትዮጵያ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሁኔታ ለይቶለት የራሱን መፍትሄ አግኝቶ በሌላ ጅምር ኩትኳቶው እንደገና በአዲስ ይጀመር ይሆናል!

ከሁሉም የከፋ ግን፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራርና አባላት ላይ ያ ሁሉ ወከባ፡ ድብድብ፡ እስርና ድግያዎች ከተፈጸሙ በኋላ፣ ሕወሃት መራሹ ኢሕአዴግ በግፍ የታሠሩት እንዲፈቱ፡ ለሟቾቹ ካሣና ለዘለቄታውም ሁኔታው እንዲመቻች ምንም ዐይነት ትርጉም ያለው ውሳኔ አለመወሰዱ፡ ከእንግዲህ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች እየተበራከቱ እንደሚሄዱ አመላካች ነው!

የዕርግምናችን ምንጭ ይህ ለጋራችን የምንሻውን ተፈጻሚ ለማድረግና ማስደረግ የሚያችል ብሩህ አዕምሮ(ዎች)፡ ለመርህ ተገዥ የሆነ አገዛዝና የተፈተነ ራዕይ ሕዝቡ በሚያምነበት መንገድ አስተዋጾኦውን እንዲያደርግ ተባባሪ የሚሆን ኃይል ሥልጣን ላይ አለመውጣቱ ነው!
 
*Updated.
 

%d bloggers like this: