ዕይታ! ሞላ አስገዶም: “የትጥቅ ትግሉ ወቅቱን ያልጠበቀ በመሆኑ ትተን መጥተናል”ይላሉ – እውነቱ የት ይሆን ያለው?

16 Sep

በከፍያለው ገብረመድኅን* – The Ethiopia Observatory (TEO)

አቶ ሞላ አስገዶም ከተናገሩት ውስጥ ምን ይህሉ እውነት ይሆን? የትኛውን ‘ተናገር ተብለው’ እንደ ተናገሩ ግለሰቡና ጉዳዩን በቅርብ የተከታተሉ/የሚከታተሉ ሁሉ በተለይም ድርጅታቸውን፡ ኤርትራንና የኢትዮጵያን አስተዳደሮች በቅርብ የሚያጠኑት ጠለቅ አድርገው ይገነዝቡታል።

አሥራ ሶስት ዓመታት በትጥቅ ትግል ከቆዩና የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሁኔታ፣ የተቃዋሚ ድርጅቶችና የኤርትራን ሁኔታ ‘በጥልቀት ከገመገሙ በኋላ’፡ አቶ ሞላ አስገዶም “የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱ የፍትህና የሙስና ችግሮችንእየተዋጋ በመሆኑ፣” ቀሪውን “አብረን እንሠራለን በማለት ነው ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የተገደድነው” ያሉት ያንባብያንን ትኩረት ስቧል፤ ለጥርጥርም መሠረት ጥሏል።

ከሁሉም በላይ አቶ ሞላ የተናገሩት፣ በአርበኞችና ግንቦት ሰባትና በሌሎች ሶስት ድርጅቶች መካከል ጥምረት መስከረም 8/2015 በኩል የተፈጸመውን አስመልክቶ ሲሆን፡ እርሱንም የሕወሃት መረጃ አገልግሎት ታላቅ ተልዕኮ የተከናወነበት በማለት የአቶ ሞላ የጥምረቱ ምክትል ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥን “የጥፋት ኃይሎችን ዓላማ ለማሰናከል እነ ሞላ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው” ማለቱ ነው – (በሳባት ቀናት ውስጥ)። ሰለዚሁ የሕወሃት መረጃ አገልግሎት እንዲህ ይላል፦

  “አጠቃላይ ሂደቱን መንግሥት በሚፈልገው መንገድ ሲመሩት ከቆዩ በኋላ ግዳጃቸውን እጅግ አኩሪ በሆነ መንገድ ፈጽመው ኃይላቸውን እንዳለ ከነሙሉ ትጥቁ በመያዝ ወደ እናት አገራቸው ተመልሰዋል”።

በግዮን ሆቴል በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ፡ አቶ ሞላ ግን አሥመራ ብር 25 ሺህ የሚያስከፍ ከፍተኛ ሆቴል ውስጥ እንደኖረና እንደተዝናና እንደጦር አዛዥ ሳይሆን፣ የበሉትን ከባድ ምሣ/ቁርስ እንኳ በደንቡ ለመፍጨት ያልተመቻቸው መስለው ቀርበዋል። በተጨማሪም በውጥረት (anxiety/tension) ተጠርንፈው፡ መናገር እየተሳናቸውና ከግሳት ጋር እየታገሉ፣ “የትጥቅ ትግሉ ወቅቱን ያልጠበቀ መሆኑን” ይናገራሉ! ሆኖም፡ “መምጣት በነበረብን ጊዜ ነው የመጣነው… ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ተቋርጦ ቆይቶ…ኤርትራም ጥርጥር እንዳላት ሲታወቅ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት” መገደዳቸውን ይናገራሉ።

“ሱዳን ከገባን በኋላ ከኢትዮጵያ አካሎች ጋር ትሥሥር ጀመርን” ይላሉ።

ጥያቄዬ፡ ከመሸሽ ውጭና በኤርትራ ውስጥ ምንም የረባ ጦር አለመኖሩን ከመናገር ውጭ ምን አስገኙ? መከፋፈል ካንሠር አለመሆኑ እየታወቀና፡ ጊዜ ወስዶ በብርታት ሊተካ እንደማይችል አድርገው መናገራቸው የዕይታቸውን ውሱንነት ይነካል። ከዚህ ውጭ – ምንም እንኳ ትሕዴን ትልቁ ኃይል ቢሆንም – ኢትዮጵያውያን ምን ያግዳቸዋል በሁነኛ አመራር አማካይነት ራሳቸውን እንደገና ለማሰባሰብና ትግሉን ለመቀጠል?

በመሆኑም የሃገራችንን ችግሮቿንና የፖለቲካውን ሁኔታ በቅርብ የምንከታተል ግለሰቦችም አንዳንድ አቶ ሞላ ያነሷቸው ላይ ተመርኩዘን ስንመለከት፡ አንዳንድ አጠራጣሪ አባባሎችን ለመልቀም ችለናል። እነዚህ በአንድነት ተዳምረው ለሚከተሉት ጥርጣሬዎቻችን መንሰዔና ምክንያቶች ሠጥተውናል።

አንደኛ፡ ኢትዮጵያ በልማት እየገሠገሠች ናት በማለት አቶ ሞላ ሲያመሰግኑ፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ አስተዳደርም በራሱ የፍትህንና ሙስናን ችግሮች በራሱ አነሳሽነት እየተዋጋ ነው ይላሉ። በአንጻሩ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችና የኤርትራ አስተዳደር አፍራሽ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው በማለት ይወነጅሏቸዋል። እርሳቸው የሕውሃት የፊት ለፊትና የጓሮ የመረጃ በር ክፍት ከሆነላቸው፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የአስተዳደር ብልሹነት፡ የዘረኝነትና የሙስና መስፋፋት ትልቅ የችግር መንሰኤ መሆንና ለብዙ ዓመታት በፓርቲና በመንግሥት ደረጃ ተነጋግረውበት መፍትሄ ያጣ ነገር ሆኖ፣ ፓርቲ ውስጥ ተራ አባላት የሃይማኖት አባቶች ጭምር በቅርቡ የመቀሌ ጉባዔ ላይ አቤቱታ የሚያሰሙበት ጉዳይ ለመሆን መብቃቱ እንዴት የአቶ ሞላን ግንዛቤና ትንተና አንዳመለጠ አይገባኝም።

በሚያሳፍር ደረጃ አቶ ሞላ አስገዶም ይህንን በፓሪታያቸው ውስጥ “ብዙ መስተካከል ያለበት ብለን ጉዳዩን ከገመገምን በኋላ ያሉትን ችግሮች ተወያይተን ተነጋግረን ወደ አጠቃላይ የትግሉ መቋረጥ ላይ ነው የወስነው” ያሉትን የኢትዮጵያን ችግሮች መፍታት እንችላለን ይላሉ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታ ይህን ከማድረግ ይልቅ፡ ምናልባትም በጸሎትና ትግል ብዛት እግዚአብሔር ምድርን እንዲጎበኝ ማስቻሉ ሳይቀል አይቀርም!


 

ሁለተኛ፡ እርሳቸው በወር ለሆቴላቸው ብር 25 ሺህ አሥመራ ውስጥ እየተከፈለላቸው ለሰባት የትግል ዓመታት ሲንደላቀቁና የኢርትራን ጥቅም ማስከበራቸው ጭምር እያመለጣቸው በጋዜጣዊ መግለጫቸው ሲያስረዱ፡ ምንደነው እርሳቸው የሚሉትንና በኢትዮጵያ ዐይን ለኢትዮጵያ ሰላም፡ መረጋጋትና ብልጽግና ተሟጋችና ታማኝ ተዋጊ የሚያደርጋቸው?

በሌላ በኩል ደግሞ፡ በኤርትራ ዐይን ለኤርትራ ጠቃሚው የጠላቴ ጠላት የሚያደርጋቸው ምን የተለየ አሰተዋጾ ኖሯቸው ነው የኤርትራን ጥቅም በወታደራዊ መንገድ ከማስከበር ውጭ፤ በደህነነት አስከባሪነት ታማኝነት የሥልጣን ጠባቂና አስከባሪ ያደረጋቸው የሚለው ጥያቄ መልስ ያስፈልገዋል።

እንደሚባለው ከሆነ፡ ደሚሕት የኤርትራ ኮር የደህንነት አካል ነው። ታዲያ እንዴት አድርገው ነው የኢትዮጵያንና የኤርትራ አገልጋይነታችውን የሚያስተርቁትና የኢትዮጵይ ጥቅም አስከባሪ ሊሆኑ የሚችሉት? ይህ እስካልሆነ ድረስ፡ ምናልባትም አቶ ሞላ አስገዶምን በኢትዮጵያ ታሪከ ውስጥ የመጀመሪያው ባለሁለት ወገን ሠላይ (double agent) ወይንም የቅጥር ወታደር አዝዥ (mercenary force commander) እንዳያስመስላቸው ሠጋለሁ! የአቶ ሞላ ‘አባባሌ ሃቄ ነው’ የሚሉ ከሆነ፡ በሥልጣንና ጥቅም ዙሪያ ተጨባጭ (realistic) በተለይም የአሜረካኖች ‘ነጻ ምሣ የለም’ የሚሉትን ትክክለኛ አባባል የሚጻረር ይመስላል!

ሶስተኛ፡ አቶ ሞላ አስገዶም ስለ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ሲናገሩ፣ በትግል መስክ ከነበረና የአንድ ታጋይን የልብ ትርታ እንደሚገነዘብ ሰው ሳይሆን፣ ከጦር ሜዳ ውጭ ያለ በስብዕና ጠላትነት ግለሰባዊ የአስተሳሰብ ድህነታችውን በራሳቸው አንደበት እርቃኑን አስቀርተታውል። በዚያው አንደበታቸው፡ አቶ ሞላ የገበሬ ልጅና ትምህርት የሌላቸው ሰው መሆኗቸውንና “የዶክተሩ ምክትል ለመሆን መብቃቴ…ፕሮፌሰር ነው መስለኝ” ብለው ራሳቸውን ሲፈትሹ፣ ለሰባቷ የቆዩባት የጥምረቱ ቀናት ኩራት ቢሰማቸውም ቢያሰሙም፡ ራሳቸውን አበጥሮ የሚያውቃቸው ራሳቸው ቦታቸው አለመሆኑን የነገራቸው ይመስሉ ነበር።

በዚህም ምክንያት አንዱም ስለዶክተር ብርሃኑ የጣሏቸው ጉድፎችና ስሞታዎች ራሳቸው ለዘለቄታ እንክብካቤ እንዲያገኙ የተሰሉና ለሕወሃት የቀረቡ “በረከቶች”፡ ከመሆን ባሻገር፡ እርሳቸውን በተቃርኗቸው ከማጋለጥ ውጭ ትሩፋት አለተውላቸውም።

አስገራሚ የሆነው የሚከተለው አቶ ሞላ ሰለ ዶክተር ብርሃኑ ተቃራኒ አስተሳሰብ ሳት ብሏቸው መዘባተላቸው ነው (ቪዴዮውን ይመልከቱ):-

  በጥምረቱ መሪነት እንዲመረጡ ካስደረግን በኋላ፣ አሜሪካ ሆኖ ድርጅቱን መምራት አይችልምና መምጣት ያለበት [ወደ ኢርትራ] ነው ያልነው…በእውነት ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ፣ ብርሃኑ መምጣት ነው ያለበት…ወይንም ትግሉን ይተ ው፣ ሥልጣኑን ይተወው ሌላ ሰው ይያዘው…በዚያ ደረጃ ነው ብርሃኑ እንዲመጣ ያደረግነው…” ብዙም ሳይቆዩ፡ አቶ ሞላ መለስ ብለው፡ “እርሱ [ዶክተር ብርሃኑ] የመጣበት ምክንያት…ብዙ ጊዜ ከውጭ የሚመጡ ሰዎች ገቢ ማሰባስብ ሁኔታ አላቸውና ከዚያ በፊትም የተወሰኑ ኢሣት ጋዜጠኞች መጥተው የኛን ጦር ፎቶ አንስተው ምናምን አድርገው ሄደው በጣም ብዙ ገንዘብ ነው ያሰባሰቡት። አሁንም ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መምጣቱ በንግድ ነው ያየሁት። ነጋዴ ነው ያልነው። ብዙ ተከራክረናል…

ይህንንም ማለታቸው በተለይም በትሕዴን ውስጥ በዚህ ላይ ክርክር ማስነሳቱ፣ እርሳቸው በቀየሱት ምክንያት ድርጅቱ መከፋፈሉና ትሕዴንም በሠጠው መግለጫ እንደተመለከተው፡ ድርጅቱ ሊተፋቸው ዝግጁ እንደነበረ ያመለክታል። እርሳቸውም በቪድዮው ላይ እንደሚደመጠው፡ “መገደድ” የሚለውን ቃል ደጋግመው ተጠቅመውበታል – ወደ ኢትዮጵያ ስለመምጣታችው ሲናገሩ።

አሁንም ሃቁ የትና ምኑ አነደሆነ ባናውቀውም፣ በአቶ ሞላ አስገዶም ካምፕ ያለው እውነት እጅግ የሳሳ ነው።

ከሁሉም የከፋ፡ በአዛዥነት የፈለገውንም ያልፈለገውንም የትሕዴንን እስክ 600 ያህል ጦር አሳስተው ይዘው ከዱ የሚለውም ክስ በቀላሉ የሚሻር አይደለም። ወዶ ላልዘመተው ጦራቸው እሳት ቀላቢ ከሆኑ፡ በምን ምክንያት በምን የዝምድና አመጣጥ ነው አቶ ሞላ አስገዶም ለኢትዮጵያ አሳቢ ተደርገው የኢትዮጵያ ታክስ ከፋይ ደም ተፍቶ የሚከፍለው ገንዘብ መንበሽብሺያቸው የሚደረገው?
 

ሞላ አስገዶም ጋዜጣዊ መግለጫ በአዲስ አበባ፣ ግለሰቡ በራሳቸው አንደበት – እውነቱ የት ይሆን ያለው? (ክፍል ሁለት)


 

ያን ያህል ጥሩ ተዋጊ የትሕዴን ጦር 600 ያህል ሕወሃትን ተቀላቀለ ቢባል እንኳ፡ የተባበሩት መንግሥታት ኮሚቴ (Eritrea and Somalia Sanctions Committee) ለጸጥታ ምክር ቤቱ እንዳቀረበው ሪፖርት ከሆነና (S/2014/727)፡ ትሕዴን 20ሺህ ጦር ካለው፡ ይህ ማለት ቀሪው 97 ከመቶው የትሕዴን ጦር አሁንም ሜዳው ውስጥ ነው ማለት ነው – ለነጻነትና ዴሞክራሲ ትግል ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ከሆነ!

ስለዚህ በአንድ በኩል የተሻለ ሰውና አመራር ሲመጣ፣ የተፈጠረው የዝቅተኛነት ስሜት (inferitority complex) ለዚያውም ላልተማረ ሰው፣ በተጨማሪም በትሕዴን ውስጥ ከሚያዝያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የቆየው የሂስና ሂስ ግለ ሂስ መፈላለጥ የአቶ ሞላን ናላ አዙሮና መቆሚያ አሳጥቶ እንዲፈረጥጡ ማስገደዱ ይበልጥ የሚጨበጥ ይመስላል።

ለኢትዮጵያውያን በደርግ ጊዜ “ፈረጠጠ” የሚባለው ቃል አንድ ትውስታ አለው። ይህም ደርግ መኤሶንን በሚመለከት እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ አስታዋሽ ከመሆኑ ባሻገር፡ አቶ ሞላ አስገዶም ይህን ዛሬ የጨመቁበት መንፈስና ዓላማ በሕወሃት የስለላ ድርጅት ከተሠጣቸው ተልዕኮ ተነጥሎ ሊታይ የማይችል ነው።

“ተሸናፊዎችም ታሪክ የሚጽፉ ይመስል …” በማለት በመስከረም 15 ባቀርብኩት ጽሁፌ ላይ እንዳመለከትኲት፡ በዓለም ታሪክ ውስጥ ተሸናፊዎች አሸናፊዎች ነን ብለው ቢያምኑ እንኳን ታሪክ መጻፍ አይችሉም። በትህትና ስለሽነፈታቸው በሃቅ ቢጽፉ ኅብረተስብን ሊያስተምሩ ይችላሉ። ከዚያ ውጭ ግን ትዝብት መሣቂያ መሣለቂያ ያደርጋቸዋል! ይሀ ለአቶ ሞላም ከመስከረም 15/2015 የግዮን ሆቴል መግለጫቸው ጀምሮ የተቀዳላቸው ጽዋ ይመስላል!

በኢትዮጵያ የደሞክራሲ ትግል ውስጥ ኤርትራ የሚኖራት ሚና ለብዙ ኢትዮጵያውያን በጥርጣሬ ዐይን መታየቱ የሚካድ ነገር አይደለም! ምን ጊዜም ቢሆን፣ ኢትዮጵያን የወጋ ጦር ጠላትነቱ በቀላሉ አይሽርም፤ እንዲሁም ቁስሉ ቢድንም፡ ያስከተለውን ያን ያህል ደም መፋሰስ ከውስጣችን አይጠፋም፣ በቀላሉ አይሽርም!

እነ አቶ ሞላ አስገዶም በመንደር ድረጃ የሚለካ ክህደት ፈጸመዋል – ለዚያውም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይና ጎረቤት ኤርትራ ላይ – ለ13 ዓመታት አመኔታዋን ሰጥታ ኢትዮጵያን ለመበታተን ባሰበ ኃይል አደራጅታ – ከላይ ያነሳሁትን ባለሁለት ወገን ሠላይና የቅጥር ወታደር አዝዥ የሚለውን አስታውሱልኝ!

ኢትዮጵያና ኤርትራ፡ ሰላምና ጦርነት በጋራ አብረው የሚያስተናግዱ ሃገሮች ስለሆኑ፣ ሁለቱም በሰላም ጊዜ ሥራቸውን ያከናውናሉ፣ ትሕዴንም እንዲሁ። በሁለቱ መካከል ሰላም ሲኖር፣ ትሕዴን የአሥመራን ዙፋን ሲጠብቅ ከርሟል፤ በግጭት ሰሞን ደግሞ ኢትዮጵያን በማናጋት! የኤርትራና የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ፍሎጎቶች ተጻራሪ ሲሆኑባቸው – ለእናት ሃገራቸው በማሰብና በመሥጋት – ይቸገሩ እንደነበር በሚያሳፍር የዋሾ ምሥክርነት አቶ ሞላ ሁለት ጊዜ በጋዜጣዊ መግለጫቸው አንስተዋል!

ያንን ስሰማ፣ በጡረታ ላይ የምገኝና በሥነ ሥርዓት ትምህርቴን ተምሬ በሃገር ውስጥም በውጭው ዓለምም የሥራ ልምድ ያካበትኩት እንደመሆኔ፣ እንደ አቶ ሞላ ለኢትዮጵያ ያላቸው ተቆርቋሪነት ሃስተኛና ርካሽ ራስ ጠቀም ችርቻሮ በመሆኑ ሳላስበው ከማጅራቴ በኩል ሊያርደኝ ከሞክረ ካራ ላየው አልቻልኩም። ደግነቱ ከዚህ በፊት በሥራዬ ዓለሞች ወይንም በግል ሕይወቴ ይህን መሰል ሁኔታ አጋጥሞኝ አላውቅም!

ለማንኛውም በሃገራችን ውስጥ ያለውን ሁኔታ፡ የኢትዮጵያውያን ስብዕናና ለሃገራቸው ያላቸው ፍቅር የማይቀበለው በመሆኑ፡ ዝርያን ሳይሆን፡ የኢትዮጵያውንያንን ሰብዓዊና ዜግነታዊ እኩልነትና፡ በግል መጠቀምንና ተባብሮ መጠቃቀምን ለጋራ ደህንነትና ብልጽግና ያደረገ ትግልን ልቤ አብሮት ይቆስላል፤ ይደማል።

በዚህ እምነት መሠረት ላይ የቆሙ – ዶክተር ብርሃኑም ሆኑ ሌሎቹ የስው ኃይል ያላቸውም የሌላቸውም ቢሆኑ (አቶ ሞላ ብቃታቸውንና ያለቻቸውን ለማሳየት፣ ሌሎችን ለማጥላላትና ለማጠልኮስ ቢሞክሩም) – ተባብረው ወደፊት ብቻ መመልከት እንደሚገባቸው፡ መንገዳችውን በብዙ መሥዋዕትነት ምቹ ሊያደርጉ እንደሚችሉ አምናለሁ።

ዋናው ነገር፡ ኤርትራ ለራሷ ሕዝብ ከሕወሃት ባላነሰ የዝርፍያ፡ የዘመቻና የእሥራት ሃገር እንደመሆኗ፣ ይህ በጎ ፈቃዷ በግለሰቦች ስሜት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ስለሚችል (ግምቴ ነው)፣ ይህንን በዘላቂነት ማረጋገጥ ይቻላልን የሚለውን ከአዕምሮዬ ማስወገድ አልቻልኩም!

ይህ ጥያቄም የቅንጦት ሊመስል ይችላል! የማያውቁት ሁሉ ሊያውቁት የሚገባቸው፡ ኢትዮጵያ ነፍጥ ያነገቡት ቀርቶ፣ በጨዋነትና በሰላም የሚታገሉት እንኳ በሰላም ለመሳተፍ ምርጫው የላቸውም!

ሰለሆነም፣ በኢትዮጵያችን ተቃዋሚዎች ምርጫቸው መርጦ እንደ ሁለተኛ ዜጋ መረገጥ ወይንም ሞትን መጋፈጥ ብቻ ሆኖአል።

ጅቡቲ፡ ሶማልያ – ትናንሽ ፍንጥርጣሪዎቿን ጭምሮ – ኬንያ፡ ሱዳን፡ ኡጋንዳ በጸረ-ዲሞክራሲ ሰንሰለት የተሳሰረ የብረት ግንባር ፈጥረውባቸው የል እንዴ?

በዚህም ከውስጥም ከውጭም መቀፍደድ ምክንያት ነው – ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ ለዘላለሙ ላለመቅረት – ኢትዮጵያውያን የጋራ ትግላቸው፡ የሚፈሰው ደማቸውና የሚወድቀው አካላቸው በሃገራቸው ምድር ላይ እንዲሆን፡ በራሳቸው በመተማመንና ትግላቸውን በማፋፋም ነጻነታቸውን ለመዋጀት ከፍተኛ ትግል ለማድረግ መቁረጥ የሚገባቸው።
*Updated.
 

*ከዚህ በላይ የተገለጸው የአቶ ከፍያለው ገብረመድኅን አስተያየት የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ባይሆኑም፡ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊና የእኩልነት የሚደረገውን ማናቸውም ትግልና የትግል ድርጅት ደጋፊ የመሆናቸው መግለጫ ነው።
 

Related articles:

  UPDATE: ተሸናፊዎችም ታሪክ የሚጽፉ ይመስል “ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሴራ በመቃወም ነው የወጣነው” ይላሉ አቶ ሞገስ አስገዶም ለጋዜጠኞች በሠጡትና መግለጫና የሕወሃቱ ፋና እንደዘገበው!

  UPDATE: የሞላ አስገዶምና ጓደኞቹን ከድተው ከሕወሃት ጋር መቀላቀልን አስመልክቶ ከአርበኞች ግንቦት 7 የተሰጠ መግለጫ

  UPDATE: የትሕደን ሚዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ – ሞላ አስገዶምና ጓዶቹ “በአብዛኛው ታጋይ በመድረክ ተይዘው መፈናፈኛ ስላጡ ተስፋ ቆርጠው ከትግሉ ጎራ ሸሽተዋል” – ይላል!

  UPDATE: ከሞላ አስገዶም ጋር ዓመት የፈጀ ምሥጢራዊ ግንኙነት ነበረኝ ይላል ሕወሃት!

  TPDM’s Mola Asgedom said to be in Sudan: Plausible given Khartoum’s close relations with TPLF & Eritrea, or are there other players on the chessboard?

  የትግራይ ትግል ቡድን (ደሚሕት) ሊቀመንበር አቶ ሞላ አስገዶም፣ ከጥቂት ጓደኞቻችው ጋር በአዲስ ዓመት ዋዜማ ሕወሃትን መቀላቀላቸው ተሰማ!

  ሰበር ዜና: የዴምህት ሊቀመንበርና ከ600 በላይ የሚቆጠሩ የንቅናቄው አባላት ከኤርትራ ኮበለሉ

  Addis Ababa praises Sudan for repatriating Ethiopian rebels

 

%d bloggers like this: