በጋምቤላ ብሄረሰቦችን በማጋጨት126ቱን ለሞት ዳርገዋል፥ ከሰባት ሺህ በላይ ነዋሪዎች አፈናቅለዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው ይላል ሕወሃት! አመራሩ እስካሁን ለምን ዝም ብሎ ቆየ? ሽፈራው ሽጉጤስ ለምን አልተጠየቀም?

18 Sep

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጋምቤላ ክልል የሚኖሩ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን ደም አፋሳሽ ግጭት ውስጥ እንድገቡ በመቀስቀስ 126 ሰዎች ህይወታቸው እንዲያልፍ እና ከ7 ሺህ የሚልቁ ሰዎች እንዲፈናቀሉ አድርገዋል በሚል ወንጀል የተጠረጠሩ 46 ግለሰቦች ዛሬ 46 ክስ ተመሰረተባቸው።

የፌደራል አቃቤ ህግ በዚህ ወንጀል ከቀበሌ እስከ ዞን በአመራርነት እርከን እና በተለያዩ የግል ስራ የተሰማሩ ግለሰቦችን ነው የከሰሳቸው ።

የፌደራል አቃቤህግ በህብረት የጦር መሳሪያ ይዞ ማመፅ ወይም የእርስ በእርስ ጦርነት በማስነሳት በመንግስት ላይ በሚደረግ ወንጀል የሚለውን የወንጀል አንቀፅ 35፣ 3832(1) እና 240(2)ን በመጥቀስ ነው 46 ሰዎች ላይ ክስ የመሰረተው።

በክስ መዝገቡ የሰፈሩ 46ቱም ግለሰቦች ከቀበሌ እስከ ዞን መዋቅር በአመራርነት ተሹመው ሲያገለግሉ የነበሩ እንዲሁም በድለላ እና በግብርና ስራ የሚተዳደሩም ናቸው።

ከእነዚህ መካካል የማዣንግ ዞን ፀጥታ ሃላፊው ገብርኤል ለካኒ ዑስማን፣ የክልሉ ምክርቤት የመሬት አጠቃቀም ሃላፊው አሶን ኮካስ ፣ በማዣንግ ዞን የመንገሻ ወረዳ ፖሊስ ባልደረባ ምክትል ኢንስፔክተር ኮቲል ሰርኬወርቅን የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸው።

እንደክስ መዝገቡ ወንጀሉ የተፈፀመው ከ2006 እስከ 2007 ዓ.ም ባሉት ሁለት ዓመታት ነው።

ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ዜጎችን በማስታጠቅ አንዱ በሌላው ላይ የጦር መሳሪያ እንዲያነሳ አነሳስተዋል የሚለውን ወንጀል ነው አቃቤህግ የጠቀሰባቸው።

የእርስ በእርስ ግጭት እንዲነሳሳ ለማድረግ በማስማማት፣ በማደም በቀጥታ በመሳተፍ፣ በወንጀል ድርጊቱ እና በሚሰጠው ውጤት ላይ ሙሉ ተካፋይ በመሆን ወንጀሉን ጠንስሰዋልም ብሏል አቃቤህግ ።

ተከሳሾቹ ይህን ያደረጉበት አካባቢ በጋምቤላ ክልል ማዣንግ ዞን ፣ ጎደሬ እና ሚጢ እንዲሀም በሌሎችም ቀበሌያት ነው።

በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚኖሩ የማዣንግ ብሄር ተወላጆች እና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በማምጣት፣ በህጋዊ መንገድ በማዣንግ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ሰፍረው ለዓመታተ ሲኖሩ የነበሩ የሌላ ብሄር ተወላጆችን በአካባቢው አጠራር “ደገኞች” በተባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ነው ተከሳሾቹ ድርጊቱን ፈፅመዋል የሚለው ክሱ።

ተከሳሾች በተጠቀሰው አካባቢ የሚገኙ ደገኞች ቦታችንን ለቀው ይውጡልን በሚል ሰፊ ቅስቀሳ በማድረግ ወንጀሉን አንድ ብለው መጀመራቸውን ክሱ ያትታል።

ሚያዚያ 29 በተባለ የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ በተለያዩ አደባባዮች ደገኞች በማዣንግ ዞን ውስጥ የያዙትን የእርሻና የቡና ተክል መሬት ለማዣንግ ብሄር ተወላጆች ሊያካፍሉ ይገባል የሚለው ቅስቀሳቸውም በክሱ ላይ ሰፍሯል።

የመሬት ልኬት የሚደረገው ለማዣንግ ተወላጆች ብቻ ነው የሚለውን አስተሳሰብ ማራመዳቸውም በክሱ ተመልክቷል።

መስከረም 2006 ዓ.ም አቶ ቲቶ ሃዋርያት የተሰኙ ከፍተኛ አመራር በህዝበ ስብሰባው ደገኞች በማዣንግ ዞን ያያዛችሀትን የእርሻ እና የቡና ተክል ለማዣንግ ብሄር ተወላጆች ማካፈል ይገባችኋል፣ ይህ ካልሆነ እርምጃ ይወሰድባችኋል በማለት ያስተላለፉት መልዕክትም በክሱ ላይ ተጠቅሷል።

ከ2006 እስከ ሚያዚያ 2007 ዓ.ም መሰል ቅስቀሳ በየቀበሌያቱ መካሄዱም ተዘርዝሯል፤ ህገወጥ ቅስቀሳ የተደረገባቸው ደገኞችም ያለማነውን ለማንም አንሰጥም በማለታቸው የማዣንግ ብሄር ተወላጆች የሆኑ የዞኑ ፖሊስ አባላትና ሚሊሻዎች የአመፅ ጥሪ ማስተላለፋቸውም እንዲሁ።

በዚህ ጥሪ መሰረት ተከሳሾች የማዣንግ ብሄር ተወላጆችን በማደራጀት፣ በማስታጠቅ ሙሉድጋፍ በማድረግ፣ በደገኞች ላይ ጥቃት እንዲፈፀም ትዕዛዝ ሰጥተዋል ነው የሚለው ክሱ።

ከትዕዛዝ ባላፈ ተከሳሾቹ ራሳቸው በጥቃቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆነዋል የሚለውም በክሱ ሰፍራል።

ነዚህም ከሀምሌ 17፣ 2006 እስከ ግንቦት 25፣ 2007 ዓ.ም በብሄሩ ተወላጆች እና በደገኛው ማህበረሰብ መካከል ደም አፋሳሽ ግጭት መቀስቀሱን አቃቤህግ በክሱ ጠቅሷል።

ይህን ግጭት በመሸሽ ሰላም ወዳለበት አካባቢ ሲሰደዱ የተገኙ ደገኞችን ማሰር ፣ መደብደብ ወንጀል አይደለም በማለት ትዕዛዝ የሰጡ ግለሰቦችም በክሱ ተጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ ተከሳሾች በማዣንግ ዞን በተለይም በመንገሻ እና ጎደሬ ወረዳዎች በሚገኙ ከተሞች መሳሪያ ይዘው በመንቀሳቀስ በህዝብ ደህንነትና ኑሮ ላይ ቀውስ በመፍጠር፣ በታወቀው አሀዝ ብቻ ከ126 በላይ ሰዎች ህልፈተ ህይወት፣ ለ35 ሰዎች ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት፣ ለ273 ቤቶች ውድመት እንዲሁም ከ7 ሺህ 200 በላይ ሰዎች ከቤት ንብረት መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል በሚል በአቃቤህግ ተከሰዋል።

ተደራጅተው የእርስ በእርስ ግጭት እንቅስቃሴ ውስጥ በፈቃዳቸው ተካፋይ በመሆን፣ እና በመሳሰሉት 46 ክሶችን መስርቶባቸዋል።

ተከሳሾች ዛሬ ክስ የተመሰረተባቸው ሰሆን፥ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት ተረኛ የወንጀል ችሎት መስከረም 10/2008 ዓ.ም ቀርበው ክሱ ይነበብላቸዋል ተብሏል።
 

%d bloggers like this: