78 በሬዎችና ላሞች ባለተፈቀደ ሥፍራ ለግብይት ስለቀረቡ፡ በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ፋና ዘገበ

23 Sep

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

የዜናው ፍሬ ሃሣብ ግልጽ ቢሆንም፡ ስለሰብ ዓዊ መብቶቻቸው፣ የዴሞክራሲ ሁኔታ በኢትዮጵያ ሃሣብን በነጻነት ስለመግለጽ፡ እንዲሁም የመሬት ዘረፋን በመቃወም ምክንያት ሕወሃትን የተጋፉ ወደ መቀመቅ ሲላኩ፡ ፋና ይዘግብ ከነበረው ርዕስ ጋር ተመሳሳይ ሆነብን። ይህ ለቀንድ ከብቶችም ስለተሠጠ፡ በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጣራት ይህንን ዜና ጠጋ ብለን ለማንበብ ተገደድን፡፡ በመጠኑም ቢሆን፣ በዴሞክራሲ ታጋዮች አስተሳሰብና በጨቋኞች የፕሮፓጋንዳ አውታር መካከል ያለውን ዜና አውታሩ በብቃት ለማሳየት ችሏል።

አንደውም፡ ሕውሃት ነፍሰ ገዳይ ተጧሪ ጦረኞቹን በጋምቤላ ማስፈር ከጀመረበት ከጥቂት ዓመታት ወዲህ፡ በአካባቢው በተፈጸመው ተወላጆቹን ማፈናቀል ምክንያት የደች ወራሪዎች (Boers) በ17ኛው ክፍለ ዘመን ከፈጸሙት ያላነስ ግድያዎች በሃገራችን ተካሂደዋል። በጋምቤላ ዛሬ ትግሬዎች የአብዛኛው የመሬቱ ባለቤቶች ሆነዋል።

ይህንንም በመቃወም ቅሬታ ያሰሙ ወንድ፣ ሴት፣ አዛውንትና ሕጻናት ሳይቀሩ ተገድለዋል። በዝርያ እየተመረጡም በተለይም መዠንገሮች፣ አንዋኮች፡ አማሮች፡ ኦሮምችና ሻኮዎች ጋምቤላ ውስጥ በሕወሃት ጦር ሠራዊት ተግድለዋል። በጊዜ ሠሌዳ ሲታይ፡ ይህ ከሃያ ዓመታት ያላነሰ ታሪከ ሲኖረው፣ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተፈጸመው ግን ከመዓትና ምጽዓት ተለይቶ የማይታይ ነው።

ሕወሃት በራሱ እንኳ እንዳረጋገጠው (በነፍሰ ገዳዩ አመኔታ ማለት ነው) እንኳ 146 ሰዎች ተገድለዋል – ምንም እንኳ የሟቾቹ ቁጥር ብዙ ሺህዎች መሆኑ ቢገመም! የመሬት መቀራመቱን ስፋትና መጠን በሚያሳይ ሁኔታ ሰባት ሺህ ግለሰቦች መፈናቀላቸውን አምኗል። ሆነም ተካሳሽ የሆኑት ግን 46 መዥነገሮች ናቸው – እርሱና ካድሬዎቹ መሆን ሲገባቸው – ነገ ባይቀርላቸውም!

በ1997 የሕዝብ ቆጠራ ወቅት 4,050 ሕጋዊ ትግሬዎች ሠፋሪዎች ነበሩ። ይህም የጠቅላላው የጋምቤላ ሕዝብ 1.32 ከመቶ አድርጓቸው ነበር። ከሕዝብ ቆጠራው ሶስት ዓመት በኋላ ይህ ቁጥር በሃምሳና ስድሳ ሺህ ውስጥ ተስፋፍቶና አካባቢውን በጦር ኃይል ተቆጣጥሮ ቆይቷል።

በ2012 ግን ከትግራይ መጥቶ ተወላጁን አፈናቅሎ የመሬት ባለቤት የሆነው ወራሪ የሕወሃቶች ብዛት 70 ከመቶ በላይ መድረሱን የታወቀው የኦክላንድ ኢንስቲቱት ባደረገው የመስክ ጥናት ተዘግቧል! ይህ ከሁለት መቶ ሺህ በላይ የሚያደርገርው ሲሆን፡ ዛሬ ያ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን ይገመታል!

ይህንን በግድያና ዘረፋ የተገኝ ብልጽግና ሕጋዊ ለማስመሰል የፖለቲካ መሞላደሉን ሕውሃት አጥብቆ ተያይዞታል – ታሪክ ጀንበርም እንደምትጠልቅ እንዳላስተማረው ይመስል!

ነገር ግን ሰሞኑን ፡ የራሱን ወንጀል የሸፈነ መስሎት፡ በማጃንግ ዞን ሁለት ወረዳዎች በመንገሽና ጎደሬ ወረዳ የሚኖሩ የተለያዩ ነዋሪዎች የሰላምና ልማት ኮንፈረንስ በማካሄድ በሃገር ሽማግሌዎች አማካኝነት እርቅ ፈጸሙ ይላል! ይሀ ለእርሱ – ባቄላ አለቀ…ቀለለ ነው!

ሲያብራራም፣ በሰላምና ልማት ኮንፈረንሱ ላይ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎች የክልሉ ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነርን ጨምሮ የዞኑ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል ብሏል። ትዕዛዝ ከተሠጣቸው የማያደርጉበት ምክንያት የለም። ነገር ግን ሕወሃት ገና ከመጀመሪያው ይህንን ከማድረግ ምን አገደው – ሕዝብን ከማጋጨት ውጭ በሰላም የሚያሰተዳድርበት ፖሊሲ እንደሌለው የታወቀ ቢሆንም? ካድሬዎቹ (አዳዲስ ትግሬ ሠፋሪዎች) ተወላጆቹ በተፈናቀሉበት መሬት ላይ እስኪደላደሉ፡ የባለቤትነት ሠነዶቻቸውን አዘጋጅተው እስኪጨርሱ ይሆን?

በእንግሊዞች ፊውዳል ታሪክ ውስጥ አንድ የቆየ አባባል አለ፣ በዘመነ ካፒታሊዝምም የአኗኗር ባህል የሆነ። ይህም ያንተ ሰላምና መብቶችህ ተከብረው መኖር የምትሻ ከሆነ የሌሎችን ሰላምና መብቶች ማክበር ግዴታህ ለማለት – “Live let live” ይላሉ!

እነዚህን ታሣሪ ከብቶች፡ በአቶ አባይ ፀሐዬና አርከበ ዕቁባይ መሪነትና አስተባባሪነት፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው አጫፋሪነት ሕወሃቶች ቅርጫ ያደርጓቸው ይሆን?

Photo: Courtesy of Fana Broadcast

Photo: Courtesy of Fana Broadcast


 

ባልተፈቀደ ስፍራ ለግብይት የቀረቡ 78 የቁም እንስሳት በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 12 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ንግድ ቢሮ ባለተፈቀደ ስፍራ ግብይት ሲፈጽሙ ከነበሩ ነጋዴዎች ላይ 78 የቁም እንስሳትን በቁጥጥር ስር አዋለ።

የቁም እንስስቱ በቁጥጥር ስር የዋሉት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ሲሆን፥ ለመያዛቸው ምክንያቱ ደግሞ አዲሱን የቁም እንስሳት ግብይት ደንብ በሚጻረር መልኩ ባልተፈቀደ የግብይት ስፍራ በመገኘታቸው ነው

ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ ለንግድ የቁም እንስሳትን ለማስገባት በቀዳሚነት፤ ባለንብረቱ ህጋዊ ንግድ ፍቃድ፣ የግብይት ደረሰኝ እና ከሚነሱበት ቦታ እስከ ሚደርሱበት ስፍራ ወይም የግብይት ማእከል ከመነሻቸው ከሚመለከተው አካል የመሸኛ ደብዳቤ ሊይዝ ይገባል።

የቁም እንስሳቱ እንደቀደመው ጊዜ በመኪና እና በእግረኛ መንገድ እየተነዱ ሳይሆን በተሽከርካሪ ተጭነው አዲስ አበባ መግባት ይኖርባቸዋል፤ ይሁን እንጅ ይህ ባለመሆኑ የቁም እንስሳቱ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በአዋጁ በእንዲህ መልኩ በቁጥጥር ስር የሚውሉ የቁም እንስስት በከተማዋ በሚገኙ 5 የግብይት ማእከላት ለ5 ቀናት እንክብካቤ ሲደረግላቸው ቆይቶ በጨረታ ኮሚቴ አማካኝነት ይሸጣሉ።

ገንዘቡም በዝግ ሂሳብ እንደሚቀመጥ ነው አዋጁ የሚደነግገው።

ከዚህ በዘለለ በአዋጁ በህገ ወጥ መንገድ የተገኙ የቁም እንስሳትን አጓጉዞ የተገኘ ግለሰብ በ30 ሺህ ብር እና ሁለት አመት በሚደርስ ቀላል እስራት ይቀጣል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ ያለውን 5 የቁም እንስሳት የግብይት ማእከላት እና አንድ የፍየልና በግ ግብይት ማዕከላትን ቁጥር ከማሳደግ እስከ ማሻሻል የሚደርስ ለውጥ ለማምጣት እየሰራ ይገኛል።
 

%d bloggers like this: