11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች በመጪው ጥር ግንባታቸው ይጀመራል ይላል ሕወሃት ያሉትን እንኳ በሚገባ ማስተዳደር ሳይችል!

29 Sep

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)

ኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወቅታዊ ተግዳሮቶች በሚል ርዕስ ሃፍቶም ገብረኪሮስ የጻፈውን ከተመለከትኩ በኋላ ስሜቴ በጣም ተለዋወጠ። አንደኛ የሕወሃት ሰዎቹና ቅጥረኞቹ በሌላቸው ብቃት ሁሉም ነገሮች ውስጥ እየገቡ በማማሳላቸው፡ ትምህርት ቤቶችም የዘር ፖለቲካ ማራቢያና የሕወሃቶች ፕሮፓጋንዳ ማስተጋቢያ ብቻ ሆነዋል። ሁለተኛ ካድሬነት በሚፈጥረው የባዶነት መወጣጠር ልጆቻችን በየቀበሌው ዩኒቨርሲቲ ወይንም ኮሌጅ በተባሉ ግቢዎች ሲያልፉ ከረሙ እንጂ ዕውቀት በእነርሱ ውስጥ ብርሃኗን ስታንጸባርቅ ታይቶ አይታወቀም።

ሶስተኛ ብቃት ያላቸውን ምሁራን በየደረጃው ሕወሃት አላሠራ እያለ ወደ ውጭ እይተገፉ ነው! ሕወሃት የሚፈልገው ተጥደው በደንብ ያልበሰሉ ኢትዮጵያውያንን በኮብል ስቶን አሠማርቶ እርሱ ግዥ መሆኑን ነው የሚያየው።

ይኽው ቲዲ አፍሮን ሳይቀር፡ ከፍተኛ ሃገር ወዳድነት አሳይተሃልና አንተ በሙዚቃህ የምታስተምረው መርዝ ነው ብለው አይደል እንዲ መተዳደሪያ ሊያሳጡት ብሎም ወደ ውጭ እንዲሰደድላቸው የሚገፋፉት?።

የሃፍቶም ችግር መሾምና መሿሿም ላይ ያተኮረ ነው። ለእርሱ ዋነኛ አድርጎ በትምህት መስክ ያለውን ችግር ሲያፍታታ እንዲህ ይላል፡

  አሁን ያለው የሀገራችን ልማትና ዕድገት በዘላቂነት ለማስቀጠል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈተናዎች ሊሆኑ ይችላሉ ወይም ናቸው በሚባሉ ጉዳዮችና አስተሳሰቦች በግልፅ መወያየትና መነጋገር አስፈላጊ ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህር ተቋማት ማህበረሰብ ቅር ከሚያሰኙ ጉዳዮች አንዱ የዩኒቨርሲቲዎች የበላይ አመራር (የቦርድ ሰብሳቢ፣ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት) ሹመት የሚሰጥበት መንገድ ላይ ነዉ፡፡መንግስት ጉዳዩ በጥልቀት መርምሮና አጥንቶ በአስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጥበት ይገባል እያልኩ ወደ ዝርዝር ጉዳዬ ልግባ፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች የመንግሥትን ፖሊሲ ጥያቄ ውስጥ ሳያስገቡ፣ የሕዝብ ችግር የሚያዳምጡና አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጡ ትክክለኛ መሪዎችን በትክክለኛ ቦታ ላይ ማስቀመጡ ጥሩ ሆኖ እያለ ብሄር መሰረት አድርጎ መሾም የነዚህ ሁሉ ችግሮች የመፍችያ መሳርያ ተደርጎ መወሰዱ አግባብነት የለውም፡፡ አንድ የቦርድ ሰብሳቢ፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ፣ምክትል ፕሬዝደንት በመሰረቱ መንግስት ሀላፊነት የሚሰጣቸው የተቋሙን ራእይ፣ዓላማና ተልእኮ ለማሳካት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ማለት ይቻላል በተቋሙ ውስጥ ያለት ማህበረሰብ (መምህርና ተማሪ) የብሔር ስብጥር ብንመለከት ከ70% በላይ አካባቢው ያለበት ዩኒቨርሲቲ ብሄር ተወላጆች ያልሆኑና ለስራ ወይም ለትምህርት ከሌላ አካባቢ የመጡ ናቸው፡፡ ስለሆነም ይሄን ማህበረሰብ የሚመራ አመራር መሾም ያለበት ብሄሩ ታይቶ ሳይሆን በሜሪት (በሕግና ስርዓት) መሰረት ያደረገ ውድድር/ሹመት መሆን አለበት፡፡ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ዓላማና ራዕይ ተልዕኮ የሚያሣካ፣ የመንግስት ፖሊሲዎችና ስተራተጂዎች ጠንቅቆ የሚያውቅና በትክክል የሚያስፈፅምና ቆራጥ አመራር ሰጭነት ችሎታ ያለው መሆን አለበት፡፡ ይህ አሰራር ከየትኛው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ ዓንቀጽ እንደተወሰደ አላውቅም ነገር ግን እንደአሰራር ሆኖ በሁሉም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች እየተተገበረ ይገኛል፡፡

ሃፍቶምም በየየኑቨርሲቲዎች ውስጥ የሚደረገው ዘር ተከል የአመራር ሹም ሽር ላይ አተኮረ እንጂ እርሱም ዋናውን የቀበሌ ዪኒቨርሲቲዎች ሶስተኛ ደረጃ ሕንጻ መስፋፋትና የዕውቀትን ጉዳይ ወደጎን ገፍቶ ማለፉ ለሹመት የሚታገል አስመስሎታል። ለነገሩ እርሱ ካነሳው ዘንዳ ትግራይ ውስጥ የሌሎች ኢትዮጵያዊ ብኄረሰብ አባሎች ከትግራዊ ውጭ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲን ወይንም የአካባቢውን ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ለመምራት እንደማይታሰቡ እንዴት እንዳልተገነዘበ ይገርመኛል! እርሱ አሁን ስለሌሎቹ ክልል ውስጥ ያሉት ክፍት ሥፍራዎች ላይ አተኩሯል። በጣም በሚያስገርም መንገድ ሃፍቶም ክትግራይ ውጭ ባሉት የዩኒቨርሲቲ ክፍት የሹመት ሥፍራዎች ወይንም ለትግራውያን መከፈት ስላለባቸው የሥራ መደቦች ላይ ዐይኑ አንዣቧል!

በእርሱ አስተሳሰብ ከሄድንማ፡ ምንድነው ሕወሃት በጡንቻው ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተቆጣጣረው? አንድ የሃገር ቅርስ የሆነውን የኢትዮጵያን አየር መንገድ በትግራዊ ተወላጆች የሥልጣን እርከኑን በተወልደ መልክተኛነት በመሠግሠግ፡ ውድቀትን እየጋበዘ መሆኑ በሠፊው ውስጥ ባሉ ሠራተኞች እየተነገረ ነው! እስከሚገባን ድረስ አየር መንገዱ በውጭ ዕዳ ተወጥሮ ተወልደ ተአምር ሠራ ተብሎ በየቦታው ሕወሃት ስሙን እየቸረቸረው ነው!

ለነገሩ ኩላሊት ነቀላ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጀመረ ተብሎ ዜናው ለሕዝባችን ሲገለጽ በቴክኒኩ መስክ እንኳ ሥራውን ያካሄዱት ትግራዊ ያልሆኑ ሰዎች እያሉ፡ ትግራዊ ፕሮፌሰር ተጠርቶ አብራሪ እንዲሆን መጋበዙ፡ ምን ያህል ሃገራች ይህ ሕወሃት በዘራው የዘር አደጋ ውስጥ እንደገባች ያመላክታል።

ለማንኛውም አሁን ትምህርትን በተመለከተ ዛሬ ጧት የቀረበው ዜና 11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች በመጪው ጥር ግንባታቸው እንደሚጀመር ነው። ይህ መንግሥት በሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ ጣራን ግድግዳ እያቆመ፡ ዩኔቨርሲቲና ኮሎጆች ማለቱ ሕዝብን ብቻ ሳይሆን ራሱንም ጭምር የሚያታልል ነው!

ጥራት የሌለበት ትምህርት ብሎ ነገር ምንድነው? ምናልባትም ለሕወሃት የኮንስትራክሽንና የንግድ ድርጅቶች ትርፍ ሊያስገኝ ይችል ይሆናል!

የዘር ፖለቲካና ባዶ ፕሮፓጋንዳ ሃገራችንንም ሆነ ሕወሃትን ጭምር ያጠፋል እንጂ ማንም ተጠቃሚ አይሆንም!
///000///
 

ዜናው እንደሚከተለው ቀርቧል-

11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች በመጪው ጥር ግንባታቸው ይጀመራል

  አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የ11 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ከጥር ወር 2008 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚጀመር የትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ።

  ዩኒቨርሲቲዎቹ በ2010 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹን ተማሪዎች እንደሚቀበሉም አስታውቋል።

  በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት አስተዳደር ጉዳዮች ጀነራል ዳይሬክተር ዶክተር ሣሙኤል ክፍሌ እንደገለጹት፥ አዳዲሶቹ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሁለት ዓመት በኋላ የመጀመሪያዎቹን 7 ሺህ 700 ተማሪዎች ይቀበላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

  ለዩኒቨርሲቲዎቹ ግንባታ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ በ2008 ዓ.ም የበጀት ዓመት ለዩኒቨርሲቲዎቹ ቅድመ ግንባታና ሌሎች ስራዎች ማስፈጸሚያ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር መንግሥት መድቧል።

  የዩኒቨርሲቲዎቹ የዲዛይን ሥራ በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን፥ የአፈር ምርመራና የሰቬይንግ ሥራም ከሁለት ዩኒቨርሲቲዎች በስተቀር የሌሎቹ ከሞላ ጎደል ተጠናቋል ብለዋል።

  ሚኒስቴሩ ዝርዝር የዲዛይን ጨረታ ለማውጣት በዝግጅት ላይ እንደሆነም ነው ዶክተር ሳሙኤል የተናገሩት።

  ግንባታቸው ከሚካሄዱት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተጀመሩት የጋምቤላና የአርሲ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙበት መሆኑንም አመልክተዋል።

  በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፈሮሜሽን ዕቅድ ዘመን የራያ፣ ደባርቅ፣ እንጀባራ፣ መቅደላ አምባ፣ ደምቢ ዶሎ፣ ሰላሌ፣ ኦዳቢልቱ፣ ጂንካ፣ ቦንጋ፣ ወራቢ እና ቀብሪዳሃር ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ይከናወናል።

  የ11ዱ ዩኒቨርሲቲዎች አጠቃላይ ቅበላ መጠን በ2012 ዓ.ም 110 ሺህ እንደሚሆንም ይጠበቃል።

 

ተዛማጅ ጽሁፍ:

Disparity in The Quality of University Education Prevails
 

%d bloggers like this: