ነጣቂውና አፋኙ የቻይና ኩባንያዎች ክንድ ድቆሳ ኢትዮጵያም ውስጥ እያስቸገረ ስሞታ ከረረ!

14 Oct

የአዘጋጁ አስተያየት:

  አመራር ችሎታ የሌለው ግለሰብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ተቀምጦ፡ ዐይኑ የሚያይ ከሆነ፥ የሚያነጣጥረው በአገልጋይነት የሚያገኘው የግል የሥልጣን ፍቅሩ ላይ ነው። ስለሆነም የሚያሳስበው ጥያቄ ሁሉ የሚያተኩረው “ማን ተባበረን? ማን ተቃወመን? ማን ተጠቀመ?” የሚለው ላይ ስለሆነ፡ ብሩ እስከተገኘ ድረስ፡ ቻይና እግራችንንም ቆርጣ ብትወስድ ምንም አይስገርምም!

  ሰሞኑን የቻይና ኤምባሲም በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የማንደሪን ቋንቋን ለማስፋፋት ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ማስታወቁም አንዱ የዚህ መገለጫ ነው!

  ማንም ይሁን ምንም ቋንቋ መማሩና ማወቁ ይረዳል – ሥራ ለማግኘትም ሆነ መካከለኛ ገቢ ያለው ሃገር ደረጃ ላይ ሕውሃት ‘ሲያደርሰን ምናልባት ወደቻይና ቱሪስት ለመሆን ሁሉ ይጠቅማል!

  ማነው ይህንን የሚወስነው ሲባል ግን የ’ነፃይቱ ኢትዮጵያ’ ትምህርት ሚኒስቴርና እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ሳይሆን፡ የቻይና ኤምባሲ ሆኖ መታየቱ ሃገሪቱ ለሃራጅ ሽያጭ መዘጋጀቷን ያሳያል!

  ይህ የተወለድኩባትና ያደኩባት ነፃይቱ ኢትዮጵያ ባህል ሳይሆን፣ ሕወሃት ያዋረዳት ኢትዮጵያ ናት! ነፃይቷን ኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ የሚያውቀውስ ዓለም እንዴት ይሆን የሚመለከተን?

  ለነገሩ የሠራተኛውን ማኅበር አመራር የያዙት የሕወሃት ሰዎች ስለሆኑ፡ አብዛኞቹም የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ያሉዋቸውም እነርሱው ስለሆኑ፡ አሁን የቻይና ዘረፋው እነርሱንም ያሳሰባቸው ይመሰላል!

==========
 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

  –   “የተባረሩት ሥራ እንዳይሠራ በማሳደማቸውና አልታዘዝ በማለታቸው ነው፡፡ የተባረሩት እንደ ሠራተኛ እንጂ እንደ አመራርም አይደለም፤”

  –   በኢትዮጵያውያን የሚሠሩ ሥራዎች በውጭ አገር ዜጎች እየተሠሩ ነው ብሏል!

የሠራተኞችን መብትን በሚጥሱና በማኅበር መደራጀትን በሚከለክሉ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎች እየተቸገረ መሆኑን፣ ችግሩም ከአቅም በላይ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን እንጨት፣ ብረታ ብረት፣ ሲሚንቶና የመሳሰሉት ሠራተኛ ማኅበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ዘገየ ኃይለ ሥላሴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመንገድ ሥራና በቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታ በተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎች ከሠራተኛ መብትና ጥበቃ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ውይይቶች ቢደረጉም ችግሮችን መፍታት አልተቻለም፡፡

የሠራተኛን መብት ከሚጥሱና የመደራጀት መብትን ከማያከብሩ ኩባንያዎች ፌዴሬሽኑ በተደጋጋሚ ውይይት መደረጉን፣ ከዚህም ባለፈ ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ የተገደዱባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህም ቢሆን ግን በአሁኑ ወቅት ችግሩ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማኅበሩ በውይይትና ጉዳዮችን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ችግሩን ለመፍታት የሚሞክር ቢሆንም፣ በተለያዩ ጊዜያት ጥያቄ የሚነሳባቸው እንደ ሲሲኢሲሲ (CCECC) ያሉ የቻይና ኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ጋር የተፈጠረ ችግርን በውይይትም ሆነ በፍርድ ቤት መፍታት ሳይቻል፣ ኩባንያዎቹ ሥራቸውን እያጠናቀቁ ሠራተኞች በማሰናበት ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሠራተኞች በማኅበር እንዲደራጁ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሃያ ያህል የቻይና ኩባንያዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ዘገየ፣ ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ቀደም ሲልም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስለችግሩ አሳሳቢነት ቢጻፍም፣ የቻይና ኩባንያዎች ከፌዴሬሽኑ አቅም በላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ፌዴሬሽኑ ጥቅምት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ለአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የጻፈው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ ኤችኤንቤይ የተባለ የቻይና የእንጨት ሥራ ኩባንያ ከአምስት ዓመታት በፊት በድርጅቱ የሠራተኛ ማኅበር ሲቋቋም የማኅበር አመራሮችን አባርሮ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ከዚህ በኋላ ማኅበሩ ሌሎች አመራሮች መርጦ ከኩባንያው ጋርም የኅብረት ስምምነት አድርጎ ሲንቀሳቀስ የቆየ ቢሆንም፣ በቅርቡ በሠራተኛ ማኅበሩና በኩባንያው አመራር መካከል ግጭት መፈጠሩ በደብዳቤው ተመልክቷል፡፡

ፌዴሬሽኑ ጣልቃ ገብቶ ችግሩን በውይይት ለመፍታት ቀጠሮ በተያዘ ማግሥት፣ ኩባንያው የሠራተኛ ማኅበሩን ሊቀመንበር አቶ መለስ ዘሩን፣ ምክትል ሊቀመንበሩን አቶ ፈቃዱ ሙላትና ገንዘብ ያዥ አቶ ጌትነት አብዲን አላግባብ ከሥራ ማሰናበቱን ይገልጻል፡፡ ፌዴሬሽኑ አመራሮቹ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የድርጅቱን ሥራ አስኪያጅ ቢያነጋግርም፣ ድርጅቱ ፈቃደኛ መሆን አለመቻሉን አቶ ዘገየ ተናግረዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ ለአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የጻፈው ደብዳቤ በቻይናውያን አሠሪዎች እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያውያን የሚሠሩ ሥራዎች በውጭ አገር ዜጎች እየተሠሩ መሆኑ ሊታይ እንደሚገባ ያሳስባል፡፡

የቻይናው የእንጨት ሥራ ኩባንያ ረዳት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ማኅሌት ገዛኸኝ የሠራተኛ ማኅበሩ አመራሮች መባረርን በማስመልከት ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ “የተባረሩት ሥራ እንዳይሠራ በማሳደማቸውና አልታዘዝ በማለታቸው ነው፡፡ የተባረሩት እንደ ሠራተኛ እንጂ እንደ አመራርም አይደለም፤” ብለዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ደብዳቤ ለጻፈላቸው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽንም ይህንኑ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል፡፡
 

ተዛማጅ ጽሁፎች:

  10 states live with most prevalent slavery – Ethiopia ranks 12th globally and 7th in Africa

  Businesses boom & investor profits rise, as Ethiopian workers are exploited, mistreated & increasingly getting angrier

  Control by China of geological study concession in Ethiopia worries upstart local mining companies

  May Day fails to resolve many of Ethiopia’s labor problems: Denial of labor rights & TPLF’s inability to get Chinese firms to abide by nation’s laws

  Chinese company accused of terrible human rights abuses in Ethiopia; TPLF regime dismisses complaints as anti-development, terrorism

  China’s persistent refusal to recognize rights of Ethiopian workers drags national labor leader into the fray

  On languages & investors: AAU dabbling with Chinese, Korean, Persian, soon Turkish too, etc

 

%d bloggers like this: