ምነው ከሕወሃት ሰዎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ ዴሞክራሲ፡ ሰብዓዊ መብቶችና መልካም አስተዳደር ችግሮች ለጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት ብቻ ገሃድ ሆኑላቸው?

19 Oct

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

ብልሹ አስተዳደር የዴሞክራሲ ምህዳርን በማስፋትና ቀጣይነት ባለው የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ በወሳኝነት ይፈታል! የሚለው የሜ/ጄነራል አበበ ተክለሃይማኖት ጽሁፍ አይጋ ፎረም ላይ የወጣው ጥቅምት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲሆን፣ እርሳቸው ግን የጻፉበት ጊዜ መስከረም 29 መሆኑን በጹፋቸው ላይ ይጠቁማሉ።

አይጋ ፎረም ላይ እንዳየሁት ወዲያው የመጀመሪያውን ገጽ እንዳነበብኩ፣ መነበብ ያለበት ብዬ እስካለፉት ጥቂት ቀናት አቆየቸው ነበር። ዛሬ ጥቅምት 19 ቀን 2015 ማንበብ ጀምሬ ላቆመው አልቻልኩም።

ይህ ማለት ግን ሙሉ ለሙሉ በጽሁፉ ሃሣብ እስማማለሁ ማለቴ ባይሆንም፡ ከሕወሃት ወገን ሆኖ አንድ የቀድሞ ወታደራዊ ባልሥልጣን፣ ማለትም ለአጭር ጊዜ እስከ ኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥነት ደርሰው ከነበሩ ዐይነት ሰዎች የማይስማ ዐይነት ድምጽ በማሰማታቸው ነው።

ሁለተኛ ጽሁፉን በትግሪኛ ወይንም እንግሊዝኛ ሊያደርጉት ሲችሉ በአማርኛ ማቅረባቸው፡ በኢትዮጵያውያን መካከል ውይይት እንዲደረጉበት መሆኑን ገምቻለሁ። ምናልባትም የእርሳቸው ያለውን ሁኔታ መጥፎነትና አሳሳቢነት በመገንዘብ ከገደሉ ጫፍ ሃገሪቱን ለመመለስ ያግዝ ይሆናል፣ ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር መነሳሳትም ይፈጥር ይሆናል የሚል እምነት ያላቸው አስመስሏቸዋል!

ይህንን ለማድረግ በሕወሃት ውስጥ ያለው እርሳቸው የሚያነሷቸው የመከፋፈል ነጥቦችም አነሳስተዋቸው ሊሆንም ይችላል ይህንን 52 ገጽ ጽሁፍ ያቀረቡት።

ዋናው ቁም ነገር ግን፡ ለሕወሃት በርከት ላሉ ዓመታት በጽሁፎቻችን ምክር ሠጥተን ጆሮ ዳባ ልበስ ብቻ ሳይሆን፡ ካለኔም አዋቂ ለአሳር በሚል ዘይቤ በማሠርና በማስፈራራት ሲያስፈልገውም ግለሰቦችን በማጥፋት ሃገሪቱን በዞግና በዘር በመከፋፈልና ማጋጨት ሲጀምር፣ ውጭ ያለው አመቺ ሁኔታን በመጠቀም የሽፍታና ወንበዴ ባህሪውን ብዙ ጊዜ ለመጠቆም ሞክረናል! የዚያም ዓላማ ማንነቱን በማሳየት ለመታገልና መንገዱን እንዲቀይር የሚደረግ የዜግነት ትግል አካል አድርጎታል፡፡

ለኔ ዘውትር ከዐይኔ ላይ የማይጠፋው የጥቅምት 4/2013 የጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ከተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ በተመለሰ ማግሥት 26 ጋዜጠኞች የተገኙበት አስቸኳይ ቃለ መጠይቅ አዘጋጅቶ ስድስት ጥያቄዎች ካዘጋጃቸው ጋዜጠኞች ብቻ ተቀብሎ ደም ለብሶ ደም ጎርሶ ሕጋዊ የሆኑትን የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የእስልምና እንቅስቃሴ አባላት ዜጎች እንዳልሆኑ አንኳሶ፣ አሥሮ እንደሚገርፍ ሴቶቹን እንደሚቆነጥጥ በሕዝብ ፊት መደንፋቱ ምንም ዐይነት መስዋዕትነት ለማስከፈል የሚያስገድድ ነበር/ነውም!

አበበ ተክለሃይማኖት/ጆቤ (ሜ/ጄ) (ፎቶ አይጋ ፎረም)

አበበ ተክለሃይማኖት/ጆቤ (ሜ/ጄ) (ፎቶ አይጋ ፎረም)

የሕወሃት መጥፎ ባህሪው፣ ፀረ-ዲሞክራሲያዊነቱና የአስተዳደሩ ብልሹነት ብዙዎች ኢትዮጵያውያንን ስላስቆጣ፡ የሽፍታ/ወንበዴ መንግሥት በኢትዮጵያ ብለን መሰየማችን ይታወሳል – አሁንም ይህንን በቀላሉ ያቆማል የሚል እምነት ባይኖረንም!

ምን ይደረጋል አንድ መንግሥት ነኝ የሚል አካል ሥራው ሁሉ ጥፋትና ዜጎችን በየፈርጁ በሃገራቸው ውስጥ ባለቤትነት ሲነፍግ? ሕወሃት ቃሉን አጥፎ የዴሞክራሲን ተስፋና ጭላንጭል ሙልጭ አድርጎ ባጠፋበት የምርጫ ማግሥት ይህ ጽሁፍ መቅረቡ የሚያበረታታ ነው።

በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ የሌለባት፡ ሰብዓዊ መብቶች በግፍ የሚረገጡባት ሃገርና ዜጎች በፍርሃት የሚኖሩባት ኢትዮጵያ መሆኗን የቀድሞው የሕወሃት ወታደራዊ ሹም ግልጽ ያደርጋሉ!

ዋናው ቁም ነገር በሕወሃቶች መካከል ያለው መነካከስ ሳይሆን፣ ሃገራችንን እንዴት ነው ከሕወሃት አፍራሽነትና ከፋፋይነት የምንታደጋት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንጊዜውም በላይ አልረገጥም ብሎ ራሱን ለመከላከል በሚሞክርበት ሰዓት በየቀኑ ስንትና ስንት ሕይወት እንደሚጠፋ ልናስታውስ ይገባል!

ይህንን መግለጫ ያቀረብኩበት ምክንያት፣ አንባብያን የጄኔራሉን ጽሁፍ እንብበው የራሳቸውን አስተያት እንዲወስዱ ነው። ከጽሁፋቸው እንኳር ነጥቦችን ጥቂቶቹን እንደሚከተለው ተውሼያቸዋለሁ፦

  *   ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በትጥቅ ትግል የነበረዉን አደረጃጀት እና አስተሳሰብ በመሰረቱ ሳይቀይር ነው መንግስትነትን የቀጠለው። እዚህ ጋ መሰመር ያለበት ጉዳይ የትጥቅ ትግል task እና መንግስት ከተሆነ ወዲህ የሚኖሩት tasks በአጠቀለይ በተለይ ከዴሞከራሲ ስርኣት በመሰረቱ የተለያዩ መሆናቸው ነው። በትጥቅ ትግል ወቀት እንድን ህዝብ ወይ አከባቢ በብቸንነት እንድትቆጣጠር የሚያስገድድ ህዝቡን በዋናነት ደርግን ለመድምስስ ሞቢሊዝ ማድርግ ሲሆን በኢፊዴሪ ሕገ-መንግሰት ግን ሕብረ-ፓርቲ ስርኣት መሆኑን መገንዘብ
  አለብን፡፡ ኢህአዴግ ለሕብረ-ፓርቲ ስርኣት በተማላ አልተዘጋጀም፡፡

  *   መንግስትና ገዢ ፓርቲ አንድ እና አንድ ሆነዉ የማይለዩበት በሆኑበት ምክር ቤት አባላት ለሶስቱም በአንዴ ተገዥ መሆን ስለማይቻል፡ ለተወካዩ ከህሊናው ጋር ለመሆንና የሕዝቡን ጥቅሞችና ፍላጎቶች ለማስከበር ስለማይቻል ውጥረት ይፈጠራል። ይሄ ውጥረት በተወካዮች ህሊና፣ ለወከሉት ማህበረሰብ እና ለህገ መንግስቱ ባላቸው ታማኝነት፣ ለፓርቲ ማስመስከር በሚገባቸው ታማኝት እና የኑሮ ጉዳይ በሚፈጥረው ግፊት ምክንያት የሚፈጠር ውጥረት ነው፡፡ ባጭሩ ሲገቡ በሚፈፅሙት መሃላ እና የፓርትያቸው ዲሲፒሊናዊ አሰራር እና ኑሮ መሃከል የሚከሰት ውጥረት ነው፡፡

  *   ይሄ ውጥረት በተወካዮች ህሊና፣ ለወከሉት ማህበረሰብ እና ለህገ መንግስቱ ባላቸው ታማኝነት፣ ለፓርቲ ማስመስከር በሚገባቸው ታማኝት እና የኑሮ ጉዳይ በሚፈጥረው ግፊት ምክንያት የሚፈጠር ውጥረት ነው፡፡ ባጭሩ ሲገቡ በሚፈፅሙት መሃላ እና የፓርትያቸው ዲሲፒሊናዊ አሰራር እና ኑሮ መሃከል የሚከሰት ውጥረት ነው፡፡

  *   ከፍ ያለ ኢ-ህገ-መንግስታዊነት ሲበረታ ሶስቱ በሽታዎች የራሳቸው ሰንደቅ አላማ እያውለበለቡ ‘አሸናፍናቹህ፤ ረታናችሁ’ ይሉናል:: አጠቃላይ የዲሞክራሲ ከባቢው እየጠበበ
  ሲሄድ ሶስትም በሽታዎች (መልካም አስተዳደር ማረጋገጥ አለመቻል፣ ሙስናና የፍትህ እጦት) ተጠናክረው፤ ተበረታተው፤ ተባዝተው እና ተኳኩለው ይፈነጩብናል፡፡ በዴሞክራታይዜሽን እና ኢ-ዴሞክራታይዜሽን ሂደቶች ሁሌም መሳሳብ እና ዉጥረት ይኖራል። መንግስት እንደ መንግስት ግን የዴሞክራታይዜሽን አጋዥ አልያም የኢ-ዴሞክራታይዜሽን አሳላጭ ነው መሆን እሚችለው፤ መሀል ላይ የሚንገዋለል መንግስታዊና ተቛማዊ አቛም ሊኖር አይችልም።ስለዚ ምርጫው አንድና አንድ ነው፤ ለዴሞክራሲ መስራት ወይም የፀረ ዴሞክራሲ ሃይል መሆን።

  *   ባጠቃላይ ሲታይ ብዙ ማንነቶች፤ በርካታ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች፤መልስ እንሻለን የሚሉ የተለያዩ ጥያቄዎች ባሉበት አገር አንድ ግንባር (ኢህአዴግ) እና አጋሮቹ 100% መቀመጫውን መቆጣጠር እሚያሳየን ነገር፤ አንድም ባጠቃላይ ፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ ችግር መኖሩን አልያም የምርጫ ስርዓቱ ችግር እንዳለበት ወይም ተግባራዊነት ላይ ችግር እንደነበረበት ነው፤ 100% እሚባል ውጤት አስቂኝ ግን ደግሞ አደገኛ ነው ፡፡ ይሄ ዉጤት አርቆ ለሚያስብ ሰው የአደጋ እንጂ የድል ምልክት ተደርጎ መቆጠር አይችልም። መሬት ላይ ያለዉን የተለያየ ፖለቲካዊ ፍላጎት እማያንፀባርቅ የምክር ቤት ሁኔታ የስጋት እንጂ የኩራት ምንጭ መሆን አይችልም።

  *   ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ በጠበበ ቁጥር የዜጎች ተስፋ እተሟጠጠ ስጋታቸው እና ፍርሃታቸው እየጨመረ ከቁጥጥር ውጪ የመሆኑ እድል ይሰፋል፡፡

  *   “የህግ አስፈፃመሚ አካል የህግ የበላይት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉ እንደ ፖሊሲና የመከላከያ ሃይል ያሉ ተቋሞችን የሚቆጣጠር በመሆኑ ለዴሞክራያዊ ስርዓት ግንባታው ታማኝ ካልሆነ የዴሞክራሲ ተቋሞችን አፈራርሶ ስርአቱን ለአደጋ ሊያጋልጠው ይችላል፡፡ በተግባርም የዴሞክራሲ ስርአትን የመፈታተን አደጋ የሚመነጨው በአብዛኛው ከህግ አስፈፃሚው አካል ነው”

  *   አንድ ለአምስት አደረጃጀትም ለህዝቡ የቀረበና የሚወስዱት እርምጃዎችም ቀጥተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ሊጠኑ እና በጥልቀት ሊዳሰሱ ይገባቸዋል፡፡ ይህ አደረጃጀት እታች ወርዶ የተፈጠረ ተቋም ሲሆን አጠቃላይ ህዝቡን ለልማት አነቃንቆ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ አወንታዊ ለውጦችን በማስመዝገብ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ሊያግዝ እሚችል ፈጠራ የታከለበት አደረጃጀት ነው፡፡ በአግባቡ ካልተያዘ ግን የድህንነት ተቋም ተቀጥያ ሊሆን ይችላል፡፡ ለጠባብ የፓርቲ ፖለቲካዊ መሳርያነት ከተጠቀምንበትም ጉዳቱ የከፋ ይሆናል፡፡ በቤተሰብ ዉስጥ ስለላን እና ጥራጣሬን ሊተክል ይችላል፤ አለን እምንለው የቆየ ማህበራዊ እሴትንም ድምጥማጡ ሊያጠፋው ይችላል።

 

%d bloggers like this: