በቃል ትዕዛዝ ብቻ በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ ግዥ እየተፈጸመ ነው ይላሉ አሁን! ይህን እስካሁን ያላወቁ እንዴት አልገባቸውም ብር ያለበት ቦታ የሕወሃትን ሰዎች ምንም እንደማያቆማቸው!

26 Oct

የአዘጋጁ አስተያየት፡

    ኢትዮጵያ እኮ የሌሎች ሃገሮችን ገንዘብ ማለትም የእንግሊዝ ፓወንድ ወይንም የአሜሪካን ዶላር አታትምም። በሻንጣ ጭነው በደህንነቱና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ውጭ በየጊዜው የሚሸሸው ገንዘብ ከፊሉ ከሕዝብ ሃብት ከፊሉ ደግሞ በበጀት ከተያዘውና ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከሚሆነው ተግምሶ እየተወሰደ ነው! ነገርየው እኮ ስንበት ብሏል። ከ2005 ምርጫ ጀምሮ ሕወሃቶችና ቅጥረኞቻቸው በዚህ ብዙ ተጠቅመዋል – ያቺ ሰዓት ደርሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስኪፋረዳቸው ድረስ! እስከዚያ ድረስ እነርሱ ይጨፍሩ፡ ይብሉ፡ ይምነሽነሹ ሕዝባችን እየተራበ!

    ለነገሩ ሕወሃትም እንደ … በፈለኩበት ጊዜ የምፈልገውን ትፈጽምልኛለህ ብሎ ስለሆነ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው እንደውም የት ላሸጋግርላችሁ ገንዘቡን ብሎ ሳይጠይቅም አይቅርም። ከንቲባው እንኳ ሁኔታው ሁሉ ስለቀፈፈው አፈትልኮ ጭንቅላቱ ውስጥ መኖር ከጀመረ ሰንበት ብሏል!

 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ከሕግ ውጪ፣ በቃል በሚሰጥ ትዕዛዝ ብቻ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጭ በማድረግ ግዥ እየፈጸመ መሆኑ ታወቀ፡፡

የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥቆማ ደርሶት ምርመራ በመጀመር መረጃዎችን እያጠናቀረ መሆኑ ታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የግዥ መመርያ ከ500 ሺሕ ብር በላይ ወጪ የሚደረግ ከሆነ፣ በውስን ጨረታ ግዥ መፈጸም ይከለክላል፡፡ ነገር ግን የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት ሲባል፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ውስን ጨረታዎችን እያወጣ በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ ግዥ ሲፈጽም መቆየቱ ታውቋል፡፡

ይህ ሕግን ያልተከተለ ግዥ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ትኩረት የሳበ በመሆኑ፣ ኮሚሽኑ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የፈጸማቸውን የተለያዩ ግዥዎች ለመመርመር መረጃ ጠይቆ ወስዷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለሚመራው ኮማንድ ፖስት ተጠሪ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራው የቤቶች ግንባታ ሥራ አመራር ቦርድ፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱን ሥራ በቅርብ እየተከታተለ መመርያ ይሰጣል፡፡

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ፣ በቃል በሚሰጥ ትዕዛዝ ብቻ ግዥ እየፈጸሙ መሆናቸውን በግልጽ ተናግረዋል፡፡

አቶ ይድነቃቸው እንዳሉት፣ የበላይ አመራሮች በቃል በሚሰጡት ትዕዛዝ ብቻ ከሕግ ውጪ ግዥ እየተፈጸመ ነው፡፡ በተጨማሪም የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት እየተመራ ያለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው ኮማንድ ፖስት፣ በምክትል ከንቲባውና ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ መሆኑን ገልጸው፣ በአብዛኛው በጽሑፍ ሳይሆን በቃል ትዕዛዝ መመርያ እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የሕግ ማዕቀፍ እንዲስተካከል ወይም ሰርኩላር እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ጠይቀናል፣ እስካሁን ምላሽ አላገኘንም፤›› ያሉት አቶ ይድነቃቸው፣ ‹‹የፀረ ሙስና ኮሚሽን ግዥ ስንፈጽም የቆየንባቸውን መረጃዎች ወስዷል፤›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 6.3 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ግዥ ፈጽሟል፡፡ ‹‹ያለምንም የጽሑፍ ትዕዛዝ አመራሮቻችንን አምነን በ1.6 ቢሊዮን ብር የአርማታ ብረት ግዥ አከናውነናል፤›› በማለት ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው አቶ ይድነቃቸው ሳይሸሽጉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ ይህንን ገንዘብ እያንቀሳቀስን የአዲስ አበባ የግዥ መመርያ ውስን ጨረታ ከ500 ሺሕ ብር በታች ነው ይላል፤›› በማለት የሕግ ማዕቀፉ ሊሻሻል እንደሚገባም አቶ ይድነቃቸው አሳስበዋል፡፡

ነገር ግን የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ግዥዎቹን ለመፈጸሙ በጽሑፍ ሰርኩላር እንዲወርድለት ቢጠይቅም፣ እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የፀረ ሙስና ኮሚሽን የተለያዩ ሰነዶችን በመውሰድ በግዥ አፈጻጸሙ ላይ ምርመራ ማካሄዱን ቀጥሏል፡፡
 
ምንጭ፡ ሪፖርተር
 

%d bloggers like this: